ማቲዎስ- ህያው ብላቴና

ትንሹ ብርሀን …

ሁለት ልጆችን በፍቅር የሚያሳድጉት ባልና ሚስት ትዳራቸው ደስታና በረከት የሞላበት ነው። አሁን ደግሞ ከአስር ዓመት በኋላ ወይዘሮዋ ሶስተኛውን ልጅ አርግዘዋል። ይህ እውነት ለጥንዶቹ የተለየ ስሜት ፈጥሮ የልጃቸውን የመወለድ ቀን በጉጉት እየጠበቁ ነው። ከህጻኑ መምጣት ጋር ቤቱ ተሰርቶ አልቋል። አሮጌው በአዲስ ተተክቷል።

እነሆ ! ቀኑ ደረሰ። በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው እንግዳም በጊዜው ዕውን ሆነ። አሁን እናት ልጇን ወልዳ ስማለች። አባወራው የአዲሱ ጨቅላ የምስራች ውስጣቸውን በሀሴት ሞልቷል። ይህ ህፃን ለቤቱ ሌላ ድምቀት ሆኖ ቤተሰቡን ተቀላቀለ። ‹‹የእንኳን ማርያም ማረችሽ›› ወግ የወዳጅ ዘመዱ ጉብኝት ሲጎርፍ ሰነበተ።

ቀናቶች መቆጠር ይዘዋል። አራሷም ህጻኑም እየበረቱ ነው። ትንሽዬው ማቲዎስ፣ ለስላሳ እግሮቹን እያፈራገጠ ይጫወታል። የሚያምሩ ዓይኖቹ ያሳሳሉ። የአንገቱ ስር ሽታ፣ የከናፍሮቹ መዓዛ፣ ልዩ ነው። እሱ ለቤቱ ደማቅ ብርሀን ነው። ዓይኖቹ ሲጨፈኑ ዕንቅልፉ አይታመንም። ሲነሳ ደግሞ መልሶ እንዳይተኛ የሚሳሱለት ሆኗል።

ደስተኛው ማቲዎስ በቤተሰቡ መሀል በፍቅር እያደገ ነው። ሁሉም በጉጉት እያየ ይሳሳለታል። አንደኛ ዓመቱ በድምቀት ከተከበረ በኋላ በእግሩ እየሄደ መሮጥ ጀምሯል። በየሰበቡ፣ ይስቃል፣ በደስታ ይቦርቃል። ዕንባና ሳቁ ለመላው ቤተሰብ ናፍቆት እየሆነ ነው። ‹‹እማማ፣ አባባ ይሏቸው ቃላቶች በኮልታፋ አንደበቱ ውብ ናቸው። በየቀኑ ‹‹አፌ ቁርጥ ይባልልህ›› ሲባል እጅ፣ ጉንጮቹ ሲሳም ይውላል።

አሁን ማቲዎስ የሁለተኛ ዓመቱን የልደት ሻማ ለኩሷል። እንዲህ በሆኑ ጥቂት ጊዚያት በኋላ ግን አዲስ ዓመል ይታዩበት ያዙ። በየምክንያቱ መነጫነጭ፣ ማልቀስና ማኩረፍ ልምዱ ሆነ። የባህሪው ለውጥ የገባቸው ወላጆቹ በብዙ ተጨነቁ። ማቲዎስ ገና ህጻን ነው። በወጉ ‹‹እንዲህ ሆኛለሁ›› ሲል ችግሩን አይገልጽም። ለቀናት ባህርይውን እያጤኑት ቆዩ።

ድንገቴው ስብራት…

ከቀናት በአንዱ ሆስፒታል የደረሱት ወላጆች ደሙን አስመርምረው የሚባሉትን ጠበቁ። በወቅቱ ከእጃቸው የገባው የማቲዎስ የምርመራ ውጤት አስደንጋጭ ነበር። በደሙ ካንሰር ስለመኖሩ ያመለክታል። እናት አምሳለ በየነ የሰሙትን ማመን ተሳናቸው። ይህ ህመም በትንሹ ማቲዎስ ቀርቶ በሌሎችም ይከሰታል ብለው የሚቀበሉት አልሆነም።

በግርምታና በድንጋጤ የከረመው ቤተሰብ ለህጻኑ መፍትሄ ለመሻት ሩጫውን ጀመረ። በውጣ ውረድ የተሞሉ ፈታኝ የጭንቅ ቀናት አንድ ሁለት ብለው ተቀጠሩ። ለመዳን የሚታገለው ትንሹ ልጅ ለሁለት ወራት በሆስፒታል ቆይቶ ከቤት ተመለሰ። ጊዜው የአዲስ ዓመት ጅማሬ ዕለተ ዕንቁጣጣሽ ነበር። መላው ቤተሰብ አዲሱን ዘመን በተስፋ ተቀብሎ ዓይኑን በማቲዎስ ላይ አሳረፈ።

ማቲ ከነበረው ማንነት ተለውጧል። ያሳለፈው ህክምና ከባድ የሚባል ነው። ጸጉሩ፣ ሰውነቱ እንደቀድሞው አይደለም። ውሎ አድሮ ግን ድንቡሽቡሽ መልኩ ተመለሰ፣ ደስታ፣ ፈገግታው ደምቆ ታየ። አባቱ አቶ ወንዱና እናቱ ወይዘሮ አምሳለ ስለልጃቸው ታላቅ ተስፋን ይዘዋል። ሀኪሞቹ ‹‹ድኗል›› ካሏቸው ወዲህ ፈጣሪን በእጅጉ እያመሰገኑ ነው። ቀሪ ህክምናው ለሁለት ዓመታት በምልልስ የሚቆይ ይሆናል። እንደተባለው ሆኖ ማቲዎስ ቆይታውን በወጉ አጠናቀቀ። ሌላው ተስፋ ፈነጠቀ። ከዚህ በኋላ እንደ እኩዮቹ ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት ይገባል። ቀለም ቆጥሮ ዕውቀት ይገበያል።

ማቲዎስ የአራተኛ ዓመቱን ኬክ እንደቆረሰ በድንገት ጤናው ተቃወሰ። ህመሙ እንዳገረሸ የገባቸው ወላጆቹ በድንጋጤ ተሯሯጡ። መፍትሄ ወዳሉትም ፈጠኑ። እናት አባት ስለ ትንሹ ልጅ መትረፍ ብዙ ሆኑ። ቤታቸውን ለመሸጥ ለደለላ አሳዩ።

በዚህ መሀል አሜሪካን አገር የሚገኘው የሜሪ ላንድ ናሽናል ካንሰር ኢንስቲትዩት ሊቀበላቸው ይሁንታውን ሰጠ። የውጭ አገሩ ሂደት በታሰበው ፍጥነት ተሳካ። ከዚያ በፊት ግን ሌሎች ህክምናዎች መቅደም ነበረባቸው። እነሱን እየወሰደ መቆየት እንዳለበት ተወሰነ። አሁን ማቲዎስ ለቦንማሮ ህክምናው ‹‹ኬሞቴራፒ›› እየወሰደ ነው። በወቅቱ በአፍ በአፍንጫው የበዛ ደም ይፈሰዋል።

ይህ ጊዜ አምጣ ለወለደች እናት፣ የልጁን ነገ ለሚያልም አባት በእጅጉ ከባድ ነበር። አቶ ወንዱ የትንሹ ልጅ ስቃይ ካቅማቸው በላይ ቢሆን ራሳቸውን ለማጥፋት እስከማሰብ ደርሰዋል። በኋላ ግን በቅርብ ሰዎች እገዛ ተረጋጉ፤ መለስ ብለውም ብዙ አሰቡ።

መስከረም 13 ቀን 1996 ዓ.ም

ይህ ቀን ለትንሹ ማቲዎስ እጅግ ከባድ ሆኖ ነበር። መድሀኒት መቋቋም የተሳነው የልጅነት አካሉ እየደከመ ነው። ስቃዩ በርትቷል፣ ውስጡ ተሸንፏል። ዓይኖቹን በተሰፋ የሚያዩ ቤተሰቦች አሁንም ትንፋሹን ያዳምጣሉ። እሱ ቢደክም፣ ቢዝልም ለመኖር ትግል ይዟል።

ደቂቃዎች እየቆጠሩ ነው። ጊዜው ገፍቷል፣ ጨለማው በርትቷል፣ ጭንቀቱ አይሏል። ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ግን ሁሉ ነገር አበቃ። የማቲ ትንፋሽ ተቋርጦ የአካሉ ሙቀት ቀዘቀዘ። ተስፋ ላይቀጠል ተቆረጠ። ትንሹ ብርሀን ዳግም ላይታይ ጨለማ ሆነ። ‹‹ደህና ሁን ትንሹ ማቲዎስ፣ አንተ የጎጆው ድምቀት፣ አንተ የእኛ ብርሀን ደህና ሁን…›› መላው ቤተሰብ፣ በእንባ እየታጠበ ተሰናበተው።

ማግስቱን የትንሹ ማቲዎስ ስርዓተ ቀብር ነበር። በቦሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን። ሀዘኑ ለእናት አባት እጅግ ከባድና መራር ነው። ትንሹን ብላቴና ለመሸኘት ስፍራው የተገኙ ሁሉ በዕንባ ይራጫሉ። በዚህ መሀል አንድ ጎልማሳ ወደ አውደ ምህረቱ ብቅ አለ። ሀዘን ያጠላበት ገጽታው ዕንባ ሲያጥበው መዋሉ ያስታውቃል።

ይህ ሰው የማቲዎስ አባት አቶ ወንዱ በቀለ ነው። ሁኔታውን ላየ ለራሱ ቃል የገባ ይመስላል። ሀዘኑን ቻል፣ ዕንባውን ዋጥ አድርጎ ሲቃ በያዘው አንደበት ንግግር ጀመረ። ‹‹ እኔ ልጄ ማቲዎስን አጥቻለሁ፣ ሌሎች ማቲዎሶችን ለማትረፍ ግን እሰራለሁ›› ይህ ብርቱ ቃል ዕለቱን በብዙሀን ጆሮ ደረሰ። ሀሳብ ዕቅዱ የገባቸው ሁሉ የተግባሩን ዕውን መሆን ጠበቁ።

ጠንካራው ድልድይ…

እነሆ ፈታኞቹ የሀዘን ቀናት አለፉ። የትንሹ ብላቴና ትዝታዎች ከቤተሰቡ መሀል ነው። ውሎ አድሮ ግን በሀዘን መብሰልሰሉ ተገቢ አለመሆኑ ታመነበት። አሁን አባወራው ስለሌሎች ህጻናት ቃል የገባው ሀሳብ ሊተገበር ግድ ይላል። ማቲዎስ ቢያልፍም የእሱ ስቃይ በሌላ ትውልድ መደገም የለበትም የሚለው ሀሳብ ሚዛን ደፍቶ እንቅስቃሴው ተጀምሯል።

የዚህ ሀሳብ ጥንስስም በማቲዎስ የመታሰቢያ መቃብር ላይ እንዲህ ዕውን ሆነ። ‹‹ከምወዳችሁ ውድ ቤተሰቦቼ በተሻለ በፈጣሪዬ እጅ ስለሆንኩ እስከምንገናኝ ለኔ አታስቡ፣ እንግዲህ ለንስሀ የሚገባ ፍሬ አድርጉ›› ይህ ቃል ውሰጠትን ገዝቶ ለተግባር አነሳሳ። በማቲዎስ ሞት ሌሎች ይድኑ ዘንድ ምክንያት ሆኖም ፍሬውን ዘራ።

አቶ ወንዱ ልጃቸው በታመመ ጊዜ የሌሎች ካንሰር ታማሚ ህጻናትን ስቃይ አስተውለዋል። ይህ እውነት ደግሞ ስለ ማቲዎስ በማልቀስ ብቻ እርካታ አልሰጣቸውም። አሻራው ደምቆ ማንነቱ እንደ ጠንካራ ድልድይ እንዲያሻግር ትግል ጀመሩ ተሳካላቸው።

በወቅቱ አቶ ወንዱ የትንቧሆ ድርጅት አስተዳዳሪ ነበሩ። ስለማቲዎስ ህያውነት በታሰበ ጊዜ ከእራሱ ኪስ የተገኘች አንዲት ብር ከእርሾው ታክላለች። በአስራ አንድ ሰዎች ማህበሩ ሲቋቋም መኖሪያ ቤታቸው ቢሯቸው ጭምር ነበር።

በወቅቱ እሳቸውን ጨምሮ ባለቤታቸው ያለአንዳች ደሞዝ ለዓመታት የማህበሩን ህልውናውን አስቀጥለዋል። ኋላ ላይ ማዕከላቸው የዓለም ካንሰር ድርጅት አባል ሆነ። ይህን ተከትሎም የፀረ -ትንቧሆ ዘመቻን ማካሄድ ጀመሩ።

ለካንሰር ህመም ሰበብ ከሚሆኑት መሀል ትንቧሆ በዋናነት ይጠቀሳል። አቶ ወንዱ ደግሞ በኃላፊነት የትንቧሆ ድርጅትን ይመራሉ። የተቀጠሩበት ስራ ከያዙት ዓላማ ጋር በግልጽ ይጋጫል። በአንዱ ላይ መወሰን ነበረባቸው። እሳቸው ግን ወደያዙት መንገድ ለማድላት አፍታ አልዘገዩም። ቃል የገቡለትን ዓላማ ለመጠበቅ ስራቸውን ለቀው ወጡ።

ውሎ አድሮ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሰር አሶሴሽን በሁለት እግሩ ቆሞ ተራመደ። የካንሰርና ተያያዥ ጉዳዮች አትኩሮቱ ሆነ። የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ድርጅቶችን በመመስረትና መሳተፍም ዕውቅናን አተረፈ። በተለይ የህጻናት ካንሰርን ‹‹ጉዳዬ›› ነው ያለው ይህ ማህበር ማቲዎስ ያለፈበትን የስቃይ መንገድ ላለመድገም ሞትና ጉዳትን ለመቀነስ አበክሮ መስራት ዓላማው ነው።

በሀገራችን የመጠጥና የሲጋራ ማስታወቂያዎች እንዳይቀጥሉ በማድረግ በኩል ታላቁን ሚና ተጫውቷል። ማህበሩ በአፍሪካ አገራት ጭምር ጥብቅ ቁጥጥር እንዲኖር ጥረቱ ከፍተኛ ነው። በዚህ እንቅስቃሴ አቶ ወንዱ ከአፍሪካ ምርጥ ስድስቶች አንዱ በመሆን ሽልማት አግኝተዋል።

በድርጅቱ ፕሮጀክት የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ህሙማን እየታገዙ ነው። ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ያለው ተሳትፎም በተለያዩ ተግባራት ይገለፃል። ማህበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለሳንባ ካንሰር የኬሞ ህክምና ግብአቶችን በማሟላት የራሱን ጡብ ማስቀመጥ ችሏል። በዚህ እንቅስቃሴው ዓላማውን የሚያግዙ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከጎኑ ናቸው።

በሀገራችን ለካንሰር ያጋልጣሉ ተብለው የሚታሰቡ የፋብሪካ ምግብ አመራረቶች ላይ ትኩረት መስጠት የማህበሩ ተቀዳሚ ዓላማ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ካንሰርን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት በተለያዩ ክልሎች የካንሰር ህሙማን ማዕከላት ተቋቁመዋል። ለህፃናት ካንሰር የሚያገለግል የሬዲዮ ቴራፒ መሳሪያ ከአሜሪካን አገር በማስመጣት ለጤና ሚኒስቴር ለማስረከበብ ተችሏል።

በአሁኑ ጊዜ ማህበሩ ከ1400 በላይ አባላቶችን ይዞ ይንቀሳቀሳል። በድርጅቱ 152 የካንሰር ህሙማንና ቤተሰቦቻቸው ይታገዛሉ። የዚህ ድርጅት ዋንኛ ዓላማ የህፃናት ካንሰር ቢሆንም በተያያዥ ጉዳዮችም ይንቀሳቀሳል።

የብዙሀን እስትንፋስ

ስለማቲ ቤተሰቦቹ ሲያስቡ ስለሌሎች ሲባል በፈጣሪ የተመረጠ ብላቴና አድርገው ይስሉታል። የማቲዎስ የምድር ላይ ቆይታ እጅግ አጭር የሚባል ነበር። ዛሬ በህይወት ባይኖርም በእሱ ሞት ግን የበርካታ ማቲዎሶች እስትንፋስ ተቀጥሏል። የብዙ ህጻናት ተስፋ ለምልሟል። ይህ እውነታ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች በማሳያ ተመስክሯል።

በአንድ ወቅት አቶ ወንዱ አሜሪካን አገር ይጓዛሉ። የመሄዳቸው ዋና ምክንያት በካንሰር ላይ ስላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅኦ ለመሸለም ነበር። ጊዜው ደርሶ ከመድረክ ሲወጡ ግን ዕለቱ ትዝ፣ ትውስ አላቸው። ለካንስ እየተሸለሙ፣ እየተደነቁ ያለው ማቲዎስ በሞተበት ቀን ኖሯል።

ይህ ሲታወቅ በአዳራሹ የነበሩ ሁሉ በዕንባ ታጠቡ። እሳቸው ግን የትንሹ ብላቴና የአደራ መንፈስ አብሯቸው መሆኑን አውቀው ውሰጣቸው ለዳግም ብርታት ተዘጋጀ። የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የበርካታ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤት ነው። ወደፊት በሚኖረው እንቅስቃሴም ካንሰርን መከላከል በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ተቀናጅቶ የመስራት ዕቅድን ነድፏል።

ያልደበዘዙ ትዝታዎች …

ድፍን አርባ ዓመታትን በአንድ ጎጆ ያሳለፉት ጥንዶች በተለይ ገሚሱን የትዳር ዘመን ለበጎ ተግባራት ሲተረጉሙት ኖረዋል። ይህ ይሆን ዘንድ ብላቴናው ማቲዎስ ከእነሱ መፈጠር ነበረበት። ጥንዶቹ ሁሌም እንደሚሉት እሱ ለነገሮች ሁሉ ምክንያት ሆኖ የማያልፍ በጎነት ሊከወንበት ግድ ብሏል። አሁን በቤታቸው ማቲዎስ ከነትዝታው ህያው ሆኖ ቀጥሏል። ዛሬ የልጅነት ለዛው፣ ጣፋጭ አንደበቱ፣ የሳቅ ለቅሶው ቅላፄ ከነሱ ጋር ነው።

ሮጦ ባደገበት፣ ዘሎ በተጫወተበት፣ ሳሎን የእግሮቹ ዳና ርቆ አልሄደም። ባቀፋቸው አሻንጉሊቶች፣ መልካም መዓዛው ላይለቅ ታትሟል። ኳሱ፣ ብስክሌቱ፣ ህመሙን ያዘናጉት መጫዎቻዎቹ ጋደም እስከሚልበት አልጋው በክብር ተቀምጠዋል። እነዚህ እውነታዎች አይረሴውን ብላቴና ህያው አድርገውት ይኖራሉ።

ወርቃማው መስከረም

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር አሶሴሽን ላለፉት ሀያ ዓመታት የህጻናት ካንሰርን መሰረት በማድረግ ሲንቀሳቀስ የቆየ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ነው። ማህበሩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንዲቻል ፕሮጀክቶች በመንደፍ ይንቀሳቀሳል። የመስከረም ወር የህጻናት ካንሰር ህሙማን ወር ነው። ይህን ወር ብዙዎች ‹‹ወርቃማው መስከረም›› ሲሉ ይጠሩታል።

እነሆ ማቲዎስ ወንዱ ካረፈ መስከረም 13 ቀን 1996 ዓ.ም ድፍን ሀያ ዓመት ሞላው። ብላቴናው ወደዚህች ምድር ሲመጣ በምክንያት ሆነና ህይወቱ ካለፈ በኋላ በስሙ የተተገበሩ በጎነቶች የብዙሀንን ነፍስ ይታደጉ ይዘዋል። ይህ እውነት ሲታሰብ ደግሞ ብላቴናው ማቲዎስ ዛሬም ህያው ሆኖ የመቀጠሉ ትርጉም ደምቆ ይታያል።

መልካም ሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መስከረም 19/2016

Recommended For You