‹‹ውሀ ሲወስድ አሳስቆ ነው›› የሚለው አባባል ቁልፍ መልዕክቱ ድንገቴነቱ ነው ስለሆነም ሳንዘናጋ ቀድመን ለመከላከል የሚያስችል ስራ መሰራት እንዳለበት አመላካችም ነው በአገራችን በተለይ ነጎድጓዳማው ሐምሌ እና ጠዋት ማታ መውጫ መግቢያችንን የሚያስተጓጉለው ነሐሴ ክረምት በመጣ ቁጥር የአደጋ ስጋት ብቻ ሳይሆን ውደመት በማስከተል ይታወቃል አደጋን አስቀድመን ለመከላከል እንደ ሀገር ምን ያህል ዝግጁ ነን? ብሎ አስቀድሞ መፈተሽ፣ መነጋገርና መስራት ግድ ይላል
በተለይ በመጪዎቹ ሐምሌና ነሐሴ ከአንድ ወር በፊት ቀድሞ ከተተነበየው በላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ከፍተኛ ዝናብና ያልተጠበቁ የወንዞች ሙላት ሊከሰት ስለሚችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ዝግጁነት ወሳኝ እና አስፈላጊ ነው፡፡ ክረምቱን ተከትሎ የሚከሰትን ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋዎች ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያስከትል አስቀድሞ በመዘጋጀት የሰው ህይወትና ንብረት ከጉዳት መታደግ ያስፈልጋል
የጎርፍ አደጋው በገጠርና በከተማ የሚከሰትበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ፣ ስለሆነም የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ለይቶ ቀድሞ የመከላከል ሥራ መስራት ይገባል በተጨማሪም በጎርፍ ወቅትም ሆነ በድኅረ ጎርፍ ወቅት ለሚያጋጥም ችግር ምላሽ ለመስጠትና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ላይ ምን ያህል ነን የሚለው ዛሬ መመለስና ዝግጅቱ አጠናቆ መጠበቅ ግድ ይላል
የጎርፍ አደጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ማስቀረት ባንችልም መቀነስ የሚቻለው ደግሞ የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ቀደም ሲል የተሠሩ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ፣ የመከላከልና የማቅለል ሥራዎች ላይ ባለን ዝግጁነት ነው በአገራችን በመጪዎቹ የክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል ዋና ዋና የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች በጥናት መለየታቸውን መፈተሽና ማረጋገጥ ተገቢ ነው
በአሁኑ ወቅት አዋሽ ተፋሰስ፣ ድሬዳዋ፣ መካከለኛውና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ፣ በአማራ ደቡብና ሰሜን ወሎ እንዲሁም ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋዎች ሊከሰት እንደሚችል በጥናት መለየቱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል። በዘንድሮ በልግ ወቅት በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ አፋርና ጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ መድረሱ የቅርብ ጊዜ እውነታ ነው።
በተለይ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን የደረሰው አደጋ 5 ሺህ 630 ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ ሲሆን 700 ቤቶች ፈርሰዋል፤ ከቤቶቹ መካከልም 60 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ይታወሳል በተመሳሳይም በአፋር ዞን 1፣ 2፣ 4፣ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ አካባቢ በደቡብ ክልል ሀድያ፣ ስልጤና ጉራጌ እንዲሁም ሲዳማ የጎርፍ አደጋው ተጋላጭ ናቸው በሱማሌ ክልል ጅግጅጋም ተመሳሳይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ይደርስባቸዋል ተብሎ ከተለዩ ቦታዎች መካከል ይጠቀሳል
ቀጣዩ የክረምት ወቅት የአየር ንብረት ክስተት ተፅዕኖ ሥር የሚወድቅ ከሆነ፣ ከሚዘንበው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ጋር ተያይዞ ቅፅበታዊ ጎርፍና የወንዞች ከመጠን በላይ ሞልቶ የመፍሰስ ዕድል ከፍተኛ ስለሚሆን በሰው፣ በሰብል፣ በእንስሳትና በንብረት ላይ ጉዳት ያስከትላል በመሆኑም በከተሞች አካባቢ የከተማ አስተዳደሮችና ማዘጋጃ ቤቶች በቆሻሻ የተዘጉ ቱቦዎችን የመክፈት፣ አዳዲስ የሚሠሩና ነባር መንገዶች ተገቢው የጎርፍ ማፍሰሻ እንዲኖራቸው የማድረግ፣ የጎርፍ መቀልበሻ አውታሮች የመገንባትና የማጠናከር ሥራዎች መከናወን ይገባቸዋል
በዚህም ምክንያት በዩኒቨርሲቲዎች፣ በምርምር ተቋማትና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጥናት እንዲያካሂዱ በማድረግ ዘላቂና በቅንጅት በመስራት መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል
በተደጋጋሚ ለጎርፍ አደጋ በሚጋለጡና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ከመሬት አቀማመጥና በአፈር ባህሪይ ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ ከእነዚህ አካባቢዎች ጥናት ላይ በመመሥረት ህብረተሰቡን ለጎርፍና ለመሬት መንሸራተት በማይጋለጡ አካባቢዎች በዘላቂነት እንዲሰፍሩ ማድረግ የቅድመ ዝግጅቱ ወሳኝ ስራ ሊሆን ይገባል
በአጠቃላይ ችግሩን በተደራጀ መንገድ ለመከላከል ይቻል ዘንድም ከውኃ፣ ግብርና፣ ትምህርትና ጤና ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ግብረ ኃይል የተቋቋመ ቢሆንም አደጋውን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ግን በሚገባ ሊፈተሹ ይገባል ክልሎችም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀውን የመጠባበቂያ እቅድ ወስደው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው እንዲጠቀሙበት በሚገባ ሊስራበት ይገባል የፍሳሽ ቦዮችን በቆሻሻና ባዕድ ነገሮች መሙላት የጎርፍ አደጋውን ከሚያባብሱት ምክንያቶች መካከል በመሆኑ ኀብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ከማድረግ መቆጠብ ይገባዋል እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በማከናወንና ቀድሞ በመዘጋጀት የጎርፍ አደጋ መከላከል ይቻላል
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011