በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተመዘገበው ውጤት ብዙዎችን እያነጋገረ ነው:: ገሚሱ ተማሪውን ሲወቅስ፣ ከፊሉ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱን ያነሳል:: በትምህርት ዘመኑ ለፈተና የተቀመጡት ተማሪዎች 845 ሺህ 188 ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥም ከ356 ሺህ 878 የተፈጥሮ ሳይንስ፣ 488 ሺህ 221 የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ናቸው:: በተፈጥሮ ሳይንስ የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 22 ሺህ 974፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8 ሺህ 250 ተማሪዎች መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል::
በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 845 ሺህ 188 ተማሪዎች ውስጥ 27 ሺህ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ናቸው።
ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 3.2 በመቶ (3.2%)ብቻ ናቸው:: ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ0.01 ቀንሷል። በትምህርት ዘመኑ ተማሪዎች ያስፈተኑ ትምህርት ቤቶች 3 ሺህ 106 መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል:: ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 328 ትምህርት ቤቶች ደግሞ አንድም ተማሪ ማሳለፍ እንዳልቻሉም ተመልክቷል:: ይህም በመቶኛ ሲታይ 42.8 ከመቶ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ ያልቻሉ እንደሆነም ተጠቅሷል::
በትምህርት ዘመኑ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የተመዘገበው 649 ሲሆን፤ ይህም ውጤት የተመዘገበው በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ በሴት ተማሪ ነው። ይህን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ሃናን ናጂ ትባላለች:: በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ክሩዝ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችውን ሃናን ናጂን አግኝተን አነጋግረናታል::
ተማሪ ሃናን እንደነገረችን፤ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ትምህርቷን የተከታተለችው ክሩዝ ትምህርት ቤት ነው:: እስከ ሰባተኛ ክፍል በነበረው የትምህርት እርከን የደረጃ ተማሪ እንደነበረች ታስታውሳለች:: ይሁን እንጂ በጣም ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አልነበረችም:: ሰባተኛ ክፍል ስትደርስ ግን ከክፍል አንደኛ መውጣት እንዳለባት ዓልማ ትኩረቷን ትምህርት ላይ አደረገች:: የሚሰጣትን የቤት ሥራ በወቅቱ በመሥራት፣ በክፍል ውስጥም በመከታተልና በጥናትም ጊዜ በመስጠት ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ የአንደኝነቱን ደረጃ ለማንም አሰልፋ ሳትሰጥ እስከመጨረሻው ዘለቀች።
በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 100% በማምጣት ነው ወደ ሚቀጥለው ትምህርት ያለፈችው:: በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታዋ እንዲሁ ሙሉ ጊዜና ትኩረቷን ለትምህርቷ በመስጠት በክፍል ውጤት 9ኛ ክፍል 97፣ 10ኛ ክፍል 98፣ 11ኛ ክፍል ደግሞ 99 አማካኝ ውጤት በማስመዝገብ ስኬታማ እንደነበረች አስታውሳለች::
የ2015 ብሔራዊ ፈተናንም እንዲሁ በስኬት ለማጠናቀቅ ቀድማ ዝግጅት ማድረጓን የምትገልፀው ሃናን፤ ”አስራ አንደኛ ክፍል ከጨረስን በኋላ የአስራ ሁለተኛ ክፍል የክረምት ትምህርት ነበረን ከዛን ጊዜ ጀምሮ ለፈተና እየተዘጋጀሁ ነበር” ትላለች። ባስመዘገበችው ውጤት በራሷ እንደኮራችና ደስተኛም እንደሆነች የምትገልፀው ሃናን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ውጤት አመጣለሁ ብላ ባትጠብቅም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እንደምትችል ግን እርግጠኛ እንደነበረች ተናግራለች።
ሃናን ስለትምህርት ተሞክሮዋ እንዳጫወተችን፤ ወደ ክፍል ከመሄዷ በፊት ቀድማ የማንበብና የመዘጋጀት ልምድ አላት:: ይህ ልምዷ በአጠቃላይ የትምህርት ውጤቷ የተሻለ እንዲሆን አግዟታል:: ሁሉም ተማሪ ጊዜውን በአግባቡ ከተጠቀመበትና ለትምህርቱ ትኩረት ከሰጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ትገልጻለች::
ከፍተኛ ቁጥር ካለው ተፈታኝ መካከል ከፍተኛ ውጤት ማምጣት የተለየ ስሜት እንዳለው የምትናገረው ሃናን፤ ጥረት ከተደረገ ስኬት ላይ መድረስ እንደሚቻል ከራስዋ ተሞክሮ ማግኘቷንም ታስረዳለች::
ተማሪ ሃናን ከሥር ጀምራ ለትምህርት የሰጠችውን ትኩረት በመቀጠል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚኖራት የትምህርት ቆይታም በስኬት ለማጠናቀቅ መዘጋጀቷን ነው የነገረችን:: ወደፊት በባዮ ሜዲካል የትምህርት ዘርፍ ተመራማሪ የመሆን ፍላጎት አላት:: በመድኃኒት ልማት ላይ መሥራት ስለምትፈልግ በዚህ ዙሪያ ተሰማርታ ለሀገሯና ለሕዝቧ አንድ ትልቅ አበርክቶ ማኖር እንደምትፈልግ ገልፃለች።
“የእኔ ትልቁ አቅምና ለዚህ ስኬት ያበቃኝ የጊዜ አጠቃቀሜ ጥሩ ነው”› የምትለው ሃናን፤ በተለያዩ ነገሮች ጊዜ ከማባከን ይልቅ ሙሉ ሰዓቷን ለትምህርትና ለትምህርቷ ብቻ መዋሏ እንደሆነ ገልፃ፤ ከትምህርቷ ውጪ ለሌላ ነገር ጊዜ እንዳልነበራት ነው የተናገረችው:: ይህ ሁሉ ልፋት በመጨረሻ በስኬት በመጠናቀቁ ደስተኛ መሆኗን ገልፃለች።
ሃናን ስለፈተናውም እንደገለጸችልን፤ ፈተናው ከሌላው ዓመት የተለየና ከባድ ነው የሚባል አይደለም:: ጥሩ ዝግጅት ከተደረገ መሥራት ይቻላል:: በፈተናው ስለተመዘገበው ውጤትም አብዛኛው ተማሪ ለፈተናው የሚመጥን ዝግጅት አድርጓል የሚል እምነት የላትም:: እርስዋ እንዳለችው፤ ፈተና ሲቃረብ ብቻ ሳይሆን ከታች ጀምሮ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል:: “ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው የተሰጠው:: በዚህ ምክንያት ኩረጃ የለም:: ሁሉም የራሱን ነው የሠራው:: ይህ ለተገኘው ዝቅተኛ ውጤት ምክንያት ይሆናል የምል ግምት አለኝ” ስትልም ገልጻለች::
ከእርስዋ በኋላ ላሉ ተማሪዎችም በሰጠችው ምክር ጊዜያቸውን ላልተገባ ነገር ከማዋል ተቆጥበው በትምህርታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ለውጤት ለመብቃት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል:: በኋላ ላይ ለቁጭት እንደሚዳረጉ ከወዲሁ ሊረዱ ይገባቸዋል:: በጥረት የሚገኝ ውጤት ደስታን እንደሚሰጥ ከእርስዋ ውጤት እንዲማሩም ምክሯን ለግሳለች::
ሃናን ለውጤቷ ማማር የቤተሰቦችዋ እገዛም ከፍተኛ መሆኑን ተናግራለች:: ቤተሰቦቿ በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ ከጎኗ ሆነው ሲያግዟት እንደነበር የምትናገረው ሃናን፤ ለፈተናው በአዕምሮ ዝግጁ እንድትሆን፣ እንዳትፈራ፣ እንዳትጨናናቅ በማድረግ የምትፈልገውን ነገር በማመቻቸት እንዳገዟት ገልጻለች:: ላደረጉላት ድጋፍም ቤተሰቦችዋን አመስግናለች::
ሁሉም ሰው ዓላማና ግብ ካለው ውጤታማ መሆን ይችላል የምትለው ሃናን፣ ማንኛውም ሰው ነገ ማሳካትና መድረስ ለሚፈልገው ደረጃ በሚችለው አቅም ተግቶ መሥራት እንዳለበት ገልጻለች:: ሌላው በትምህርት ዘመኑ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ኖላዊ ጌትዬ ይባላል:: ኖላዊ በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ 617 ነጥብ በማስመዝገብ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል:: ኖላዊ ሁሉንም ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ማሳለፍ ከቻሉ ጥቂት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው:: ከመጀመሪያው የትምህርት ደረጃዎች ጀምሮ በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ካላቸው ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል እንደነበር የሚናገረው ኖላዊ፤ በዘንድሮው ብሔራዊ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት ሙሉ ጊዜውን ትምህርቱ ላይ ብቻ በማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ይናገራል።
በ2011ዓ.ም የስምንኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣትና የኮተቤ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ቤት ያወጣውን የመግቢያ ፈተና በብቃት በማለፍ ትምህርቱን የቀጠለው ኖላዊ፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ውጤታማ ለመሆን ግብ አስቀምጦ ሲሠራ እንደቆየና የመጨረሻ ውጤቱም መልካም በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነ ተነግሯል።
ለፈተናው ዝግጅት ያደረገበት መንገድ ምን ይመስል እንደነበር ኖላዊ እንደነገረን፤ የትምህርት አይነቶች ተመሳሳይነት አላቸው፣ የአስራ አንደኛ ክፍል ከአስራ ሁለተኛ ክፍል ጋር ተዛማጅነት አለው፣ የትምህርት አይነቶቹን አነጣጥሎ ከማንበብ ይልቅ የሁለቱንም የትምህርት አይነቶች መጽሐፍት ጎን ለጎን አስቀምጦ አንድ ኖት/ማስታወሻ እንደሚያወጣና በዚህ መሠረት የያዘውን ማስታወሻ በማጥናት ነበር የሚጠቀመው:: እንዲህ ያለው የጥናት ዘዴ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤታማ መሆን አግዞታል።
የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ መምህራኖቻችን ይህንን የመሰለ ውጤት እንድናመጣ ለፍተዋል የሚለው ኖላዊ፤ የተለያዩ የማትሪክ ጥያቄዎችን በመስጠት፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመከለስ ለፈተናው ብቁ እንዲሆኑ መምህራኖቻቸው ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ይገልፃል።
ቤተሰቦቹም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በማቅረብ ድጋፍ ሲያደርጉለት እንደቆዩ የሚናገረው ኖላዊ፣ በተረጋጋ መልኩ መጨናነቅ ሳይኖር ትምህርቱን ማጥናት እንዲችል እገዛ ሲያደርጉለት እንደነበር ይናገራል። በመጣው ውጤት ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ኖላዊ ውጤቱ ግን ከዚህ በላይ ቢያንስ እስከ 625 ድረስ ከፍ ይላል ብሎ ጠብቆ እንደነበር ነገር ግን አሁን በተገኘው ውጤት እንዳልተከፋ ተናግሯል።
የአብዛኛው ተማሪ ውጤት ዝቅ የማለቱ ምክንያት ‹‹አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርቱን የመሥራት አቅምና ችሎታው እያላቸው ነገር ግን ጊዜያቸውን በአግባቡ አልተጠቀሙም:: በአዕምሮም ዝግጁ ሆነው አይደለም ለፈተና የተቀመጡት:: ይህ መሆኑም በመጣው ውጤት ላይ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል›› በማለትም አስተያየት ሰጥቷል::
ለፈተና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ባመሩበት ወቅት ያየው ነገር እንዳሳዘነው የሚናገረው ኖላዊ እንደገለጸው፤ አብዛኛው ተማሪ ዝም ብሎ ገብቶ ግቢ አይቶ ለመምጣት የመጣ በሚመስል መልኩ ግቢ ውስጥ በመጮህ፣ በመሮጥ ነው ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ የነበረው:: ብዙ ተማሪዎች ለፈተናው በአግባቡ ስላልተዘጋጁ ተስፋ በመቁረጥ ነው ለፈተና የተቀመጡት ሲል ትዝብቱን ይገልፃል።
በተጨማሪ ተማሪ ኖላዊ ሲናገር፤ ጥሩ ተማሪ ለመሆን፣ የአስተማሪ ጥረት በእጅጉ ያስፈልጋል:: እርሱ እንዳለው ለተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን ችግሩ የተማሪዎች ብቃት ከማነስ ጋር ብቻ አይያያዝም፤ የመምህራንም የማስተማር ብቃት መፈተሽ ይኖርበታል:: አንዳንድ ተማሪዎች ይህን ጉዳይ እንደሚያነሱም ያስረዳል:: እንዲህ ያለው ሀሳብ ለፈተና ወደ ግቢ ከገቡና ከእርሱ ጋር አብረው ከቆዩ ከሌሎች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ሲጫወቱ የተነሳ እንደሆነም ተናግሯል:: ይህም ዝቅተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያምናል:: በአጠቃላይ ለውጤት ቀውሱ የተማሪው፣ የመምህራን፣ የትምህርት ከባቢያዊ ሁኔታ የየራሳቸው ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግሯል።
“አንድ ነገር ለማሳካት እራስን ለዛ ነገር መስጠት እና ለሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ሳይበገሩ ለማለፍ ቁርጠኛ መሆን ወሳኝ ነው›› የሚለው ኖላዊ፤ ‹‹እንደ እኔ ያሉ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙ መልካም ነው” ይላል።
የወደፊት ዕቅዱን እና ምን ማሳካት እንደሚፈልግ ኖላዊ ሲናገር፤ ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ በማጥናት ባለሙያ የመሆኑ ሐሳብ አለው:: ከዚህ ውጪ በተለያየ ዘርፍ ዕውቀት እንዲኖረው ይሻል። ዘርፉ በጣም ሰፊ እንደሆነና ጠቅላላ ዕውቀትም እንደሚፈልግ ይገልፃል። ይህንን ለማሳካትም ትምህርቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በዘርፉ ጥሩ ዕውቀት ይዞ ወደ ሶፍትዌር / ኮምፒውተር ዘርፍ ተቀላቅሎ መሥራት እንደሚፈልግ ገልጿል።
ኢትዮጵያን በሶፍትዌር ልማት የሚያስጠራ እና ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርገውን ሥራ በተግባር መሥራት እና ማበርከት እንደሚፈልግ የተናገረው ተማሪ ኖላዊ፤ አሁን ላስመዘገበው ጥሩ ውጤት በመጀመሪያ ለአምላኩ፣ በመቀጠልም ሁለንተናዊ ድጋፍ ላደረጉለት መምህራኖቹ፣ ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብና በተለይ ደግሞ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹ ያለውን ምስጋናና አክብሮት ገልጿል።
በ2015 የ12ኛ ብሔራዊ መልቂያ ፈተና ባስመዘገቡት ውጤት ኮከብ መሆን የቻሉት ተማሪ ሃናንና ኖላዊ ለቀጣይ ተማሪዎች መልእክት አስተላልፈዋል:: የተማሪዎቹ መርሕ ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና ለትምህርትም ትኩረት መስጠት ለስኬት እንደሚያበቃ ነው:: ተማሪዎቹ አፅንኦት ሰጥተው ያስተላለፉት መልእክትም ተማሪዎች ዋና ሥራቸው ትምህርት መሆኑን ተገንዝበው አልባሌ ቦታ ከመዋል ተቆጥበው ጊዜያቸውን ለትምህርት ማዋል እንዳለባቸው ነው:: ተማሪዎቹ እንዳሉት ቀድሞ ባለመዘጋጀት በሚመጣ ውድቀት ከመቆጨት በየእለቱ አስፈላጊውን ነገር በማድረግ ለውጤታማነት መትጋት ይጠበቃል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2016