ቻይና – የፈጣን እድገት ምርጥ ተሞክሮ

ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በፈጠረችው ጥምረት ከመሰረተ ልማት እና ንግድ ግንኙነት ባሻገር በርካታ አፍሪካውያንንም ወደሀገሯ በመውሰድ ስልጠና ሰጥታለች፤ ከፊሉንም አስተምራለች። በነዚህ እድሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል፡፡ ለልምድ ልውውጥ በሚል ቻይናን ያልጎበኘ የኢትዮጵያ ባለስልጣን የለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ የተነሳ በአንድ ወቅት “ከሞትና ከቻይና የሚቀር የለም” እስከመባል ተደርሶ ነበር፡፡

እኔም በቅርቡ የቻይና መንግስት ለኢፕድ የሰጠውን የስልጠና እድል በመጠቀም ለሁለት ሳምንት ያህል ቻይናን የመጎብኘት እድል አጋጥሞኛል፡፡ በዚህም ከስልጠናው ባሻገር የተለያዩ የቻይና ግዛቶችና ታሪካዊ ስፍራዎችን ለመጎብኘት ችያለሁ፡፡ ታዲያ በቆይታዬ ሁሉ የታዘብኩት ቀደም ሲል ስለቻይና የነበረኝን ግምትና ስሰማቸው የቆየኋቸው ትርክቶችን ሁሉ የቀየረ ነበር፡፡ በተለይ የቻይና የሆነን ነገር ሁሉ ቀለል አድርጎ የማየትና የማናናቅ ልምዶቼን እንድቀይር አድርጎኛል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከቻይና ተሞክሮ ለመውሰድ የሄዱ ሰዎቻችን ከቻይና ከሚገዙት እቃ ውጭ ምን ይዘው ተመለሱ፤ እንደ ሀገርስ ከዚህች በእድገት ተዓምር እየሰራች ካለች ሀገር ምን ተምረው፣ ምን አስተማሩን የሚለው ትልቅ ጥያቄ ፈጠረብኝ፤ እናም በጥቂት ቀናት የቻይና ቆይታዬ የታዘብኩትን ለአንባቢዎቼ ለማካፈል ብዕሬን ከወረቀት አገናኘሁ፡፡ ወደ ቻይና ትዝብቴ ከመግባቴ በፊት ግን በጉዞ ወቅት ስላየሁት በጎ ጎን በጥቂቱ ላካፍላችሁ፡፡

ከሕዳር 2 እስከ ሕዳር 14 በቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአምስት የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ዜጎች ተሳትፈዋል። የተሳታፊዎቹ ብዛት ታዲያ እንደ ሀገሩ ስፋትና የሕዝብ መጠን የተለያየ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በአጠቃላይ የተሳታፊዎቹ ቁጥር ከኢትዮጵያና ከናይጄሪያ ከፍ ያለ ነው፤ ሁለቱም እያንዳንዳቸው 13 ተሳታፊዎችን ልከዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ከኮሞሮስ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከሴራሊዮን እና ከታንዛኒያ የተውጣጡ ተሳታፊዎች በድምሩ 16 ነበሩ፡፡

እነዚህ ሁሉ ተሳታፊዎች ወደ ቻይና ሲጓዙ ታዲያ በቅድሚያ አዲስ አበባ መሰባሰብ የግድ ብሏቸዋል፡፡ ምክንያቱም ስልጠናው ወደሚሰጥበት የቻይና መዲና ቤይጂንግ ሊወስድ የሚችለው ብቸኛ የአፍሪካ አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነውና፡፡ እናም የኢትዮጵያ አየር መንገዱ “ET604 Aerocraft” በርካታ ቻይናውያንን እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሁም ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ከ350 በላይ ሰዎችን ጭኖ ጉዞውን ወደ ቤይጂንግ አደረገ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ደረጃ ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ከፍ ብሎ ውስጣችንን እና ስሜታችንን ከፍ አደረገን፡፡ በዚህ ጉዞ ኢትዮጵያዊ መሆን ያኮራል፤ ትልቅ መሆናችንንም በተግባር ያረጋግጥልናል፡፡ ይህ ትልቅ ኩራትና በራስ መተማመንን የሚፈጥር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረው መስተንግዶም ሆነ የአውሮፕላኑ ምቾት እንዲሁም ትልቅነት ሲታይ ሀገራችን እውነትም ትልቅ ሀገር መሆኗን እንድናስብ እድሉን ይሰጠናል፡፡

በዚህ ጉዞ ለ9 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ከበረርን በኋላ ቤይጂንግ አየር ማረፊያ ደረስን። እዚያም የሚቀበሉን ወጣት ቻይናውያን ነበሩ፡፡ በቀጥታም በተዘጋጀልን አውቶቡስ ጉዞ ወደማረፊያ ስፍራ ሆነ። የቻይና ትዝብቴ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡

በመንገዳችን ላይ በአንድ በኩል የመንገዱ ጥራት፤ በሌላ በኩል በቻይና አንድም አሮጌ ተሽከርካሪ አለማየቴ ምናልባት የአጋጣሚ ነው ወይስ ይህ በትክክልም የቻይና ነባራዊ ሁኔታ ነው የሚለው ጥያቄ ውስጤን እያብከነከነኝ ወደማደሪያ ስፍራችን ደረስን፡፡ በስልጠናችን ወቅት የመጀመሪያው ርዕሰ ጉዳይ የቻይና አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ አጭር ዳሰሳ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ጉዳዮችን እንዳውቅ ረድቶኛል፡፡

ቻይና ከአምስት ሺህ ዓመታት የሚልቅ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ እዚህም እዚያም በነበሩ ንጉሳውያን ከመተዳደር የዘለለ ታሪክ አልነበራትም። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ221 እስከ 206 የመጀመሪያው የፊውዳል ስርወ መንግስት ሀገሪቷን አንድ በማድረግ አስተዳድሯል፡፡ ይህ ስርወመንግስት ታዲያ ዛሬም የሚታወስ ታሪክ ጥሎ አልፏል፡፡ ቻይና ዛሬም ድረስ የምትታወቅበትንና የምትጠራበትን የቻይና ግንብ የጀመረው ይህ ስርወ መንግስት የሚታወስበት ነው፡፡ ግንቡ በአጠቃላይ ከ21 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለውና 54 ዓመታት የፈጀ የጥንታዊ ታሪካቸው መገለጫ ነው፡፡

የቻይና የመጨረሻ ስርወመንግስት ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ1644 እስከ 1911 ድረስ የዘለቀው ነው፡፡ በዚህ ስርወመንግስት ቻይና በርካታ ፈተናዎችን የተጋፈጠችበት እና ቻይናን መልሶ ቁልቁል የከተታት እንደነበር ታሪካቸው ያስታውሳል፡፡ በዚህ ዘመን ቻይና በበርካታ ምዕራባውያን ወረራ ተፈጽሞባታል፤ ብዙ መሬቶቿንም በወረራ አጥታለች፡፡

በዚህ ወቅት ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩስያ፣ ጣልያን እና ጃፓን በተለያዩ ጊዜያት ቻይናን ወርረዋል፡፡ ቻይናዎች እንደሚሉት ይህ ዘመን የመከራ ዘመናቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጥንካሬአቸው ምንጭም ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ አሮጌዋ ቻይና በአዲሲቷ ቻይና እንድትተካ ምክንያት ሆኗል፡፡

ቻይና ከፍተኛ ቁጥር ካለው የሕዝብ ብዛቷ ጋር ከማይመጣጠነው አነስተኛ ምርት እንዲሁም ከውስጣዊና ውጫዊ ጫና ጋር ተደማምሮ ትልቁን ፈተና እንድትጋፈጥ አድርጓታል። በዚህም ዜጎቿን ለመመገብ ከማትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰችባቸውን ጊዜያት አልፋለች፣ በዚህም በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች፡፡

በሌላም በኩል ከውጭ የሚመጣው ጫናም ሌላው ፈተና ነበር፡፡ በተለይ በ19ኛው ክፍለዘመን ወራሪዎች ቻይናን ለመቆጣጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች ለቻይና ሕዝብና መንግስት ትልቁ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የዕርስ በዕርስ ግጭቶችም ትልቅ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ የጤና ጉዳይም ሌላው ፈተናዋ ነበር፡፡

በተለይ የዘመናዊ ሕክምናም ሆነ መሰረተ ልማት አለመስፋፋቱ ቻይናውያን ለተለያዩ የበሽታ ወረርሽኞች አጋልጠዋታል፣ ብዙ ዋጋም አስከፍለዋታል፡፡ በአጠቃላይ በነዚህና ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ቻይና እንደ ሀገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ ተገድዳለች፡፡ በዚህ የተነሳ ቻይና እስከ 1992 ድረስ ለቤተሰብ የምግብ ራሽን ማደል ጭምር ግድ የሚልባት ሀገር ነበረች፡፡

ይህ ራሽን ለአንድ ሰው ሊሰጠው አልያም ሊገዛው የሚችለውን ቁሳቁስም ሆነ ምግብ የሚገድብ ነበር፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው በቤተሰቡ ልክ እየተተመነ የሚሸጥበት አልያ የሚታደልበት አሰራር ተግባራዊ ተደርጎም ነበር፡፡ ይህ ካለው የምግብ እና ቁሳቁስ እጥረት የመነጨ የድህነት አንዱ ክፉ ጎን ነው፡፡

እነዚህ የቻይና ክፉ የድህነት ዘመናት ነበሩ። እነዚህ እና መሰል ፈተናዎች ግን የቻይና ሕዝብንም ሆነ መንፈስን ተስፋ አላስቆረጡም። ይልቁንም ጠንካራ ሕዝቦች እንዲሆኑ እድል ሆኗቸዋል። እነሆ ቻይናውያንም ይህንን የዘመናት የድህነትና የችግር ጊዜ እንደታሪክ በመውሰድ ሀገራቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለወጥ ቆርጠው የተነሱበት ዘመን ሆነ፡፡

የቻይና የትንሳኤ ዘመን

የቻይና የትንሳኤ ዘመን የሚጀምረው እአአ ከ1949 ዓ.ም ነው፡፡ በተለይ ከ1949 እስከ 1978 ያለው ዘመን የቻይና የስኬት መነሻ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ቻይና በዋናነት የመሰረተ ልማት ግንባታዋን እንደ አዲስ የጀመረችበት ወቅት ነው፡፡

በወቅቱ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ በርካታ ሪፎርሞችን አካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት የየአምስት ዓመቱን እቅዶች በማዘጋጀት ወደትግበራ የገባ ሲሆን በየአምስት ዓመቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታው እንዲገመገምም ከስምምነት በመድረስ ቻይናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድህነት ለማውጣት ሁሉም ቁርጠኛ የሆነበት ወቅት ነው፡፡

በዚህም መሰረት በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ብቻ 156 ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም 700 የሚሆኑ ትላልቅና መካከለኛ ደረጃ ያላቸው ግባታዎችን አቅደው ወደስራ አስገብተዋል፡፡ አጠቃላይ የአምስት ዓመቱ አማካይ የኢኮኖሚ እድገትም 6ነጥብ9 በመቶ የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የለውጥ ትግል አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በርካታ ፈተናዎችም ነበረበት። ከነዚህም ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የባሕል አብዮት ተግዳሮት፣ ወዘተ ትላልቅ ፈተናዎች ነበሩ። በዚህ የተነሳ ኢኮኖሚው ቢያድግም ቻይና በቢሊየን የሚቆጠር ሕዝቧን ገና በአግባቡ እንኳን መመገብ አልቻለችም ነበር፡፡

ሀገሪቱ ስትከተል የነበረው የሶሻሊስት ስርዓት የሚፈለገውን እድገት ለማምጣት ከባድ መሆኑን የተገነዘበው የቻይና ሶሻሊስት ፓርቲም ሌላ ሪፎርም አካሄደ፡፡ በዚህም ከ1978 እስከ 1984 የሚቆይ ሌላ ሪፎርም በማካሄድ ቻይናን ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ ቆርጦ ተነሳ፡፡

ቻይና እንዲህ እንዲህ እያለች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ስርነቀል እመርታ እንድታመጣ ያስቻላት ግን እአአ ከ1992 ጀምሮ ያካሄደችው የኢኮኖሚ አብዮት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል በመሆን በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ቻይና ውስጥ እንዲያለሙ በሯን ክፍት አደረገች፡፡

ለቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ትላልቅ ስራዎችን ማከናወን ተያያዘች። አዳስ የስራ ባሕሎችን በማስተዋወቅና ቁርጠኛ በመሆንም ለለውጥ ተነሳች፡፡ በዚህም በአጭር ዓመታት ከከፋ የድህነት ታሪክ ተላቃ በዓለም ላይ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቃች፡፡ አዲሲቷ ቻይናም እውን ሆነች፡፡

አዲሲቷ ቻይና

ዛሬ የቻይና ታሪክ ሌላ ነው፡፡ ቻይና ትናንት እንደ ሀገር ያየቻቸውን ብዙ ፈተናዎችና የድህነት ታሪኮች ቀልብሳ ፍጹም ሌላ ሀገር ሆናለች፡፡ ቻይና ስለዛሬ ብቻ ሳይሆን ስለነገ ትውልድም አስተማማኝ ሀገር ገንብታ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል አቅም ፈጥራለች። የተፈራረቁባት ወራሪዎችም ዛሬ ሊደፍሯት አይሞክሩም፤ የትናንቱ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯልና፡፡

ከዚያ በመቀጠል ግን በየዓምስት ዓመቱ ሲከናወኑ የነበሩ የትራንስፎርሜሽን እቅዶች ድክመቶችን የማረምና ጥንካሬዎችን የማስቀጠል አቅጣጫን በመከተል ሲከናወን የቆየ ነው። በዚህ መልኩ የቀጠለው ለውጥ በ1992 የገበያ መር ኢኮኖሚን መከተል የሚያስችል መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ ኢንቨስተሮች በቻይና ኢንዲሳተፉ በር የከፈተ ነበር፡፡ ይህ በቻይና እድገት ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ዛሬ ቻይና 15ኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ላይ ደርሳለች፡፡ ይህም በዓለም ላይ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቻይና ኢኮኖሚ በ120 ትሪሊየን ዩዋን የዓለምን 18 ከመቶ ሀብት መያዝ ችሏል፡፡

የመሰረተ ልማት ሁኔታ

ቻይና ለአጠቃላይ እድገቷ ትልቁ መሰረት መሰረተ ልማት የገነባችበት መንገድ ነው። በከተሞችም ሆነ ከአንዱ ከተማ ወደሌላ ለመጓዝ በርካታ አማራጮች አሏት፡፡ የቻይና አንዱ ስኬታማ የመሰረተ ልማት ግንባታ መንገዶቿ ናቸው፡፡

የቻይና መንገዶች በጥራትም ሆነ በስፋት ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ከአንዱ ስፍራ ወደሌላው ስፍራ ሲኬድ ዳገትና ቁልቁለት መውጣት በቻይና አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ዳገት ሲያጋጥም ቆርጦ መሄድ አልያም በውስጡ ቦርቡሮ ማለፍ የቻይና መንገዶች መገለጫ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በቻይና የሚገኙ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ለማስተናገድ ሲቸገሩ አይስተዋልም፡፡

ከዚህም አልፋ ዓለምን በመንገድ መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የቻይና አነሳሽነት የተጀመረው የሮድ ኤንድ ቤልት ግንባታ ቻይና የእድገቷን ምንጭ ለሌሎች ሃገራትም ለማካፈል ፍላጎትና ቁርጠኛ መሆኗን አመላካች ነው፡፡

ቻይና በመንገድ ብቻ አይደለም፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በቴሌኮም አገልግሎት፤ በዲጂታል ቴክኖሎጂና መሰል የዘመናዊ እድገት መሰረቶች እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በዓለም ላይ የ5ጂ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅም የስልጣኔን መንገድ እየመራች ስለመሆኑ ለዓለም አሳይታለች። እጅግ የዘመኑት የሞባይል ቴክኖሎጂዎቿና አገልግሎት መስጫ ቁሶቿ ለቻይና ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ማየት ይቻላል።

በቻይና ጎዳና ላይ እዚህም ከላይ ወደታች እና ከታች ወደላይ የሚፈሱት ተሽርካሪዎች እጅግ ዘመናዊ ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ቻይና በቀጣይ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ከሀገሯ ለማስወጣት ያለመች እስክትመስል ድረስ በርካታ ተሽርካሪዎችና የሞተር ብስክሌቶች የሚሰሩት በኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡

ሰላምና ጸጥታ

የቻይና እድገት ቁሳዊ ሀብት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ማሕበረሰባዊ ስኬትንም እንድታረጋግጥ ያስቻላት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላምን ያረጋገጠችበት መንገድ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በቻይና ከተሞችም ሆነ ከአንዱ ስቴት ወደሌላው ስቴት ሲጓዙ የሰላም ጉዳይ አስጊ አይደለም፡፡ በከተሞችም ውስጥ ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ ቢያድሩ አልያም የሚፈልጉት አካባቢ ቢንቀሳቀሱ ስጋት የለም፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ በከተሞች ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች ሲዘዋወሩ አይስተዋልም። ከዚያ ይልቅ በቻይና የሴኪዩሪቲ ካሜራዎች በየቦታው በመገጠማቸው የጸጥታውን ስራ ለመቆጣጠር ሌት ተቀን ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ቻይና ስኬታማ ከሆነችባቸው ዘርፎች አንዱ ሰላምና ጸጥታን ያረጋገጠችበት መንገድ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል በቻይና እያንዳንዱ ሰው መስራት እስከቻለ ድረስ ገንዘብ የማግኘት እድሉ አለው፤ ገንዘብ እስከያዘ ድረስ ደግሞ ለመግዛት የሚፈልገውን ነገር ሁሉ በገበያ ለማግኘት አይቸገርም፡፡ ምክንያቱም በቻይና የማይሰራ ነገር የለም፡፡

አረንጓዴ ልማት

ቻይና እድገቷን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ “ተፈጥሮን መጠበቅ” የሚል መርህ ተከትላ እየሰራች ስለመሆኑ በብዙ ስራዎች ላይ የሚታየው አረንጓዴ ልማት ማሳያ ነው፡፡ ከአንዱ ግዛት ወደሌላው ግዛት ሲጓዙም ሆነ በከተሞች ውስጥ ሲዘዋወሩ በዙሪያዎት የሚያዩት ነገር ሁሉ አረንጓዴ ነው፡፡ የቻይና ከተሞች በዘመናዊ ሕንጻዎችና ግባታዎች የመድመቃቸውን ያህል በአረንጓዴ ልማትም ያሸበረቁ በመሆናቸው ለመኖሪያ ምቹ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ቻይና በአሁኑ ወቅት የደረሰችበት የእድገት እና የስልጣኔ ደረጃ እጅጉን አስደማሚ ነው፡፡ ቻይናን ለመለወጥ በወሰደችው ቁርጠኛ ውሳኔ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከፍጹም ድህነት ወደከፍተኛ ስልጣኔ ተሸጋግራለች። ለዚህ ደግሞ የመንግስት ቁርጠኝነትና የተከተለው ፖሊሲ፤ የዜጎች ለለውጥ መነሳትና የስራ ባሕል አብዮት እንዲሁም መለወጥ የሕልውና ጉዳይ ነው በሚል መርህ ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን ሁሉ ወደጎን በመተው ለስራ በመነሳት ያካሄዱት አብዮት ለዚህ ድል አብቅቷታል፡፡

እዚህ ላይ ግን አንድ ሳልጠቅሰው ማለፍ የማልፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት በርካታ የሀገራችን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቻይናን የማየት እድል እንደገጠማቸው ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ከዚህ ተዓምረኛ እድገት ተምሳሌት ሀገር ምን ትምህርት ቀሰምን? ቻይናን አይናችን እያየ በዚህ ደረጃ ወደከፍታ ማማ ስትጓዝ ምንስ የመንፈስ ቅናት አደረብን? ቻይናን ጎብኝተን የብልጽግናቸውን ሚስጢር እንደተሞክሮስ ካልወሰድን ምን ትርጉም አለው? የሚሉ ጥያቄዎች ሊታሰብባቸው የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው!!

ወርቁ ማሩ

አዲስ ዘመን  ህዳር 14/2016

Recommended For You