“የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለልና ተጠቃሚነትን ለማሳደግበትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን”ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፡- የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫና ለማቃለልና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአቃቂ ሰብል ምርት ገበያና የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከልን ትላንት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል። ከንቲባ አዳነች በመርሐግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የሰብል ምርት ገበያና የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከል ፕሮጀክቶች የመዲናዋን ነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ይረዳሉ።

ምርት ገበያውና ማዕከሉ ኅብረተሰቡ በቀጥታ ከአምራቹ እንዲሸምት ያግዛሉ ያሉት ከንቲባዋ፤ ማዕከሉ የተለያዩ ምርቶች ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገኝና ገበያውን እንዲረጋጋ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለዋል።

የምርት ገበያው ሱቆችን፣ መጋዘንና ወፍጮ ቤት ጨምሮ የተለያየ አገልግሎቶች የሚቀርቡበት መሆኑን አስታውቀው፤ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለአምራቾችና አርሶአደሮች የሥራ እድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የእንስሳት ልህቀት ማዕከሉ በበኩሉ የዶሮና የወተት ላም ርባታ፣ የከብት ማድለብና የመኖ ማቀነባበሪያን ጨምሮ የምርት ማሳያና መሸጫ ቦታዎችን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘርፉ የሚሰማሩ 485 የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በ97 ማኅበራት ተደራጅተው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ማዕከል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተሠሩባቸውን ቦታዎች ለልማት የለቀቁ አርሶ አደሮች ሳይበተኑ እንዲቋቋሙ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘላቂነት ሕይወታቸውን መምራትና ማምረት የሚችሉበት የልማት ማዕከል እንዲሆን የተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

ማዕከሉ የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የምርምር፣ የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ያሉት ከንቲባዋ፤ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫናዎች ለማቃለል በታማኝነትና በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ አርሶአደሮችን ወደ ሥራ በመመለስ ሀብት እንዲፈጥሩ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። ተነሺ አርሶአደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ለከተማው የሚተርፍ ምርት ለማቅረብ የተቋቋመው ማዕከል የአዲስ አበባን የልማት ሂደት በአግባቡ የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የሚጠቀሙበትን ፕሮጀክቶች ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ ፕሮጀክቶቹ የበርካቶችን ሕይወትን የሚቀይሩና አዲስ ታሪክን የሚጀምሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የመዲናዋ ፕሮጀክቶች የብልጽግና ህሳቤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና እያፈናቀሉ መበልጸግ እንደሌለ የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ሥነሥርዓት ላይ የከተማ አስተዳደሩ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድርንና የተለያዩ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአቃቂ የሰብል ምርት የገበያ ማዕከል ከ70 በላይ የመሸጫ ሱቆች የተካተቱበት ሲሆን የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከሉ ደግሞ በ140 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደተገነባ ተገልጿል።

 ማርቆስ በላይ

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *