አቶ ፍቃዱ ሽፈራው እና ወይዘሮ ሐረገወይን አሰፋ ቀሪ ዘመናቸውን በፍቅር ሊኖሩ ታላቁን የጋብቻ ተቋም በ2004 ዓ.ም መሰረቱ። ጋብቻው ለሕይወት ዘመን በሙሉ በፍቅር ለመኖር መወሰን ነው፤ (ሮሜ 7:1-3፤ 1ኛ ቆሮ. 7:27፣39) ይላል፡፡ ነገር ግን አቶ ፍቃዱ እና ወይዘሮ ሐረገወይን ለዚህ የታደሉ አልነበሩም። ምንም እንኳ የዘሩት ዘር ፍሬ አፍርቶ ሁለት ልጆችን ባሩክ ፍቃዱን እና ሀሴት ፍቃዱን ወልደው ለመሳም፤ አይናቸውንም በአይናቸው ለማየት ቢታደሉም ፍቅር ርቋቸው ነበር።
ቤታቸው በልጆች ጨዋታ ደምቆ ሃብትና ንብረትም አፍርተው እንዲህ እንደዋዛ 11 ዓመታትን ሲያሳልፉ፤ በመካከላቸው ከደስታ ይልቅ ሃዘን ተነጋግሮ ከመግባባት ይልቅ ጭቅጭቅ መለያቸው ሆኖ ከራርሟል። ይህን ያህል ዓመት በአንድ ጣሪያ ሥር ሲኖሩ ጠባቸው እግር እና እግር እንደሚጋጨው ሁሉ በጥንዶቹ መካከል ጠብና ጭቅጭቅ አልፎ አልፎ ይከሰት ተብሎ እንደሚታለፈው ዓይነት አልነበረም። ጭቅጭቃቸው ወደ አለመግባባት አምርቶ 80ያቸውን ለመቅደድ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የፍርድ ቤት በራፍ እረግጠዋል። ሽማግሌ “አንተም ተው፤ አንቺም ተይ” ብሎ እያስማማቸው ካንዴም ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት የከፈቱትን የፍቺ ፋይል ዘግተዋል። እነርሱ ለመለያየት ቢያስቡም እህል ውሃቸው ስላልተቆረጠ አለመግባባቱ ከዛሬ ነገ ይፈታል በሚል ተስፋ ሕይወትን አንድ ላይ ቀጠሉ።
ነገር ግን ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጥንዶቹ መካከል የነበረው ጭቅጭቅ ከወትሮው በተለየ ከረር ያለ ነበር። ጭቅጭቁ የተጠነሰሰው ከተጠቀሰው ሁለት ሶስት ቀናት በፊት ቀደም ብሎ ነበር። ይኸውም አባወራው “በእኔ ላይ ወስልተሻል፣ እምነት አጉድለሻል” በሚል ጭቅጭቅ ይጀምራል። እማወራዋም ነገሩ እስኪበርድ ብላ ልጆቿን ይዛ ወደ እናቷ ቤት (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ቀበና አካባቢ) ሄዳ ሁለት ቀን ትቆያለች። ነገሩ “በርዶለት ይሆናል” ብላ ከሁለት ቀን ቆይታ በኋላ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 01 ቀበሌ ልዩ ቦታው አርሴማ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ከምሽቱ 12:00 ስዓት አካባቢ ልጆቿን ይዛ ትደርሳለች።
የግቢውን በር ስታንኳኳ የሚከፍትላትም ሆነ የሚሰማት ሰው ታጣለች። ይህኔ ወደ ባለቤቷ ስልክ ደውላ “ቤቱን ክፈትልኝ” ትለዋለች። እርሱም የወንድሜ ልጅ ከደቡብ አፍሪካ መጥቶ ኤርፖርት ልቀበል እዛው ነኝ። ቀድመሽ ብትደውይልኝ ቤቱን ከፍቼልሽ እሄድ ነበር። አሁን ስለመሸ መምጣት አልችልም፤ ወደ ቤተሰቦችሽ ቤት በታክሲ ወይም በኪሎ ሜትር ታክሲ ተመልሰሽ ሂጅ ይላታል። ጥንዶቹ በሃሳብ ሳይስማሙ በመሃል ስልኩን ይዘጋባታል።
ወይዘሮ ሐረገወይንም “ቤቴ ከደረስኩ በኋላ በጨለማ ልጆቼ አይንከራተቱም፤ ተመልሼ ወደ ቤተሰቦቼ ቤት አልሄድም” ትልና በአጥር ዘላ ከውስጥ የግቢውን በር ከፍታ ልጆቿን ይዛ ወደ ቤቷ ትገባለች። አባወራው አቶ ፍቃዱ የወንድሙን ልጅ ከኤርፖርት ተቀብሎ እናቱ ቤት አስኮ አሳይ ትምህርት ቤት አካባቢ አድርሶ ወደ ቤቱ እኩለሌሊት ላይ ይደርሳል። ወደ ቤቱ ሲገባ ባለቤቱና ልጆቹ እልም ያለ እንቅልፍ ላይ ነበሩ። እርሱም ባለቤቱን እንዴት ብላ ወደ ቤት እንደገባች ይጠይቃታል። እርሷም እንዴት እንደገባች ታስረዳዋለች። እርሱም ‹‹ ለምን በር ትሰብሪያለሽ? ለአንድ ቀን ለምን እዛው ቤተሰቦችሽ ጋር አታድሪም?›› ይላታል። እሷም በምላሹ ‹‹በሩ አልተሰበረም›› ትላለች። እንዲህ እሱ አንድ ሲናገር እሷ ስትመልስ እንዳይነጋ የለም ለሊቱን በጭቅጭቅ ነጋ።
ለሊቱን ሳትተኛ በነገር ስትጠበስ ብታድርም፤ ልጆቿን ቁርሳቸውን አብልታ ወደ ትምህርት ቤት መላክ ነበረባት። ስለዚህ ከላይ በተጠቀሰው ቀን እንደምንም ከእንቅልፏ ማልዳ ተነስታ ምድር ቤት በሚገኘው የምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ለልጆቿ ምግብ እያበሰለች ነበር። አባወራውም 1:00 ሰዓት ገደማ ከእንቅልፉ ተነስቶ ፊቱን ከታጠበ በኋላ ቀጥታ ወደ ምግብ ማብሰያ ክፍል ያመራል። በዚያም ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ምግብ እያዘጋጀች ያገኛታል። እሱም ወንዱ ልጃቸው በዕለቱ ታሞ መድሃኒት እየወሰደ ስለሆነ ትምህርት ቤት ስለማይሄድ፤ ሴቷ ልጃቸውም ከትምህርት ትቅር ይላታል። እሷም “በልጆቼ ጉዳይ አያገባህም” ስትለው፤ እርሱም ” በልጆቼ ላይ የምትወስኚው አንቺ ብቻነሽ? ” በሚል አንዱ ሲናገር ሌላኛው መልስ ሲሰጥ ንጋት ላይ ጋብ ያለው ጭቅጭቅ እንደገና ጧት ላይ በዚህ መልኩ ተጀመረ።
ጭቅጭቁ ሲጋጋል ልጆች ከመኝታቸው ባነው በወጉ እንኳን ልብስ ሳይለብሱ አባትና እናታቸው ወደ ሚጨቃጨቁበት ማብሰያ ክፍል አምርተው በፊታቸው ተኮለኮሎ። ጥንዶቹ ልጆቻቸው ፊት ለፊታቸው ቆመው እያዩ እንኳን ጭቅጭቃቸውን አላባሩም ነበር።
በመሀል አባወራው ብልጭ ብሎበት ባለቤቱ ላይ በአምስት ጣቱ ጸጉሯ ላይ ሲሰፍርባት ሚስትም ልጆችም ተደናግጠው አንድላይ ሲጮኹ አሽቀንጥሮ ገፍትሮ ይለቃታል።
‹‹በልጆቻችን ፊት እየተጨቃጨቅን ለምን እናሳቅቃቸዋለን? ልጆቹ ወደ ውጭ ወጥተው እንዲጫወቱ አድርገን ለምን ብቻችንን አናወራም? የሚል ሀሳብ አባወራው ያቀርባል። ›› ሚስትም በሀሳቡ ተስማምታ ልጆቹ ከቤት ወጥተው ግቢ ውስጥ እንዲጫወቱ ታደርጋለች። ባልና ሚስትም በራቸውን ጥርቅም አድርገው ዘግተው አንደኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው ሳሎን ቤት ለመነጋገር ቦታ ይዘው ተቀመጡ።
ባልም ለምን ሌላ ነገር ከመፈጠሩ በፊት አንለያይም ይላታል። ይሁን እንጂ ሚስት የእጅ ስልኳን እየነካካች መልስ ሳትሰጠው ዝም ትላለች። መልስ ስላልሰጠችው ተበሳጭቶ ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ የያዘችውን የእጅ ስልኳን በኃይል ሲጨብጠው የእጅ ስልኳ ተሰነጣጠቀ። እሷም “ስልኬን የምትሰብረው አንተ ስለገዛኸልኝ ነው?” ብላ መልስ ስትሰጠው፤ እሱ ግን ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጣት በቀጥታ ወደ ፍቺ ጉዳይ አመራ። ወይ በአንቺ ወይ በኔ ፋይል ይከፈትና ፍቺ እንፈጽም ይላታል። እሷም በአንተ ፋይል ይከፈት ትለዋለች። እሱም በአንቺ ይከፈት እየተባባሉ ጭቅጭቁ ጦዘ።
ጭቅጭቁ ወደ መዘላለፍ አምርቶ ‹‹አንተ ወንድ ነህ እንዴ? ብትፈታኝ ባትፈታኝ›› ብላ ሚስት ትናገራለች። እሱም በአጸፋው “አንቺ እንትን … ” ብሎ ይሰድባታል። ይህኔ ከተቀመጠችበት ብድግ ብላ ቢላዋ አንስታ ወደሱ ስትጠጋ አባወራው ደግሞ ወደ ማብሰያ ክፍል ዘሎ ገብቶ የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ ከተቀመጠበት አንስቶ እሱን ለማጥቃት ስትጠጋ ወደ ኋላ አንድ እርምጃ አፈግፍጎ በያዘው መጥረቢያ አንድ ግዜ የቀኝ እጇን ሲመታት ተዝለፍልፋ ትወድቃለች።
እራሷን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ የልጆ እናት ወድቃ እያያት በሕይወት እንድትቀጥል አልፈቀደላትም። “አንቺ እንትን … ” እያለ በያዘው መጥረቢያ መላ አካሏን ቆራርጦ ከላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ ሕይወቷ እንዲያልፍ አደረገ፡፡ ወንጀሉ ሲፈጸም በጥንዶቹ መካከል ማንም ሰው ስላልነበረ፤ በወቅቱ የነበረው ጭቅጭቅና ምልልስ ጭምር ምን ይመስል እንደነበር ከላይ በተገለጸው መሰረት ተጠርጣሪ ፍቃዱ ሽፈራው ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክደት ቃል ተገልጿል።
ጥንዶቹ በፍቅር እድሜ ዘመናቸውን አንድ ላይ ሊኖሩ የገቡበት ትዳር በጭቅጭቅና ቅናት ተበርዞ በአሳዛኝና ከኢትዮጵያዊነት ባህል ባፈነገጠ መልኩ ተቋጨ። በደስታ ሊኖሩበት የሠሩትን ቤት አንድ ዓመት ሞልተው ኖረው ሳያጌጡበት፣ ሳይኩሉበት፣ ሳይድሩበት በደም ጎርፍ ጨቀየ። ባል ወደ ዘላለማዊ እስር ቤት፤ ሚስት ደግሞ ወዳማይቀረው ዓለም በአሰቃቂ ሁኔታ እስከወዲያኛው ተሸኘች። በመሀል ልጆች ያለ እናትና አባታቸው አውላላ ሜዳ ላይ ወደቁ። የቀን ጨለማ ዋጣቸው። በእናትና በአባታቸው እንክብካቤ በቅንጦት ያደጉ ልጆች ዛሬ የወላጆቻቸው እንክብካቤና ፍቅር እርቋቸው ሕይወት ፊቷን አዙራባቸዋለች።
የሟች እህት የምስክርነት ቃል
የባንክ ሠራተኛ የሆነችው የሟች ሐረገወይን እህት ወይዘሮ ወሠን አሰፋ ለፖሊስ በሰጠችው የምስክርነት ቃል ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተጋብተው በትዳር መኖር መጀመራቸውንና ሁለት ልጆች መውለዳቸውን ገልጻለች፡፡ እንደምስክሯ ገለፃ፤ የእህቷ ባለቤት አቶ ፍቃዱ ከ2004 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር (ካናዳ) እየሄደ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት የሚመለስበት ሁኔታ ነበር። እንዲህ ውጭ ሀገር እየተመላለሰ በትዳር አብረው ሲኖሩ፤ ከ2013 ዓ.ም ከፋሲካ በዓል በኋላ ወደ ውጭ ሀገር መሄዱን አቁሟል።
ከ2013 ዓ.ም ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ አቶ ፍቃዱ ይኖር የነበረው እናቱ ቤት እንደሆነ ትናገራለች። ሆኖም በ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት ባልና ሚስቱ አሁን ወንጀሉ የተፈጸመበት መኖሪያ ቤታቸው ገንብተው መኖር ጀመሩ። ይሁን እንጂ ቤቱ በባልና ሚስቱ ስም ስላልሆነ ‹‹ቤቱ በእኛ ስም ይሁን›› በሚል ብዙ ጊዜ ይጨቃጨቃሉ። መደባደብ ደረጃ ባይደርሱም እየተጣላች ከነልጆቿ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ትመጣለች። ከዚህ ባሻገር የቤት አስቤዛ አቶ ፍቃዱ እራሱ ገዝቶ ስለሚያመጣ ገንዘብ ለአስቤዛ መግዣ ስለማይሰጣት ገንዘብ ስጠኝ በሚልም ይጨቃጨቃሉ።
ሆኖም ሟች እህቷ ቀደም ሲል ከሌላ ወንድ ጋር እንደምትወሰልት ወይም ባለቤቷ አቶ ፍቃዱ ከሌላ ወንድ ጋር እንደሚጠረጥራት ከእህቷ ጋር ሚስጥር በሚያወሩበትና እንደቤተሰብ በሚወያዩበት ወቅት የነገረቻት ነገር እንደሌለ ተናግራለች። ነገር ግን ገንዘብ እንደማይሰጣት እና ልጆቿን ቤተሰብ ጋር ይዛ ሂዳ ቤተሰብ ገንዘብ እንደሚሰጣት እንዲሁም አንዳንዴ እሷ እራሱ ገንዘብ እንደምትረዳት ወይዘሮ ወሠን ተናግራለች።
የዓቃቤ ሕግ ምርመራው
በጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 3 ሰዓት ከ 30 በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ አርሴማ አደባባይ አካባቢ ወንጀል ተፈፅሟል፡፡ በዚሁ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤት ውስጥ ተጠርጣሪው የትዳር አጋሩ የሆነችውን ሟች ሐረገወይን አሰፋ የተባለችውን “ከሌላ ወንድ ጋር ትወሰልችብኛለሽ” በሚል ምክንያት ያለመግባባት እንዲፈጠር በማድረግ ምግብ ማብሰያ ቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረን የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ በማንሳት አንገቷን፣ ትክሻዋን፣ የግራ አይኗን፣ ክንዶቿን እና ጭንቅላቷን በመምታት በቀኝ በኩል የአንገቷን 1/3ኛ ክፍል እና ከእርሱ ዝቅ ብሎ በስለት ጉዳት እንዲደርስባት አድርጓል።
እንዲሁም የቀኝ ትከሻዋ፣ በግራ ደረቷ የላይኛው 1/3ኛ ክፍል፣ የግራ ክንድ የታችኛው 1/3ኛው ክፍል፣ በግራ አይኗ ላይ እስከ አጥንት የዘለቀ የቆዳ መጋጋጥ እንዲደርስ ከማድረጉ ባሻገር በአንጎሏ ውስጥ ደም እንዲፈስ በማድረግ ሟች በአንገቷና በጭንቅላቷ ላይ በደረሰባት ጉዳት የተነሳ ተከሳሽ ፍቃዱ ሽፈራው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።
ይህ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 (1) (ሀ) ሥር በተደነገገው መሠረት ሰውን ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያ፣ ዘዴ እና ያገዳደሉ ሁኔታ ሲታይ ጨካኝነቱን እና አደገኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ የተፈፀመ በመሆኑ ተከሳሽ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ፈፅሟል ሲል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።
ዐቃቤ ሕግ 9 የሰው ማስረጃ፤ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍል በቁጥር ጳሀ8/1978 በቀን 26/03/2015 እና በቁጥር ጳሀ8/2234 በቀን 14/04/2015 ዓ.ም ስር የተሰጠ የሟች የሞቷ ምክንያት የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ ውጤት እና ማብራሪያ ከነትርጉሙ 12 ገጽ ቅጂ፤ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና መርማሪ በደብዳቤ ቁጥር ፌፎ/ባ-88/2070/15 በቀን 14/03/2015 ዓ.ም የተላከ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ የተገኘው መጥረቢያ ላይ ያለ ደም መሰል የሰው ደም መሆኑን የሚያሳይ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት 02 ገጽ ቅጂ፤ የሟችን የአማሟት ሁኔታና ጉዳት፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት መጥረቢያ፣ ተከሳሽ የድርጊቱን አፈጻጸም ሲመራ የሚያሳይ እንዲሁም የወንጀል ስፍራውን የሚያሳዩ አጠቃላይ 29 ገላጭ ቅጅ ፎቶ ግራፎችን እንዲሁም ተከሳሽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 27(2) መሰረት ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ ቃል ሲሰጥ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልን የያዘ 01 ሲዲ በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በፍጥነት እንዲታይ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቢ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።
ውሳኔ
ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሽ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እና ህዝባዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻር እንዲሁም ሟችን የገደለበት በኤግዝቢትነት የተያዘው መጥረቢያም በሚመለከተው አካል እንዲወገድ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም