ከህጻን እስከአዋቂ፣ ከተማረ እስካልተማረ፣ ያለምንም የብሄር፣የጾታና የሃይማኖት ልዩነት ሁሉም ሰው ከምንም ነገር በላይ አገሩን እንደሚወድ ይናገራል። ለሉዓላዊነቷ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈልም አገር መወደድን በተግባር የገለጹ ብዙ ዜጎች እንዳሉንም አይካድም። ለአገርና ለህዝብ ታማኝ በመሆን በየተሰማሩበት መስክ የሚተጉ፣ ግብርን በአግባቡ የሚከፍሉና ከአገር የማይሰርቁ አርአያ ዜጎችም አሉን።
ከዚህ በተቃራኒም በአፋቸው ስለ አገር መውደድ እየሰበኩ ተግባራቸው ግን አራምባና ቆቦ የሆነ ለአገርና ለህዝብ የማይታመኑ፣ ከድሃ ወገናቸው ጉሮሮ የሚሰርቁ፣ ኃላፊነትን ለግል ጥቅም ያዋሉ ዜጎችም አይጠፉም። በተግባር ያልተገለጸ የአገር ፍቅር ፋይዳ የለውም የሚል የፈረንሳዮች አባባል አለ። እውነት ነው በተግባር የማይገለጽ ፍቅር ትርጉም የለሽ ነው።
ዛሬ በዕድገትና ስልጣኔ ከዓለም ቀደምቶቹ ተርታ የተሰለፈችው የደቡብ ኮሪያ ዜጎች የአገር ፍቅር ተግባር ለብዙዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው። አገራቸው በከፍተኛ ድህነትና የውጭ ወረራ ህልውናዋ ተስፋ አስቆራጭ በነበረበት ወቅት ሴት ደቡብ ኮሪያውያን ወርቅና ጌጦቻቸውን ሁሉ አውጥተው ለአገር በማበርከት እንዲሁም ጸጉራቸውን እየቆረጡ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለአገራቸው ልማት እንዲውል በማድረግ ታሪክ የማይዘነጋውን አገርን የመውደድ ተግባር ፈጽመዋል። ይህንን በማድረግም ለዛሬዋ የበለጸገች ደቡብ ኮሪያ መሰረት ከመሆናቸውም በላይ ለልጆቻቸው የተሻለች አገርን ማውረስ ችለዋል። የዛሬዎቹ ደቡብ ኮሪያውያንም የእነዚህን እውነተኛ ዜጎች ተግባር ለማወደስ በስማቸው አንድ ቀን ሰይመው እያከበሯቸው ይኖራሉ።
ታማኝ ግብር ከፋይ መሆን፣ ህዝብን መውደድ፣ አገርን ከሚጎዳ ተግባር መታቀብ፣ ራስን ከሌብነት ማራቅና ለአገር ሉዓላዊነት መሰለፍ የአገር ፍቅር ከሚገለጽባቸው ተግባራት መካከል ይመደባሉ። አገር በችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ የችግሯ ተካፋይና የመፍትሄው አካል መሆንና ለዛሬውና ለነገው ትውልድ የተሻለ ኑሮ አሻራን አኑሮ ማለፍም ከአገር ፍቅር መገለጫዎች ሌለኞቹ ናቸው።
ለነገው ትውልድ መልካም ዕድልን ከምንፈጥርበትና አገር መውደዳችንን በተግባር ከምናረጋግጥባቸው ዕድሎች መካከልም የአካባቢ ጥበቃና የችግኝ ተከላ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ለአንዳንዶች የአረንጓዴ ልማቱ የቅንጦት ጉዳይ መስሎ ቢታያቸውም ይህ ልማት የልማቶች ሁሉ መሰረትና የአገርና ህልውና ምሰሶ ነው። ምክንያቱም ያለአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ለሰው ልጆች ምቹ መኖሪያ መፍጠር አይቻልምና።
የአብዛኛው የአገራችን ህዝብ የህይወት መሰረት የሆነው ግብርናም ያለአረንጓዴ ልማት የሚታሰብ አይደለም። ስለሆነም ስለአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስናወራ ስለ 100 ሚሊዮን ህዝብ ህልውና እያወራን እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል። በዚህ ስራ ላይ አሻራችንን ስናሳርፍ ደግሞ በአገር ልማትና ህልውና መጠበቅ ላይ አንድ ጡብ እየጨመርን መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ተገቢ ባልሆነና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ለረጅም ዓመታት በደን ሀብታችን የደረሰው ውድመት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። አገራችንን በተደጋጋሚ ጎብኝቶ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈው ድርቅ ዋነኛ መንስዔም የደን ውድመት ነው። ከድርቁ ጋር ተያይዞ አሁንም በየዓመቱ ብዙዎች ለረሃብ እየተጋለጡና የአገራችንን ገጽታ እየጠለሸ መሆኑም የአደባባይ ሀቅ ነው። ቀደም ብሎ በመልካም የአየር ጸባይ የምናውቃቸው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የአየር ጸባያቸው ተቀይሮ ብዙዎች ሲያማርሩት እየታየ ነው።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ለአረንጓዴ ልማቱ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠውን የሸገር ፕሮጀክትና አራት ቢሊዮን ችግኞች በመላ አገሪቱ የመትከል ዕቅድ በማንኛውም መስፈርት ቢመዘን ትክክለኛነቱና ተገቢነቱ ጥያቄ ውስጥ አይወድቅም። ይልቁኑ ሊያሳስበንና ሊያስቆጨን የሚገባው ጉዳይ እስካሁን ለምን ዘገየ የሚለው ነው።
አሁን ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቀው ነገር አገር መውደዳችንን በተግባር የማረጋገጥ ዕድል በሰጡን በእነዚህ ዕድሎች በሙሉ ልብ መሳተፍ ነው። በዕቅዱ እንደተመላከተው እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ 40 የሚደርሱ ችግኞችን መትከል ይጠበቅበታል። መትከል ብቻ ሳይሆንም ተንከባክቦ ለፍሬ ማብቃትም ግድ ነው።
ይህንን ማድረጉ ደግሞ እጅግ ቀላል ከመሆኑም በላይ በአገር ዕድገትና ህልውና ላይ የራስን መልካም አሻራ ለማስቀመጥ መልካም አጋጣሚም ነው። ስለሆነም መንግስትና አስተባባሪ አካላት ተፈላጊውን ችግኝ በሚፈለገው መጠን ለህዝብ ማድረስ ህዝቡም የተላለፈለትን ይህን መልካም ጥሪ ተቀብሎ አገሩን መውደዱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል እንላለን!
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011