የሕይወት ሰሌዳ

እንደ ልጅነቴ እግዜር ቢወደኝ እላለሁ። በልጅነቴ ውስጥ እግዜር የሌለበት አልነበረም። አይደለም ለምኜውና ደጅ ጸንቼው እንዲሁ ያማረኝንና ያሰኘኝን ካላንዳች ልፋት ነበር የሚሰጠኝ። ሌላው ቀርቶ የሆነ ወዳጄ ላይ ያየሁትንና ያማረኝን ልብስ ቤት ግዙልኝ ብዬ ሳላለቅስ ነበር ቅዳሜ ወይም ረቡዕ በአንዱ የገበያ ቀን አባቴ ሸምቶ የሚያመጣልኝ። ፍላጎቴን በአባቴ ፍላጎት ውስጥ አስቀምጦ ያዘባንነኝ ነበር… አይ እግዜር።

በልጅነቴ ጥብቆዬ ላይ በተፈጠረች ትንሽዬ ቀዳዳ ገላዬ ይታይ ነበር። ያልተቀደደ ሱሪና ጥብቆ የለኝም። እንዴት እንደሚቀደድ ሳላውቀው ከኋላ በኩል ሱሪዬ ሳስቶ ቀዝቃዛ ንፋስ ሲጀልጠኝ ነው የማውቀው። የሰፈራችን አስቀያሚው ልጅ እኔ ነኝ። በፉንጋነት የሚበልጠኝ አንድ ጓደኛ የለኝም። በሰፈር ጓደኞቼ የወጣልኝ ‹ዲያቢሎስ› የሚል ቅጽል ስም አለኝ። ይሄን ስም አባቴ ፊት ደፍሮ የሚጠራ አንድ ጓደኛ የለኝም። ለአባቴ የነፍሱ ጌጥ ነኝ። በአባቴ በኩል ከጓደኞቼ ሌላ ነኝ። ጓደኞቼን የምበልጣቸው የአባቴ ጥላ ሲያርፍብኝ ነው። ሁሌ እሁድ እሁድ ሰፈራችን ካለ ሆቴል ይወስደኝና ኬክና አይስክሬም ይገዛልኛል። እንዲህ ዓይነቱን ነገር እኔ ካልሆንኩ የትኛውም ጓደኛዬ በአባቱ በኩል አድርጎት አያውቅም። አባቴ በሄድኩበት ሁሉ ከጓደኞቼ ተንኮል የሚሰውረኝን እግዜርን ይመስለኛል። እንዲህ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?

ጓደኞቼ በእኔ ተፈጥሮ ነው የሚዝናኑት። ነፍስ የሌለው ወይም ደግሞ የማያመኝ እየመሰላቸው ለየትኛውም ክፉ ነገር እኔን ነው የሚመርጡት። ለምንም ነገር መሞከሪያቸው ነኝ። የፈሩትንና የሰጉትን ነገር በእኔ በኩል ነው የሚደፍሩት። አንድ ጊዜ ደፈቃ እንለማመድ ብለው ሁሉም ጓደኞቼ በየተራ አንገታቸውን ውሃ ውስጥ ከተቱ። እኔ እበልጣለሁ… እኔ እበልጣለሁ ከሚል ክርክር በኋላ የእኔ ተራ ደርሶ በል አንተ ደሞ ጀምር አሉኝ። ስፈራ ስቸር ወደ ውሃው ገባሁ። እንዳልወጣ ጭንቅላቴን ይዘው ተባብረው ደፈቁኝ።

ሳንባዬ አየር ሲያልቅበት ሁለመናዬ በአየር ናፍቆት ደበነ። መንፈራገጥ ሳቆም፣ አቅም አጥቼ እጃቸው ላይ ስዝለፈለፍ፣ ስሞት ለቀቁኝ። ግን እግዜር እንደ አላዛር በሙት ነፍሴ ላይ ሕይወት ዘርቶ ቀሰቀሰኝ። በዛ በድንነቴ ውስጥ ለማንም ያልተሰማ… ‹ነጋ..አንተ ነጋ ተነስ? የሚል ድምጽ ስሰማ ነበር። ከዛ ድምጽ በኋላ ነው የነቃሁት። የዛ ቀን የደፈቃ ቆይታዬ ማንም ያልቻለው የምንጊዜም ሪከርድ ሆኖ ተቀመጠልኝ። እግዜር ሁሌ ሪከርዴ ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ጓደኞቼ በምንም ችለውኝ አያውቁም። በግድና በውድ ፈቅጄም ይሁን ተገድጄ በተወዳደርኩባቸው የልጅነት ጨዋታዎች ውስጥ ፊተኛ ነበርኩ።

በሕይወቴ ያልተመለሱልኝ ዛሬም ድረስ የሚያመራምሩኝ ሁለት ነገሮች አሉ። አንዱ የሊዲያ ውበት ነው። ሌላኛው ደግሞ ሊዱ ከስንት ሸበላ እና ባለጸጋ ወንድ መሀል እኔን መምረጧ ነው። ትዝ ይለኛል… የሊዱ ውበት… አበባዎች ቀንተው ሲገላምጧት። ጤዛዎች አፍረው ሲያጎነብሱ። ትዝ ይለኛል ሳቋ… ብዙ ወንዶችን ሲያደናብር፣ ብዙ ትዳሮችን ሲያፈርስ። ትዝ ይለኛል አይኗ… በአንድ ጊዜ ጥቅሻ እኔ ነኝ ያለን ወንድ አፍር ከድሜ ሲያስግጡ። እንደጨረር ሲዋጉ… እንደ ጦስ ዶሮ ሲያንደፋድፉ። ትዝ ይለኛል አፍንጫዋ..ወጭ ወራጁን ሲያደናብር። አልፎ ሂያጁን ሲያስቀላውጥ። በውበት ሰገነት ላይ ሲንጎማለል።

ትዝ ይለኛል ከናፍርቷ… የዘመን ጌጥ አልቦ ሆኖ ከፊት ለፊት ጸዳሏ ላይ ተሰይሞ። የነፍስ ብርድ… የልብ ወበቅ ይሄን ሆኖ ላያት ሁሉ እዳ ሲሆን። ትዝ ይለኛል አረማመዷ… ትዝ ይለኛል እግር አጣጣሏ። የመላዕክት በሚመስል ዝማሜ ስትዘም። ሥርዓት በዋጀው ቄንጠኛ ርምጃ ስታገድም። ትዝ ይለኛል ሰውነቷ… ትዝ ይለኛል አካል ምስሏ..በውብ ጥበብ እንዳጌጠ የሸራ ላይ እንጥፍጣፊ ግርማ ለብሶ… ጸዳል ወርሶት። ትምህርት ቤታችን ውስጥ ውድና ንጹህ ልብስ ከሚለብሱ አስር ዘመነኛ ሴቶች ውስጥ አንዷ ናት። ትዝ ይለኛል… የጸጉሯ ርዝመት… የሰውነቷ ቅላት። ትዝ ይለኛል… ቆመው የሚያዩዋትን ወንዶች አልፋ ወደእኔ ስትመጣ። ከክላስ ስትወጣና ስትገባ እንደቦርሳዋ ጎኗ ለጥፋኝ እዩን ስትል።

በሊዱ በኩል ልጅነታችን ተመለሰ። በልጅነታችን አንድ ዓይነቶች ነበርን። ስናጠፋ፣ ስንደሰት፣ ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ አብረን ነበር። በአንዲት ሴት ነፍስ ላይ ዳግም ለመለምን። ፍቅር ትዝታ ያጠፋል፣ ወዳጅነትን ያስረሳል ሲባል የምሰማው ወሬ በእኔና በጓደኞቼ ላይ ሰርቶ እውነት ሆኖ አገኘሁት። በሊዱ በኩል አብዛኞቹ ጓደኞቼ ኩርፍ ናቸው። በእሷ በኩል ፍቅር መልኩን ጥሏል። ምንም ከሌለኝ ከእኔ በቀር ሁሉም ጓደኞቼ በእሷ ፊት አሪፍ ሆኖ ለመታየት የብኩርና ውድድር ይዘዋል። እኔ ድህነቴንና ፉንጋነቴን አምኜ ለውድድር አልቀረብኩም። ምን ባምር ነፍሷን እንደማልማርካት ስላወኩ አርፌ ቁጭ ብያለሁ። ወደእኔ እንደማትመጣ እያወኩ ግን አፈቅራት ነበር። በታሪክ በብዙ ወንዶች የተፈቀረች የመጀመሪያዋ ሴት ትመስለኛለች።

ክፍላችን ውስጥ 60 ተማሪ አለ። ከስልሳው 28ቱ ወንዶች ነን። በ28ቱም ተፈቅራለች። ፍቅራቸውን ከደበቁና ከሚያስመስሉ አንዳንድ ተማሪዎች በቀር በሁሉም ተጠይቃለች። ሊዱ እንደ ክሊዮፓትራ የጓደኞቼን አስተሳሰብ እንዳለ ነው የቀየረችው። በክሊዮፓትራ አፍንጫ የዓለም ካርታ እንደተቀየረ የጓደኞቼም አስተሳሰብ፣ ሥነ ልቦና ተቀይሮ ነበር። ለእሷ ያልገጠመ፣ ስለእሷ ያላዜመ አንደበት የለም። በሊዱ ውበት በኩል ብዙ የተደበቁ ተሰጥኦዎች አደባባይ ወጥተዋል። ከተንኮልና ከውሸት ውጭ ተሰጥኦውን የማያውቀው ፋንታ እንኳን በእሷ በኩል ነው ምርጥ ገጣሚ የወጣው።

እኔ ከምኑም ውስጥ የለሁበትም። ፍቅሬን በልቤ ይዤ ዝም ጭጭ። በዛ መልኬ ባወራት ነበር የሚገርመው። ወዳጆቼ የጣሉብኝ የትንሽነት መንፈስ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ነው ነፍስ የሚዘራው። ዲያቢሎስ እየተባልኩ አድጌ፣ በመልኬ የወዳጆቼ መሳቂያ ሆኜ ኖሬ እሷን ለመቅረብ አቅም አጣሁ።

የሆነ ነገር ትውስ አለኝ። ጉዳዬን ለፈጣሪ ስሰጥ እንዲህ ነኝ። ከረሳሁት የሆነ ጠቃሚ ነገር ጋር ተገናኘሁ። የሆነ ጊዜ ላይ ምን አሰኝቶት እንደሆነ እንጃ እናቴን እንዴት እንዳገባት ነግሮኝ ነበር። ያ የአባቴ ንግግር መጣብኝ። ‹እናትህ በጣም ቆንጆ ሴት ነበረች። እኔ ደግሞ እንደምታየኝ አልቅት ነኝ። ከውበቷ የማይወዳደር መልኬን፣ ከሴትነቷ የማይቆም ወንድነቴን ያስጠጋሁት በዝምታ ነው… ሁሉም ስለእሷ ሲጮሁ ዝም በማለት› አለኝ። በእጁ የያዘውን ጉርሻ ወደአፉ እያለ ‹የምትፈልገውን ነገር የአንተ ለማድረግ ከሌሎች ጋር አትዋደቅ… አትፎካከር ዳር ሆነህ ተመልከት። እናትህን የእኔ ያደረኳት ከሚፈነካከቱላት እልፍ ወንዶች ውስጥ ሳልደባለቅ ዳር ቆሜ በማየት ነው› አለኝ አላምጦ የጨረሰውን ምግብ ወደሆዱ እየሰደደ።

ንግግሩን ሲቋጭ በአንዲት መቼም በማትረሳ ወርቃማ ንግግር ነበር ‹ፍቅር ከጩኸት ይልቅ ዝምታ ውስጥ ነው ያለው። ዝም ካላልክ በጩኸት ፍቅርን አትደርስበትም። በመተው ውስጥ ብዙ መፈላለግ አለ። የምትወዳትን ሴት የረሳሃት ምሰል። በጥበብ ውስጥ ዝም ካልክ በሞኝነት ከሚጮሁ እልፍ ነፍሶች በላይ የአንዲትን ሴት ነፍስ መማረክ ትችላለህ› አለኝ። በተለይ የመጨረሻዋ ንግግሩ ስሰማ በአባቴ አፍ እግዜር የተናገረ ነበር የመሰለኝ።

የእናቴንና የአባቴን ታሪክ በሊዱ ላይ ልተገብረው ሀ አልኩ። በአባቴ ምክር ሄጄ… ሊዱን የውሸት ረሳኋት። በብዙ ወንዶች ከበባ ውስጥ ያለችውን ነፍሷን የዘነጋኋት መሰልኩ። ሊዱ የእኔ ትሆናለች ብዬ አይደለም በውኔ በህልሜም አልገመትኩ። ለዛ ፊትና ለዛ ወንድነት ሚስት ትሆናለች የሚል አንድም ጥርጣሬ በአእምሮዬ ውስጥ አልነበረም። የሆነው ሆነና… ሊዱ የኔ ሆነች። ዝምታዬ ፈጠራት። በነዛ ሁሉ በሚጮሁ አፎች ላይ ተረማምዳ ዝም ወዳልኩት ወደ እኔ መጣች። በሊዱ ጉዳይ እግዜር ቀድሞ አባቴ ይከተላል። ለዛች ነፍስ ከዝምታ ሌላ አስተዋጽኦ አልነበረኝም። ከልጅነቴ ጀምሮ ላልተወኝ ጌታ እኩል ባይሆን የማያሳፍር ውለታ ባስብ አጣሁ።

የአባቴ ንግግር መነሻውና መድረሻው አሁን ነው የገባኝ። ማንም እንደማያገባኝ ስላወቀ፣ የትኛዋም ሴት እንደማትቀርበኝ ስለገባው ይመስለኛል እንደዛ ያለኝ። በእማዬ ማህጸን በእኔ በኩል ራሱን ደግሟል። በሊዱ ማህጸን እኔን እንዳልደግመው ለፈጣሪ ሌላ አደራ አለኝ። በአንድ ቤት ውስጥ እኔና አባዬ በቂዎች ነን። ልጄ እንደ እኔ ለምንም ነገር እግዜርን የሚያስቀድም ሆኖ እንዲኖር አልፈልግም በአንዳንድ ነገሮች ላይ ራሱን እንዲያጋፍጥ… ራሷን እንድታጋፍጥ ከእኔ መልክ የራቀ ሰውነት እሻለሁ። እግዜር ባይቀድምለት ኖሮ ይሄ ፊት ከዛ እዚህ ለዛውም ሊዱ ላይ በምን ኃይሉ ይወድቅ ነበር? አይረባም በተባለው ልጅነቴ ውስጥ ብዙ መርባቶችን አኑሮ፣ በሊዱ ደጅ ላይ ሲያቆመኝ እግዜርን ከልቤ ሻትኩት። ለሆነልኝ የምሆንለት ባይኖርም፣ ላደረገልኝ የማደርግለት በጣም እንዲሁ ግን አፈቅረዋለሁ። ነፍሴ በእሱ ጫንቃ ላይ እሽኮኮ ላይ ባታርፍ ምን ይውጣት ነበር?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2016

Recommended For You