ጥላ

 ነፍስ ጥላ ናት… ከዚህ ወደዛ መራመጃ፡፡ ብዙ ደክሞኝ የማርፈው በፈገግታዋ ጥላ ውስጥ ነው፡፡ ማንንም የሚያሳርፍ የደግነት ጥላ አላት፡፡ ምን እንደሆንኩ አልነግራትም መከራዬን ላጋባባት ስለማልፈልግ ደህና መስዬ እታያታለሁ፡፡ መኖር አባዝኖኝ፣ ሕይወት አንከራቶኝ እየሳኩ መጥቼ ጉያዋ ውስጥ አርፋለሁ። የሴት ነፍስ የወንድ ልጅ ከዘራው ናት፡፡ አጎብድዶ መጥቶ ቀና ብሎ የሚሄድባት፡፡ አለመኖሯን ሳስብ እፈራለሁ። እሷ ባትኖር የሚሆነውን ለማሰብ ድፍረት አግኝቼ አላውቅም። ብዙ እልልታዎቼ ከእሷ መኖር ውስጥ ያገኘኋቸው ናቸው፡፡ ብዙ ምስጋናዎቹ በእሷ መኖር የተቀበልኳቸው ናቸው፡፡ አለመኖሯ ያስፈራኛል..ማሰብ የማልፈልገው ብፈልግ እንኳን ጀምሬ የማልጨርሰው የእሷን በእኔ ውስጥ አለመኖር ነው፡፡

ባትኖር የምሆነውን መገመት አልችልም፡፡ በእሷ በኩል ፈሪ ነኝ፡፡ ማንም የሚጎዳኝ በእሷ በኩል ነው። ብዙ የመከራ ፀሐዮችን፣ ብዙ የሕይወት ጠራራዎችን ተከልዬባታለሁ፡፡ የነፍሴ ጥላ ናት… ሀሩርና ብርዱን ያለፍኩባት..

ከድባቴ የሚያነቃ ከሞት የሚቀሰቅስ የሚመስል ሳቅ አላት፡፡ ከዘላለም እስከዘላለም እንደገደል ማሚቱ በጆሮ ላይ የሚያረብብ ሳቅ፡፡ የእየሱስን ድምጽ ሰምተው እንደለመለሙት ሣሮች፣ አፋቸውን ለዝማሬ እንደከፈቱት የቢታንያ ድንጋዮች ሳቋን ሰምቶ ማንም ዝም ማለት አይችልም፡፡ አባዬ ስትለኝ ያን ጊዜ ነው ሞትን የምንቀው።

እሷን ከምትመስል ሴት ነው የወለድኳት፡፡ በልጄ ውስጥ ቀይ ረጅም ሴት፣ ፀጉሮቿን ጀርባዋ ላይ የምትለቅ፣ ፒጃማ የሚያምርባት ሴት ትታወሰኛለች፡፡ ዝግ ብላ የምታወራ… ብዙ ቁጣዎቼን በትዕግስት አልፋ ባሏ ያደረገችኝ ሴት፡፡ በግራ ድዷ ላይ ድርብ ጥርስ ያላት… ስትስቅ መላዕክቶች የሚቀኑባት፣ ወጥቼ ስዘገይ አስር ጊዜ የምትደውል፣ ውጭ ቆማ የምትጠብቀኝ ሴት ትታወሰኛለች፡፡

ሀሳብ ወሰደኝ..

እለተ ሰኞ… ረፋዱ ላይ አረፋፍጄ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ቁርስ በልቼ ነፍሰ ጡር ሚስቴን ግንባሯ ላይ ስሜ ከቤት ወጣሁ። ስወጣ ተሰምቶኝ ከማያውቅ ከሆነ ባዶነት ጋር ነበር፡፡ ሃሳቤ ውስጥ እየተሰነቀረ የሚረብሽ የሆነ ሃሳብም አብሮኝ ነበር፡፡ ከቤት እንደወጣሁ ቀጥታ ወደሥራ ነበር የሄድኩት፡፡ ልቤ አላረፈም..ምን እንደሆንኩ ሳላውቅ ይጨንቀኝ ጀመር፡፡ በዛ ጠዋት ከሚስቴ ‹ሰላም ገባህ? ቀጥሎ እናቴ ነበረች የደወለችልኝ፡፡ እናቴ የሆነ ነገር ልትነግረኝ ፈልጋ እንዳልነገረችኝ በድምጽዋ ተረዳሁ። ምን ሆነሻል! ደህና አይደለሽም እንዴ? አልኳት ደም ብዛቷ ተነስቶ ከሆነ ብዬ፡፡

‹ጥሩም ህልም አላየሁ ብቻ ፈጣሪ ያውቃል.. ‹አንቺ ደግሞ በሆነ ባልሆነው መጨነቅ ትወጃለሽ› ብዬ ሰላም ዋይ ብያት ተለያየን፡፡ የእናቴ ሁኔታ ሲሰማኝ ከነበረው ስሜት ጋር መገጣጠሙ የእውነት እንድፈራ አደረገኝ፡፡ አንዳንድ ቀኖች ነገን የሚናገር አንደበት አላቸው የሚለው የእናቴ የዘወትር ንግግር ታወሰኝ፡፡ እናቴ በምታምነው በዛ ቀን ላይ ከእንቅልፌ እንደነቃሁ አመንኩ፡፡ ቀኑን እንዲችው ስጨነቅ ዋልኩ፡፡ ከአሁን አሁን አዲስ ነገር ተከሰተ እያልኩ ስሰጋ ቀኑ መሸ፡፡ ማታ እንደ ጠዋት አይደለም። ጠዋት የተስፋ መብቀያ ነው ማታ ደግሞ መድረቂያ። ሲመሽ ፈሪ ያደርጋል፡፡ ንጋት እንጂ ምሽት አቅም ይሰልባል። አቅሜ ተሰልቦ ወደቤት ገባሁ። ማታ ቤት ስገባ ምንም የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር እንደነበረ ሆኖ ጠበቀኝ፡፡ ሚስቴ እንደወትሮዋ በር ላይ እየጠበቀችኝ አገኘኋት፡፡ ግንባሯን ስሜ ተቃቅፈን በነፍሰ ጡር ርምጃ ቤት ገባን፡፡ ዝም ብዬ እንደተጨነኩ ሳስብ በሞኝነቴ ሳኩ፡፡

ራት በላን፡፡ ስለምትወለደው አዲሷ ልጃችን አውርተን፣ ስለሚወጣላት ስም የፍቅር ጭቅጭቅ ተጨቃጭቀን…ትራስ ተወራውረን ወደመኝታችን ሄድን። መኝታ ክፍል ስንደርስ እጄን ለቀም አድርጋ ‹እቀፈኝ! አለችኝ፡፡ እንኳን እቀፈኝ ተብዬ ወትሮም እሷን የማቀፍ ሱሰኛ ነኝ እንደተባልኩት ሆዷን በማይጎዷ መልኩ አቀፍኳት፡፡ ዛሬ አንተኛም… እያወራን እንድናድር እፈልጋለሁ› አንሾካሾከችልኝ፡፡

‹ማረፍ አለብሽ ባይሆን ነገ ከሥራ ቀርቼ እያወራን እንውላለን› አልኳት፡፡

እሺም እምቢም ሳትለኝ ትክ ብላ አስተዋለችኝ፡፡

‹ለምንድነው እንዲህ የምታይኝ?

እያየችኝ አይኖቿ እንባ ሲያመነጩ አየሁ፡፡ ‹ምን ሆነሻል?

‹እናቴ እኔን እንደወለደች ነው የሞተችው› አለችኝ፡፡

‹እሱን አውቃለሁ! ታዲያ ይሄ ካንቺ ጋር ምን ያገናኘዋል? ዝም ብለሽ ራሽን አታስጨንቂ› ስል በቀስታ ወደ አልጋው ጎተትኳት፡፡

‹ፈራሁ..! አለችኝ፡፡

አይዞሽ በሚመስል እቅፍ አደረኳት፡፡ ዝም ብላኝ ወዳልጋው ሄደች፡፡ የእናቴ የስልክ ጥሪ ሁለታችንንም ከሃሳብ መነጠቀን፡፡ ስልኩን ማንሳት ፈራሁ፡፡ ቀን ሙሉ የተጨነኩበት ስልክ አሁን ደግሞ ምን ሊነግረኝ ነው?

‹ስልኩን አንሳው እንጂ..! የሂሩት ድምጽ ተሰማ፡፡

‹መልሼ እደውልላታለሁ› አልኳት፡፡

ተቃቅፈን ተኛን..

ከሁለት ቀን በኋላ ሥራ ቦታ እያለሁ የማላውቀው አንድ ስልክ ተደውሎልኝ ሆስፒታል ድረስ ተባልኩ፡፡ የተባልኩት ሆስፒታል ስደርስ ሂሩትን ሬሳ ማቆያ ክፍል ሲወስዷት ከመንገድ ተገናኘን፡፡ ሂሩት የሞተችበት ሆስፒታል ውስጥ ራሴን ስቼ አስራ አምስት ቀን ተኛሁ። ከረጅም ጊዜ ራስን መሳት በኋላ ከሴት ልጄ ጋር ተዋወኩ። ሂሩት እንደ እናቷ የመጀመሪያ ልጃችንን ወልዳ ነበር የሞተችው፡፡ ሂሩትን ካጣሁ እንሆ ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

ከሃሳቤ መልስ ወደ መና አየሁ… ክንዴ ላይ አንቀላፍታለች። እንደ እናቷ ናት… ከእኔ የወሰደችው አንድም ነገር የለም፡፡ ሂሩት አንድ ሳታስቀር ራሷን ነው የሰጠችኝ፡፡ እግዜርን የታረኩት ሚስቴን በምትመስል ልጄ በኩል ነው፡፡ ሚስቴን ወስዶ ሚስቴን ሰጠኝ፡፡ ልጄን አግብቼ የምኖር ነኝ፡፡

መና የሚለውን ስም ያወጣችላት ሂሩት ናት፡፡ ሁሌ ማታ ማታ በልጃችን ስም በኩል የፍቅር ጭቅጭቅ እንጨቃጨቅ ነበር። እኔ ግን ሂሩት ነው የምላት። የሚስቴን ስም ለልጄ ሰጥቼ… በሚስቴ ስም ልጄን እጠራለሁ፡፡ አዳልጦኝ መና ብያት አላውቅም። ግን አሁንም አለቅሳለሁ፡፡ ሂሩትን ለማስረሳት ልጄ ብቻ በቂ ናት አልልም፡፡ እግዜር እንዴትም ቢባርከኝ ስለሂሩት መጽናኛ የማገኝ አይመስለኝም፡፡ ባሰብኩት ቁጥር ሁሌ የሚያስለቅሰኝ ለእኔ ስትል ዶክተር ልጅሽን ስትወልጂ ትሞቻለሽ ያላትን ደብቃ ለብቻዋ ተሰቃይታ መሞቷን ሳስብ ነው፡፡

የምኖረው ትላንትን ነው፡፡ ዛሬ ላይ ያለሁ እመስላለሁ እንጂ ትላንትን ነው የምኖረው፡፡ ሳቄ እና ታሪኬ ከትላንት ተመዞ ዛሬን ያደመቀ ነው፡፡ ሂሩት የነበረችበት ትላንት ሁሉ ይናፍቀኛል… በምንም አልቀይረውም፡፡ እሱን ብሎ ወንድ የሚሉትን እኔን ነው ከመሬት አንስታ ባሏ ያደረገችው… ለዛውም በብዙ ፍቅርና ጥሩነት፡፡

መቼም እንዳልበረታ ከእሷ ዘንድ የነፈሰ ንፋስ ነፍሴን አጠውልጓታል፡፡ መቼም እንዳልሽር፣ መቼም እንዳልቆም ያደረገኝ ትዝታ በእኔ ውስጥ አለ፡፡ እንደ ሸረሪት ድር የተጠላለፈ ከእኔ ውጭ ውሉን የማያውቅ፣ ከእሷ ውጭ ውሉን ያልደረሰበት የፍቅር ውርስን ተወራርሰናል። በልጄ ነፍስ ውስጥ ግን አያታለሁ… አልሞተችም ሞታለችም፡፡ ልጄ ሚስቴም ልጄም ናት… አንድ ነፍሷን በሚስትነት እና በልጅነት አፍቅሬው የምኖር ነኝ፡፡

በሂሩት ሞት ላይ እግዜር ቢሳሳት… እሷን መች አልኳችሁ? ብሎ መላዕክቶቹን ቢቆጣ… ሂሩትን ለዳግም ሕይወት እድል ቢሰጣት ስል እብድ የማያስበውን ሃሳብ አስባለሁ፡፡ ወደፊትም እንዲህ ነኝ… በዛሬና በነገ የምዳክር..

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You