ጠዋት ታይቶ ረፋድ ላይ እንደሚጠፋ ጤዛ፤ ዛሬ ላይ በዙሪያችን የምናያቸው ነገሮች ሁሉ ነገ ላይገኙ ይችላሉ። ይህን ዓይነት ክስተት በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ አልፎ ይታያል። ታላቅ ሥራን የሠሩና በክብር የቆዩ ሰዎች ተረስተው፤ ደግሞ ጊዜ አልፎ ሲነሱ ታዝበናል። ጊዜ አንዴ ሲጨፈግግ ደግሞ ሲፈካ፤ ብዙ ታሪኮችና እውነቶችን ሹክ ይለናል።
የዛሬው እንግዳችን ለበርካታ ዓመታት በውትድርና እንዲሁም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሕይወታቸውን አሳልፈዋል። የሶማሊያ መንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሰው በመግባት በኢትዮጵያ ወሰን ክልል ላይ ከፍተኛ ወረራ ባካሄዱበት በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ላይ ለአገራቸው ተሰልፈዋል። ያንን ወራሪ ለመከላከልም ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረጉ፤ የተጋድሏቸውንም ፍሬ ለማየት ከታደሉ ኢትዮጵያውያን ሰዎች መካከል ናቸው።
በወቅቱ ውጊያ ላይ ተሳትፈው እግራቸውን በጥይት ተመተው የነበሩ፣ ከዚያም በኋላ ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ዘብ በመቆም ቀጥለው አገልግለዋል። የመንግሥት ለውጥ ሲሆን ግን ያለጡረታ ተሰናብተዋል፤ ከፍተኛ እንግልትም ደርሶባቸዋል። በአሁን ወቅትም በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ። የዛሬ የ«ሕይወት እንዲህ ናት» እንግዳችን ሻምበል ጥላሁን መንግሥቴ ናቸው፤
ልጅነት እና የትምህርት ሕይወት
ምዕራብ ጎጃም ዳንግላ የሚባል ስፍራ ነው ቆራጡ እና አገር ወዳዱ ሻምበል ጥላሁን መንግስቴ የተገኙት። ከአባታቸው አቶ መንግስቴ እንዳለው እና ከእናታቸው እማሆይ ጠየቁ በላይ በ1946 ዓ.ም. ተወለዱ። የእናት ልጅ አንድ ታላቅ ወንድም ሲኖራቸው የእርሳቸው ታናሽ የሆኑ በአባት የሚገናኙአቸው ሁለት ወንድምና አንድ እህት አሏቸው፡፡
እናታቸው እማሆይ ጠየቁ ወደ አዲስ አበባ ከመጀመሪያ ልጃቸው ጋር ሲያመሩ ትንሹን ጥላሁንን አብረው ይዘው ነበር። ወንድማቸው አቶ ቦጋለ ጋሹ የተባሉ ሰው በወቅቱ ጥይት ፋብሪካ እየተባለ በሚጠራ መሥሪያ ቤት የሚሰሩ ባለትዳር ነበሩ፡፡ እማሆይም አቶ ቦጋለ ጋር ጥገኛ መሆን ስላልፈለጉ ህጻን ልጃቸውን ለማሳደግ አዲስ አበባ ቄራ አካባቢ የቀድሞ ከፍተኛ 20 ቀበሌ 43 አልማዝዬ ሜዳ አጠገብ ቤት ተከራይተው ጠላ በመሸጥ መተዳደር ጀመሩ፡፡
በወቅቱ ገና ብላቴና የነበሩት ሻምበል ጥላሁን በቅድሚያ ቄስ ትምህርት ቤት በመቀጠል ነፃነት ጮራ ከ1ኛ እስከ 6ተኛ ክፍል ተማሩ። ቀጥለውም 7ተኛ እና 8ተኛ ክፍል በፊታውራሪ ላቀ አድገህ ትምህርት ቤት ተምረው መጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በመጨረሻም ንፋስ ስልክ አካባቢ በሚገኘው ሲቢስቴ ትምህርት ቤት እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡
በጦር ሰራዊት ቤት
እናታቸውን ለመርዳት ሲሉ ትምህርታቸውን አቋርጠው የቀን ስራ መስራት ቢጀምሩም ለእርሳቸው ብሎም እናታቸውን ለማስተዳደር በቂ ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም። እናም በንጉሠ ነገሥቱ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1965 ዓ.ም ጦር ሠራዊት ውስጥ ወታደር ሆነው ተቀጠሩ። ጥቂት እንዳገለገሉ ምን እንደሆነ መናገር በማይፈልጉት ምክንያት በዓመቱ በራሳቸው ፍቃድ ስራቸውን አቆሙ::
ንጉሡ ከስልጣን ሲወርዱ የደርግ መንግሥት “ሠራዊት ውስጥ የነበራችሁ መመለስ ትችላላችሁ” ስላለ በ1966 ዓ.ም. ዳግም የሠራዊት አባል ሆነው ተቀላቀሉ። አባልነታቸውም በአራተኛው ክፍለ ጦር ነበርና በደቡብ በነገሌ ቦረና የሶማሊያ ወራሪ ጦርን ከጓዶች ጋር በመሆን መክተው በመደምሰስ አኩሪ ገድል ፈፅመዋል።
የሶማሊያ ጦርነት አገሪቱ ላይ ጦርነት የከፈተው ባልተጠበቀበት ሁኔታ እና ጊዜ ላይ ነበር ።፡፡ ታዲያ ቀድሞውንም በአገር ድርድር የለም የሚሉት ሻምበል ጥላሁን መንግሥቴ የሶማሊያ ውጊያ ላይ ዘመቱ፣ ተዋግተውም ከጨረሱ በኋላ ማዕረግ ተሰጥቷቸው ወደ ሰሜን ዘመቱ፡፡ ስለ ሰሜኑ ውጊያ አንዳንድ ጉዳዮችን ያጫወቱን ሲሆን… «ወደ ሰሜኑ ስንዞር ውጊያው አንድ አይደለም። ይሄ “ኮንቬንሽናል” ነው፡፡ ያኛው (የሶማሊያው) የሰርጐ ገብ ውጊያ ነው:: እንግዲህ በሰሜኑ በኩል ትዋጋለህ፣ ታሸንፋለህ ትሄዳለህ::” ብለዋል፡፡ ውጊያው በዛን ጊዜ ከባድ እንደነበርም ያስታውሳሉ። «ከባድ ከሚያደ ርጉት ውስጥ አንዱ ረጅም ርቀት በእግር መሄድ አለ፤ ሌሎችም ፈተናዎች ነበሩ:: ስለውጊያው አሁን ባለኝ የማስታወስ አቅም ልነግርህ የምችለው ይህንን ነው፡፡ ነገር ግን የነገርኩህ በጣም ጥቂቱን ነው::» ብለዋል።
ሻምበል ጥላሁን በዚህ ውጊያ እግራቸው ላይ ቆስለው በ1970 ዓ.ም. በመጀመሪያ በነገሌ በመቀጠል ለከፍተኛ ህክምና አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ታክመዋል፡፡ ሆኖም ህመማቸው ከውትድርና ሥራቸው አላራቃቸውም። በማገገሚያ እስከ 1972 ዓ.ም. ከቆዩ በኋላ ወደ ክፍላቸው ተመልሰው ወታደራዊ አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡
በሠራዊቱ ውስጥ በተራ ወታደርነት እግረኛ ሆነው ጀምረው የጓድ መሪ በመሆን የምክትል አስር አለቃ፣ የአስር አለቃ እና የሃምሳ አለቃ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በ1973 ዓ.ም. ከክፍላቸው ተመልምለው አየር ኃይል ማሰልጠኛ በመግባት ለዘጠኝ ወር የሚሰጠውን የአየር ተቃዋሚ መሪ ወይም ጀት አስተኳሽ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡
ስልጠናው ሲጠናቀቅ የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ያገኙና በመድፈኛ ሻለቃ ምድብ ይመደባሉ። ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ የሰባተኛ ክፍለ ጦር መድፈኛ ሻለቃ የአየር አስተኳሽ መሪ ወይም ጀት አስተኳሽ በመሆን ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ሲደረግም መተማ ግዳጅ ላይ ነበሩ፡፡
ይህ ሁሉ አልፎ አገር በልጆቿ መስዋዕትነት ክብሯ ተጠብቆ ቆየ። ለዚህ የተጋው ሠራዊት ግን ተበተነ። ታዲያ ሠራዊቱ ሲበተን እርሳቸውም አዲስ አበባ ተገኙ። አዲስ አበባ ሰዓሊተ ምህረት አካባቢም አንድ ግለሰብ ጋር ህጋዊ ያልሆነና በተለምዶ «የጨረቃ ቤት» የሚባለውን ቤት እየጠበቁ እንዲኖሩ ስለተፈቀደላቸው የጉልበት ስራ እየሰሩ በዚሁ ቤት መኖር ቀጠሉ፡፡
የቤተሰብ ሕይወትና ፈታኙ ጊዜ
በ1986 ዓ.ም ላይ ከወይዘሮ አወቁ ታደለ ጋር ጋብቻ ፈጽመው የአንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆች አባት ሆነዋል። የጥንዶቹ ሕይወት ላይ ልጆች ሲጨመሩ ሩጫውና ድካሙም አብሮ ይጨምራል። ሻምበል ጥላሁን ግን በጊዜ ሂደት አቅማቸው ደከመ። በሶማሊያ ጦርነት ወቅት እግራቸው ላይ ያረፈችው ጥይት ህመም በማገርሸቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባቸው። በሙሉ አቅማቸው መሥራት አልቻሉም።
ጊዜን ጊዜ እየወለደው በመጨረሻ የጉልበት ስራ መስራት አቅቷቸው እቤት ዋሉ። የጡረታ መብታቸው ስላልተከበረና የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ልጆቻቸውን ማሳደግ አልቻሉም። የሕይወት ፈተና እየተደራረበ ተጫናቸው። እናም ሁለቱን ልጆቻቸውን በጉድፈቻ ለአሳዳጊ ሰጡ፡፡ እየጠበቁ ከሚኖሩበት የግለሰብ ቤትም (ጨረቃ ቤት) ባለቤቶቹ ስላስወጧቸው ከባለቤታቸውና ከመጨረሻ ሴት ልጃቸው ጋር ጎዳና ላይ የላስቲክ ቤት ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡
በላስቲክ ቤት ኑሮ ቀጠለ። በዛም በመኖር ላይ እያሉ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ባለቤታቸው ትተዋቸው ይሄዳሉ። አቅማቸው በደከመ ጊዜ ያለ አጋር መኖራቸው በጣም ያብከነክናቸው፣ ያናድዳቸውም ጀመር፡፡ ኑሮ ደግሞ ከዛ በኋላ እየባሰና እየከበደ ሄደ እንጂ አልቀለለም። ባለቤታቸው ትተዋቸው ከሄዱ በኋላም የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም ከስድስት ዓመት በላይ እነዚህን የሕይወት ፈተናዎች ተቋቁመው ለመኖር ከፍተኛ ጥረት አደረጉ፡፡
በውትድርና ቆይታቸው እግራቸው ብቻ ሳይሆን የግራ ዓይናቸው ላይም ጉዳት ደርሶ ነበር። በዚህ አላባራም፤ ይኸው በቆየባቸው የአንድ ዓይን ችግር ላይ ደግሞ ሁለቱም ዓይናቸው የማየት ኃይሉ ቀነሰ። የሕይወት በትር ደጋግሞ አረፈባቸው፤ አሻራውንም ጣለ። በአንድ ዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ መኪና ገጭቷቸው ጭንቅላታቸው ተጎድቷል፤ ፍንክቱ ጭንቅላታቸው ላይ በጉልህ አሁን ድረስ ይታያል።
የህይወት ፈተናው ተደራርቦ ቀጠለ። ትግሉም እንደዛው፤ ሆኖም በመጨረሻ ማየት ስለተሳናቸው ካለ መሪ መንቀሳቀስ አቃታቸው፡፡ በዚህ ጊዜ መኖር አስመርሯቸው ሕይወታቸውን ለማጥፋት የተለያዩ ተግባራዊ ሙከራ አድርገዋል። ግን የፈጣሪ ፈቃድ እንደዛ አልነበረምና፤ እንዲህ ቀን አልፎ ታሪካቸውን እንዲያወሩ ተፈቅዷልና በተደጋጋሚ ከሞት ተርፈዋል፡፡
ኑሮ በመርጃ ማዕከሉ
በጎዳና ላይ ላስቲክ በመዘርጋት ከመተኛት ወጥተው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እንዲገቡ አቶ ከበደ የሚባሉ ጓደኛቸው ያደረጉት አስተዋጾ ከፍተኛ ነው፡፡ መቄዶንያ በ2006 ዓ.ም. ከገቡ በኋላ ሕይወት እንደ አዲስ ጀመረ። ህክምና አግኝተው የቀኝ ዓይናቸው ማየት በመቻሉ ያለመሪ መንቀሳቀስ ቻሉ፡፡
ሕይወታቸው ከነበረበት አስፈሪ ጨለማ ወደ አዲስ ተስፋ ሲሸጋገር መለስ ብለው ማሰብ ጀመሩ። ስለልጆቻቸው፤ በጉዲፈቻ የሰጧቸው የ20 እና 18 ዓመት ልጆች መጀመሪያ ስፔን ሄደዋል ተብለው ነበር፤ አሁን ግን “አድራሻቸው አይታወቅም” ተብለው ያሉበትን አያውቁም። የመጨረሻዋ የ12 ዓመት ልጃቸው አያት አካባቢ ኬር የተባለ የህፃናት ማሳደጊያ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆና እየኖረች ትገኛለች፡፡ ከህፃናት ማሳደጊያው ይዘዋት እየመጡ አባቷን ትጠይቃለች፡፡
ሻምበል ጥላሁን በመቄዶንያ የተደላደለ ኑሮ ሲያገኙ ጥለዋቸው የሄዱት ባለቤታቸው ወይዘሮ አወቁ ምን አይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማጠያየቅም ጀመሩ፡፡ ያገኙት ምላሽ በጣም የሚያሳዝን ነበር፤ ባለቤታቸው በጎዳና ላይ ሕይወትን እየገፉ ነበር። እናም ባለቤታቸውንም ከጎዳና ተነስተው እርሳቸው ወዳሉበት ማረፊያ እንዲመጡ ጥረት አደረጉ፤ ተሳካላቸው። አሁን ባለቤታቸው አስተባባሪ ሆነው በመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ተቋም እያገለገሉና እየተገለገሉ ነው። ይህንን በማድረጋቸው ለህሊናቸው እርካታ እንደሰጣቸው ሻምበል ጥላሁን ይናገራሉ።
ትውስታ
በነፃነት ጮራ የአምስተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ ዓርብ በእግር ኳስ ጨዋታ በአጥቂ ቦታ የሚሳተፉበትን ሁኔታ፤ ሰኞ በሰንደቅ ዓላማ ማውጣት ስነስርዓት ላይ የሚያቀርቡትን ዘገባ መለስ ብለው ያስታውሳሉ። ያኔ በነዚህ እንቅስቃሴዎች የጀመራቸው የስነጽሁፍ ፍቅር ከልጅነትም አድጎ በሠራዊቱ ቤት እውቅና እንዲኖራቸው አድርጓል።
በዛን ጊዜም ለታጠቅ እና ሠርቶ አደር ጋዜጣም የተለያዩ ይዘት ያላቸው ግጥሞች እየላኩ ይሳተፉ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከላኩት ግጥም “መስከረም ሁለት” የሚለውን ያስታውሳሉ።
ሻምበል ጥላሁን የላስቲክ ቤት ውስጥ ሲኖሩም በካርቶን ላይ ግጥም ይጽፉ ነበር።መቄዶኒያ ከገቡ በኋላም ቢሆን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የግጥም ስራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በራሳቸው ህይወት ዙሪያ የሚያተኩር ግጥምም አላቸው፡፡
አንገቴ ለገመድ ነበር የታጨች፤
ሆዴ በረኪና ቀድማ ቀመሰች፤
ምን አይነት ነፍስ ናት ከዚህ የተረፈች፤
ያ ሁሉ አለፈና ከረባት አሰረች።
በእግር ኳስ በኩል የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊ ናቸው፡፡ መቄዶንያ ከገቡ በኋላም የክለቡ አባላት ለመጎብኘት ሲመጡ አጠናክረውት ከህዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የደረጃ አራት አባል ደጋፊ በመሆን መታወቂያ አላቸው፡፡ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስቴዲዮም ባደረገው ጨዋታ ክለቡ ባመቻቸላቸው ግብዣ ተገኝተው ድጋፋቸውን እንደሰጡና አንድ ለዜሮ ሲያሸንፍ “ቡና ይፈላ ቡና” እያሉ መምጣታቸውን በፈገግታ አጫ ውተውናል፡፡
በ1970 ዓ.ም. ከሶማሊያ ጋር የተደረ ገውን ጦርነት ሲያስታውሱ በዋናነት ሁለት ነገር ከአዕምሯቸው እንደማይረሳ ይናገራሉ። «አንደኛው ኩባውያን ኢትዮጵያውያን ሆነው ከልብ የተዋጉበት ሁኔታ ነው:: የውጊያ አመራሩንና የጦር መሳሪያውን ያስተማሩን እነሱ ናቸው:: በወቅቱ በውጊያው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳትና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የኩባ ወታደሮች ውለታ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለማውራት የሚቻል አይደለም» ይላሉ፡፡
ሁለተኛው የማይረሳቸውን ጉዳይም እንደሚከተለው ያነሳሉ፤ «በ1970 ዓ.ም. ሁለተኛው በደቡብ የውጊያ ወረዳ ቢልቱ በሚባል አካባቢ የተከሰተ ነው። በዚህ ስፍራ ሶማሊያን መክተን ስንደመስስ ከጎንደር ክፍለ አገር የመጣችው የዘጠና ስምንተኛ ሚሊሻ ብርጌድ አባል የነበረችው ሴት ሚሊሻ ፋንታዬነሽ በላይ የጠላትን ታንክ የእጅ ቦንብ ወርውራ ስታቃጥል በወገን በኩል በኢህአፓ አባላት በጥይት ተመታ ስትሞት ያየሁበት አሳዛኝ ሁኔታ ነው።ከሞተች በኋላ ነገሌ ስትቀበር የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ተሰጥቷታል፡፡ የክፍለ ጦራችን አዛዥ ኮሎኔል (በኋላ ብርጋዴር ጀነራል) ከበደ ጋሼ ነበሩ፤ አሁን በጡረታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ወራሪውን የሶማሊያን ጦር መክተን መደምሰሳችን ሲያስደስተኝ፣ በወገን ተመትታ ህይወቷን ያጣችው ኢትዮጵያዊ ሚሊሻ ሁኔታ ሁልጊዜ ያንገበግበኛል” ብለዋል፡፡
ሞቴ መቄዶንያ
ስፔን ሄዱ የተባሉት ልጆችዎ መጥ ተው እኛ ጋር እንውሰድዎት ቢሉ ምን ይላሉ? ተብለው ሲጠየቁ «ለእኔ የሚጦረኝ መቄዶንያን አግኝቻለሁ፤ ላስቲክ ላይ መተኛቴ ቀርቶ አልጋ ላይ ፍራሽና ብርድ ልብስ ቀርቦልኝ እተኛለሁ፤ በቀን ሦስትና አራት ጊዜ እመገባለሁ፤ የህክምና አገልግሎት በፈለኩኝ ቀን አገኛለሁ፤ ግቢው ውስጥ ከሚገኙ አባላት ጋር በየቀኑ እነጋገራለሁ፤ ከዚህ በላይ ምን አገኛለሁ ብዬ ነው ልጆቼ ጋር የምሄደው። እኔ ያለሁበት ሁኔታ መንግሥተ ሰማያት ማለት ነው። ሞቴ መቄዶንያ ውስጥ ይሆናል።» በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ሻምበል ጥላሁን የሶማሊያን ወራሪ ጦር ኃይል ለመመከትና ለመደምሰስ የሚጠበቅ ባቸውን ግዳጅ በወቅቱ ተወጥተዋል። ከዚያ በኋላም ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ዘብ በመቆም አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ እድሜያቸው ገፍቶ አቅማቸው ሲደክም ግን የጡረታ መብታቸው አልተከበረም፡፡ ይህ ሁኔታ በሻምበል ጥላሁን ብቻ የደረሰ ሳይሆን በሌሎችም የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች አባል የነበሩ ወታደሮች ታሪክ ነው።
በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ መጠነ ሰፊ ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሰው አዲሱ የመንግሥት አመራር ለእነዚህ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች አባል የነበሩ ወታደሮች ተገቢውን የጡረታ መብት የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ቢያመቻች መልካም ነው:: መልካም አስተዳደር ባለውለታዎችን በማክበርና በማሰብም ይገለጻልና፡፡
ለተመስጋኝ ምስጋና
በመጨረሻ ሻምበል ጥላሁን ሊያመሰ ግኗቸው የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ እድሉን ሰጥተናቸዋል። እርሳቸውም «የዚህን ድርጅት /መቄዶንያ/ መሥራች አቶ ቢኒያምን እና በጐ ፈቃደኛ ሆነው እኛን የሚያገለግሉትን ሁሉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት የአገር ባለውለታ የነበርን ሰዎች ነን መንገድ ላይ ወድቀን የነበርነው። አሁን ከየቦታው ተሰብስበን ቀሪ ዘመናችንን በደስታና በጤና እንድናሳልፍ ሆነናል፤ ደስተኞች ነን።
እናንተም ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአገር አንድነት ሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እንድትኖሩም እመክራለሁ፡፡ ብዙ ቢኒያሞች እንዲፈጠሩም እመኛለሁ፡፡» አሉ። እኛም ለሻንበል ጥላሁን ረጅም እድሜ እና መልካም ጤንነት ተመኘን፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2011
አብርሃም ተወልደ