ቀይ ባህር የአብሮ ማደግ ተስፋ

ከሰሞኑ ሀገራዊ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ የቀይ ባህር /የወደብ/ ጉዳይ ፊተኛ ነው። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ እንደራሴዎችን ሰብስበው ስለጉዳዩ አጽንኦት ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ሽፋን ያገኘ ሆኗል። ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተነሱ እና ከተተነተኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ቀዳሚው ነው።

የቀይ ባህር ጉዳይ አጽንኦት ተሰጥቶት ርዕስ ከመሆን ባለፈ ወደተጨባጭ እውነታ እንዲመጣ ያደረገው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። የመጀመሪያው የሀገራችን የሕዝብ ቁጥር አሰፋፈርና በየዓመቱ እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ምጣኔ ነው። ከቀይ ባህር እና ከህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ መገኘታችን የባህር በር ጥያቄያችንን ምክንያታዊ ከማድረጉ ጎን ለጎን ተዓማኒነት ያለው ያደርገዋል።

ይሄን በመሰለው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ያነሳችው ጥያቄ በበጎ ጎኑ ሊታይ የሚችል፤ አሁን ካለው የሕዝብ ቁጥርና የፍላጎት መናር አኳያ ደግሞ እንደህልውና ሊታይ የሚችልም ነው።

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ታሪክ ውስጥ ቀይ ባህርን እና ዓባይን ለይቶ ማየት አይቻልም። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት የተሰማውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር መጥቀስ ይቻላል። ‹ቀይ ባህርና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተቆራኙ፣ ለኢትዮጵያ እድገትና ጥፋት መሠረት የሚሆኑ ናቸው። ከዚህ የተነሳም ከርዕሱ መሸሽ አይቻልም።

እውነት ነው ታሪካችን ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የተቆራኘ ነው። ይሄን የተፈጥሮ ሀብት በነጻነትም ሆነ በይገባኛል መንፈስ ስንጠቀመው አንታይም። የአፍሪካ የውሃ ገንቦ የሚል ቅጽል ስም የወጣላት ሀገራችን ተፈጥሮ ሀብቶቿን እንዳትጠቀም የነበረውን ጫናና ጣልቃ ገብነት ሁላችንም የምናውቀው ነው።

በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለማመልከት እንደሞከሩት፤ በውሃ ተከቦ ውሃ መጠማት ዘመኑን የማይመጥን፣ ለትውልዱ ምክንያታዊ ሆኖ የሚቀርብ ምላሽ የማያስገኝ እሳቤ ነው። የትኛውም ሀገር ተፈጥሮ ሀብቱን ለፈለገው አላማ በኃላፊነት መንገድ የመጠቀም መብት አለው። ይሄን መብት ለማረጋገጥ አንቀጽ መጥቀስም ሆነ ስምምነት መፈራረም እምብዛም የሚያስፈልገው ሆኖ አይገኝም። አሁን ባለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወሳኙ ነገር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ውይይት መግባባት ነው።

ከቀይ ባህር ጋር የተያያዘውም ሰሞነኛ አጀንዳ መነሻው ውይይት ነው፤ መድረሻው የጋራ ተጠቃሚነት ነው። በውይይትና ታሪክን መሠረት ባደረገ የተግባቦት መርህ ካልተኬደ የሚጠበቀውን የአብሮ ማደግ ምኞት ላይጸንስ ይችላል። ከፖለቲካና ከብቻ ተጠቃሚነት ወይም ደግሞ፤ ከአንዳንድ አሉባልታዎች ለማጽዳት መነሻና መድረሻውን አላማና ግቡን ብዙኃነት ማድረግ የተሻለ እምርታን ያመጣል።

የጋራ ተጠቃሚነት በአንድ ሀገር የበላይነት ወይም ደግሞ ተጽእኖ ፈጣሪነት ሳይሆን ሁሉንም ማዕከል ባደረገ የአብሮ መልማት መርህ የሚሆን ነው። በቀይ ባህር ላይ የተነሳው ወቅታዊ ጥያቄም ከዚህ አንጻር የሚቃኝ ነው። የህዳሴ ግድባችንን ስንጀምር የነበረው ንትርክና ሰጣ ገባ የሚታወስ ነው። የባህር በር የማግኘቱ ጥያቄም ከዚህ እውነታ ጋር ተቆራኝቶ የሚታይ ነው።

በቀይ ባህር ጉዳይ በጋራ ተጠቃሚነት መግባባት ላይ መድረስ ይቻላል። አሁን የሚሰማው የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ራስ ወዳድ ወይም ደግሞ ጊዜውን ያልጠበቀ ጥያቄ ሳይሆን በብዙኃነትና በፍላጎት በሕዝብ ቁጥሯም እያደገች ለመጣችው ሀገራችን እጅግ የዘገየ ጥያቄ ነው። አብሮ ከማደግ ጎን ለጎን ጉርብትናን የሚፈጥር፣ በፖለቲካ በኢኮኖሚ በማህበራዊ ሕይወታችን እርስ በርስ የሚያስተሳስር ሌላው የአብሮነት ተምሳሌት ነው።

አንዳንዶች እንደሚሉት ትኩሳትን የሚፈጥር ሳይሆን የትውልዱን ጥያቄ፣ ፍላጎትና መሻት የሚመልስ፣ እኛ ያለንን ለሌሎች በመስጠት ሌሎች ያላቸውን ለእኛ በማካፈል የትብብር መንፈስን የምንፈጥርበት የትስስር በር ነው። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገ ለሚመጣው ትውልድና ፍላጎት የመኖር ዋስትና ከመሆን አኳያ የላቀ ዋጋ ያለው ነው።

ዓለም ላይ የባህር በር የሌላቸው ወደ 44 የሚጠጉ ሀገራት አሉ። አስገራሚው ነገር ከነዚህ ሀገራት ውስጥ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ይዛ የባህር በር የሌላት የእኛ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። በአፍሪካም ስናየው ተመሳሳይ ነው። በአህጉሩ ካሉ 17 የሚሆኑ ወደብ አልባ ሀገራት የሕዝብ ቁጥራቸው ተደምሮ የእኛን የማያክልበት አስገራሚ ሁኔታ አለ። ፍትህና እውነት በነገሰበት ፖለቲካ ጥላ ስር ብንሆን ያነሳንው ጥያቄ ተገቢ ነው። የማንንም ለመውሰድ ጥያቄ አላነሳንም። ታሪክ የሚያውቀውን በጊዜ ሂደት የራቀንን እውነት ለመመለስና አብሮ ለመጠቀም ነው።

የባህር በር ጥያቄ አንድ ነጠላ ትርጉም ያለው ሳይሆን ሰፊና በብዙ አቅጣጫ ሊታይ የሚችል ጉዳይ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ላሉና ብዙ ተስፋን ለሰነቁ ሀገራት ሚናው የት የሌለ ይሆናል። ከዘርፈ ብዙ ጠቃሚነቱ ጥቂቱን ብናይ፤ ‹ከጠብታ ውሃ እስከ ባህር ውሃ› በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር ላይ በስፋት ተነስቶ ለእንደራሴዎች የቀረበበትን ሁኔታ ማስታወስ ይቻላል።

ከኢኮኖሚያዊ አመክንዮ አንጻር ሲታይ የሀገር ህልውና ጥያቄ መሆን የሚችል ነው። በአንድ ሀገር ላይ ለድህነት እንደ ምክንያት ከሚወሰዱ መነሻዎች ውስጥ የባህር በር ከ20 እስከ 30 ከመቶ የሚሆነውን የሚይዝ ነው። ከመጪው ዘመን ሁለንተናዊ ፍላጎት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ፣ ለድህነትም ሆነ ለእድገት እንደዋነኛ መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ከማደግና ከመልማት የብዙኃነት መሻት ጋር ትስስር ያለው የተስፋና የብሩህ ነገ መነሻ ነው።

ከፖለቲካ እና ደህንነት አኳያ ሲተነተን ዘርፈ ብዙ አበርክቶ ያለው ነው። ከሉዓላዊነት አንጻር የሀገርን ሚስጢር ለመጠበቅ፣ ከተለያዩ የእቀባ ተጋላጭነት ለመዳን፣ ተፎካካሪ ኃይል ለመፍጠር እና በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ ወሳኝ ሚና ያለው ለመሆን የላቀ ሚና አለው። በታሪክ እና በትርክት መነጽር ስንቃኘው ደግሞ አሁናዊ ብዥታዎችን የሚያጠራ እውነትን እናገኛለን። ቅድመ ቅኝ አገዛዝ ኢትዮጵያ የባህር በር ነበራት። በአክሱም ዘመነ መንግሥት ሰፊ ግዛት ስለነበራት አዶሊስ የሚባል የባህር መተላለፊያ ነበራት። ይህን ወደብ በመጠቀም ከእስያ፣ ከሰሜን አፍሪካና ከጎልፍ ሀገርት ጭምር የንግድ እንቅስቃሴ ታደርግ ነበር።

በጊዜው በነበረው የባህር በር የአክሱም ስልጣኔ በዓለም ላይ ካሉ ፈር ቀዳጅ ስልጣኔዎች አንዱ ነበር። ለዚህ ስልጣኔ መነሻ ተደርገው የሚወሰዱት ደግሞ በባህር በር በኩል የተስተናገዱ የንግድ ልውውጦችና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተደማጭነቶች ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የታሪክ ተመራማሪው አየለ በከሪ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ላይ የባህር በርን በተመለከተ ‹የባህር በር ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው›።

የቀይ ባህር ጉዳይ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ አኗኗር፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጋር የነበረው ቁርኝት ጥብቅ እንደነበር ወደኋላ መለስ ብሎ ታሪክን ማስታወስ ያሻል። ጥንታዊ ስልጣኔዎቻችን ከዓለም ታላላቅ ሀገራትና ስልጡን ማህበረሰቦች ጋር በንግድና በሌሎች መስኮች መስተጋብር እንደሚያደርጉ ታሪክ አለን። እንደ ታሪከ አተያይ የትላንትዋ ባለ ወደብ ሀገር ዛሬ ላይ ለጎረቤት ሀገራት ብዙ ዶላር እየከፈለች እንድትገለገል ያደረጋት የራሱ የሆነ የተዛባ ትርክት ቢኖረውም እውነቱ ግን ቀይ ባህርና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የሚለው ነው።

ወደቀደመ ስማችን እንድንመለስ የራሱ የሆነ የተግባቦት አካሄድ ቢኖረውም ውይይትና መሰል የሰላም አማራጮች ግን ከየትኛውም በላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ከእርጋታና ስክነት በላይ አርቆ ማሰብን የሚጠይቁ ናቸው። በእርጋታና በስክነት አርቆ በማሰብም የጥያቄዎቻችንን ምላሽ መጠበቅ ከጋራ ተጠቃሚነት አንጻር የሚመከር ነው።

የባህር በር ባለቤትነትን ወይም ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው ርምጃ ውይይት ነው። ከውይይት ውጭ ለምንም ምቹ ባልሆነ ዘመን ላይ ነን። ለእንዲህ ዓይነቱ የጋራ ህልውና በጋራ ከመምከር ባለፈ ሌላ የተግባቦት አማራጭ የለም። የኃይል ርምጃ ትውልዱን ቁርሾ ውስጥ አሊያም ደግሞ በአብሮነት የዳበረውን ጉርብትና ከማጠልሸት ባለፈ ለማንም የሚበጅ አይሆንም።

ለዚህም የባህር በር ባለቤትነትን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተነሱ አንዳንድ የአካሄድ መርሆችን ማንሳት ይቻላል። የመጀመሪያው የይገባኛል ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ነው። ይሄ መርህ ከላይ ካወራነው የውይይት ጽንሰ ሃሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ሌላው የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረጉ ሰላምና አንድነት ፈጣሪ ሃሳቦችን መለዋወጥ ነው።

ይሄም ከመነሻ ሃሳባችን ጋር የሚስማማ ሁሉን አቃፊ ምክር ነው። በመቀጠል ከቅደመ ቅኝ ግዛት ይልቅ አሁናዊ የአብሮ መሥራትን ተጠቃሚነት ማስቀደም ነው። እንዲሁም ደግሞ በፍትህና በርትዕ ላይ የተመሰረተ ግብን መጥቀስ ሌላኛው የአካሄድ መርህ ሲሆን በመጨረሻም በኢኮኖሚያዊና በሕዝብ አሰፋፈር የተደገፈ ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው ሌላው ነገር ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት ነው። የባህር በር ጥያቄ የአንድ ግለሰብ ወይም ደግሞ የአንድ ፓርቲ ጥያቄ ሳይሆን ሁለንተናዊ መልክ ያለው ነው። በዚህም ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ንቃትና ዝግጁነትን በእጅጉ ይጠይቃል። ሌላው ከዚህ ጋር የተነሳው ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች ናቸው። ከጉዳዩ ጋር ልምድና ተሞክሮ ያላቸውን መልዕክተኞች መሰየም እንደዚሁ የተነሳ ሃሳብ ነው። አጀንዳውን አፍሪካዊ ማድረግና የሩቅ እና የቅርብ ወዳጅ ሀገራትን ይሁንታ ማግኘት በባህር በር ጉዳይ ላይ ልዩነት የምናመጣበት አካሄድ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ይሄን በመሰለው አካሄድ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ካላቸው ሀገራት ጋር ለውይይት መቀመጥ ተቀባይነት ለማግኘት የተሻለው መንገድ ነው። ቀጣይ በሚኖረው ሂደትም የወደፊቱን የተስፋ ብርሃን እንመለከታለን የሚል የጋራ ሃሳብ አለን። በውሃ ተከበን ውሃ መጠማታችን በህዳሴ ግድባችን ታሪክ እንደሆነ በወደብ ተከበን ወደብ ማጣታችንም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ ውይይት ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ እናደርጋለን።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You