እንደመነሻ …
ጠንካራ እጆቹ ለሥራ ብርቱ ናቸው። ለመንገድ የማያርፉት እግሮቹም ስንፍናን ይባል አያውቁትም። ሰፊ ትከሻው ሁሌም ለሸክም ዝግጁ ነው። ‹‹ደከመኝ››ን ሊናገረው አይሞክርም። በቀን ውሎው ሲባክን ቢውልም መሽቶ በነጋ ቁጥር እንደ አዲስ ይታደሳል። አካሉ ይበረታል፣ መንፈሱ ይነቃል። ቀጣዩ ቀን ለእሱ ሁሌም አዲስ ነው። ተስፋን ያሲዘዋል፣ ብርሀን ያሳየዋል።
ወፍ ሲንጫጫ ጀምሮ ጓዙን ሸክፎ ለጉዞ ሲዘጋጅ አፉን በእህል አይሽርም። ይህን ‹‹ላድርግ›› ቢል እንኳን ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም። ቤቱ ለጎን ማረፊያ እንጂ ለምግብ ማብሰያ አትበቃም። ትንሽዋ ቤት ከእሱ ውሎ የሚያድረውን ጓዝ ጨምሮ አብሮ አደግ የአጎቱን ልጅ አሳድራ የምትሸኛቸው በጭንቅ ነው።
ከአቅሟ በላይ በሚከፈሉባት ጠባብ ክፍል ትንፋሽ ተጋርተው፣ ሕይወት ተካፍለው ያድራሉ። ሁለቱም ሮጦ አዳሪ ናቸው። ከገጠር አዲስ አበባ ያመጣቸው የእንጀራ ጉዳይ ነው። ስለነገው ማንነታቸው ጥረው፣ ግረው መለወጥን ይሻሉ። ለእነሱ የከተማ ኑሮ እንደገጠር አይደለም። ከጓዳ እጅ ሰደው አይቆርሱበትም። እንዳሻቸው ከማጀት አይቀዱበትም። የዚህ ሕይወት ሩጫን ይጠይቃል፣ የላብ ዋጋን ያስከፍላል።
ወጣት በቃሉ ኖረ ይህን ዕውነት አሳምሮ ያውቃል። ስለነገው ማንነትም በዛሬው ትጋት ይበረታል። እሱ ሁሌም ከዕንቅልፉ እንደነቃ ፊቱን ውሀ አስነክቶ፣ ቸር ላሳደረው ፈጣሪ ምስጋናን ማቅረብ ልማዱ ነው። በቃሉ ከቤቱ ሲወጣ እንደሌሎች ቀለል ብሎት አይደለም። ትከሻው፣ እጆቹ፣ ወገቡ መላ አካሉ ለሥራ ይዘጋጃል ።
በየቀኑ ተሸክሞት የሚውለው ጓዝ የእንጀራ ማስገኛው ከሆነ ሰንብቷል። በአንገቱ አጥልቆ፣ በደረቱ ደርድሮ የሚሸከማቸው በርካታ የቆዳ ቀበቶዎች፣ የገቢ ምንጮቹ ናቸው። ሁለት እጆቹ ለአፍታ እረፍት ይሉትን አያውቁም። በግራ ቀኝ አንጠልጥሎ በሚይዛቸው በርከት ያሉ ዕቃዎች ተወጥረው ይውላሉ። ትከሻውም ቢሆን ከሸክም የዳነ አይደለም። በዕቃዎች የታጨቀ ሻንጣ ከጫንቃው አርፎበት ሲዞር፣ ሲባትል ይውላል።
አስሩ ጣቶቹ እያንዳንዳቸው የተሰጣቸውን ተግባር አይስቱም። የኪስ ቦርሳዎችን፣ የስልክ ቻርጀሮችን፣ ሶኬቶችን፣ የጆሮ ማዳመጫዎችን ይዞ የሚዞረው በእነሱ ብርታት ነው። አንዳንዴ ሞቅ አድርጎ የሚያሰማው ገመድ አልባ የስፒከር ሬዲዮ የመንገደኞችን ጆሮ ይስባል። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚም ገበያ ለማግኘት ከአጋጣሚው ያገናኘዋል። እንዲህ በሆነ ጊዜ በመንገዱ ጠያቂዎች አይጠፉም። ‹‹እንግዛህ›› ባዮች ይበረክታሉ፣ ያለምክንያት አስቁመው የሚያደርቁት፣ የሚከራከሩት ይበዛሉ ።
በቃሉ ማልዶ ከቤት ሲወጣ እግሮቹ የት እንደ ሚያደርሱት አያውቅም። ለእሱ ሁሉም አቅጣጫ ወደ እንጀራው መንገድ ይመራዋል። ጥልፍልፉ የላስቲክ ጫማው በየቀኑ አርቆ ሊወስደው ዝግጁ ነው። ፈጽሞ ድካምን አያውቅም። በዓይኖቹ ግራናቀኝ እየቃኘ፣ ዕቃዎቹን እያስተዋወቀ፣ ወደፊት ይጓዛል።
ብርቱ እግሮቹ ከአውቶቡሱ፣ ከታክሲው ለመግባት አይሽቀዳደሙም። ከአስፓልቱ፣ ከጉራንጉሩ፣ ከውስጣውስጡ መንደር እያደረሱ ኪሎ ሜትሮችን ያስቆጥሩታል። በላዩ የከመረውን ጓዝ እንደያዘ፣ ቀኑን ሙሉ በትጋት ይራመዳል፣ ድምጽና ጥሪ እያዳመጠ፣ አቅጣጫ እየፈለገ ስለ ገበያው ይባዝናል።
በእሱ ዘንድ ዝናብና ፀሐይ፣ ሙቀትና ደመና ትርጉም የላቸውም። ሁሉንም በብርታት አሸንፎ ቀኑን ለመርታት ትግል የገጠመው ከራሱ ጋር ሆኗል።
የልጅነት ምኞት…
የልጅነት ሕይወቱ የሚቀዳው ከገጠሩ ክፍል ነው። በሕጻንነቱ ወላጆቹ ያሳደጉት በእንክብካቤ እንደነበር ያስታውሳል። ለቤቱ የመጀመሪያ ልጅ ነውና የጎደለበት አልነበረም። የጠየቀው፣ እየተገዛ የፈለገው ሲሟላለት አድጓል። በቃሉ በወላጆቹ ፍቅርና ትኩረት ደስተኛ ሆኖ ልጅነቱን ተሻገረ።
ዕድሜው ከፍ ማለት ሲይዝ እናት አባቱ አርቀው አሰቡ። ልጃቸው ከመንደሩ አስኳላ ገብቶ ቢማር እንደሚበጅ መከሩ። ምክራቸው ከመሬት አልወደቀም። እንዳሰቡት ሆኖ የልባቸው ሞላ። ልጃቸው ፊደል ይቆጥር፣ ዕውቀት ይሸምት ዘንድ ከተማሪ ቤት ላኩት።
የአስኳላ ውሎ…
በቃሉ ከእኩዮቹ ቢውል፣ ከባልንጀሮቹን ቢቀላቀል ለጊዜው ደስ አለው። ትምህርት ቤት ውሎ መግባቱ የልጅነት ፈገግታውን አደመቀው። ውሎ አድሮ ግን ስሜቱ እንደቀድሞው አልሆን አለ። ትምህርት ቤት መሄድ አስጠላው። ፊደል መቁጠር፣ ቀለም መለየቱ ሰለቸው። ባልንጀሮቹ ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት ሲሄዱ እሱ ከቤት መዋልን መረጠ። ትምህርት ይባልን ጉዳይ ‹‹ዓይንህ ላፈር›› ሲል ከቤቱ ቀረ፤ ከመንደር ዋለ ።
በቃሉ ልጅ ሳለ ጀምሮ የተጠናወተው ሕመም ከፍ ማለት ሲይዝ አልተወውም። ውስጡን የሚያስጨንቀው ስሜት ለትምህርቱ ጭምር ሰበብ፣ ምክንያት ሆነበት። እያመመው፣ እየጨነቀው ዕድሜውን ቆጠረ። ወላጆቹ ልጃቸውን ለመታደግ አልቦዘኑም። የአቅማቸውን ጣሩ።
ከሕክምናው፣ ከጠበሉ አመላለሱት
የበቃሉ ጤና እንደታሰበው አልሆነም ደርሶ ውስጡን የሚያስጨንቀው ስሜት ማንነቱን ይገዳደር ያዘ ጭንቀቱ ከልብ ሕመሙ ተዳምሮም ትምህርቱ ሊቋረጥ ግድ ሆነ ቀድሞም የመማር ፍቅር ያልነበረው ጉብል ከቤት፣ ከቀዬው መታየት ያዘ አርሶ አደር ቤተሰቦቹ አሁንም ስለእሱ ግድ ቢላቸው አጥብቀው አሰቡለት፣ ተጨነቁለት።
በቃሉ በዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር አርቆ ማሰቡ አልቀረም ከአዲስ አበባ ወደ መንደራቸው ዘመድ ጥየቃ የሚመላለሱ ወጣቶችን ሕይወት ተመኘ አብዛኞቹ ከቀያቸው ርቀው አዲስ አበባ የከተሙ ናቸው በአጋጣሚ ከመንደሩ ሲዘልቁ ራሳቸውን ቀይረው በኑሮ ተለውጠው ነው።
ጥቂት የማይባሉት አገራቸው ሲገቡ በሚያምር ልብስ ይዋባሉ ከኪሳቸው ገንዘብ፣ ከእጃቸው ጥሩ ሞባይል አይጠፋም ይህ ሁሉ ለውጥ ለበቃሉ የሚሰጠው ትርጉም የተለየ ነው ትምህርቱ ካልተሳካ፣ ጤናው በጎ ካልሆነ ገጠር ተቀምጦ መተከዝ፣ ማሰቡ እንደማይበጅ ከገባው ቆይቷል።
እሱም እንደእነሱ ካለበት ርቆ የከተማ ሰው መሆንን እየተመኘ ነው ምኞቱ ደግሞ እንዲሁ በባዶው አይደለም ከሚያስበው ደርሶ መሥራትና መለወጥን ይሻል ይህን መሻቱን ለማሳካት ከራሱ መክሮ መወሰን አለበት።
በቃሉ ሚስጥሩን ለሌሎች ማካፈል አልፈለገም የሚያስበው ቀን ደርሶ ከቀዬው እስኪወጣ ጊዜውን ማስላት ይዟል ወላጆቹ ያጡ፣ የነጡ አይደሉም ቤቱ የሞላ አገሩ የለመለመ ነው።
መሬቱ የሰጡትን ያበቅላል ገበሬው በለም መሬቱ ያሻውን ያመርታል በየዓመቱ ጎተራ ሙሉ ይታፈሳል ይህ እውነት ግን የበቃሉን የሸፈተ ልብ አልመለሰም አሁንም መንገዱን እያሰበ፣ ነገውን እያለመ አጋጣሚውን ይጠብቅ ጀምሯል።
ከቀናት በአንዱ …
የበቃሉ ልብ አሁንም ከመንገዱ እንዳተኮረ ነው ከሰሞኑ ደግሞ ከተማ የሚኖር አንድ የአጎቱ ልጅ ከቀዬው ደርሷል የእሱ መምጣት ይበልጥ ያነቃው ወጣት የአዲስ አበባን ኑሮና ሕይወት፣ እየጠያየቀ ሰንብቷል ከእሱ የሚሠማው እውነት ለውስጠቱ የሚጎረብጥ አልሆነም ይበልጥ ውስጡን አንቅቶ ለመንገዱ አዘጋጅቶታል።
አንድ ቀን በቃሉና የአጎቱ ልጅ በጉዳዩ ሲመክሩበት ዋሉ እንግዳው ወጣት እሱ ያሰበውን ዕቅድ አልተቃወመም እንደውም አብረው ቢሄዱ የተሻለ እንደሚሆን ነግሮት ልቡን አነሳሳው።
ይህን ካወቀ ወዲህ በቃሉ ጓዙን ሸክፎ ለመንገዱ ተዘጋጀ ቀናቶች አለፉ እንግዳው የአጎቱ ልጅ ወደአዲስ አበባ ሊመለስ ዘመዶቹን ተሰናበተ አንድ ማለዳ በቃሉ እሱን ተከትሎ ከትውልድ ቀዬው ወጣ ምዕራብ ጎጃም ‹‹አዴት›› ወረዳን ለቆ ከሰፈሩ ራቀ በልቡ አገሩን፣ ቤቱን፣ወላጆቹን ተሰናበተ።
ይህ ሲሆን ማንም አልሰማም እናት አባቱ፣ ወንድሞቹ፣ ዘመዶቹ አላወቁም እሱ ይህን ማድረግ አላስፈለገውም ዕቅድ ሀሳቡ አዲስ አበባ ገብቶ እንደሌሎች መለወጥ፣ እንደእኩዮቹ ራስን ማሸነፍ ነው።
ኑሮ በአዲስአበባ …
አሁን በቃሉ ከተማ ደርሶ የአዲስ አበባ ልጅ ሆኗል አብሮት ያለው የአጎቱ ልጅ ካገሩ ከወጣ ዓመታትን አስቆጥሯል ኑሮውን የሚመራው ሽቶዎችን እያዞረ በመሸጥ ነው ከመርካቶ የሚያመጣቸውን የሽቶ ምርቶች እያዞረ መሸጡ ጥቂት ትርፍ ያስገኝለታል ለበቃሉ ይህ መነሻ ሆኖ የሥራውን አይነት እንዲለይ ምርጫ ሰጥቶታል።
ቀናትን ውሎ ያደረው ወጣት ለውሳኔው አልዘገየም ከቀረቡለት የሥራ አማራጮች ‹‹ይበጀኛል›› ባለው ላይ ልቡ አርፏል የቀበቶ፣ የቻርጀር፣ የገመድ አልባ ሬዲዮና መሰል ዕቃዎችን እያዞረ የሽያጭ ሥ ራውን ጀምሯል
በቃሉ ከአካባቢው፣ ከነዋሪው ለመላመድ አልቸገረውም ዕቃዎቹን ከአንገት ከትከሻው አንጠልጥሎ ከተማውን መዞር የጀመረው በአጭር ጊዜ ነው በየቀኑ ረጅም መንገድ በእግሩ ይጓዛል ከሚኖርበት ልደታ ሰፈር ተነስቶ መገናኛ ፣አራትኪሎ፣ ፒያሳ የሚደርሰው ጠንካራ እግሮቹን ተማምኖ ነው እነዚህ እግሮች በአዕምሮው አቅጣጫ እየተመሩ ካሻው ያደርሱታል መልሰው ከቤት ያመጡታል ማግስቱን ከነጓዙ ርቆ ለመራመድ ዋስትናው እግሮቹ ናቸው።
በቃሉና አዲስ አበባ ትውውቃቸው ከሁለት ወር አይዘልም እሱ ግን ከበርካቶች ጋር የዓመታት እውቂያ ያለው ይመስላል ያገኘውን ሁሉ በአክብሮት ‹‹ጋሼ፣ እትዬ›› ማለቱ ለገበያው በር ከፍቷል ቋሚ የሚባል ደንበኛ የለውም ቀን በቀናው ጊዜ ግን የእጁን ጨርሶ ሌላ ለማምጣት መጣደፉ አይቀሬ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ እንዳሰበው አይሆንም አንድም ዕቃ ሳይሸጥ ውሎው በመንገድ ድካም ያልፋል እግረኛውን ነጋዴ የጠየቀው ሁሉ አይገዛውም አንዳንዱ ዋጋ ሲከራከር፣ ሲያደርቀው ቆይቶ ትቶ ይሄዳል እሱ ግን ሁሉንም እንዳመጣጡ መመለስን ለምዷል ለጠየቁት አግባብቶ መሸጥን፣ ላልተመቻቸው በምስጋና መሸኘትን አውቆበታል።
የአጎቱን ልጅ ጨምሮ ሌሎች የሀገሩ ልጆች የአዲስ አበባ ሕይወታቸው ሽቶ አዙሮ በመሸጥ የተመሠረተ ነው የእሱ እንጀራ አሁን ያለበት ሥራ ሆኖ ዋጋ ይከፍልበታል አንዳንዴ በመንገዱ ሊያጋጥም የሚችል ክፉ ጉዳይ እንደሚኖር አይጠፋውም
ዕቃ መያዙን፣ ገንዘብ መቁጠሩን ያዩ ቀማኞች ሊዘርፉት፣ ሊያስደነግጡት ይችላሉ ይህ ስጋት ግን በፍራቻ ከቤት አውሎት አያውቅም መንገዱን ለፈጣሪው አስረክቦ ቀኑን በሥራ ይዋትታል በዚህ መሐል ‹‹ውል..›› የሚለው የነገ ሕይወቱ ለውስጡ ተስፋ ሲያቀብለው መንፈሱ ይበረታል፣ ኃይሉ ይጨምራል።
የወላጆች ነገር …
የበቃሉ ወላጆች የልጃቸው ከቤት መጥፋት አስደንግጧቸው ከርሟል ቆይተው ያለበትን ባወቁ ጊዜም ካገሩ እንዲመለስ ፣ ከቤቱ እንዲገባ በእጅጉ ለምነውታል እሱ ግን ከዓላማው መናጠብን አልፈለገም ስለነገ ዛሬን መድከም ትልሙ ሆኗል አልመጣም፣ አትጠብቁኝ ‹‹እምቢኝ›› ብሏል።
የበቃሉ የሁልጊዜ ሀሳብ ሠርቶ መለወጥ ነው ውስጠቱ ግን በየቀኑ አንድ ጉዳይ ሹክ ይለዋል በእጅጉ ከፍ ያለ ሀብት ቢያገኝ ፈጣሪውን እንዳይረሳ እየሰጋ ነው ይህ እውነትም ‹‹በልኩ ካለኝ ይበቃኛል›› ከሚል አቋም አድርሶታል።
እንዲያም ሆኖ ካስቀመጠው ልኬታ ላለማለፍ አይቦዝንም ጊዜና ሰዓቱን አስታርቆ፣ የመንገድ ርቀቱን ገምቶ ለመጓዝ የፈጠነ ነው እሱ ሁሌም በዋዛ ፈዛዛ ቆሞ የማውራት ልምድ የለውም መንገዱን ከመንገደኞች ለማዋደድ ጀንበሯን አንጋጦ እያየ ይጣደፋል እረፍት አልባ እግሮቹ ለአፍታ መቆምን አይሹም እንደልማዳቸው ፈጥነው ለመራመድ ይገፉታል
በቃሉ የአዲስ አበባ ቆይታው ረጅም አይደለም እንደ እንግድነቱ ግን ሁኔታዎችን ሲያማርር አይሰማም ከዚህ ስሜት ይልቅ በነዋሪው ባሕሪ፣ በሥራው ዕድልና በከተማው ድምቀት፣ ስፋት ይገረማል እንዲህ መሆኑ ሕይወቱን በምስጋና፣ ኑሮውን በደስታ እንዲመራ አስችሎታል።
የገጠሩ ወጣት የከተማ ኑሮ ቀላል እንዳልሆነ ገብቶታል ሲዞር ውሎ ከሚሸጠው ገቢ ላይ ለምግቡ፣ ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች ያስባል በእሱ ዘንድ ነገ ሌላ ቀን ነውና ፈጽሞ አይሰለችም አሁን ባለበት ዕድሜ ተሯሩጦ ነገን የተሻለ ለማድረግ ዕንቅልፍ የለውም።
እሱና እግሮቹ …
የበቃሉ እግሮች መራመጃ ብቻ አይደሉም እሱን ይዘው ፣ ጓዙን ተሸክመው የዕለት ጉርሱን ይሠጡታል እግሮቹ የየዕለት መሰላል ናቸው ነገን በተስፋ፣ ዛሬን በብርታት ያሻግሩታል እግሮቹ የሕይወቱ ፣ የመኖሩ ዋስትና ናቸው ከምኞቱ፣ ከሀሳቡ ያደርሱታል ትኩሱን እንጀራ ያጎርሱታል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2015