የፋሽን ዘርፍ አመለካከት በለውጥ ጎዳና

 በአብዛኛው ሰው ዘንድ ስለ ፋሽን ያለው ግንዛቤ፣ አረዳድና አመለካከት የተለያየ ነው:: በተለይ ቀደም ካለው ከሀገራችን ባህልና ልማድ አንጻር ስለፋሽን የነበረው ግንዛቤና አመለካከት ፋሽንን ለቅንጦት ከሚለበሱ አልባሳትና ጫማዎች ጋር ብቻ የሚያያዝ ችግር ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አመለካከት እየተቀየረ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::

ፋሽንን እንደ አንድ የትምህርት ክፍል የሚያስተምሩ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተቋማት መፈጠራቸው እንዲሁም በግሉ ዘርፍ በርካታ ተቋማት ትምህርቱን መስጠታቸው ለአመለካከቱ መለወጥ አንድ ምክንያት ተደርጎ እየተወሰደ ነው:: በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎች ተምረው በሙያው እየተሰማሩ ያሉበት ሁኔታም እንዲሁ ለአመለካከቱ መቀየር ምክንያት ሆኖ ይቀርባል::

አሁን ላይ ስለፋሽን ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል? የፋሽን ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ሌሎችንስ ተጠቃሚ ለማድረግ ምን መሥራት አለበት? ስንል የጠየቅናቸው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና የፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የፋሽን መምህር እስጢፋኖስ ምንቸግሮት እንደሚሉት፤ እንደኛ ሀገር ኅብረተሰቡ ስለ ፋሽን ያለው ግንዛቤና አመላለከት ዝቅ ያለ ነው:: የእጅ ሥራ የሚሠራ ወይም ልብስ ዲዛይን የሚያደርግን በአጠቃላይ ፋሽን የምንላቸውን ነገሮች የሚሠሩትን ማንም ሰው በፋሽን ሙያ ውስጥ ያሉ ናቸው ብሎ የመመልከት ጉዳይ የለም:: ይህ አመለካከት የፋሽን ዘርፉ እንዳያድግ ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ኖሯል:: ይህንን አመለካከት ለመቀየር በርካታ ዓመታት መውሰዱንም ይገልጻሉ:: አሁን ግን የፋሽን ኢንዱስትሪ ገና ጅምር ላይ ቢሆንም፣ የአመለካከት ለውጦች እየመጡ ነው ይላሉ::

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እንደኛ ሀገር ሙያው ትኩረት ተሰጥቶት በትምህርት ደረጃ መሰጠት የተጀመረው እና ባለሙያውም እንደ ባለሙያ መጠራት የጀመረው

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው:: አሁን ሙያው ትኩረት እያገኘ በመምጣቱ በእርግጠኝነት ከሕፃናት ጀምሮ እስከ አዋቂ ድረስ ያሉ በርካታ ሰዎች ዲዛይነር የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ እየተሰማ ነው::

ሕፃናት ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? ሲባሉ በፋሽን ዘርፉ ካሉ ሙያዎች አንዱን በመጥራት የፋሽን ባለሙያ ለመሆን እንደሚፈልጉ እየገለጹ መሆናቸውን መምህሩ ይጠቅሳሉ:: በዘርፉ ይህን መሆን እፈልጋለሁ እስከማለት የሚደርስ ራዕይ መሰነቃቸውን ሲገልጹ እንደሚሰሙ ይናገራሉ:: በሙያው ተመስጠው ራዕይ የሚሰንቁ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ከሌላ ሙያ ወደዚህ ሙያ የሚገቡ በርካታ ሰዎች እንዳሉም ነው መምህር እስጢፋኖስ የጠቆሙት::

«ለፋሽን የሚሰጠው አመለካከት ከተቀየረ፤ ብዙ ባለሙያዎች በዘርፉ ላይ ሲኖሩ ማምረት የሚፈለገውን ያህል ማምረት እንችላለን:: እኛ እንደ ሀገር በጣም ብዙ ሕዝብ ነን፤ ብዙ ሕዝብ ደግሞ ብዙ ልብስ ይፈልጋል፤ ያንን ማሟላት መቻል በራሱ አንድ ትልቁ ነገር ነው›› ያሉት መምህር እስጢፋኖስ፣ ‹‹እንደ ሀገር የበርካታ ባህሎች (ቱባ ባህል) ባለቤቶችን ነን:: እነዚያን ባህሎች መጠበቅ ማሳደግ ስለሚገባ ባህላዊ አልበሳትን እንደአካባቢው ሁኔታ ለሰው በሚመች መልኩ ማቅረብ ያስፈልጋል›› ሲሉም ይገለጻሉ:: ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ለመሥራት ለሙያው የሚሰጠው ትኩረትና የባለሙያ መኖር በራሱ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ::

የፋሽን ኢንዱስትሪ እያሳየ ያለውን ለውጥ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉና የዘርፉን ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ እየተከናወነ ካለው ተግባር አኳያም መመልከት ይቻላል ሲሉም ይገልጻሉ:: በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ታዋቂ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች እንደተሰማሩበት ጠቅሰው፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑት እንደ ሜቼንዴም እና ሌሎቹም ብራንዶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ምርቶቻቸውን እያመረቱ ቀጥታ ለውጭ ገበያ እንደሚልኩም ይናገራሉ:: እነዚህን ብራንድ ዓለምአቀፍ ተቋማት መሳብ መቻሉ በራሱ እንደ ሀገር የደረስንበት ደረጃ የሚያሳይ ነው ሲሉም ያብራራሉ:: ‹‹ተቋማቱ በዚህ ደረጃ ሀገራችንን አምነው መጥተው በእኛ ሀገር የተመረተውን ምርት በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ስያሜ ያለው ምርት ይዘው በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያ ላይ መሸጥ መቻላቸው በራሱ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትልቅ ስኬት ነው›› ይላሉ::

‹‹ሌላው ዘርፉን ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ተሰጥኦና ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ የኢትዮጵያ ዲዛይነር መባል የሚችሉ በዚያ ደረጃ ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ» የሚሉት መምህሩ፤ በዘርፉ የፈጠራ ችሎታ ላላቸው ሰዎች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ:: እነዚህን ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች የማፍራቱን ሥራ በአንድ ላይ አቻችሎ ማስኬድ እንደሚጠቅምም ይገልጻሉ::

መምህሩ እንዳሉት፤ አሁን በዘርፉ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ወደ ኢንዱስትሪው እየመጡ በመሆኑ እንደ ሀገር ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ይታያል:: አውሮፓና

 አሜሪካ እየሄዱ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ የሀገራችን ዲዛይነሮች አሉ፤ ይህ ትልቅ ጅማሮ ነው::

‹‹ጨርቃችን፣ ሽመናችን እና ባህላችንን በዘርፉ ያሉንን በሙሉ በማስተዋወቅ ከእኛ ሀገር ሲተርፍ ደግሞ መልሰን ኤክስፖርት የምናደርግበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን ሲሉም ይገልጻሉ:: ይህ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ ቢመስለንም ጠንክረን ከሠራን በቅርቡ ብዙ ነገሮችን መቀየር ይቻላል ›› ይላሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ ልክ የምዕራባውያን አለባበስ በእኛ ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ሁሉ የእኛ ሀገር አለባበስ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች ሀገራት ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል:: እነሱ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው ዲዛይነሮቹ የሚፈጥሩበት የዲዛይን መንገድ ነው:: እኛም የላቀ ዲዛይን በመፍጠር ተፅእኖ ፈጣሪ መሆን የምንችልበትን መንገድ ማሳየት አለብን::

በአጠቃላይ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ቱሩፋት ስንመለከት፤ የሥራ ዕድል የመፍጠር፣ ኢኮኖሚውን በማነቃቃትና ገቢ በማመንጨት ደግሞ ስንመዝነው ከአምስት ሰዎች አንድ ሰው በዚህ ኢንዱስትሪ ተሰማርቶ ይገኛል ሲሉ አመልክተው፣ ዘርፉ ከየትኛውም ዘርፍ በበለጠ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር በቀላሉ በትንሽ ኢንቨስትመንት በጣም ብዙ የሰው ኃይል ቀጥሮ ማንቀሳቀስ የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል:: በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች ጠቅም ያለ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችልም ጠቁመዋል::

‹‹የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ማህበረሰቡ በዘርፉ ላይ ያለውን አመለካከት መቀየር ይኖርበታል:: በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ማገዝና መድገፍ አለበት›› ሲሉም ያስገነዝባሉ:: ማህበረሰቡ የሀገር ውስጥ የፋሽን ምርቶችን ማድነቅ፤ መግዛትና ማበረታታት እንዳለበትም አመልክተዋል:: ተስፋ ቆርጠው ከገበያው የሚወጡ ሰዎች እንዳሉም ታሳቢ በማድረግ የባለሙያዎቹን ምርቶች በመግዛት ፣ ሀሳብ በመስጠት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ማገዝ ይጠበቅበታል ሲሉም ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል::

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *