የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም የበለጠስኬታማ እንዲሆን

 የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ተግባራዊ ካደረጋቸው ሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የሌማት ትሩፋት ነው። የፕሮግራሙ ዓላማ በዋናነት በሀገሪቱ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የአመጋገብ ሥርዓትን ማሻሻል ነው።

ከዚህም ባለፈ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ጀምሮ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለማሳደግ የሚያስችል ዓላማ ሰንቆ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሲሆን፤ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበበት የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡

ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግር የሆነውን የሕፃናትን መቀንጨር መከላከል የሚያስችል፤ ዜጎች ባላቸው አቅም፣ በአነስተኛ ድጋፍ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበትን አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። እንደሀገር ያለንን ሥርዓተ ምግብ ጤናማ በማድረግ ሂደትም ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዮሐንስ ግርማ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንዳስታወቁት፣ በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በ2016 በጀት ዓመት አምስት ወራት አምስት ቢሊዮን 726 ሊትር ወተት፣ 328 ነጥብ ሁለት ሺህ ቶን ስጋ፣ 96 ነጥብ ሰባት ሺህ ቶን ማርና ከሶስት ቢሊዮን በላይ የእንቁላል ምርት ተገኝቷል።

በእነዚህ ወራትም 315 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭተዋል። የወተት ላም ዝርያ ማሻሻል፤ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን የማቅረብ ሥራም የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።

የእንስሳትን ጤና አገልግሎት ከማሻሻል አኳያም የክትባት አገልግሎት ሽፋንን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ የድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ጨምሮ፣ የቆላ ዝንብና ገንዲ በሽታን የመከላከል እና በበሽታው የተያዙ አዳዲስ አካባቢዎችን ከበሽታው የማፅዳት ሥራ ተሠርቷል፡፡

ሀገራችን ያሏትን ሀብቶች በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ ሀገራት በዋነኛነት ተጠቃሽ ስለመሆኗ በስፋት የሚነገር የአደባባይ ሚስጥር ነው፤ይህንን እውነት ለመቀልበስ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ስኬታማ መሆን ሳይቻል ቀርቶ ከፍ ያለ የሀብት ብክነት ሲስተዋል ኖሯል።

ከዚህም የተነሳ እንደ ሀገር በብዙ ፈተናዎች አልፈናል። በምግብ እህል እራስን ያለመቻል እና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ችግሮች በብዙ ፈትነውናል። በዚህም ምክንያት አንገት በሚያስደፉና የሀገርን ክብር በሚፈታተኑ ክስተቶችን ለማለፍ ተገድደናል።

የድርቅ አደጋ በመጣ ቁጥር ለከፋ አደጋ ተጋላጭ መሆን፤ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ መግፋት፤ ከተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መሆን፣ ወዘተ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ያስከፈሉን፣ ዛሬም እያስከፈሉን ያሉ የችግሩ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ፈተናዎቻችን ናቸው።

በእጃችን የነበሩትን /ዛሬም ያሉትን እነዚህን አቅሞች እና በጓሯችን ሊፈጠሩ የሚችሉ እድሎች በአግባቡ ማስተዋል፤ ለነሱ የሚሆን ስትራቴጂክ እይታ መፍጠር የሚያስችል ብቃት ያለው አመራር አለመኖር፤ የአቅሞቹና እድሎቹ ተጠቃሚዎች ሳንሆን ረጅም ዘመናትን እንድናሳልፍ ሆነናል።

ይህን የአመራር ክፍተት በማስወገድ የለውጡ መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ ፣ በተለይም ሀገር በብዙ ችግሮች እየተፈተነች ባለበት አሁናዊ ሁኔታ ውስጥ ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገቡ፤ የሚበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ነው።

ፕሮግራሙ ሰፊው የገጠሩ ማህበረሰብ በቀላሉ ተጨማሪ ሀብት ማመንጨት የሚያስችለው ከመሆን ባለፈ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ከፍተኛ ፍልሰት በመከላከል፤ የገጠሩ ማህበረሰብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ የተሻለ እድል የሚፈጥር ነው። ወደ ውጪ የሚደረግ ስደትንም ሊቀንስ የሚያስችል ነው።

ከዚህ አንጻር ፕሮግራሙ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት፤ ተሞክሮዎችን ከማስፋት ጀምሮ፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በየጊዜው አግባብ ባለው መልኩ በመገምገም እና ዘላቂ መፍትሄዎችን በማስቀመጥ በትኩረት እና በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚገኙ የፕሮግራሙ አስፈጻሚ አካላት፣ የፕሮግራሙን ዓላማ ከማስረጽ ጀምሮ ለተግባራዊነቱ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶችን ማሳጠር፤ አስፈላጊ ድጋፎችን አግባብ ባለው መልኩ ማቅረብ፤ችግሮችም ሲያጋጥሙ ፈጥኖ በመንቀሳቀስ ለፕሮግራሙ ሁለንተናዊ ስኬት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You