ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን በተያዘው አጠቃላይ ግብ ውስጥ የሚካተት “ለግብርናው ትራንስፎርሜሽን የአመራሩ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ አንድ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ወቅታዊው የአገሪቱ የግብርና ይዘት ተገምግሟል፤ በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው አበይት ጉዳዮችም አቅጣጫ ተቀምጧል። በርግጥም የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአብዛኛው የተመሰረተው በግብርና ላይ ነውና ዘርፉን መለወጥ የግድ ይላል።
በአሁኑ ሰዓት በግብርናው ኋላ ቀርነት ምክንያት አምርተን በምግብ ሙሉ በሙሉ ራሳችንን አልቻልንም። ዘርፉ የሸማቹን ፍላጎት ማርካት ይቅርና በዚያው በገጠር አካባቢ የሚኖሩትን ሃያ አምስት ሚሊዮን ያህል ዜጎች በቂ ምግብ እንዲያገኙ አለማስቻሉ በመድረኩ የተገለጸ እውነታ ነው። ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ በምግብ ለስራ የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ታቅፈው የፕሮግራሙ መንገራገጭ የሚያሰጋቸው የድጎማ ኗሪዎች ናቸው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው እውነቶች ሁሉ እያሉ ግን፤ አሁንም አገሪቱ አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ የምትጠብቀው እና የኢኮኖሚዋ ወሳኝ መሰረት ናቸው የሚባሉት የወጪ ምርቶች የሚገኙት ከዚህ ዘርፍ መሆኑ ይበልጡኑ የትኩረት ማዕከል ያደርገዋል።
ያም በመሆኑ፤ ግብርናውን ማዘመን ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል። በሁለቱ ቀናት የምክክር መድረክም ይህ ዘመናዊነት “እንዴት?” እና “በምን መልክ?” ይጣ የሚሉት ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በመጨረሻም አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመድረኩ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ “የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ከማረጋገጥ አኳያ ግብርናው የማይተካ ሚና አለው።” አዎን! ግብርናው እንዲህ ያለውን አይተኬ ሚናውን እንዲወጣና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን ደግሞ እንደተባለው የግብርናው ልማት ስራ ቀጣዩ የሪፎርም ግብ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህም የአርሶ አደሩን የመስራት አቅም ማሳደግና ማዘመን፤ ምርትና ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል።
ግብርናውን በማዘመን ረገድ በዘርፉ ይሰራሉ ተብለው ከታያዙት ዕቅዶች መካከል፤ የወጪና ገቢ ምርቶችን ማመጣጠን፤ እስከዛሬ በስፋት ያልተሰራበትን የኩታ ገጠም ግብርናን ማስፋፋት፤ በተለይ ደግሞ፤ ከውጭ የሚገቡ ስንዴና መሰል ምርቶች በአገር ውስጥ በማምረት መተካት፤ ውሀን መሰረት ያደረጉ ሰፋፊ ስራዎችን ማከናወን፤ ገበያ መር የሆነ የግብርና ኤክስቴንሽንን ማስፋፋት እና ከሁሉም በላይ፤ የመስኖ ልማትና የቴክኖሎጂ ልህቀትን ማሳደግ ይገኙበታል።
በሌላ በኩል፤ ግብርናውን በመለወጥ ረገድ፤ በቀጣይ የፋይናንስ በጀቱ እንዲጨምር እንደሚደረግና በምርምር እንዲታገዝ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው ተገልጿል። በዚህ ረገድ፤ ከዚህ ቀደም ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ለዘርፉ ሃያ ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተመድቦ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ አጋጣሚ እንደገለጹትም “መንግስት የግብርናውን ዘርፍ እንደአንድ ዘርፍ ሳይሆን ቀዳሚና መሰረታዊ ጉዳይ አድርጎ በቀጣይ ሃያና ሰላሳ ዓመታትም ይሰራበታል” ብለዋል። አዎን! እስከዛሬ በነቢብ ብቻ የነበረው ትኩረት እንዲህ በተግባር ሲገለጽና እስከዛሬ ባልታየ መልኩ ይህንን ያህል በጀት ሲመደብለት ማየት መንግስት ለዘርፉ ምን ያህል ትክክለኛ ትኩረት እንደሰጠው የሚያመለክት ነው።
ትክክለኛ ትኩረት የምንለው ደግሞ፤ አብዛኛው ህዝብ አርሶ አደር፤ ከፍተኛው የኢኮኖሚ መሰረትም ግብርና በመሆኑ ዘርፉን ማዘመን የብልጽግናውም የልዕልናውም መጀመሪያ በመሆኑ ነው።
አዎን! ዶ/ር አብይ እንዳሉት፤ “አገርን የማልማት፤ የመገንባትና የመንከባከብ ስራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።” በዚሁ ልክ ግብርናውን የማዘመን ተልዕኮም በግንባር ቀደምትነት የመንግስት ሲሆን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው በዘርፉ ያለው አመራር ይሆንና ሁሉም ባለድርሻ አካል ደግሞ የተሳታፊነትም ሚና ይኖረዋል።
ከፍተኛውን የመንግስት አካል ጨምሮ በዘርፉ ያለው አመራር አርሶ አደሩን ከኋላ ቀር የግብርና ዘይቤ አላቅቆ በዘመናዊ ቴከኖሎጂ የታገዘ አስተራረስንና የእንስሳት አረባብ ዘዴ በማስተማር፤ በማሰልጠንና ክህሎት በማስጨበጥ፤ ብሎም ውጤታማ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይጠበቅበታል።
በተለይ በመጪው የክረምት ወቅት የሚሰራው የሰብል እርሻና ልማት የቀጣዩን መኸር ውጤት የሚወስን በመሆኑ፤ በአርሶ አደሩ በኩል ተገቢው የመሬት ዝግጅት እንዲደረግ ሙያዊ ድጋፍና ምክር በመስጠት፤ የዘር ወቅት መስተጓጎል እንዳይኖር የማዳበሪያ፤ የምርጥ ዘርና መሰል ግብዐቶች በወቅቱና በበቂ መጠን እንዲቀርቡ በማድረግ በዘር ወቅትም ድጋፍና ክትትል በማድረግ የማይተካ ሚናውን መወጣት አለበት።
የመስኖን ስራ ማዘመን ከምንም በላይ ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራርም የባለሙያም ተልዕኮ እንደሆነ ይታመናል። በዚህ ረገድ፤ አፋርና ሱማሌ ክልሎችን ጨምሮ በመስኖ የሚለሙ አካባቢዎችን በመለየትና ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ከውጭ የሚገቡ የግብርና ውጤቶችን ማስቀረት የሚያስችል ስራ ለመስራት መጀመር የግድ ይላል። እናም፤ በቀጣዩ ዓመት ቢያንስ የስንዴን አቅርቦትና ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት መተካት፤ ለዚህም ሽንጥን ገትሮ መስራት ተገቢ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ “ግብርናው የሚሰጠን እኛ በሰጠነው ልክ ነው” እናም አብዝቶ እንዲሰጠን አብዝተን ልንሰጠው ይገባል። ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ከምንም በላይ የአርሶ አደሩን የመስራት አቅም ማሳደግ፤ ከጉልበት ስራ ወጥቶ የግብርና ሜካናይዜሽንን መጠቀምን፤ ከአነስተኛ መሬት ላይ ከመስራት ይልቅ ኩታ ገጠም የሆኑትን በአንድ ላይ በማስተባበርና እንደአየሩ ጠባይና የመሬቱ አቀባበል፤ አቅምም ተገቢውን ምርጥ ዘር ከተሟላ ግብዐት ጋር ማቅረብ ያስፈልጋል።
ለዚህ ሁሉ ደግሞ፤ በመንግስት የተተለሙትን ዕቅዶችና በሁለቱ ቀናት የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አቅጣጫ በውል ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የዘርፉ የስራ ኃላፊዎችም ቀጣይ ተልዕኳቸው ከዚህ ቀደሙ የተለየ ስለመሆኑ ተገንዝበዋልና ለተስማሙባቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት ተገቢውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አዎን! መጻኢውን የአገሪቱን ዕድል ብሩህ ለማድረግ፤ የህዝቦቿን በልቶ ማደር ለማረጋገጥና የምንመኘውን የኢኮኖሚ እድገት ዕውን ለማድረግ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011