ታታሪዎቹ እህትና ወንድም

እንዴት ናችሁ ልጆች? ሁሉ ሠላም ? ትምህርት ጥናት እንዴት ይዟችኋል? ‹‹ሁሉም ጥሩ ነው::›› እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ:: ልጆችዬ ከትምህርታችሁ ጎን ለጎን ምን መሥራት ያስደስታችኋል? መጻፍ፣ ማንበብ፣ ስዕል መሳል፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወት፣ የፈጠራ ሥራቸውን መሥራት እና ሌሎችንም እንደምትጠቅሱልኝ ምንም ጥርጥር የለኝም:: ልጆችዬ በዛሬው ጽሑፋችን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሦስተኛ መጽሐፋቸውን ፅፈው ስላስመረቁት ቅዱስ የሺዋስ እና ህሊና የሺዋስ የምንላችሁ አለን::

ከህሊና የሺዋስ እንጀምር አይደል ልጆች? መልካም:: ልጆችዬ ህሊና በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት:: በትምህርቷም በጣም ጎበዝ ናት:: ከዚህ ቀደም ሁለት መጽሐፍቶችን አሳትማለች:: የመጀመሪያ መጽሐፏ “Anatomy and physiology of the Heart” የተሰኘ የልብ ሳይንስ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው:: ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ስለ ልብ የተነገሩ ምርጥ አባባሎች›› ይሰኛል:: በአማርኛ፣ በአረብኛ፣በእንግሊዝኛ እና በግዕዝ ቋንቋዎች ስለ ልብ የተነገሩ አባባሎችን የተሰባሰቡበት መጽሐፏ ነው:: ‹‹The Heart’s layers እና ሌሎች አርቲክሎች ስብስብ›› ደግሞ ሦስተኛ መጽሐፏ ነው::

ህሊና የልብ ታማሚ ቁጥር እየጨመረ ስለመጣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደፊት የልብ ሀኪም (ካርዲዮሎጂስት) ለመሆን ፍላጎት አላት:: ከልብ ህመም ጋር ለሚወለዱ ልጆች ለማከም እንደርሷ ፍላጎቱ ላላቸው ተማሪዎች ‹‹በርትታችሁ አጥኑ::›› የሚል ምክር ትለግሳለች:: ህሊና ፒያኖ የመጫወት እና የሥዕል ችሎታም አላት:: በተቻላት መጠንም ተሰጥኦዋን ማውጣት ትፈልጋለች:: እንደ ስዕል ፣ ሙዚቃ እና የመሳሰሉት ተሰጥኦ ላላቸው ልጆችም ‹‹ተሰጥኦ ካላችሁ አትደብቁት:: አውጡት እና ተጠቀሙበት::›› ትላለች::

ዶክተር ኤሌዘር ኃይሌ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የህጻናት ሀኪም ናቸው:: እርሳቸው ምን አሉ መሰላችሁ ልጆች? ህሊናን በዚህ ዕድሜዋ ስለ ልብ መጽሐፍ መጻፏ በጣም የሚደነቅ ነው:: ህሊና ዶክተር ስትሆን አብረው እንደሚሠሩ ተስፋ በማድረግ አበረታተዋታል::

አሁን ደግሞ ልጆች ስለ ቅዱስ የሺዋስ እንነግራችኋለን:: ተማሪ ቅዱስ 16 ዓመቱ ነው:: እንደእህቱ ህሊና ከዚህ ቀደም ሁለት መጽሐፍቶችን ጽፏል:: የመጀመሪያው መጽሐፍ ‹‹የአውሮፕላን የበረራ ምስጢሮች›› ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “The Fundamental of Airplane Design” ይሰኛል:: ‹‹737 MAX 8 አውሮፕላን እና ሌሎች አርቲክሎች ስብስብ›› የቅዱስ ሦስተኛ መጽሐፍ ርዕስ ነው:: ቅዱስ በ2024 ዓ.ም የራሱን አውሮፕላን ዲዛይን የመሥራት ህልም አለው:: ታዲያ ይህንን ሲሠራ አውሮፕላን ከሰዎች ጋር የተቆራኘ ወይም ወደ ሰዎች በይበልጥ ለማቅረብ ፍላጎት አለው::

ቀለል ያለ አውሮፕላን ማለትም ልክ እንደ መኪና ለሁሉም ሰው ተደራሽ ለማድረግ የመሥራት ሃሳብ አለው:: ቅዱስ ይህንን እቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል:: ከነዚህ ውስጥ አንደኛው ወደ ህልሙ እንዲቀርብ መጽሐፍትን መጻፍ ሲሆን፤ሌላው ደግሞ ለብቻው አውሮፕላን ለማብረር ማቀዱ ነው::

ቅዱስ ለእናንተ ለልጆች ምክርም አለው:: ምን መሰላችሁ ምክሩ? ልጆች ተሰጥኦቸውን ፈልገው እንዲያገኙት ነው:: ሁሉም ሠው የተሰጠው ነገር አለው የሚለው ቅዱስ፤ እሱን ፈልጋችሁ ካገኛችሁት ትልቅ ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ ይላል:: ይህም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ሀገራቸውን እና ዓለምን የሚጠቅም ይሆናል:: ይህን ለማድረግ ንባብ እና ጠንካራ ሥራ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል:: የወላጅና የመምህራን ድጋፍም እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳል::

ልጆችዬ! የህሊና እና የቅዱስ ሦስተኛ መጽሐፋቸው ኅዳር 15 ቀን 2015ዓ.ም በኢትዮጵያ ልጆች ሚዲያ አስተባባሪነት በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ተመርቋል:: በመጽሐፍት ምርቃቱ ላይ በክብር እንግድነት ከታደሙት መካከል አንጋፋው ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለ ማርያም አንዱ ናቸው:: እርሳቸው እንደገለጹት፤ ተማሪ ቅዱስ ስለ አውሮፕላን ቀለል ባለ አማርኛ ቋንቋ መጻፉ ያስመሰግነዋል:: በዚህ ዕድሜው ካፒቴን (የአውሮፕላን አብራሪ) ለመሆን ራሱን አግኝቶ መጽሐፎችን በመጻፍ እንዲሁም የት ሊደርስ እንደሚችል ራዕይ ማስቀመጡን አድንቀዋል:: የሙያ እገዛ ለማድረግም ቃል ገብተውለታል::

ሌላው ልጆችዬ፤ ቅዱስ እና ህሊና በራሳቸው ስም የተከፈተ የቴሌግራም ገጽ አላቸው:: ታዲያ ታዳጊዎቹ በገጾቻቸው ስላነበቡት መጽሐፍት፣ የነሱን ትኩረት ስለሳቡ ጉዳዮች እንዲሁም የተለያዩ ጽሑፎችን ለተከታዮቻቸው በማጋራት ላይ ይገኛሉ:: ሁለቱ ታዳጊዎች በአንድ ላይ ስድስት መጽሐፎችን ለማሳተም በቅተዋል:: ታዲያ ልጆችዬ ሦስተኛ መጽሐፋቸውን በህትመት ወረቀት የታተመ አይደለም:: ስለዚህም መጽሐፍቱን ለማንበብ ለሚሹ ልጆች ‹ማራኪ ቡክስ›› መተግበሪያ ላይ ማግኘት ይችላሉ::

ልጆችዬ! የእነቅዱስ አባት የሺዋስ አሰፋ እና እናታቸው መምህርት ሙሉ ብርሃን ትልቅ ብርታት እንደሆኗቸው በመግለጽ ለወላጆቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል:: ወላጆችም ልጆቻቸውን ማበረታታት እንዳለባቸው ተናግረዋል:: ደራሲ ታገል ሰይፉ በምርቃቱ ላይ እንዳለው፤ ታዲጊዎቹ በታዳጊነት ዕድሜያቸው እንዲህ ያለ መጽሐፍ መፃፋቸው የሚበረታታ ሲሆን፤ የወደፊት ህልማቸውን እንዲያሳኩ መታገዝ ይኖርባቸዋል::

የሁለቱ ታዳጊዎች እናት እና አባት በበኩላቸው ፤ በልጆቻቸው በጣም እንደተደሰቱ እና እንደኮሩባቸው በመናገር፤ ልጆች በትምህርታቸው እንዲጎብዙ በርትተው ማንበብ እንዳለባቸው፣ ልጆች ላይ መሠራት እንዳለበት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ማዳመጥ እንደሚገባ በተጨማሪም ማገዝ እና ማበረታታት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016

Recommended For You