ዓለም ፅናትና ብርታት፤ ጭካኔ እና የዋህነት የሚፈራረቅባት፣ በቢሆንና በሚሆን ክስተቶች የተሞላች ናት። ይህች ዓለም ሁሉ ነገር ይፈራረቅባታል። ዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› በሚለው አምዳችሁ ፅናትና ብርታትን በውስጡ ስለተሸከመው ወጣት ብሎም ጭካኔን በመርዝ ብልቃጥ ጭልጥ አድርጎ ስላጣጣመውና የህግ የበላይነትን የሚዳስስ ታሪክ ይዘን ቀርበናል።
በልጅነቱ ለፍትህ የቆመ
ዳግማዊ አሰፋ ነዋሪነቱ ሐዋሳ ነው። የተወለደው 1981 ዓ.ም አሰላ ነው። ቤተሰቦቹ በሥራ ምክንያት ወደ ሃዋሳ ሲመጡ እርሱም በልጅነቱ ሀዋሳ ከተመ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም ሃዋሳ ማውንቴን ሊፍት እና አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ተምሯል። ታቦር መካነ እየሱስ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀበት ሥፍራ ነው። ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል። አባቱ አሽከርካሪ ናቸው። እናቱ ደግሞ በመንገድ ትራንስፖርት ውስጥ ባለሙያ ናቸው። ዳግማዊ ለቤተሰብ ሁለተኛ ልጅ ነው።
ወደ ሥራ ዓለም ከመቀላቀሉ በፊትም በሐዋሳ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የህግ ድጋፍ ማዕከል ነፃ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የህግ ድጋፍ ማዕከል ይሰራ ነበር። ጠበቃ ዳንኤል ዋለልኝ ከሚባል ሰው ጋር ደግሞ በትርፍ ጊዜ አብሮት ይሰራ ነበር። ሐምሌ 2006 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ ሥራ በማፈላለግ ሂደት ላይ ሳለ ጠበቃ ዳንኤል ዋለልኝ ዘንድ እየሰራ ሥራ ማፈላለግ ጀመረ።
አሳዛኙ ነገር!
ዳግማዊ ከጠበቃ ዳንኤል ዋለልኝ ጋር እየሠራ ሳለ ከዕለታት በአንዱ ቀን አንድ ባለጉዳይ ወደ ቢሯቸው ይመጣል። ይህ ሰው በሃዋሳ ውስጥ ‹‹ኢቭኒንግ ስታር›› የሚባል ሆቴል ይገዛል። በሽያጭ ውል መሰረት ለመንግስት የሚከፈለውን ክፍያ ሻጩ ይፈጽማል ይላል። ሆቴሉ 30 ሚሊዮን የተገዛ ነበር።
ይሁንና በውሉ ላይ የተቀመጠውን ነገር ሻጩ ላለመክፈል አንገራገረ። ከዚያ ባለጉዳዩ ጠበቃ ዳንኤል ዘንድ ሄደው ጉዳዩን አስረዱት። ከዚያም ጠበቃ ዳንኤል ክስ መስርቶ ብሩ እንዲከፈል መደበኛ ሥራውን ጀመረ። በዚህን ጊዜ ሻጩ ሰውዬ ጠበቃ ዳንኤል ዘንድ ደውሎ 600ሺ ብር እንደሚሰጠውና ጉዳዩን አበላሽቶ እንዲሸነፍ ካልሆነ ግን እንደሚገድለው ይነግረዋል። ጠበቃ ዳንኤል ግን ፈጽሞ አላደርገውም፤ ፍትህ መዛባት የለበትም ሙያዬንም እንደሸቀጥ አልቸረችርም ሲል እንቢኝ አለ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ጠበቃ ዳንኤል እና ዳግማዊ ስለጉዳዩ ይመካከሩ ነበር።
መስከረም 28 ቀን 2007 ዓ.ም ጠበቃ ዳንኤል እና ዳግማዊ ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ፍርድ ቤት ስለነበራቸው ቀጠሮ ስለችሎት ጉዳይ እየተነጋገሩና እየተዘጋጁ ባሉበት ሰዓት ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። ሲዝት የነበረው ግለሰብ ቢሮ ድንገት ገብቶ ጠበቃ ዳንኤልን አቅፎ በሽጉጥ ተኩስ ከፍቶ ሆዱን መታውና ከመሬት ላይ ጣለው። ከዚያም ለማምለጥ ሞከረ።
በወቅቱ ዳግማዊ ኡ! ኡ! ኡ! እያለ ተከተለው። ያዙት! ያዙት! ሰው ገድሏል ብሎ ሲከተል ግለሰቡ ወደ ኋላ ዞሮ በሽጉጥ ጉሮሮው ላይ መታው። ዳግማዊ ተመትቶ ወደቀ። ገዳዩ በቁጥጥር ሥር እንዲውል በአራቱም ማዕዘናት አሰሳ ተጀመረ። ገዳዩ ከሃዋሳ ብዙ ርቋል። ሰውየው ሱዳን ለመግባት ብዙ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። ከዚያንም አማራጮችን ሁሉ አይቶ አልሆን ሲለው ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ መግቢያ አካባቢ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ።
ከአደጋው በኋላ ዳግማዊ ወደ አዳሬ ሆስፒታል ተወሰደ። ከዚያም ሪፈር ተደርጎለት ኮርያ ሆስፒታልም ሁለት ወር ህክምና ላይ ቆየ። ጠበቃ ዳንኤል ግን ያችን ማዕልት ማለፍ አልቻለም፤ እስከወዲያኛው አሻለበ። ግን ዳግማዊ ሁለት ወር ሙሉ ጓደኛው ስለመሞቱ አያውቅም ነበር። ወደራሱ ተመልሶ ማሰብ ሲጀምር የጓደኛውን ነገር ይጠይቅ ነበር። ግን ህክምና ላይ ነው እያሉት ስለመሞቱ አልነገሩትም። ወዲህ ግን ቢሻለውማ ይጠይቀኝ ነበር እያለ ጓደኛው በከፋ ሁኔታ እንደተጎዳ ያስብ ነበር። የሚያሳዝነው ነገር እርሱ ከሚያስበው ተቃራኑ መሆኑ ነው።
እርምህን አውጣ!
ዳግማዊ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ከሁለት ወር በኋላ ጠበቃ ጓደኛው ዳንኤል መሞቱን ሰማ። አሁንም ቢሆን የእርሱ ሞት ‹‹ህልም ይመስለኛል››ይላል። ጓደኛዬ፣ ወንድሜ ብሎ የሥራ ባልደረባዬ ነበር። ‹‹በቡሀ ላይ ቆረቆር›› እንዲሉት በችግር ላይ ችግር ሆነብኝ። ዋጋም የከፈልኩት ለእርሱ ነበር፤ ሳይተርፍ ሲቀር ግን ለእኔ ከባድ ነው፤ ዘላለማዊ ፀፀት ጥሎብኝ አልፏል። ተናግሬም፤ አልቅሼም አልወጣ ያለኝ ነገር ይህ ነው። ይህን መቼም ቢሆንም ልረሳው አልችልም ይላል።
ዳግማዊ በአደጋው ‹‹የመተንፈሻ እና የምግብ ቱቦዬ ሙሉ ለሙሉ ተበጥሷል፣ ከአንገቴ በታችም በፈለጉት መጠን ምንም ማዘዝ አልችልም›› ብሏል። በአሁኑ ወቅት መቆም አይችልም። ብዙ ህክምና ሞክሯል፤ ወደ ውጭ ሄዶ ለመታከም አልቻለም። የውሃ ሽንቱንም መቆጣጠርና ራሱን መመገብ አይችልም። ሁሉ ነገር በሰው እገዛ ነው። ግን ተስፋ አይቆርጥም፤ ሁሌም ከሕይወት ጋር ትግል እንደገጠመ ነው።
ማን አሳከመው?
ዳግማዊ ጤናማ በነበረበት ጊዜ ለበርካቶች ነፃ የህግ ድጋፍ ሲያደርግ፤ የድሆችን እንባ ሲያብስ ነበር። ታዲያ ይህ አደጋ በደረሰበት ወቅት ለህክምና በትንሹ 500ሺ ብር አውጥቷል። ይህን ለመሸፈን ለቤተሰቦቹ ከባድ እንደነበር ያውቃል። ግን የከተማው ነዋሪዎች አዋጥተው፤ በጎ አድራጊዎች እየተባበሩት ሁኔታውን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ታልፎ ነፍሱ ዛሬ ደርሳለች።
ግን ከአሁን በኋላ የሁኔታችን ክብደት ሳስበውና ለህክምና የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ሳሰላው ግራ ይገባኛል ይላል። ብቻ ምንም ይሁን ምንም ፈጣሪ ዝም አይለኝም ይላል። ዳግማዊ ግን በአንድ ከምንም በላይ ያስገርመዋል። ጥብቅና የቆሙለት ባለጉዳይ አሸናፊ ሆኖ ሆቴሉንም እያስተዳደረ ነው። ግን ይህ ሁሉ አደጋ ሲደርስባቸው አንዳችም እገዛ ያለማድረጉ ብሎም በአካል መጥቶ አለመጠየቁ ዛሬም እንቆቅልሽ ሆኖበታል።
ዳግማዊ እስካሁን አራት ጊዜ ከባድ ቀዶ ህክምና አድርጓል። ግን አገር ውስጥ ታክሞ የሚፈልገውን ያክል ለውጥ አላመጣም። ስለዚህ ወደ ውጭ ሄዶ ለመታከም ጥረት እያደረገ ነው። ሁኔታዎች ከተሳኩ የመሄድ እቅድ አለው። ግን ነገሮች አስቸጋሪ እንደሆኑ ነው የሚናገረው።
ምን ተፈረደ?
ይህን ሁሉ ጥፋት ያደረሰው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ሲውል አጃኢብ አስብሏል። በወቅቱ 250 ጥይቶች፣ አምስት ሽጉጦች ጋር ነበር የተያዘው። በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በከባድ አካል መጉደል፣ በነፍስ ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎች ተጠያቂ ሆነ። የህግ ሂደቱ ረጅም ጊዜ ወሰደ። በፍርድም የሞት ፍርድ ተፈረደበት። ለዳግማዊ ህክምናም 700ሺ ብር እንዲከፍል ተወሰነ። ግን ሰውየው አደገኛና ሁሉን ሃብት አሽሽቶ ስለነበር ለዳግማዊ ምንም ገንዘብ ሊሰጥ አልቻለም።
ለመኖር ብዬ …
ዳግማዊ ይህ ሁሉ ፈተና ደርሶበት ሃሳቡ እና ሰውነቱ እየተጠገነ ሲመጣ በቤተሰቡ ግቢ ውስጥ አንድ ክፍል ቤት ሰጥተውት ቢሮ ከፈተ። በእርግጥ ለጤናው ከባድ
እንደሚሆን በመስጋት ቢከለክሉትም እርሱ ግን ስለፍትህ ስማር ኖሬ፤ ፍትህ ለሚፈልግ አንድ ሰው ብጠቅም እንኳን በሚል ወደ ሥራው አተኮረ። በእርግጥ ገና ከጅማሬው የህግ ትምህርት ሲጀመርም ብዙዎች ከልክለውት እንደነበር ያስታወሳል። ‹‹ሙሰኛ እና ሌባ›› እየበዛ ባለበት አገር ለምን ዋጋ ትከፍላለህ ሲሉት ተቃወሙት። እርሱ ግን ረጅም ዘመኑን በሐዋሳ ገብርኤል በመንፈሳዊ ሕይወት ታንፆ ያደገ ነው።
እናም ፍትህ ለሁሉም፤ ሃቅ ለሁሉም የሚል አቋም አለው። የሕግ ሥራ በአብዛኛው ማማከር ስለሆነም ስራዬን ማቆም አልፈለኩም ይላል። ለፀሁፍ ሥራዎችንም ፀሐፊ ቀጥሯል። በርካቶች ትንሽ ችግር ሲገጥማቸው ጓዳ ይደበቃሉ። ‹‹እኔ ግን በሥነ ልቦናም ሆነ በተግባር ለሰው ተምሳሌት መሆን አለብኝ ብዬ ስለማሰብም በተማርኩት ሙያ የምችለውን እያደረኩ ነው›› ይላል። እናም ዛሬ በመንፈሳዊ ሕይወት የቀሰመውን እውቀት እና ልምድ ብሎም ከመደበኛ ትምህርቱ ጋር አጣምሮ እየሠራ ነው።
‹‹አዲስ ሕይወት››
እጆቹ ኮምፒዩተርም ሆነ እስኪሪቢቶ መያዝ አይችሉም። ግን ‹‹አዲስ ሕይወት›› በሚል ርዕስ መፅሐፍ አሳትሟል። በመጀመሪያ ጓደኞቹን እያሰባሰበ ሃሳቡን ይነግራቸው ጀመር። እነርሱ ወደ ፅሁፍ ቀየሩት። መፅሐፉ የራሱን ሕይወት በብዛት የተረከበትና ለሌሎች አርዕያ እንዲሆን አስቦበት የደረሰው ነው። በተለይ እርሱ ካሳለፈው ከባድ ወቅትና እየኖረ ካለው አስቸጋሪ ሕይወት ሌሎች ምን ይማራሉ የሚለውን ሲያስብ መፅሐፍ ማሳተም የሚለው ሃሳብ ቀድሞ በጭንቅላቱ አቃጨለ። ሃሳቡንም ወደ ተግባር ቀየረ።
በመፅሐፉ ውስጥ ችግሮች ሲገጥሙ እንዴት መቀበልና መወጣት እንደሚቻል ይዳስሳል። በዚህ መፅሐፍ ውስጥም የሌሎች ዓለም አቀፍ ሰዎችን ተሞክሮ ዳሶበታል። ሰዎችን በሚረብሽ ሳይሆን ተስፋ በተሞላበት መንገድ የተቀናበረ እንደሆነም ነው የሚናገረው።
ዳግማዊ ምን ያስባል?
‹‹እኔም ሆንኩ በእኔ ላይ ጉዳት ያደረሰው ሰው ለህዝብ መማሪያ›› እንሆናለን ይላል። ይህ ሰው 30 ሚሊዮን ብር ንብረት ሸጦ ለመንግስት የሚገባውን ቢከፍል ምንም ችግር አልነበረውም። በወቅቱ ቁጣ እና እልህን በትዕግስት ቢያሳልፍ እርሱም ዛሬ በዚህ መልኩ ባልኖረ ሲል ስለበዳዩም ያዝናል።
በእኔ ዘንድ ደግሞ ምንም እንኳን በችግር ውስጥ ብሆንም እሠራለሁ። የተጋነነ ባይሆንም ለሦስት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ። ለችግር እጅ ሳልሰጥ ይህን ከሰራሁ በእኔ ሕይወት ሚሊዮኖች ይቀየራሉ ብዬ አስባለሁ፤ በርካቶችም እንደሚለወጡ ተስፋ አደርጋለሁ ይላል። ዳግማዊ በቀጣይ ህግ ነክ የሆኑ መፅሐፍቶችን በስፋት የመፃፍ እቅድ አለው። በዩቱብ፣ ፌስቡክ እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን መንገዶች ተሞክሮውን እያካፈለ ሲሆን፤ ወደ ፊትም በዚሁ እንደሚቀጥል ይናገራል። ዳግማዊ በዚህ ሁሉ ችግርና መከራ ውስጥ የቤተሰቡን፣ የጓደኞቹንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ ጉልህ ድርሻ አላቸውና ምስጋናዬ ይድረሳቸው ይላል። እኛም ምስጋናህ ይድረሳቸው እያልን፤ ብርታትህና ጽናትህ በርካቶችን እንደሚያንፅ እምነታችን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር