ያልተሻገርናቸውን የትናንት ችግሮች ተነጋግሮ ለመሻገር

ምእራባውያን ‹‹ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም›› (Rome wasn’t built in a day) የሚሉት አባባል አላቸው። ትልቅ ነገር የአንድ ቀን ውጤት ሳይሆን በሂደት የሚመጣ ነው ለማለት የሚጠቀሙበት አባባል ነው። እኛም ዘንድ ተመሳሳይ ነው፤ የአክሱም ሐውልት፣ የፋሲል ቤተመንግሥት፣ የሐረር ግንብ ሌሎችም በአንድ ቀን አልተፈጠሩም።

ከማሰብ እስከ መገንባት በርካታ ቀናትን አለፍ ሲልም ዓመታትን ወስደዋል። አዲስ ነገር ለመገንባት አንድ ቀን በቂ አይደለም፤ የተገነባን ለማፍረስ ግን አንድ ቀን ሊበቃ ይችላል። ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን ለመውደዳችን ማንንም እማኝ መጥራት አያሻም። ለዘመናት የተለያዩ ትውልዶች ስለሀገራችን የከፈሏቸው መስዋእትነቶች ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው። የሀገር ጉዳይ ገፍቶ ሲመጣም እንደ ሕዝብ ያለን መነሳሳት ሌላው ማሳያ ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራችን ላለፉት ዘመናት አንድ የሚያደርገን ነገርን በጋራ አክብረን፤ የተናጠል ልዩነታችንን ውበት መሆኑን ይዘን ከመቀጠል ይልቅ በዳይና ተበዳይ በሚል መቧደን ምርጫችን ሲሆን ተስተውሏል። ይህ ደግሞ የተማሩ ተብለው የፖለቲካ ቦታ ባገኙ ሰዎች ይበልጥ መቀንቀኑ ችግሩን ይበልጥ የከፋ አድርጎታል።

አንድ በሚያደርገን የአትሌቲክስ ድል እንኳን ብሔር እየቆጠሩ ወደመደሰት ተሸጋግረናል። በጋራ ለሀገር አንድነት አብረው የዘመቱ ጀግኖችን ወደኋላ ተመልሰን እነሱ ያልለበሱትን የብሔር ካባ መደረብ ምርጫችን ሆኗል።

በሰዎች መካከል ትክክለኛ ተግባቦት ለመፍጠር አንድ ብሔር እንዲህ ነው ብሎ አስቀድሞ መፈረጅ ተገቢም ልክም አለመሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ግን በሀገራችን አንዱን ጠባብ፣ አንዱን ትምክህተኛ፣ አንዱን ተስፋፊ እያልን የዳቦ ስም እየሰጠን ዳቦ ሳንቆርስ አለን።

ድሮም አሁንም አፈር ገፊ የሆነው አብዛኛው ሕብረተሰብ አሁንም በኑሮው ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ የለም። ዳሩ ‹ነገዬን ብሩህ ያደርጉልኛል› ብሎ ጥሪቱን ሸጦ ሳይማር ያስተማራቸው ልጆቹ የአሁኗን ኢትዮጵያ ከመኖር ይልቅ የድሮዋን ኢትዮጵያ ጉድለቶች ማስታወስ ምርጫቸው አድርገዋል።

ትናንት የተዘራ መርዝ ለዛሬ እንደተረፈ ሁሉ ዛሬ የሚዘራ መርዝ መዘዙ ከዛሬ ይሻገራል። ትውልድ በታሪክ አጋጣሚ መልካምም ሆነ መጥፎ እድል ይሰጠዋል። የአሁኑ ትውልድ ስለድሮውም ሆነ ስለአሁኑ በደቂቃ ውስጥ የፈለገውን ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ችግሩ ቴክኖሎጂውን አለመፍጠራችን ሳያንስ፤ የተፈጠረውን ማኅበራዊ ሚድያ በተገቢው መልኩ መጠቀም አለመቻላችን ነው። የደበረውና ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ ያሰበ ሁሉ፤ ከእውቀት ነጻ በሆነ መልኩ ሰዎችን ሲሳደብ አንዱን በአንዱ ላይ ሲቀሰቅስ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች ሰዎች የተሻለ ተጨንቀውና አስበው ከሚሰሯቸው መልዕክቶች የተሻለ ተመልካች ያገኛሉ።

አሁን አሁንማ የመገናኛ ብዙኃንም ለእንግድነት ከሚያቀርቧቸው አብዛኞቹ ሰዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች በኩል ከሕዝቡ ጋር የተዋወቁ መሆን ከጀመሩ ሰነበቱ። ሀገር ሰላም ሁሉ አማን ሲመስል ዋነኛ ትኩረታችን ዳንኪራ መደለቅ ይሆናል። አለፍ ሲልም የሀገሪቷን ሕዝቦች የተለያዩ እንደሆኑ አንዱ አንዱን ሲበድል እንደነበር ይወሳል።

ያም ቢሆን ሀገር ተወረረች ሲባል ሁሉም ለሀገር ሰላም በአንድነት ዘብ ይቆማል። ሆኖም በሰላም ጊዜም አንዱ በአንዱ ላይ ያለውን ቂም ሲያውጠነጥን ከሚከርም ለሀገር አንድነትና እድገት በጋራ ብንሰራ ዛሬያችንም ነጋችንም መልካም ይሆናል።

ሌሎች ሀገራት የትናንት መጥፎ ጠባሳቸውን በጋራ አክመው ተሻግረውታል። ከተለያዩ ሀገራት እንደ እንስሳ አካላቸው ተገምቶ በዋጋ የተሸጡ ዜጎች ልጆች በዳዮቻቸውን ይቅር ብለዋል።

የትናንት ተበዳዮች ሁሉን ትተው ስለዛሬያቸውና ስለነጋቸው ዛሬን በትጋት መሥራት መርጠዋል። እኛ ስለአያት ቅድመ አያቶቻችን ሥራ ዛሬን እንገዳደላለን። የዛሬ መገዳደል ደግሞ ለነገ ቂም ያስቋጥራል።

በርካቶች ዛሬን ከመኖር ይልቅ ምርጫቸው ስለድሮው ማውጠንጠን ሆኗል። ችግሩ የድሮውን ዘመን አሁን ባለን አረዳድ መመዘናችን ነው። ለምን ልክ እንደኛ አላሰቡም? ለምን እንደኛ አልሆኑም? ብለን ስንብሰለሰል ለእኛ የተሰጠን ዘመን ሳንጠቀምበት ባክኖ ይቀራል። ፉክክራችን ከሞተና ካለፈ ሥርዓት ጋር ሲሆን አሁን ያሉት ይበልጥ ጥለውን ይሄዳሉ።

እኛ የድሮዎቹ ‹እንዲህ ቢያደርጉ› ኖሮ ብለን ስንቆጭ እኛ ማድረግ ያለብንን ማድረግ ሳንችል ቀርተናል። እስከመቼ ያለፉትን ወቅሰን እንዘልቃለን? ዓለም ምድር ጠቧት ሰዎች ስለአማራጭ መኖሪያዎች ይጨነቃሉ። እኛ አሁንም ሃሳባችን ከቀበሌዬ ውጣ፤ ቅድመ አያትህ አያቴን አሰቃይቶታል ላይ ተቸክሎ ቀርቷል። ለመሆኑ በዚህ ዓይነት እሳቤ እስከመቼ ድረስ እንቆዝማለን?!

በደሉን ያልናቸውን ቀደምቶቻችንን እንብለጣቸው፤ እኛ ከእነሱ ተሽለን ለነገ ትውልድ የተሻለች ሀገር ማቆየት ላይ እናተኩር። በያዝንበት ከቀጠልን የዛሬ ሂሳብ አወራራጆች ነገ ሂሳብ ይወራረድባቸዋል። ይሄ አዙሪት አንድ ቦታ ካልተሰበረ ድግግሞሹ ሀገርንም ሕዝብንም ወደኋላ ያስቀራል።

ለመጪው ትውልድ ከብቀላ አዙሪት በመውጣት ርግማንን ሳይሆን ምርቃት ማሻገር ላይ መስራት ይጠቅመናል። ለዚህ እስካሁን ብንዘገይም በፊታችን ባለው ሀገራዊ ምክክር መድረክ እውን ልናደርገውና ዘመን ተሻጋሪ ለሆኑ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ልናገኝ እንችላለን።

 ከትዝታ ማስታወሻ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2015

Recommended For You