በአፍሪካ የመጀመሪያው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) የተማሪዎች ውድድር በቅርቡ በአብርሆት ቤተመጻሕፍት ተካሄዷል:: ውድድሩን አብርሆት ቤተመጻሕፍት አፍሪካ ቱ ሲሊከን ቫሊ ኤ2ኤስቪ (A2SV) ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመሆን ነው ያዘጋጀው:: በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ 47 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፤ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ስምንት ተወዳዳሪዎች ወደ መጨረሻው ዙር አልፈዋል::
ለፍጻሜ ውድድር የደረሱት ስምንቱ ተወዳዳሪዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያበለጸጓቸውን ሥራዎች ይዘው ቀርበዋል:: የፈጠራ ሥራዎቹም በሕክምና፣ በትምህርት፣ በሳይንስና በምህንድስና ዘርፍ የበለጸጉ ሰው ሠራሽ ውጤቶች ናቸው፤ ከስምንቱ ደግሞ ሦስቱ አሸናፊ ሆነዋል:: ለፍጻሜ ውድድር ከደረሱት ከስምንቱ ተወዳዳሪዎች የተወሰኑትን ሥራዎች በዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችንን እንዳስሳለን::
ተማሪ ሂዝሚና ተሩዝ እና የቱኒዚያ ጓደኞቿ ለሕክምናው ዘርፍ አጋዥ የፕሮጀክት ሃሳብ ይዘው ቀርበዋል:: በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ ለሕክምናው ዘርፍ አጋዥ የሆነ የዌብሳይትና የሞባይል መተግበሪያ ነው ያበለጸጉት:: መተግበሪያው በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመጠቀም በአእምሮ ሕክምና ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመቸር ትምህርቱን በቀላሉ ለመስጠት ያስችላል:: ለመላው አፍሪካ እንዲሰራ ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በተለይ የአእምሮ ሕክምናን የበለጠ ለማወቅና ለመረዳት ይጠቅማል::
ተማሪ ሂዝሚና እንደምትለው፤ ይህ መተግበሪያ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ስለአእምሮ ሕክምና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት ይጠቅማል:: ስለአእምሮ ሕክምና ማወቅ ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚያገለግል ሲሆን፣ በተለይ የሕክምና ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች እና በመስኩ የሚሰሩ ሙያተኞች የአእምሮ ሕክምናን በተመለከተ የሚኖሯቸውን ጥያቄዎች በሙሉ ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በማቅረብ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኙበት ነው::
ከዚህ በተጨማሪም ስለአእምሮ ሕመምና ስለሕክምናው ዓይነት በደንብ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች ማወቅ በሚፈልጉት ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ፈጣን ምላሽ ማግኘት ስለሚያስችላቸው በቀላሉ እንዲያውቁት እና በደንብ እንዲረዱት ያስችላቸዋል:: ይህ ደግሞ በተለይ የሕክምና ተማሪዎችን ጊዜና ወጪ በመቀነስ በቀላሉ የአእምሮ ሕክምና ሥራዎችን ለመሥራት ያስችላል ብላለች::
መተግበሪያው አሁን ሥራ ላይ መዋሉን የምትገልጸው ተማሪዋ፤ በተለይ በአእምሮ ሕክምና ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎች ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብላለች:: በቀጣይም ከአፍሪካ በመሻገር ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መተግበሪያ እንዲሆን እንደሚሰሩ ተናግራለች::
ተማሪ ኤመን ብሪጅ እና ጓደኞቹ በውድድሩ ለመሳተፍ ከአልጄሪያ ነው የመጡት:: በውድድሩ ለህጻናት መማሪያ የሚያገለግል የሞባይል መተግበሪያ ይዘው ቀርበዋል:: መተግበሪያው ህጻናት በወላጆቻቸው እየታገዙ ተረት፣ ታሪክ፣ የትኛውንም ዓይነት የሳይንሳዊ መጽሐፍ፣ ስለማንኛውም ጉዳይ እውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው:: ይህም መተግበሪያ ወላጆች ልጆቻቸው እድሜያቸው የሚመጥነውን ትምህርት መርጠው እንዲከታተሉ ለማድረግ ይረዳል::
ለህጻናት መማሪያ ተብለው የሚዘጋጁትን መጻሕፍትንም ሆነ ሌሎች አጋዥ ማስተማሪያዎችን መተግበሪያው ሰው ሠራሽ አስተውሎቱን ተጠቅሞ መምረጥና መለየት እንደሚያስችል የሚጠቆመው ተማሪ ኤመን፤ በተለይ በዚህ ዘመናዊው ዓለም አፍሪካዊያን የራሳችን የሚሉትን ሁሉ አብሯቸው እንዲቀጥል ለማድረግ ይረዳል ይላል:: ለምሳሌ ህጻናት የእንግሊዘኛ ቋንቋን ለመማር በመጽሐፍ፣ በስዕልና በድምጽ ያፈለጉትን እንዲያውቁ ለማድረግ እንዲሁም ወላጆች በልጆቹ እድሜ መሠረት ለእነሱ የሚሰማማቸውን ዓይነት ትምህርት እንዲያገኙ መምረጥ እንደሚያስችላቸው ይጠቁማል::
በአልጄሪያ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ለተማሪዎች የሚሰጠው ከአምስት ዓመት እድሜ ጀምሮ መሆኑን ጠቅሶ፤ “የትኛው ትክክለኛ ነው? የትኛው ደግሞ ትክክለኛ አይደለም?” የሚለው በወላጆች ተመርጦ እንዲማሩ ለማድረግ እንደሚጠቅም አስታውቋል:: አሁን የሰሩት ሞባይል መተግበሪያዎችን መሆኑን አስመልክቶ፣ በቀጣይ የድረገጽ መተግበሪያና ሌሎች ተጨማሪ እሴቶችን በማከል ለመላው አፍሪካ ተደራሽ የመሆን እቅድ እንዳላቸውም ተናግሯል::
ተማሪ አሴር ኃይሉ እና ጓደኞቹ ኢትዮጵያውያውን ተወዳዳሪዎች፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሶፍት ዌር ተማሪዎች ናቸው:: ‹‹ዘ-አርትቴክቸር›› የተሰኘ ዌብ ሳይትና የሞባይል መተግበሪያ ይዘው ቀርበዋል::
እነ ተማሪ አሴር የሰሩት መተግበሪያ አርክቴክቸሮች መሥራት የሚፈልጉትን ነገር ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በሚሰጡት ጊዜ ቴክኖሎጂው የሚፈልጓቸውን ዲዛይኖች (ለመነሻ ሃሳብ የሚጠቅሙ) ሰብስቦ ያመጣላቸዋል:: በተጨማሪ መተግበሪያው ላይ ባለሙያዎች ገብተው ሃሳባቸውን እና ሥራቸውን በማጋራት እርስበርስ እንዲወያዩና ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ ነው:: ዲዛይኖቻቸውን መተግበሪያ ላይ በመለጠፍ እንዲሸጡም ያስችላል::
አርክቴክቸሮች አንድን ሥራ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ፕላትፎርም እንዳለውም ጠቅሶ፣ ለምሳሌ ሁለት አርክቴክቸሮች አንድ ሥራ በጋራ የሚስሩ ከሆነ በፕላትፎርሙ እየተነጋገሩ ሁለቱም በእኩል ጊዜ ሥራቸውን መሥራት እንደሚያስችለው ተማሪ አሴር ይጠቁማል::
ብዙ ጊዜ አርክቴክሮች ሥራቸውን ሲሰሩ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ተደጋጋሚ በሆነ ሥራ ላይ መሆኑን የሚገልፀው ተማሪ አሴር፤ ይህ መተግበሪያ አርክቴክቸሮች ሥራቸውን ሲሰሩ እንዳይሰላቹ እንደሚያደርጋቸው ይናገራል:: መተግበሪያው ለአርክቴክቸሮች መነሳሳትን የሚፈጥር እና የተለያዩ ዲዛይኖችን ፈጥሮ የሚያቀርብ ሞዴል እንዳለው አመላክቷል ::
“ይህንን ሥራ የሰራነው አርክቴክቸሮች ዘንድ በመሄድና ጥናት በማድረግም ነው” የሚለው ተማሪ አሴር፤ በቅርባቸው ያዩትን ችግር መነሻ በማድረግ ይህንን መተግበሪያ ለመሥራት እንደቻሉ ይገልፃል:: ይህ መተግበሪያ አሁን በኢትዮጵያ ላሉ አርክቴክቸሮች ብቻ እንደሚሰራ ጠቅሶ፣ በቀጣይ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቋል::
ተማሪ አራርሳ ደረስ እና ጓደኞቹም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ናቸው:: እነ ተማሪ አራርሳ ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚያገለግል የዌብ ሳይት ፕላትፎርም ይዘው ቀርበዋል:: የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በመታገዝ መጽሐፍን መሠረት ያደረገ ጥያቄ የሚያቀርቡበትና ጥያቄውን መሠረት ያደረጉ ምላሾችን የሚያገኙበት ለተማሪዎች አጋዥ የሆነ መተግበሪያ ነው ያበለጸጉት::
ተማሪዎቹ በመተግበሪያው በመጠቀም ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ብቻ ሳይሆን፣ የሙከራ ፈተና መውሰድም ይችሉበታል:: በየሳምንቱ የሚዘጋጅ ውድድር ስላለ ተማሪዎች በአንዴ በዚህ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ:: ከዚያም ውጤታቸው ስለሚቀመጥላቸው ራሳቸውን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በማነጻጸር ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና ራሳቸውን ለማትጋት ይረዳቸዋል::
ተማሪው አጋዥ መጽሐፍ ካለው መጽሐፉን በመጫን ከመጽሐፉ ጥያቄዎች እንዲወጡ እያደረገ መጠቀም ያስችለዋል ሲል ገልጾ፣ ይህንን መተግበሪያ መጠቀም የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ድረ ገጹ ገብቶ መጠቀም ይችላል ብሏል::
ተማሪ አራርሳ ስለድረ ገጹ አጠቃቀም ሲናገር እንዳለው፤ አንድ ተማሪ የፈለገውን መጽሐፍ ወይም የሚፈልገውን ርዕስ ጉዳይ ብቻ በመምረጥ በማንበብ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ጥያቄ ካለው ለሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ያቀርብለታል። ሰው ሠራሽ አስተውሎቱም ምላሽ ይሰጠዋል:: ከዚህ በተጨማሪ ምን ያህል እንዳነበበ (እንዳወቀ) ራሱን ለመፈተሽ ከፈለገም ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ጥያቄ እንዲሰጠው በመጠየቅ መፈተን ይችላል::
ይህ መተግበሪያ ለተማሪዎች ብዙ ነገሮችን ያቀልልላቸዋል የሚለው ተማሪ አራርሳ፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ በጣም ዘመናዊ መሆኑንና ተማሪዎች ማቅረብ የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች ብዙ ሳይለፉ በፍጥነት ለማቅረብ ያግዛቸዋል ይላል::
“አሁን ላይ ድረ ገጹን ማንኛውም ሰው የፈለገውን ዓይነት መጽሐፍ በመጫን መጠቀም ይችላል” የሚለው ተማሪ አራርሳ፤ በቀጣይም መተግበሪያውን በማሻሻል ብዙ ነገሮች በመጨመር በቀላሉ ለማንበብ፣ ለማጥናትና ለፈተና መዘጋጀት እንዲችሉ ለማድረግ እንሰራለን ብሏል::
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ተማሪ አማኑኤል አያሌውና ጓደኞቹ ‹‹አድ ማስተር›› የተሰኘ ለሥራ ቀጣሪዎች እና ተቀጣሪዎች የሚያገለግል የዌብ ሳይት መተግበሪያ በውድድሩ ይዘው ቀርበዋል:: ተማሪዎቹ ያበለጸጉት ይህ መተግበሪያ፤ ሥራ ቀጣሪዎች እና ተቀጣሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው የሚፈልጉትን ለሥራ ብቁ የሆነ ሰው መለየት ያስችላል::
ለምሳሌ አንድ ቀጣሪ ድርጅት ሠራተኛ ፈልጎ ቅጥር ሲያወጣ ለዚያ የሥራ መደብ እስከ 300 ሰዎች ሊያመለክቱ ይቻላሉ:: ተማሪ አማኑኤል እንዳለው፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ሦስት መቶ ሰዎች ያቀረቡትን የሥራ ማስረጃ በሚገባ ከመረመረ በኋላ ከእርሱ ውስጥ ከተቀመጠው መስፈርት የሚያሟሉትን ለሥራው የሚመጥኑ ብቁ አመልካቾች በየደረጃቸው በማስቀመጥ እስከ 70 በመቶ ውጤት ያላቸውን በመምረጥ ማለፋቸውን ያመለክታል:: ሌላኛው ፕላትፎርም ደግሞ የሰው ሠራሽ አስተውሎቱን ተጠቅሞ የቃል ፈተና በመፈተን ከእነዚያ ውስጥ ለሥራው ብቁ የሆኑትን በመመረጥ በደረጃቸው ማስቀመጥ የሚያስችለው ነው::
ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ለተቀጣሪ ሠራተኞችም እንዲሁ ሥራ ለመቀጠር ሲያመለክቱ ያቀረቡትን የትምህርት ማስረጃ በመመልከት “ይህንን እንደዚህ ብታሻሻሉት” የሚል ምክረ ሃሳብ እንደሚያቀርብም ነው ተማሪ አማኑኤል የገለጸው:: የተረሱ ሌሎች ነገሮች ካሉም እንደሚያስታወስ ይናገራል:: ይህም ለቀጣሪዎችም ሆነ ለተቀጣሪዎች ሥራዎችን በማቅለል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራና ሠራተኛ ለማገናኘት ያስችላል ይላል::
መተግበሪያው ላይ ለቀጣሪ ድርጅቶች ዳሽ ቦርድ እንደሚኖረው ጠቅሶ፣ በዚህም የሚፈልጉትን መለጠፍ እንደሚችሉም ጠቁሟል:: በቀጣይ ሌሎች መካተት ያለባቸው ነገሮች ካሉም በመጨመርና በማስፋት የተሻለ ነገር ይዘው እንደሚቀርቡ ጠቁሟል::
የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየው ማሞ በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የማንበብ ባሕልን ከማሳደግ ባሻገር ሀገሪቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ላይ የምትሠራውን ሥራ ለማሳለጥ ነው ውድድር እና ዓውደ ርዕዩ የተዘጋጀው።
በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ47 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ሦስት ሺህ 709 ተማሪዎች ተሳትፈዋል:: ውድድሩ በተለየ ሁኔታም ከ500 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን ያሳተፈ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ስምንት ተወዳዳሪዎች ወደ መጨረሻውን ዙር ማለፍ ችለዋል::
“ውድድሩ በተለይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ተማሪዎቹ ያቀረቧቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ችግር ፈቺ የሆኑና በአፍሪካ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ውድድሩ በአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የተካሄደ ሲሆን፣ ቱኒዚያ፣ ናሚቢያ እና አልጄሪያ በቅድመ ተከተል ከ1 እስከ 3ኛ በመውጣት የ30 ሺህ ዶላር አሸናፊ መሆን ችለዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም