ቂምና መዘዙ!

በሰው ልጅ የሕይወት ግንኙነት ውስጥ ለሰው ጥሩ የሚያስብ፣ ቸር፣ እሩህሩህ፣ … እንዳለ ሁሉ በተቃራኒው ሰው ሲወድቅ፣ ሲያዝን፣ ሲከፋ፣ … ማየት የሚያስደስተው ሰው አለ። ይህ ደግሞ የገሃዱ ዓለም እውነተኛ ነጸብራቅ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በድሎኛል ወይም ክፉ ነገር ፈጽሞብኛል ብለን ብዙዎቻችን ቂም እንይዛለን። ነገር ግን ቂምን ከውስጥ አውጥቶ እርግፍ አድርጎ ካልጣሉት የሰውን ልጅ ውስጥ ውስጡን እየቦረቦረ የሚበላ ነቀዝ ነው። “ይቅር ለእግዚአብሔር” ብሎ ከልብ አውጥቶ ካልጣሉት ቂም በቀልን ይወልዳል። ብዙ ሰዎች በቂም በቀል ተገፋፍተው ሰው ላይ ወንጀል በመፈጸም ከዓላማቸው ተሰናክለው ዘብጥያ ወርደዋል። ቤታቸው ተበትኗል። ልጆቻቸው ጎዳና ወድቀዋል። የሰውንም ሕይወት አመሰቃቅለዋል።

የ32 ዓመቱ ወጣት ፍቃዱ ፈለቀ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሜክሲኮ አካባቢ ነው። ወጣቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመዲናዋ ተከታትሏል። እህቱ ወደ ጋምቤላ ከተማ ወስዳው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዚያው ቀጥሏል። በጋምቤላ ከተማ መምህራንና ጤና ሳይንስ ኮሌጅም የኮሌጅ ትምህርቱን ተከታትሎ ጨርሷል። ለሁለት ዓመት ያህል በዚያው በመምህርነት ካገለገለ በኋላ ለተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ ትውልድ አገሩ አዲስ አበባ ይመለሳል። በመዲናዋም እንዳሰበው የተሻለ ሥራ እድል ግን አልገጠመውም። ይሁን እንጂ እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ የቤተሰብ ሸክም መሆን ስላልፈለገ ተደራጅቶ የመኪና ጥበቃ ሥራ እየሠራ ሕይወቱን ይመራ ጀመር።

ነገር ግን ማስረሻ አባይነህ ከተባለ የሰፈሩ ልጅ ላይ ቂም ቋጥሮ መቼ እንደሚበቀለው በውስጡ ሲያብሰለስል ቆይቷል። ቂሙን በሆዱ ይዞ እንዴት እንደሚበቀለው ሁሌ ሲያሰላስል የኖረው ወጣት ፍቃዱ፤ በ26/06/2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 6፡ 00 ገደማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ሜክሲኮ ከኬኬር ህንፃ ጀርባ ካለው የፖሊስ ኮሚኒቲ ጣቢያ አጠገብ አቶ ማስረሻን ያገኘዋል። በዚህ በውድቅት ሌሊት ቂም የቋጠረበትን ግለሰብ ሲያገኘው ቂሙን ለመወጣት የሚያግደው አንዳች ነገር እንደሌለ ተማመነ። ከዛም አቶ ማስረሻን “ከአንተ ጋር ቂም አለኝ፤ አንተ ጸብ ታውቃለህ እንዴ? ፈሪ ነህ” በማለት በእርግጫ አንድ ጊዜ ሆዱ ላይ ይመታዋል። ቀጥሎም ምንነቱ ባልታወቀ ስለታማ ነገር አንድ ጊዜ ሰንዝሮ ሆዱ ላይ ይወጋዋል። ይሄኔ ሟች ጩኸት ሲያሰማ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ እሩጦ ያመልጣል። ሟችም ሆዱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ደም ፈሶት ሕይወቱ ያልፋል። ፖሊስም ወንጀሉ በተፈጸመበት ቅጽበት ወደ ተጠርጣሪ ቤት አቅንቶ ከተደበቀበት አውጥቶ በቁጥጥር ስር አውሎ የእምነት ክህደት ቃሉን እንደሚከተለው ተቀብሏል።

የተጠርጣሪ የእምነት ክህደት ቃል

ከላይ በተጠቀሰው ቦታና ጊዜ ተጠርጣሪ ፍቃዱ ፈለቀ ካልተያዙ አባሪዎቹ ጋር በመሆንና በመመሳጠር ሟችን በስለታማ ነገር መሃል ሆዱን ከእንብርቱ በላይ አንድ ቦታ ላይ በመውጋት ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል በሚል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎታል። ፖሊስም ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ ላቀረበት ተራ የሰው መግደል ወንጀል ክስ የሚከተለውን የእምነት ክህደት ቃል ሰጥቷል።

ተጠርጣሪ የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈጸመና ጥፋተኛ እንዳልሆነ ጠቅሶ፤ ከሟች ማስረሻ አባይነህ ጋር ቀደም ሲል ሰፈር ላይ እንደሚተዋወቁ ይናገራል። እርሱም ከላይ በተጠቀሰው ዕለትና ሰዓት ወደ ቤቱ እያመራ እያለ ሟችን ብቻውን ከላይ ከተጠቀሰው ቦታ ቁሞ እንዳገኘው ያስረዳል። ሟች “አንተ አቃጣሪ” ብሎ ሲሰድበኝ “አንተ ወንድ ከሆንህ ለምን አትመታኝም? ለምን ትሳደባለህ? ስለው “አንተ

 አቅም የለህም፤ አሁን ብመታህ ለመክሰስ ነው” ብሎ ተናገረኝ ይላል። ከዚያም ሆዱ ላይ አንድ ጊዜ በእግሩ በእርግጫ እንደመታው ገልጾ፤ ሟች በአጸፋው መልሶ ሊመታው ሲል ሰዎች ቦታው ላይ ስለነበሩ ወደ ቤቱ እየሮጠ እንደሄደ ይናገራል። እግር በእግር ፖሊሶች ተከታትለው ቤቱ እንደገባ ቂጡ ቁጭ ሳይል ይይዙታል። ፖሊሶቹም ወደ ፖሊስ ሴንተሩ ይዘውት ይሄዳሉ። በፖሊስ ሴንተሩ አጠገብም ሟች ሆዱ ላይ ተወግቶ፣ አንጀቱ ወጥቶ ደም እየፈሰሰው ማየቱን ይናገራል። ተጠግቶም ሕይወቱ ማለፉን ተመልክቷል። ሟች ከመሞቱ በፊት ከእርሱ ጋር ሲጨቃጨቁ በነበረበት ወቅት ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት ተናግሯል።

እርሱም “ጥፋቴ ነው” ብሎ ያመነው ከሟች ጋር ሲጨቃጨቁ በነበረበት ወቅት አንድ ጊዜ ሆዱ ላይ በእግሩ በእርግጫ በመማታቱ ጥፋተኛ እንደሆነ፤ ነገር ግን ሟችን በስለታማ ነገር ወግቶ እንዳልገደለው የእምነት ክህደት ቃሉን ለፖሊስ ሰጥቷል።

ምስክሮች ምን አሉ?

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 06፣ የቤት ቁጥር 264 ነዋሪ የሆነው የ45 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ዑስማን ሳልሕ አንዱ የዓይን ምስክር ነው። እርሱም ከላይ በተጠቀሰው ቦታና ጊዜ ወንጀሉ እንደተፈጸመ ገልጾ፤ ወንጀሉ በወቅቱ እንዴት እንደተፈጸመ እደሚከተለው ለፖሊስ አስረድቷል።

ሜሮን ባምላኩ ከተባለች ግለሰብ ጋር ኬኬር ህንፃ ፊት ለፊት ከሚገኘው በእምነት ባርና ሬስቶራንት ውስጥ አንድ ሁለት ፉት ሲሉ አምሽተው ይወጣሉ። ወንጀሉ የተፈጸመበት አካባቢ ሲደርሱ ሟች ማስረሻ የሰፈራቸው ልጅ፣ ዜናዊ እና ፋና (የአባታቸውን ስም የማያውቃቸው) በጋራ ሆነው ቆመው እያወሩ ያገኟቸዋል። እርሱና ሜሮንም ተቀላቅለዋቸው አብረው ያወሩ ጀመር።

የምሽቱን ነፋሻማ አየር እየማጉ ሰብሰብ ብለው እያወሩ እያለ፤ ተጠርጣሪ ፍቃዱ ፈለቀ የተባለው የሰፈራቸው ልጅ ከጀርመን መስጊድ አቅጣጫ ወደ እነርሱ ወዳሉበት ተጠጋ። በወቅቱ ባለዚፕ ሹራብ፣ ኮፍያ ያለው ጃኬት አድርጎ ነበር። የለበሰው ሹራብ እረጅም ስለነበር እጁን ከመሸፈን አልፎ ተንዘላዝሏል።

ከዛም ተከሳሽ የራሱን የሹራብ ጃኬት ዚፑን ሲከፍተው፤ ከውስጥ ደግሞ ጠቆር ያለ ጅንስ ጃኬት አድርጓል። ከግራና ከቀኝ ኪሱ አረቄ የያዙ ትናንሽ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችን አወጣና ወደ

 መሬት ጣላቸው። “ከአንተ ጋር ቂም አለኝ፣ አንተ ጸብ ታውቃለህ እንዴ? ከፈለክ አፈራርጥሃለሁ” ብሎ ሟችን ዛተበት። ሟች በምላሹ “እሺ ተወኝ በቃ እያለው” እያለ ተከሳሽ ወደ ሟች የቀኝ እግሩን አንስቶ ሆዱ ላይ በእርግጫ በመሰንዘር አንድ ጊዜ እረገጠው። ሟችም ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ ገዳይ ደግሞ ሲከተል ልክ ሜክሲኮ ኮሚኒቲ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ሲደርስ፤ ተጠርጣሪ በቀኝ እጁ በሹራብ እጁ እንደተሸፈነ ወደ ሟች ፊት ለፊት ሆዱ ላይ በቀጥታ በመሰንዘር እንደመውጋት አደረገው። ሟችም ወዲያው “ኡ! ኡ!” ብሎ ጮኸ እና ሆዱን በአንድ እጁ ይዞ በጎኑ በኩል ወደ መሬት ወደቀ። ተከሳሽም እሩጦ ከቦታው ተሰወረ።

ይህ ድርጊት ሲፈጸም አቶ ዑስማንና በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ተደነጋገጠው በየአቅጣጫው ይበተናሉ። ወንጀሉ እንደተፈጸመ ቀጥታ ወደ ቤቱ ገብቶ ከግማሽ ሰዓት የማይበልጥ ደቂቃ እንደተቀመጠ የግቢውን በር ፖሊሶች አንኳኩ። ፖሊስም አቶ ዑስማንን ወንጀሉ ወደተፈጸመበት ቦታ ይዘውት ሂደው ወንጀሉን ማን እንደፈጸመው ይጠይቁታል። እሱም ሟች ከተጠርጣሪ ፍቃዱ ፈለቀ ጋር እንደተጣለ ጥቆማ ይሰጣል።

ፖሊስም ወዲያው ወደ ተጠርጣሪ ቤት አቅንቶ ከተደበቀበት ማንቁርቱን ይዞ አውጥቶ የሟች አስከሬን ሳይነሳ አመጣው። ተጠርጣሪም ሟችን ተጠግቶ ሲመለከተው በጀርባው ተንጋሎ ተኝቶ የሆድ እቃው ወደ ውጭ ወጥቶ ደም ፈሶት ሕይወቱ ማለፉን አይቶ ምንም ሳይመስለው “ሞተ እንዴ” ብሎ በፊዝ ተናገረ። እንዲሁም ተከሳሽ በአካባቢው በተደጋጋሚ ሰዎችን በስለት ለመውጋት የሚዝት እና ይህን ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት አንድ ግለሰብን በድንጋይ ፈንክቶ ጉዳት አድርሶ በድርጊቱ ላይ የምስክርነት ቃል የሰጡ ግለሰቦችን ለመግደል ይዝት ነበር። በርካታ ጊዜ በፖሊስ ጣቢያ በወንጀል ተጠርጥሮ ታስሮ ያውቃል በሚል አቶ ዑስማን የምስክርነት ቃሉን ለፖሊስ ሰጥቷል። በተመሳሳይ ሜሮን ባምላኩ ከላይ አቶ ዑስማን የሰጠውን የምስክርነት ቃል እሷም ደግማ አንድም ልዩነት ሳይኖር ለፖሊስ የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች። እንዲሁም ሌሎች ምስክሮች ከላይ በተጠቀሰው ቦታና ጊዜ “ተጠርጣሪ ሟችን በስለት ሲወጋው ባያዩም እየተጨቃጨቁ እንደነበር ለፖሊስ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። እንዲሁም ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ ወደቤት ከገባ በኋላ የአክስቱ ልጅ የሆነችውን ተማሪ ዮርዳኖስ አየለን ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ በውሃ መያዥ ፕላስቲክ አረቄና ቢላ ውድቆ እንደምታገኝ እና ይዛ እንድትመጣ ያዛታል። እሷም “እንዴት በዚህ ውድቅት ሌሊት እሄዳለሁ? ሴት ነኝ” ስትለው ካልሄድሽ ብሎ ሲያስገድዳት ከቤት ስትወጣ ፖሊሶችን በሩ ላይ አግኝታ የሚፈልጉት ተጠርጣሪ ቤት ውስጥ እንዳለ ጠቁማ እንዳሳያዘችው የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ከ26/06/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር አውሎ፤ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ የሟች አስከሬን የህክምና ውጤትና የአማሟት ሁኔታ የሚያሳይ ምስሎችና መረጃዎች አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰርትባቸው መረጃውን አቅርቧል።

ዐቃቢ ሕግ

በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሽ ፍቃዱ ፈለቀ ሰው ለመግደል አስቦ ከላይ በተጠቀሰው ቦታና ጊዜ ሟች ማስረሻ አባይነህን ከአንተ ጋር ቂም አለኝ፤ አንተ ጸብ ታውቃለህ እንዴ ፈሪ ነህ። በማለት በእርግጫ አንድ ጊዜ ሆዱ ላይ ከመታው በኋላ ምንነቱ ባልታወቀ ስለታማ ነገር አንድ ጊዜ ሰንዝሮ ሆዱ ላይ በመውጋት ሟች ጩኸት ሲያሰማ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ እሩጦ አምልጧል። ሟች ሆዱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ደም ፈሶት ሕይወቱ አልፏል። በመሆኑም ተከሳሽ በፈጸመው ተራ በሆነ የሰው መግደል ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል።

ዐቃቤ ሕግም ስድስት የሰው ማስረጃ፤ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በ07/07/2013 ዓ.ም በቁጥር ጳሀ8/3712 ስር የተሰጠ የሟች ማስረሻ የሞቷ ምክንያት ሆዱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ደም ፈሶት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን የሚያስረዳ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከነትርጉሙ 06 ገፅ የሰነድ ማስረጃ፤ የሟችን የአማሟት ሁኔታ፣ ጉዳት እና ወንጀሉ የተፈጸመበትን ስፍራ የሚያሳይ 08 ገላጭ ፎቶግራፎችን እንዲሁም ተከሳሽ በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 27(2) መሰረት ለፖሊስ የሰጠው የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በፍጥነት እንዲታይ አቅርቧል። ተከሳሽ ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ክዶ ቢከራከረም ዐቃቢ ሕግ ተከሳሽ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳዩ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ አስረድቷል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቢ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ እንዲሁም የግራ ቀኙን ክርክር አድምጦ በተከሳሽ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።

 ውሳኔ

 የካቲት 06 ቀን 2015 ዓ.ም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 1ኛ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሽ በ13 (በአስራ ሦስት) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣና ለሦስት(3)ዓመት ሕዝባዊ መብቶቹ ተሽረው እንዲቆዩ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *