‹‹ውለታ ዶት ኮም›› – ሰነዶች ላይ በዲጅታል ለመፈረም

 የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሁሉ ወደ ዲጅታላይዜሽን እየተቀየረ ባለበት በዚህ ዘመን ከዲጅታል ቴክኖሎጂ ውጭ መሆን እጅግ ከባድ ነው። ስለዚህም ወደን ብቻ ሳይሆን ተገደንም የዲጅታሉን ዓለም እንቀላቀላለን። አሁን ጊዜን፣ ወጪንና ጉልበትን ለመቆጠብ ከፈለግን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ግድ ይለናል። ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ጊዜና ርቀት ሳይገደባቸው በቴክኖሎጂ በፈጠነ መንገድ ጉዳያቸውን ለመከወን ካሰቡም ቴክኖሎጂው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ ከእርሱ ጋር መላመድ መምረጥ ያለብን ጉዳይ ነው።

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዲጅታላይዜሽን እየተስፋፋ እና ፍጥነቱን እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ዲጅታል ቴክኖሎጂውን እየተለማመደ መጥቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ የዲጅታል ገበያውን አስፋፍቶት የክፍያ ሥርዓቶች ጭምር በቴክኖሎጂ አማራጭ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል። ለዚህም ዲጅታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ በርካታ አሠራሮች እየተዘረጉ ናቸው። በቅርብ ይፋ የሆነው በሰነዶች ላይ በዲጅታል መልኩ ለመፈረም የሚያስችለው መተግበሪያ ደግሞ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

ይህ መተግበሪያ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከወነ ሲሆን፤ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ሰነድ መፈረም የሚያስችል ነው። ‹‹ውለታ ዶት ኮም›› (weleta dot com) የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ሲሆን፤ በይነመረብን በመጠቀም ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው ሰነድን ዲጅታል በሆነ መንገድ እንዲፈርሙ የሚያስችላቸው ነው።

መተግበሪያው ቪዲቸር ቴክኖሎጂ ሶሊሽን ፒኤልሲ (Viditure Technology Solution PLC) በተሰኘ በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰራ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በአካል ተገናኝቶ በወረቀት ላይ ሲፈረም የነበረውን የወረቀት አሠራር የሚያስቀር ነው ተብሎለታል።

የኩባንያው መስራችና የውለታ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኬብሮን ጌታቸው እንደሚሉት፤ አዲሱ መተግበሪያ ሰዎች በአካል መገናኘት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ቦታ ሆነ በዲጅታል መንገድ ሰነዱ ላይ መፈረም የሚችሉበት ዘዴ ነው። ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ሊፈረምላቸው የሚፈልጉትን ሰነድ ቦታ፣ ጊዜ እና ርቀት ሳይገድባቸው ባሉበት ሆነው በፍጥነት ተፈርሞ ወዲያወኑ እንዲደርሳቸው የሚያደርግ ነው።

‹‹ቴክኖሎጂው ቀደምሲል ሰዎች ማሟላት የሚጠበቅባቸው ነገሮች ሁሉ አሟልተው ሰነድ ብቻ ለማስፈረም የሚወስድባቸውን ረጅም ጊዜ የሚቀንስ ነው። አላስፈላጊ ወጪንም ያስቀራል። እንግልትን በመቀነስ በኩልም ሁነኛ መፍትሄ የሚሰጥ ነው። በተለይም ሚኒስትሩ የለም፤ ኃላፊ የለም እና ባንከሩ የለም የሚሉ ሳይባል ፍላጎቶችን በአጭር ጊዜ ሰነዱ በእጅ ስልካቸው መጥቷላቸው ፈርመው መልሰው እንዲልኩ የሚያስችል ነው ›› ይላሉ ።

በኢትዮጵያ ሕግ 1072/2018 የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ሕግ መሠረት ሕጋዊ ተቀባይነት ያገኘው ውለታ ሕጋዊነቱን ጠብቆ የሚሰራ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ኬብሮን፤ ኩባንያው በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ደህንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ መተግበሪያ ዲጅታል ፊርማ ፈራሚውንም ሆነ አስፈራሚውን የዲጅታል ሰነድ ለመጠቀም እና በዲጅታል መንገድ ለመፈራረም ከተስማሙ በእጅ በአካል ከሚፈረሙት የወረቀት ሰነዶች እኩል ክብደት እና በሕግ ተቀባይነት ያለው ነው። ነገር ግን ፈራሚው የታመነ የማንነት መለያ መታወቂያ ሊኖረው ይገባል። የቪዲዮ ቃለመሃላ፣ የመታወቂያ ፣ የኢሜል እና የመልዕክት ማረጋገጫ በመስጠት ታማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎቱ የሚሰጥ መሆን ይገባዋልም ሲሉ ያብራራሉ።

አሁን ላይ ሁሉንም አይነት ሰነዶች በውለታ ዶት ኮም መተግበሪያ በኩል የሚፈረሙ አለመሆናቸውን የሚያነሱት አቶ ኬብሮን፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ የሰነድ ውል ላይ ለመፈረም በሁለት አይነት መንገድ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ይጠቁማሉ። ለአብነት ለኮንትራት፣ ለማማከር ሥራ እና ለሽያጭ የሚፈረሙ የሰነድ አይነቶች ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ መሄድ ሳያስፈልግ በውለታ ዶት ኮም አማካኝነት መፈረም እንደሚቻል ይገልጻሉ።

አቶ ኬብሮን፤ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ መሄድ ያለባቸው የሰነድ አይነቶች የቤት ሽያጭ፣ የመኪና ሽያጭ፣ የኢኮርፕሬሽን እና የመሳሰሉት ሰነዶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ሰነዶችንም ቢሆን ወደ ዲጂታል ለማምጣት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር ሥራዎችን እየተሰሩ እንደሆነ ያነሳሉ። ሥራዎቹ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ፤ እስከስድስት ወር ባለው ጊዜ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ይናገራሉ።

አሁን ላይ ባለው ሂደት ለዲያስፖራው ሕጋዊ ውክልና መስጠት ተጀምሯል የሚሉት አቶ ኬብሮን፤ ዲያስፖራው ባለበት አገር ካለበት ቦታ ሆኖ ሕጋዊ ውክልና ይሰጣል፤ ውክልናውን በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በኩልም ተቀባይነት አለው። በአገር ውስጥ የሚሰጠውን የውክልና ሥራ በተመለከተ ወደ ዲጅታል በማምጣት በኦንላይን አሠራር (ሲስተም) እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ አቶ ኬብሮን ማብራሪያ፤ ዲጅታል አሠራር (ሲስተም) ከውጭ ኢንቪስትመንት አቅጣጫ ሲታይ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ቢዝነስን በማቃለል ያለንበት ደረጃ ከፍ ያደርገዋል። ከዚህ ባሻገር ቢዝነሶችን ከአንድ አካባቢ ሆኖ ለብዙ ደንቦች ተደራሽ ማድረግ ያስችላል። ለአብነት ባንኮች ቅርንጫፍ የሌላቸው አካባቢዎች ላይ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ያደርጋል። አሠራራቸውን በዲጅታል በማድረግ ባሉበት ሆነውም ውሉን ተፈራርመው ሊልኩ ይችላሉ። በተመሳሳይ የሥራ ግንኙትነትን በማፍጠን ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። አንድ ሠራተኛ ፈቃድ ለመውጣት ፈልጎ በወቅቱ ፈቃዱን የሚፈርመው ኃላፊ ባይኖር ፈቃድ የሚፈልገው ሠራተኛ ኃላፊው እስኪመጣ በመጠበቅ የሚፈጀው ጊዜ አይኖርም።

የኮንስትራክሽን ሳይት ከአዲስ አበባ ውጭ ሆኖ የድርጅት ሥራ አስኪያጅ ደግሞ አዲስ አበባ ከሆነ የወረቀት ሰነዱ ፣ በሞተር ተልዕኮ ተፈርሞ እስኪመጣ ድረስ ያለው የሳይቱ ሥራ ሊቆም ይችላል። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በዲጅታል መንገድ ፈርሞ ቢልክ ግን በዲጅታል ከተላከለት የትም ቦታ ላይ ቢሆን ፈርሞ ወዲያው መላክ የሚያስችል አሠራር መሆኑም ቴክኖሎጂው ያለውን ጠቀሜታ በእጅጉ የሚያሳይ ነው ይላሉ።

ስለውለታ ዶት ኮም አጠቃቀም ሲገልጹም ‹‹አንድ ፊርማ ለማስፈረም የፈለገ ሰው ዌብ ሳይቱ ላይ ገብቶ ካሉት ፓኬጆች የሚፈልገውን ይመርጣል። እንደሚፈልገው መጠን ፣ እንደአጠቃቀሙና ባለው ቡድን ልክ ከመረጠ በኋላ ይገባል (ሎግኢን) ያደርጋል። ከዚያም ኦንላይን ክፍያ ይፈጽጻማል። ሲወጣ (ሳይንአፕ) ሲያደርግ ሰነዱን አዘጋጅቶ ፒዲኤፍ በማውረድ የሚፈለግበትን ቦታና ቀን ሆነ የሚያስፈልገውን ጉዳይ ሰነዱ ውስጥ ያስገባል። ለሚፈርምለት ሰው ኢሜልና ስልክ ቁጥር ሲስተሙ ላይ አስገብቶ ይልካል። ፈራሚው አካል መረጃው ወዲያውኑ በስልኩ መልዕክት ይደርሰዋል። ከዚያም ወዲያወኑ ፈርሞ በቪዲዮ ቃለመሃላ ‹እኔ እገሌ በዚህ ሰነድ ቁጥር ተስማምቼለሁ› ብሎ በስልኩ ላይ በእጁ ይፈርማል። አረጋግጦ ወዲያውኑ ይለከዋል። ከዚያም በኋላ አሥር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መመለስ ይችላሉ» በማለት አብራርተዋል።

ይህንን ሰነድ አዘጋጅቶ የሚልከው አስፈራሚ ሰው ሁለት ደቂቃዎች ያህል የሚፈጅበት ሆኖ ፈርሞ የሚልከው ሰው ልክ እንደዚያው ሁሉ በሁለት ደቂቃ ያህል ጊዜ ውስጥ ፈርሞ ይልካል። ሰነዱ እንዲፈረም ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ቢላክ እንኳን እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜው ውስጥ ወዲያው ተፈርሞ የሚላክበት ሁኔታ መኖሩንም ይገልጻሉ። የፈርማ ሂደቱ እንደግለሰቦች ፍጥነት የሚለያይ ሲሆን፤ ወዲያውኑ አይቶ በፍጥነት ምላሽ ለሚሰጥ ሰው ከአሥር ደቂቃ ጊዜ የማይወስድ መሆኑን ያብራራሉም።

‹‹ውለታ ዶት ኮም ›› የተሰኘው መተግበሪያ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችና በውጭ ቋንቋዎች እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በኦፋን ኦሮሞ ፣ በትግርኛ ፣በሱማሊኛ እና በአፋርኛ ቋንቋዎች የተሰራና የሚሰራ ሲሆን፤ ከውጭ ቋንቋ ደግሞ በፈረንሳይኛ፣ በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎቱን የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸውልናል።

ይህ የቴክኖሎጂ ኩባንያ እስካሁን ባለው ልምድ የሰራቸው ሥራዎች ጥንቃቄ የሚያሻቸው በመሆናቸው እንደ ውጭ ጉዳይና ኢሚግሪሽን አይነት መሥሪያ ቤቶች ጋር ነው የሚሉት አቶ ኬብሮን፤ ኩባንያው ‹‹የቴክኖሎጂው ደህንነት የተጠበቀ ነው። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ከኢንፎርሜሽን መረጃና ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የተረጋገጠ ሰርተፊኬት ማግኘቱ ነው። በቀጣይ ከኢንፎርሜሽን መረጃና ደህንነት አስተዳደር ጋር በአብረን ለመስራትም ስምምነት አድርገናል›› በማለት ተናግረዋል።

መተግበሪያውን ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኮምፓኒዎች እና የተለያዩ ድርጅቶች እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በተለይ ፋብሪካዎችና የተለያዩ ክፍተቶች ያላቸው ተቋማት በመግባት እየተጠቀሙት ነው። ውለታ ገና አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ትላልቅ ኢንተርፕራይዞች ጋር አልዘለቀም። እናም ከእነርሱ ጋር ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛል። ከአንዳንዶች ጋር የኮንትራት ስምምነት እያደረገ ሲሆን፤ 40 የሚሆኑ ትናንሽ ኢንተርፕራይዝ (ፋብሪካዎች ኮንስልቲንት) ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙ ነው ይላሉ።

እንደ አቶ ኬብሮን ገለጻ፤ ውለታ መተግበሪያ ለአጠቃቀም ቀላል ነው። የንግድ እና የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴን ያቀላጥፋል። በሥራችንም ውጤታማ ያደርገናል። አዲስ እንደመሆኑ መጠን ተጠቃሚው ላይ የሚታይ ትንሽ ክፍተቶች ቢኖሩም ችግሩ ግን እንደ ቴሌ ብር፣ ሲቢኢ ብር እና የመሳሰሉ መተግበሪያዎች ላይ እንደታየው አይነት ነው። ሕብረተሰቡ የመተግበሪያውን ጥቅም ከተገነዘበ በኋላ ለመጠቀም ወደኋላ አይልም። በተለይ ወጣቱ ቴክኖሎጂን ከለመደ ብዙ የጠቀምበታል። ለዚህ ደግሞ የሚከብደው አይነት አይደለም።

‹‹ቴክኖሎጂውን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ ይፈጃል። ከሁለት እስከ አራት ዓመት ድረስ ጊዜ ሊወስድም ይችላል። ነገር ግን ሁሉም ሰው ሊጠቀመው የሚችለው መተግበሪያ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ ›› የሚሉት አቶ ኬብሮን፤ ኩባንያው አገር ውስጥ መሥራት ከጀመረ አራት ዓመት ያህል አስቆጥሯል። በዚህ ቆይታውም በርካታ ተግባራትን አከውኗል። አንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የውክልና ሰነድ ማረጋገጥ አሰራር (ሲስተም) መሥራት ሲሆን፤ ሌላኛው የኢሚግሪሽን ጉዳዮች ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፓስፖርት እና በተለምዶ ቢጫ ካርድ (origin ID Cards) ተብሎ የሚጠራውን መታወቂያ ሲስተም መዘርጋት ነው። በጠቅላላው ለዲያስፖራው አገልግሎት የሚሰጡበት ሲስተም መዘርጋት ላይ ሲሳተፍ እንደቆየ ያስረዳሉ።

አሁን ላይ ከብዙ ተቋማት (ከንግድ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴርና ከሰነዶች ማረጋገጫ) ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነም ይናገራሉ። ቀጥለውም ‹‹ከዚህ በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከአሜሪካና ከአውሮፓ የተሻለ ከዓለም አንደኛ የሆነ ውክልና አገልግሎት መስጠት የሚችል አሠራር ዘርግተናል። አንድ ሰው ውክልና ዛሬ ሰጥቶ በነጋታ የሚደርሰበት አሠራር ነው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰራነው። ይህም ዲያስፖራው በአገር ውስጥ ውክልና መስጠት ከፈለገ በቀላሉ ሊያገኝ የሚችልበት አሠራር ሲሆን፤ ዲያስፖራው ውክልና ሰጥቶ አገር ቤት ካለው አካል ጋር ተገኝቶ በነጋታው ቤት ይገዛለታል፣ ቢዝነስ ይቋቋምለታል፤ ሥራ ይጀምራል፤ የግል ጉዳዮቹ ይፈጸሙለታል። ስለዚህ ዲያስፖራውን በቀላሉ እንድናገናኝ ሆነናል›› ይላሉ።

እንደ ቢዝነስ ውለታ መተግበሪያ አንድ ሰነድ ሲፈረም ከ50 እስከ 75 በመቶ ገቢ ያገኛል የሚሉት አቶ ኬብሮን፤ ይህ በጣም ርካሽ እና አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል እንዲጠቀመው የሚያስችል ነው። ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ከአዲስ አበባ ሆኖ ጅማ ላለው ሰው ፈርማ መጠይቅ ቢያስገባ ይህ ሰው ለላከለት ሰው እንደፓኬጁ አይነት 50 ብር ወይም 75 ብር ይከፍላል። ክፍያው በዚያው በቴሌ ብር፣ በሲቢኢ ብር የዲጅታል መክፈያ መንገዶች ሆነ ኦንላይን የሚከፍል ይሆናል። በዚህ የክፍያ ሥርዓት ከፋዩ ማሰብ ያለበት ለአላስፈላጊ ወጪ ሳይዳረግ፣ ጊዜና ጉልበቱ ሳይባክን ባለበት ቦታ ሆኖ የሚያከናወነው ተግባር በመሆኑ በእጅጉ ርካሽ የሆነ ዋጋ መሆኑን ነው።

በቀጣይ ‹‹ውለታ ፎርም›› በሚል አዲስ የሚጀመሩት ፎርም መኖሩን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ህብረተሰቡ የመንግሥትና የኢንተርፕራይዝ አገልግሎቶችን በቀላሉ መጠቀም እንዲችል አማራጭ እንደሚሆነው ይናገራሉ።

‹‹አሁን ያለንበት ሁኔታ ሁሉንም ነገር ዲጅታል ካላደረግን ኢኮኖሚውንም ሆነ አገልግሎቱን ማስቀጠል አንችልም። ዲጅታላይዜሽን ቅንጦት አይደለም፤ አስፈላጊ ነገር ነው›› የሚሉት አቶ ኬብሮን፤ መንግሥት ይህ ገብቶት ነው ትኩረት ሰጥቶት ድጋፍ እያደረገ ያለው። ይህም በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *