ጎጆ ያስዘጋ ፍቅር …

ደብረሲና

በመልካም ትዳር የታነጸው ጎጆ ደስተኛ ቤተሰቦች አፍርቶ ዓመታትን ዘልቋል። ጥንዶቹ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጠዋት ማታ ይተጋሉ። መምህሩ አባወራ ስለልጆቻው ነገ ሃሳባቸው ብዙ ነው። ዕውቀት አጋርተው ቀ ለም ለ ማስረጽ ዓ ይኖቻቸው ከ ነሱ አተኩሮ ይውላል።

ወይዘሮ እታገኝ አየለ ቤቷን ሞልታ ጎጆዋን ለመምራት እረፍት ይሉት የላትም። ይህ ልፋቷ ሥራ ውሎ ለሚገባው፣ ባለቤቷ ብርታት ሆኖ ዓመታት ተሻግሯል። መልካም ሚስት፣ ጥሩ እናት መሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል ታውቃለች ። ዛሬ ላይ ቆማ ነገን መልካም ማድረግ የእናትነት ግዴታዋ ነው።

ሁሌም ይህ በገባት ጊዜ ልጆቿ ጉዳዮቿ ይሆናሉ። እነሱን ይዛ ቤት ፣ ጎጆዋን ታያለች። ስለእነሱ መኖር፣ ጤና ውሎ ማደር በትጋት ውላ ታድራለች። አሁን ወይዘሮዋ የልፋቷ ውጥን ፍሬ ሊይዝላት ይመስላል። የመጀመሪያ ልጇ ትምህርት ቤት ሊገባ እየተዘጋጀ ነው። ይህ እውነት ለብርቱዋ እናት የተለየ ትርጉም አለው። አሁን የድካሟ ውጤት ከርምጃው አንድ ብሏል። ውስጧ በደስታ ቢሞላ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ ይዛለች።

ትንሹ ተማሪ

ዮሀንስ ፋሲል ደስተኛና ድንቡሽቡሽ ታዳጊ። ዓይኖቹ ያምራሉ፣ ጸጉሩ ውብና ለስላሳ ነው። ዮሀንስን ያዩት ሁሉ በዋዛ አያልፉትም። ያገኙት በእጅጉ ይወዱታል፣ እያቀፉ ይስሙታል ፣ ያደንቁታል። የህጻንነት ዕድሜውን እንዳበቃ እንደእኩዮቹ ትምህርት ቤት ሊላክ ጊዜው ሆነ። የዛኔ ውሰጡ የነበረው ደስታ የተለየ ነበር።

ትንሹ ዮሀንስ ቦርሳውን አዝሎ፣ ደብተሩን ይዞ የአንደኛ ክፍል ትምህርቱን ጀመረ። ውሎ ሲገባ እናቱ በፍቅር እያየች ተንከባከበችው። የሚፈልገውን እያሟላች፣ የጎደለውን እየሰጠች ፍላጎቱን ሞላችለት። እታገኝ ትንሹ ዮሀንስ የማንነት ማሳያዋ ነው። በእሱ ነገን አሻግራ ታያለች። ልጇ ነውና ምኞት ፍላጎቷ ይበዛል። ትምህርቱን ሲጨርስ ስለሚሆነው በጎ አርቃ ታልማለች።

አሁን ዮሀንስ የአንደኛ ክፍል ትምህርቱን በብቃት አጠናቋል። ክረምቱ አልፎ በጋው ሲመጣ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ይሆናል። እናት ለከርሞው ታማሪ ልጇ ፣ ልክ እንደ አምናው ከጎኑ ትሆናለች። እሱ ባሻው ሁሉ ፍላጎቱ ይሞላል። የልቡም ይደርሳል።

እነሆ ! አዲሱ ዓመት ከባተ ቀናት መቁጠር ጀምረዋል። ዮሀንስና ትምህርት ዳግም ሊገናኙ ቀጠሮ ላይ ናቸው። ትምህርቱ ሲጀመር ሁለተኛ ክፍልን ይቀጥላል። ይህ እውነት ብዙ ለሚያስቡት እናት አባት ትርጉሙ ይለያል። ይህ ጅማሬ የልፋት ድካማቸው፣ የሃሳብ ዕቅዳቸው አንዱ ፍሬ ነው።

አዲስ ዓመል…

ዮሀንስ ልክ እንደአምናው ከትምህርት ውሎ መመለስን ይዟል። ከዕውቀት ፍላጎቱ አንዳች አላጎደለም። እንደ ጓጓ ከቤት ይወጣል። ደስ ብሎት ይመለሳል። ከእኩዮቹ አላነሰም ። ውሎ አድሮ ግን ትንሹ ል ጅ ላይ ለ ውጥ ይታይ ጀም ሯል።

አብሮት የኖረው ደስታ ከእሱ ያለ አይመስልም። ፈገግታው ፈዟል ፣ ሳቅ ጨዋታው ቀዝቅዟል። በድካም ዝሎ ከቤት ሲገባ ምግብ መብላትን አይሻም፣ ወሬ ጨዋታ ያስጠላዋል። ይህኔ ሰበብ እየፈለገ ይነጫነጫል።

እናት አባት ስለዮሀንስ ተጨንቀዋል። ደርሶ የባህሪው መለወጥ እያሳሰባቸው ነው። ትናንት ሳቅ ፈገግታ የማይለየው ልጅ ደስታውን ሰርቆ ጤናውን የነጠቀው ሚስጥር ያሳስብ ፣ ያስተክዛቸው ይዟል። ራስ ምታቱ፣ ትኩሳቱ፣ ዓመል ነስቶታል። ቤተሰብ አስጠልቶታል። ምግብ አለመብላቱ ሰውነቱን እየጎዳው፣ እያከሳው ነው።

ትንሹ ዮሀንስ ‹‹ወገቤን፣ እጄን ፣ እግሬን›› እያለ ነው። መላ አካሉን እየቆረጠመ ጤና የነሳውን ህመም ቤተሰቡ ይጋራው ጀምሯል። ይህ ህመሙ ቅጭት መሆኑ የገባቸው አንዳንዶች ደግሞ መፍትሄውን ጠቆሙ። ልጁን ወጌሻ እንዲያየው ተወስኖ አካሉ ሲታሽ ፣ ሲታሰር ከረመ።

መልሶ ትምህርት ቤት ሊሄድ ሞከረ። እታገኝ ሁሌም ልጇን አታምነውም። በእረፍት ሰእቱ ብቅ እያለች ታየዋለች። ይህ አጋጣሚ ግን ይበልጥ ህመሙን ጠቆማት። ተማሪው ልጇ እየተጎዳ መሆኑን አወቀች።

ዮሀንስ አንዳች አልተሻለውም ። ስቃዩ በርትቶ ቤት መዋል ከያዘ ሰንብቷል። ሁኔታው ሲብስ ትምህርት ቤት ለመቅረት ግድ አለው። እናት በዚህ ዝም አላለችም። መላ ባለችው ጸበል አመላልሳ ድህነቱን ጠበቀች። ገዳም ወስዳ በጾም ጸሎት ተጋች። መፍትሄው ሳይገኝ እንደዋዛ ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ።

ውሎ አድሮ ቤተሰብ መከረ። የዮሀንስ ችግር በህክምና ይታወቅ ዘንድ ከሆስፒታል ሊወሰድ ተወሰነ። ከገዳም ጸበሉ መልስ ደብረብርሃን የተገኘው ዮሀንስ ሀኪም ዘንድ ቀርቦ ተመረመረ። የምርመራው ውጤት የጨጓራ ባክቴሪያና የደም ማነስ መሆኑን ጠቆመ። የተሰጠውን መድሃኒት እየወሰደ ቢቆይም የታሰበውን መፍትሄ አላገኘም።

አሁንም ምርመራው አልተቋረጠም። የደም ናሙናው አዲስ አበባ ተልኮ የሚደርሰው ውጤት ተጠበቀ ።አሁን በናሙናው ምርመራ የተገኘው ውጤት መልኩን ቀይሮ የትንሹ ልጅ ህመም ቲቪ መሆኑ ተረጋግጧል።

ዮሀንስ የታዘዘለትን የቲቪ መድሃኒት መውሰድ ጀምሯል ። እንዲህ ከሆነ በኋላ ቤተሰብ ስለ እሱ ሕይወት ተስፋን ቋጠረ። ጠዋት ማታ ዓይኑን እያየም መዳኑን ናፈቀ። ህመምተኛው ልጅ አሁንም እንደታሰበው አልሆነም። ጤናው ፣ ሰውነቱ አልተመለሰም። እግሮቹ አይላወሱም ፣ፊቱ አብጦ ገጽታው ተለውጧል።

እናት ሁሌም ስለልጇ ማሰብ አላቆመችም። በየዕለቱ መድሃኒት የሚወስደው ዮሀንስ ለውጥ አለማምጣቱ እያስጨነቃት ነው። አሁን ከአንድ ዓመት ያላነሰ መድሃኒት ወስዶ በህክምናው ቆይቷል። ለውጡ አልታየም ፣ ጤናው አልተመለሰም። ይህ እውነት ሀኪሙ ዘንድ ዳግም ያቆማት እታገኝ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር እንዲጻፍላት አብዝታ ወተወተች።

ህክምናውን የያዘው ዶክተር ከዚህ ይልቅ አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ አድራሻ ፅፎ ሰጣት። አድራሻውን ከልጇ ጋር ይዛ ስፍራው የደረሰችው ወይዘሮ በተባለችው ሃሳብ መስማማት አላሻትም። ሃሰቧን ቀይራ ወደሌላ የግል ሆስፒታል ለመሄድ ወሰነች።

የደረሰችበት ሆስፒታል ዮሀንስን ተቀብሎ ተገቢውን ምርመራ አደረገ። ህክምናውን ግን መቀጠል አልፈለገም። ለቀጣዩ ቆይታ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሄዱ ጠቁሞ አሰናበታቸው።

እታገኝ ልጇን ይዛ ብዙ አሰበች። አሁንም ውስጧ ከሌላ ስፍራ እንድትሄድ እየጠቆማት ነው። ይህ ዕቅድ አብረዋት የነበሩ ሰዎች ጭምር ሆኗል። ወዳሰቡት ሀኪም ቀርበው ዕድላቸውን መሞከር ፈልገዋል። ሀኪሙ ዘንድ ቀርበው የዮሀንስን ችግር አስረዱ። ሀኪሙ በኢትዮጵያ የሚኖር የውጭ አገር ዜጋ ነው። ታማሚውን ተቀብሎ ጥልቅ ምርመራውን ጀመረ።

የምርመራው ውጤት

እታገኝና ቤተሰቦቿ የልጁን ውጤት ጠበቁ። ፈረንጁ ሀኪም በእጁ ያለውን የምርመራ ውጤት እያሳየ ቁርጡን ነገራቸው። ዮሀንስ እስካሁን ሲሰቃየበት የቆየው ህመም የ‹‹ደም ካንሰር›› ነበር። እታገኝ በአስቸኳይ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተጻፈውን ሪፈር ይዛ ወደስፍራው ፈጠነች።

በዚህ ሆስፒታል የሚታየው ታካሚ በርካታ ነው። ብዙዎች ወረፋ ይዘው ይጠብቃሉ። ለመታከም ደጅ የሚጠኑ ፣ በቀጠሮ ቀን የሚቆጥሩ ጥቂት አይደሉም። ይህን ሁሉ አልፋ ወደ ውስጥ ዘለቀች። ስለ ልጇ የሰማችውን እውነት አምኖ መቀበል ተስኗታል። እናት ከታሰበው ደርሳ በር ብትመታ መልካም እጆች ከፈቱላት። ዮሀንስ ዕድል ቀንቶት እንደሌሎች ደጅ አልጠናም። ያለ አንዳች ወረፋና እንግልት ከሀኪም እጅ ደረሰ።

የእናትነት ዋጋ …

ለአንድ ዓመት የሳምባ በሽታ መድሃኒት ሲወሰድ የቆየው ታዳጊ በአዲስ መልክ የካንሰር ህክምናውን ጀመረ። ሳይውል ሳያድር የታዘዘለትን መድሃኒቱን ቀጠለ። አሁን ታማሚው ብቻ ሳይሆን መላው ቤተሰብ አቅሙ ተፈትኗል። በአንድ ጎጆ የነበረው ፍቅር ለሁለት ተከፍሎ ሕይወት በርቀት ሊጀመር ግድ ብሏል።

ወይዘሮዋ ከልጇ በላይ ‹‹ሕይወት የለኝም›› ብላለች ። ስለ እሱ አትሆነው፣ አትከፍለው ዋጋ የለም። ሀገሯ ትታት የመጣችው ትንሽዋ ልጅ ከአባቷ ጋር በመለያየት ጊዜ ቆጥረዋል። መልሰው ቢገናኙም እናት ከእነሱ ጋር ልትኖር አልተቻላትም። ዮሀንስ ህክምናውን ከጀመረ ወዲህ ኑሮና ሕይወቷ አዲስ አበባ ነው።

በምልልስ በቆየችባቸው ጊዜያት ፈተናዋ ብዙ ነበር። ጥቂት ታክሞ ቀጠሮ በተሰጠው ጊዜ ተመልሰው ደብረሲና ይሄዳሉ። አንዳንዴ ግን ከቀጠሮው በፊት ይታመማል። እናት ሲያተኩስ ፣ ሲጨንቀው ቀድማ ታውቃለች። እንዲህ በሆነ ጊዜ ፣ የምታቦካ የምትጋግረውን ትታ ወደ አዲስ አበባ መክነፍ ልማዷ ነው።

በእሷ ዘንድ ጨለማ ይሉት ውድቅት አይታወቅም። ከደብረሲና አዲስ አበባ ስትጓዝ ሌቱን በመንገድ ያነጋችበት ጊዜም ነበር። ዮሀንስ በአዲስ አበባ ህክምናውን ከጀመረ በኋላ ትምህርቱን ሊቀጥል ሞክሯል። እናቱ አብሮ የመማር ያህል ከጎኑ ሆና አበርትታዋለች። እንዲያም ሆኖ ‹‹ዳነ›› ሲባል የሚያገረሽበት ህመም ሲፈትነው ቆይቷል።

የደም ካንሰር በባህርይው ለኢንፌክሽን የሚያጋልጥ ነው። ሰበብ ባገኘ አጋጣሚ ሁሉ ህመምተኛውን ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል። ዮሀንስ ልጅ በመሆኑ ይህን በወጉ ለመከላከል ይቸግረዋል። መድሃኒቱን በወሰደ ጊዜ አቅሙ ይዳከማል ፣ በዚህ ወቅት ጉንፋንና ክፉ ሽታ ካገኘው ለኢንፌክሽን መጋለጡ አይቀርም። ይህ አይነቱ ጊዜ ለጤናው የከፋ ፈተና ነው።

እታገኝ ከበሽታው ይልቅ የሚደጋገም ኢንፌክሽን ለሞት እንደሚያደርስ ታውቃለች። በተጓዳኝ የሚከሰት ህመምና የእንሳት ንክኪም አደገኛነቱ ይገባታል። ይህ ችግር እንዳይመጣ ጥንቃቄዋ ልዩ ነው። ዝናብ በጣለ ጊዜ ልጇ ከደጅ እንዳይወጣና ፣ ርጥበት ባየው የመሬት ሽታ እንዳይጎዳ ትጠብቃለች።

ይህ ሁሉ ሃላፊነት የእናትን ብርታት ይጠይቃል። በትንሽ ክፍተት የሚከሰት ችግር የበዛ ዋጋ ያስከፍላል። በእታገኝ ዘንድ ድካምና መሰልቸት አይታወቅም። እንደሰው ማረፍ መተኛት ቢያሻትም ስለልጇ ዕንቅልፍን ካጣች ቆይቷል። አንዳንዴ ዮሀንስ የበሽታው ጫና ሲያስከፋው ይውላል። እንዲህ በሆነ ጊዜ በእናቱ ላይ አብዝቶ ይነጫነጫል።

ዮሀንስ ብዙ ጊዜ ሰበብ ፈላጊ ነው። ለማኩረፍ ዓመሉን ለመለወጥ ጥቂት ነገር በቂው ነው ። አንዳንዴ እናቱ እሱን ማሳመኛ ቃል ይጠፋታል። እንደሌሎች ልጆች መቆጣት፣ መገሰጽን አትሞክርም። ሁሉን ችላ ማሳለፍ ግዴታዋ ነው። እሱ እንዳይከፋ ፣ ሀዘኗን ችላ ፈገግታን ትቸረዋለች።

አሁን እታገኝ ለዮሀንስ ቋሚ ህክምና አዲስ አበባ ትገኛለች። ህክምናው ተከታታይ ትኩረት ይጠይቃል። እሱን ይዛ ለመኖር ቤት ምግብና የዕለት ወጪ ሊኖራት ግድ ነው ። ከቤት ካገሯ የወጣችው ወይዘሮ ግን ቤት ጎጇዋን ከዘጋች ቆይቷል።

እታገኝ በዮሀንስ ህመም ከሴት ልጇና ፣ ከባሏ ርቃ ጊዜያትን መቁጠር ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። እነዚህን ጊዜያት እንደገና ለመጀመር የተገደደችው የዮሀንስ ህመም ዳግም በማገርሽቱ ነበር። ይህ ካገር ያራቀ፣ ጎጆን ያዘጋ ፣ ፍቅር የተመነዘረው ለመጀመሪያ ልጇ ለዮሀንስ ፋሲል ሲባል ነው።

ዮሀንስ አሁን አስራሶተኛ ዓመቱን ይዟል። እናቱ ደግሞ እሱን በማስታመም ሰባተኛ ዓመትን ቆጥራለች።

እንግድነትን በወጉ…

እናትና ልጅ በአሁኑ ጊዜ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እንግዶች ናቸው። እንግድነታቸው ግን ውሎ በመሄድ ብቻ የሚወሰን አይደለም። እነሱን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦች ረጅሙን ህክምና በዚህ ስፍራ እንዲያሳልፉ ዕድል አግኝተዋል። ሁሉም ታማሚዎችና አስታማሚዎቻቸው እንደቤታቸው ሊኖሩ ተፈቅዶላቸዋል።

በዚህ ተቋም የምግብ፣ የትራንስፖርትና መሰል ወጪዎች ይሸፈናሉ። እታገኝ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ከባድና ውስብስብ ነው። እንዲህ መሆኑ ቀላል ባይባልም አሁን እግሯ ለቆመበት ስፍራ ምስጋናዋ የላቀ ነው። ሁሌም የልጇን መዳን አሻግራ የምታየው እናት የውስጧን ጉዳት አሳባው አታውቅም።

ነገን በተስፋ …

እታገኝ ከዚህ ፈታኝ መንገድ በኋላ መልካም ነገር እንደሚኖር ታስባለች ። አንድ ቀን ልጇ ከህመሙ እንደሚድን ተስፋ አላት። ዮሀንስ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያለው ታዳጊ ነው። ጤናው ተመልሶ ያሰበው ሲሳካ የዚህ ሙያ ባለቤት እንደሚሆን አትጠራጠርም። ስለ ልጇ ፍቅር ትዳሯን ርቃ ጎጆዋን የዘጋችው እናት ከፈተና በኋላ ታላቅ ተስፋን ሰንቃ ብሩህ ነገን ታስባለች።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You