መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቁን የረመዳን ወር በፆምና በፀሎት አሳልፈው እነሆ የበዓሉ ዋዜማ ላይ ደርሰዋል። የእምነቱ ተከታዮች ባለፈው አንድ ወር ከፆምና ፀሎትም ባሻገር በርካታ የበጎ ተግባራትን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። የተቸገሩትን በመርዳት፣ ርስ በርስ በመረዳዳት፣ ከሌሎች እህትና ወንድሞች ጋር በፍቅርና በሰላም የተግባር አንድነታቸውን አሳይተዋል።
ይህ የበጎ ተግባር ደግሞ በዚህ ወር ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ምክያቱም ወሩን ሙሉ ሲፆምና ሲፀልይ እንዲሁም ለፈጣሪው ምስጋና ሲያቀርብ የነበረው መላው ህዝበ ሙስሊም በበዓሉ እለትም ተደስቶ እንዲውል ከማድረግም በዘለለ ከበዓሉ በኋላ መረዳዳትና ለጋራ ሰላም መቆም ሃይማኖቱ የሚያዘው ተግባር ነውና።
የዘንድሮ የረመዳን ወር ከሌላው ጊዜ ለየት የሚደርገው ደግሞ በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ከመቼውም ጊዜ በላይ የተግባርና የመንፈስ አንድነት የተፈጠረበት ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል በመላው ህዝበ ሙስሊም ጥረት ወደ አንድነት የመጣበት ወቅት ላይ የሚከበር በዓል በመሆኑ ለሁሉም የእምነቱ ተከታዮች ከፍተኛ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው።
በሌላ በኩል አገራችን ባለፈው አንድ ዓመት በለውጥ ላይ መሆኗ ይታወቃል። ይህ የለውጥ ወቅት ደግሞ ካመጣው ተስፋና አንድነት ጎን ለጎን ስጋቶችንም ይዟል። የስጋቱ ዋነኛ መነሻ ደግሞ የሰላም ችግር ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚገኙባት፣ የተለያዩ ባህሎች እና እምነቶች የሚስተናገዱባት አገር ናት። ህዝቡም አንዱ ሌላውን እያከበረና እየተረዳዳ ለዘመናት የመኖሩ ዋነኛ ሚስጥር ለሃይማኖቱ ካለው ክብርና እምነት ይመነጫል። እያንዳንዱ ሃይማኖት የሚያስተምረውም ስለሰላም፣ ስፍቅርና ስልመቻቻል ነውና።
የአገራችን ህዝብ የሃይማኖት አባቶች የሚሰጡትን ምክርም ሆነ ተግሳፅ ተቀብሎ ተግባራዊ የማድረግ የቆየ ልምድም አዳብሯል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የጣልያን ወራሪ ሃይሎች አገራችንን እንዳይወሩ ካስቻሉ እሴቶቻችንም አንዱ የሃይማኖት ተጽዕኖ እንደነበር ይታወቃል። በወቅቱ ህዝቡ ለወራሪው የፋሽስት ኢጣልያ እንዳይገዛና ሉዓለዊነቱን አሳልፎ እንዳይሰጥ የሃይማኖት አባቶች ያደረጉት አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰናል።
ያም ሆኖ ግን ይህ የቤተእምነቶችና ሚና አሁን አሁን እየቀነሰ መምጣቱን ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚታዩት ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ተገትተው ህዝቡ ቀደም ሲል ሲያደርግ እንደነበረው በሰላምና በፍቅር አብሮ እንዲኖር ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች ትልቁን ድርሻ ሊወስዱ ይገባል። ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አባቶች ሚና የላቀ ነው። ይህ እውን ሊሆን የሚችለው ግን የሃይማኖት አባቶች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትንም ሆነ የምንናፍቀውን እድገት ማምጣት አዳጋች ይሆናል።
በተለይ አሁን ባለንበት ሁኔታ እኛ ኢትዮጵውያውያን ሰላም ያስፈልገናል። ያለ ሰላም የምንፈለገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላም ዕዝነ ልቡናን ያረካል፤ ሃዘንን ያስረሳል፤ ጦርነትን ወደ ፍቅር ይለውጣል። ሰላም በፍለጋ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተግባር የሚተረጎም ነውና በሰላም የሚኖሩት ሰላምን በተግባር ማረጋገጥ የቻሉ ብቻ ናቸው። ምክንያቱም ሰላም ተግባር ናትና። ሰላምን በተግባር ለማዋል ደግሞ ሰላምን መሻት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።
ሰላም ያለው ሰው ፍቅር አለው፤ ሰላም ያለው ሰው ዕረፍት አለው፤ ጤና አለው፤ ደኅንነት አለው። ሰላም ከሌለ ደግሞ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ፈጽሞ አይገኙም። እነዚህ የሕይወት ቁልፍ ነገሮች ከሌሉም አንድነት አይኖርም። ይህ የሚገኘው ደግሞ በአብዛኛው በሃይማኖት ጥላ ስር ነው። አባቶቻችን ሃይማኖታቸውን ጠብቀው፣ ዳር ድንበራውን አስከብረው ከዚህ ማድረስ የቻሉት በሰላም ነው። ያለ ሰላም ዛሬን ውሎ ነገን መድገም አይቻልም። በሰላም ግን ትናንትን ማስታወስ፣ ዛሬን ማስተዋል፣ ነገን ደግሞ ተስፋ ማድረግ ይቻላል።
ፍቅር በሰው ልጆች እንዲሠርጽ፣ መግባባት እንዲኖር፣ መረዳዳትና መከባበር እንዲመጣ በመንፈሳዊ ተቋማት በኃላፊነት የሚገኙ ሰዎች ሰላምን ማስተማር አለባቸው። መሪዎች የሰላም አክባሪ ሲሆኑ ተመሪው ሕዝብ ሰላምን ይከተላል። የሃይማኖትና የቤተ እምነቶች መሪዎችና አባቶች የሰላም ሰባኪ ሲሆኑ ምእመናን የሰላም ባለቤትና አቀንቃኞች ይሆናሉ። ተማሪ ሁልጊዜም ቢሆን መሪውን ያያልና።
በመሆኑም ሃገራችን አሁን ከገጠማት የሰላም መደፍረስ አጣብቂኝ በአፋጣኝ እንድትወጣ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በሰላም መኖርን ለሚሻው ሕዝባቸው ሰላምን ማብሰርና መስበክ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ይቅር መባባል፣ ጥፋትን ማመን፣ ባለፈው ጥፋት መጸጸት፣ ስለ ቀጣዩ ሰላም ማሰብ፣ አንድነትን መናፈቅና ስለ አንድነት መቆም ይገባል።
ለአንድ ወር የዘለቀው የረመዳን ፆምና ፀሎትን በኢድ አልፈጥር በዓል በደስታና በፍቅር እንዲከበር፤ ከዚም በኋላ በአገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን መላው ህዝበ ሙስሊም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። በተለይ ሰላምን ለሚያውኩ አካላት ጀርባውን በመስጠትና ከፍቅር ሃይሎች ጎን በመሰለፍ ስለሰላም አጥብቆ ሊያስብ ይገባል። ምክንያቱም እምነታችንን በአግባቡ የምናራምደውም ሆነ ሃይማኖታችንን የምናስፋፋው በሰላም ውስጥ ብቻ ነውና። ኢድ ሙባረክ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011