በሀገሪቱ ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ያልተረጋጋ ሰላም፣ ሁከትና ብጥብጥ ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ቤት ንብረታቸው ወድሞባቸው፤ የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተው ቀያቸውን ትተው ሸሽተዋል። ወገን አለን፣ ደጋፊ እናገኛለን ብለው ይሻላል ባሉበት አካባቢ ሁሉ ተሰደው ወራቶችን በየመጠለያው አሳልፈዋል። ለብዙ ወራትም የመንግስት፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና የግለሰቦችን እጅ ሲያዩ ቆይተዋል። የሰው እጅ ሰርቶ እንደመብላት አያጠግብ፤ ሰርቶ እንደመለወጥ አያስደስትም። ያም ሆኖ ግን በተለያየ አቅጣጫ በተደረገላቸው ድጋፍና እርዳታ ህይወታቸውን ማቆየት ችለዋል።
ሆኖም ግን አሁን በየአካባቢው ሰላም እንዲፈጠር፣ በህዝቦች መካከልም ቂምና ጥላቻ እንዳይሰፍን በተሰራው ጠንካራና ተከታታይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል። ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።
በሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከልም 1 ነጥብ 2 ሚሊየኑን ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀያቸው መልሶ የማቋቋሙ ስራም በቀጣይነት ትኩረት ተሰጥቶት እስከ ያዝነው ወር መጨረሻ ድረስ የሚሰራ መሆኑ የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከምእራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው የነበሩና በጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ ተጠልለው የቆዩ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመልሰው የተቋቋሙበትን ሁኔታ ለማየት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከተመላሾቹ የቀረበው ጥያቄ ‹‹በዘላቂነት የምንቋቋምበት ሁኔታ ይመቻችልን፤ የክረምቱን የእርሻ ወቅት ሰርተን ከችግርና እርዳታ እንድንወጣ የእርሻ ግብአት የሚሆን ድጋፍ ይደረግልን ››የሚል ነው። ይሄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ፈጣን ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ይሄንን ጥያቄ መንግስት ብቻውን ሊመልሰው እንደማይችል መታመን አለበት።
መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለበት። ይሄንን ግዴታውን ለመወጣት ደግሞ አቅም ወሳኝ ነው። ሆኖም ግን “ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሀምሳ ሰዎች ደግሞ ጌጥ” እንደሚባለው ሁሉ ሁሉንም ተፈናቃዮች መልሶ የማቋቋሙ ስራ ለመንግስትም ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ያክል ነው። በመሆኑም ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና ግለሰቦች ሁሉ ርብርብ ማድረግ አለባቸው። ይሄ ሲሆን ሀምሳ ሎሚ ለሀምሳ ሰው ጌጥ እንደሚባል ይሆናል። ወገን ለወገን ደራሽነቱ ይረጋገጣል፤ ኢትዮዽያዊነት አንድነት ይጎላል።
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ወደቀያቸው የተመለሱት ተፈናቃዮች ወደ እርሻ ስራቸው እንዲሰማሩ ከእርዳታ ጠባቂነት እንዲላቀቁ የእርሻ በሬ፣ የዘር እህል እንዲሁም ሌሎች ለእርሻ ስራው የሚያስፈልግ ግብአቶችን በማቅረብ መተባበር ይገባል።
እንዲሁም ተመላሾቹ ተረጋግተው ኑራቸውን እንዲቀጥሉም መኖሪያ ቤታቸውን በመስራት ለዚሁ አገልግሎት የሚውል የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ ሚስማር እና የመሳሰሉትን በማቅረብ ጭምር መረባረብ ያስፈልጋል። የጤና እና የትምህርት ተቋማቶች ተመልሰው እንዲገነቡ ማድረግ ያስፈልጋል።
የረመዳን ወቅት የሰላም፣ የአንድነት፣ የይቅርታ፣ የመስጠትና የዕርቅ እሴቶች መገለጫ ጊዜ ነው። የሙስሊሙ ማህበረሰብም ይሄንን ሀይማኖታዊ ትዕዛዝ በማክበር ጭምርም በኢድ አልፈጥር የበዓል ወቅትም ወደቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ጭምር ድጋፍ ማድረግ ይገባል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ የወገን አለኝታነትን በሚያስመሰክር መልኩ የተለያዩ ድጋፎችንና እገዛዎችን በማድረግ ወደቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን በዘላቂነት ማቋቋም ጊዜው አሁን ነውና መልሰው እንዲቋቋሙ ርብርብ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011