ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ታላቅ ሀገር ነች፡፡ በአለማችን ጥንታዊ ከሚባሉ የመንግስትነት ታሪክ ካላቸው ሀገራት ተርታ ነበርን፡፡ የሮማው የባይዛንታይን ኢምፓየር በአለም ገናና በነበረበት፤ የግሪክ ስልጣኔ የፈላስፋና የሊቃውንቶቹ ታላቅነት ገዝፎ በአለም በረበበበት የሩቅ ዘመንም ኢትዮጵያና ልጆችዋ ነበሩ፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርት ለፈረንሳይ፤ ቢስማርክ ለጀርመን ታላቅነት በሮጡበት ዘመንም ኢትዮጵያና ልጆችዋ በአስተውሎት ይመለከቱ ነበር፡፡ጥንትም የነበርነው ዛሬም ያለነው እኛው ነን፡፡
የአባቶቻችን ልጆች የመሆናችን ልዩ ምስጢር የሚገለጠው በደም መስዋእትነት ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር እኛም ለባለተራው ትውልድ በታላቅ ክብር ጠብቀን ከነሙሉ ክብሯና ነጻነትዋ ለማስረከብ ታላቅ ሀገራዊና ትውልዳዊ አደራ በጫንቃችን ላይ መገኘቱ ነው፡፡ይህን አደራ ለመወጣት እያንዳንዱ ዜጋ በትጋት መንቀሳቀስ ሀገሩን መጠበቅ መንከባከብ ግዴታው መሆኑን መረዳት ግድ ይለዋል፡፡የተጀመረውን ለውጥ በጽናት መጠበቅ ከጥቃት መከላከል ቀዳሚ አጀንዳው ሊሆን ይገባዋል፡፡
ኃያላን መንግስታት ዓለምን ለመቀራመት በዘመቱበት፣ አዶልፍ ሂትለር ድፍን አውሮፓን በዘር ልክፍትና የበላይነት ተጠምዶ የአርያን ዘርና ደም የዓለም ደም ሁሉ የበላይ ነው በሚል እሳቤ ድፍን አውሮፓን በእሳት ባነደደበት ዘመን፤ የእርሱም አምሳያ የሆነው የኢጣሊያው ዱቼ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያና ልጆቿን ለማስገበር ቅኝ ለመግዛት እኛው ላይ በዘመተበትም ዘመን ያልተንበረከኩ ለሀገራቸው ታላቅ ፍቅር የነበራቸው ጀግኖች የነበሯት ሀገር ናት-ኢትዮጵያ፡፡ ጥንትም የነበርነው ዛሬም ያለነው እኛው ነን፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ ሀገሩን ጠብቆ የኖረው፡፡ያለው፡፡ምድር ከተፈጠረች ጀምሮ እንደ ሕዝብ የኖርን፤ የዓለም የሰው ዘር የመጀመሪያው መገኛ ምድር የሆንን፤ በቅዱሳን መጽሃፍት ኢትዮጵያዊ የሚለው ስማችን ከ54 ጊዜ በላይ ደጋግሞ የሚነሳ በታላላቆቹ የዓለም ጸሀፍት እነ ሆሜር ጭምር ስለማንነታችን የተመሰከረ የተዘከረ፤ በቀደምት የአውሮፓም የአረቢያም ተጓዦች ሰፊ ታሪክ የተጻፈልን ነን-እኛ ኢትዮጵያውያን፡፡ይሄንን ክብርና ታላቅነት ጠብቆ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ሀገርን መጠበቅ የትውልዱ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡
ዛሬ ያለው አንዱ ሩጫ ሀገራችንን ለመበታተን እኛነታችንን ለማፍረስ በብሔር ብሔረሰቦች ስም የሚደረገው መክለፍለፍና አትራፊ ያልሆነ ንግድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጥንትም በአብሮነት ኖረው ችግርና ደስታቸውን ተካፍለው ተጋብተው ተዋልደው ተቻችለው ተከባብረው ሺህ ዘመናትን የዘለቁና ዛሬም ያሉ ሕዝቦች ናቸው፡፡
ብሔራዊ ጭቆና ተወግዶ የሁሉም ነጻነት የእምነት፣ የባሕል፣ የቋንቋ፣ ነጻነት ተንቀሳቅሶ የመስራት በመረጡት ቦታ የመኖርም ሆነ የመስራት፣ ሀብትና ንብረት የማፍራት፣ የፈለጉትን እምነትና የፖለቲካ አመለካከት በነጻነት የማራመድ፣ የመደራጀት መብት ሙሉ በሙሉ በተከበረባት ኢትዮጵያ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት መሞከር ተቀባይነት የለውም፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ነጻነት በእኩልነት የተከበረባት የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በአደባባይ በታወጀባት ሀገር በጋራ ቆሞ ሀገር ከማልማት ውጪ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ መሞከር ኪሳራው መመለሻ የለውም፡፡
ዓለም በታላቅ ስልጣኔና እድገት ወደ ሕዋ እየተመመ ባለበት ሰአት እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የጎጥና የጎሳ ፖለቲካ መንስኤነት ሀገራዊ ትርምስ መፍጠር ከስልጣኔም ከዘመን እድገትም የመፋታት ድንቁርና ነው፡፡ ለዚህ ነው ቆም ብለን ማሰብ ትእግስትና አስተዋይነት ሊኖረን የሚገባው፡፡
ሀገርን ለማፍረስ መታገል ታሪክን ማፍረስ ነው፡፡ትውልድን ማፍረስ ነው፡፡የሚሊዮኖችን ቤትና ንብረት ሀገራዊ ሀብትን ማፍረስ ነው፡፡በዜጎች በሕጻናት፣ በአዛውንቶች፣ በአሮጊቶች፣ ሰርቶና ለፍቶ በሚያድረው ሕዝብ መቀለድ መነገድ ነው፡፡ማብቂያ የሌለው መመለሻም የማይኖረው የጥፋት የእልቂት የመከራ ድግስ ውስጥ መግባት ማለት ነው፡፡ይህ አጀንዳ የሕዝብ አይደለም፡፡ሕዝብ ሰላምን ፍቅርን አብሮነትን ሕብረትን ሰርቶ ማደግን የሀገርን መልማት የሕይወቱን መለወጥ ነው የሚፈልገው፡፡ሕዝብ ከሀገሩ ሰላምና ደህንነት በላይ አጀንዳ የለውም፡፡
የሚሆነው ሁሉ የሚሆነው ሀገር ስትኖር ነው፡፡ ልማቱ፣ እድገቱ፣ የኑሮ ለውጥ፤ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲም ሆነ ምርጫው የሚኖረው የሚታሰበው በሀገር ሰላም መኖር መሆኑን ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡በሀገራችን ያሉት ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት በሰላም በፍቅር ተከባብረው የኖሩ፣ በደስታና በሀዘን የማይለያዩ፣ የተጋቡ የተዋለዱ የመሆናቸውን ያህል መቼም ሆነ መቼም አይጋጩም፡፡ይህን የማጋጨት እኩይ አላማ የሚያራምዱት ግለሰቦችና የፖለቲካ ቡድኖች ናቸው፡፡
ሕዝብን ከሕዝብ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ለማጋጨት የሚደረገው ጥረት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማሰናከል የተጠነሰሱት ሴራዎች አንዱ አካል ነው፡፡አድብተው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚፈጽሙት ወንጀል ነው፡፡የእነሱ ቆይታ ደግሞ ውስን ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ጥረት ማድረግ የኋላ ኋላ ሴራው መልሶ የሚባርቀው በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ነው፡፡ጥንትም የነበርነው እኛ ዛሬም ያለነው እኛ ስለሆንን በሕዝባችን መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩትን ሁሉ ያለርህራሄ እንመከታለን፡፡ ለሀገራችን ሰላምና ክብር በጽናት እንቆማለን፡፡
በሀገራችን ውስጥ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖራቸው የውበታችን መገለጫና ድምቀታችን እንጂ የመሻኮቻና መናቆሪያ፣ የእርስ በእርስ መባያ ከቶውንም ሊሆን አይገባውም፡፡ ቻይና ከ56 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ሰፊ እምነቶች ባህሎች ቋንቋዎች እንዲሁም 1ነጥብ4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፡፡ ከድህነት ወለል ተነስታ የዓለማችን መሪ ኢኮኖሚና መሪ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ሀገራቸውን ወደ ታላቅነት ምእራፍ ያሸጋገሯት በፍቅር በሕብረት በመቻቻል በመደማመጥ ስራና ስራን ብቻ ሃይማኖታቸው አድርገው በጠንካራ ዲስፕሊን ባሕልና ስነምግባር እየታገዙ ስለሰሩ ነው፡፡
ሕንድ በዓለማችን የ1ነጥብ1 ቢሊዮን ሕዝቦች መኖሪያ ቤት ናት፡፡ከ330 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የተለያዩ እምነቶች ባሕሎች ቋንቋዎች አሏት፡፡ከድህነት ተነስታ ዛሬ ወደታላቅነት የእድገት ማማ ጉዞዋን ቀጥላለች፡እንዲህ እንደ እኛ ሲናቆሩ ሲባሉ ሲገዳደሉ አይኖሩም፡፡የእኛ አሳፋሪ አሳዛኝም ጉዳይ ነው፡፡
ያልታደልነው እኛ አይናችን እያየ ዓለም በስልጣኔ ቀድሞን ሲገሰግስ እጅግ ኋላቀር በሆነ የዘርና የጎሳ ፖለቲካ ተጠምደን፣ መሬት መኖሪያ ብቻ ሳትሆን መቀበሪያችን መሆኗን ረስተን በመሬት ፍቅር ስንንገበገብ፤ይዞታችንን ለማስፋት አልፈን ሄደን የሌላውን ወገን ወንድም ቤት ስናፈርስ፣ መሬቱን ስንነጥቅ፣ ስናፈናቅል፣ ከክልላችን ወጣ ስንል ስንደበድብ፣ ስንገድል ሴቶች ስንደፍር ውለን እናድራለን፡፡ አለመሰልጠን ብቻ ሳይሆን ወደ አውሬነትም የሚያደላ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በላይ ከንቱነት የለም፡፡
ይህ ሁሉ ከታላቅነት ይልቅ ወደ ትንሽነት፣ ከብርሀን ይልቅ ወደ ጨለማ የማሽቆልቆል ጉዞ ነው፡፡ በእውነቱ ከባሕልና ጨዋነታችንም ተፋተናል፡፡በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ለማጥፋት ለዘመናት ሲያደቡ የነበሩ የውጭ ኃይሎች የእኛኑ የእርስ በእርስ መባላት በመጠቀም ሽፍን አጀንዳቸውን ለማራመድ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ለከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲያቸው ስኬት ሁሉንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉም እናውቃለን፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ፣ መሳሪያ በማስገባት፣ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት ሕዝብ ከሕዝብ እንዲባላ እንዲጫረስ ለማድረግ ሌት ተቀን እየተጉ ይገኛሉ፡፡ ሀገራችንን ለችግርና ለመከራ አሳልፈን እንዳንሰጥ በብርቱው ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ጥንትም የነበርን እኛ ዛሬም ያለነው እኛ እንደመሆናችን መጠን የእርስ በእርስ ግጭቶችን፣ መከፋፈሎችን፣ መባላቶችን፣ ንትርኮችን አቁመን ቀድሞ በነበረው ፍቅራችን አብሮነት ወዳጅነትና ወንድማማችነት በመጽናት የሀገራችንን ሕልውና ጠብቀን ማስቀጠል ለነገ የማይባል የቤት ስራችን ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦችን በማጋጨት ትርፍ እናገኛለን በሚል የሚሰሩት ወገኖች ተላላኪዎቻቸውን በተለያዩ ክልሎች በማሰማራት በግልጽና በስውር ትንቅንቁን ይዘውታል፡፡
ለዚህም ዝግጅት ከስነልቦና ጦርነት እስከ ሽምቅ ተዋጊ ስምሪት ድረስ ተራምደዋል፡፡ ድንገተኛና ያልተጠበቁ ጥቃቶችን መፈጸም አንዱ የእርምጃቸው አካል መሆኑን እያየን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጥንትም የነበሩ ዛሬም ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው፡፡ እርስ በእርስ እንዲባሉ እንዲፋጁ የተወጠነው ሴራ አብሮነቱና አንድነቱ ከአለት በጸና ሕዝብ ውስጥ ፍሬ አያፈራም፡፡ሊዘልቅም አይችልም፡፡ ጥንትም የነበርነው እኛ ዛሬም ያለነው እኛ ነን፡፡ በጸና አንድነትና ፍቅር ኢትዮጵያን መጠበቅ የትውልዱ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡