ጉልት ቸርቻሪዋ …
ከአስፓልቱ ማዶ፣ ከመንገዱ ዳርቻ፣ ከሰዎች ግርግር መሀል አሻግሬ እያየኋት ነው። የተጎሳቆለ ገጽታዋና ፣ አዳፋ ልብሷ አሁንም ከእሷ ናቸው። የልብሷ መቆሸሽ ጉዳይ ስንፍና ያመጣው ችግር አለመሆኑን አውቃለሁ። እንዲህ ይሆን ዘንድ የእንጀራዋ ውሎ፣ የሥራዋ ባህርይ ያስገድዳል።
ዘንድሮን ግን በትካዜና መከፋት ውስጥ መሆኗ አልጠፋኝም። ከፊቷ እንደነገሩ በማዳበሪያ የዘረጋቻቸውን አትክልቶች ቃኘት እያደረገች በሀሳብ ትዋጣለች። አብዛኞቹ እጇ ላይ መበላሸት ጀምረዋል።እነሱ ላይ እያፈጠጠች መልሳ ትካዜ ውስጥ ትገባለች።
አንዳንዴ ያለችበትን ሁሉ የምትረሳ ይመስላል። እንደ ዕንቅልፍ እልም የሚያደርጋት ድካም አብዝቶ ይፈትናታል። በመሀል እንደመባነን ስትነቃ ደግሞ አላፊ አግዳሚውን በዓይኖቿ ትማጸናለች። የያዘችው ድንች፣ ጎመንና ፣ ቃሪያ ዛሬን ተሸጦ ማለቅ አለበት። እንዲህ ካልሆነ ኪሳራዋ ይበዛል፣ በውድ ዋጋ የገዛችው አትክልት በስብሶ ይባክናል።
ሙሪዳን የማውቃት ከጥቂት ዓመታት በፊት በጉልት ሥራዋ ነው። ደንበኛዬ ነች። ዓይነ ሰፊ፣ እጀ ሙሉ የሚሏት ደግ። እሷ ዘንድ ‹‹መርቂበት፣ትንሽ ጣይበት›› ይሉት ጥያቄ የለም።ማንም ሳይላት ቸሩ እጇ ያዛታል። ጨመርመር፣ ጣል ጣል ማድረግን ታውቅበታለች።
ለእኔም ቢሆን ከምገዛት ላይ መረቅረቅ አድርጋ ስለምትሰጠኝ ምርጫዬ ሆናለች። ይህ ብቻ አይደለም። ብሷቷን፣ ችግሯን ስታወራ በግልጽነት ነው።‹‹አህ!›› ብሎ ጆሮውን ለሰጣት ደግሞ ማንነቷን አትደብቅም። ለሚያደምጣት ሁሉ የውስጧን ተንፍሳ ‹‹እፎይ›› ማለት ትወዳለች።
ማንነት በትጋት…
ሙሪዳ የኑሮ ውጣውረዱ፣ ቤተሰብ የማስተዳደር ጫናው ዐሻራውን ጥሎባታል። ሁሌም እረፍት የለሽ ባተሌ ናት። ማለዳ ወጥታ ቀኑን ስትለፋ ብትውል ‹‹ደከመኝ››ን አታውቅም። ምሽቱን ቤቷ ስትደርስ የጎጆዋ ጣጣ ይቆያታል። እጆቿን የሚናፍቁ ልጆቿ ደጅ ደጁን እያዩ ይጠብቋታል። ቀሪውን ሰዓት ለእነሱ የሚያስፈልገውን ስትስጥ፣ የጎደለውን ስትሞላ፣ ታሳልፋለች።
በእሷ ዘንድ ‹‹መሸ፣ በጊዜ ልተኛ›› ማለት አልተለመደም። ቤተሰቡ ለዕንቅልፍ ጎኑን ሲያሳርፍ የሌሊት ትጋቷ ይጀምራል። ለነገው ውሎ እንጀራውን፣ ወጡን ታዘጋጃለች። ያልታጠበውን፣ የቆሸሸውን ታፀዳለች፣ የጎደለውን ሁሉ ትሞላለች።
ሌሊቱ ተጋምሶ ውድቅቱ ሲዳረስ ድካምና ዕንቅልፍ ገፍትረው ሊጥሏት ይዞሯታል። መቼም ቢሆን እጅ አትስጥም። ከሁሉም እየተጋፋች ፣ የኑሮ ምሰሶዋን ለማቆም፣ የሕይወት ግዴታዋን ለመወጣት ትግተረተራለች። እሷ ሁሌም ለቤተሰቦቿ የሚነድ ሻማ ሆና ብርሃን መለገስ፣ ጨለማን ማብራት ልማዷ ነው። ለቤቷ፣ ለልጆቿ ካሏት ፈጽሞ አትደክምም።
ባለቤቷ እንደሷው ሮጦ ያድራል። የልጅነት ባሏ ነው። ትውውቃቸው ካገር ቤት ይጀምራል። ጉራጌ ምድር ‹‹እነሞር››ን ለቀው አዲስ አበባ ሲመጡ ሁለቱም ሠርተው የመለወጥ፣ ተለውጠው የማደግ ዓላማን ሰንቀው ነበር።ጥንዶቹ በትዳር ዓመታትን ሲገፉ ‹‹አንተ ትብስ፣ አንቺ›› በሚል መተሳሰብ ነው።
ሁለቱም አብረው ተባብረው ጎጇቸውን አቁመዋል። በሦስት ጉልቻ ዘመናቸው ያገኟቸውን ሦስት ልጆች በወጉ እያሳደጉ ነው። እንደነሱ ሳይማሩ እንዳይቀሩ ትምህርት አስጀምረዋቸዋል። ሁሉም ትምህርት ቤት ውለው ይገባሉ። ባልም ቢሆን እሷ በፈለገችው ጊዜ ከሚስቱ ጎን አይርቅም። ገበያ ስትውል በሀሳብ ያግዛታል። ስታማክረው መፍትሔውን ያመጣል።
መከፋት..
ሙሪዳ ሀሰንን ሳውቃት እንደዛሬው በእጅጉ ተጎሳቁላ አይደለም። የኑሮ ውጣውረዱ የሕይወት ጫናው ቢፈትናትም ፈገግታ በሞላው ገጽታዋ ቀኗን በደስታ ስታበራው፣ ስታደምቀው ነበር።
ከሙሪዳ ጋር እንደልማዳችን ጭውውት ይዘናል። እንዳልኳችሁ ከእሷ ለማውራት ብዙ አይከብድም። በቀላሉ ከማንም ለመግባባት የቀረበች ናት። ገጽታዋን በስጋት እያስተዋልኩ እንደሁልጊዜው ስለኑሮና ሕይወቷ ጠየኳት። እንደልማዷ የሆዷን፣ ልትዘረዝርልኝ፣ የልቧን ልታወጋኝ ተዘጋጅታለች። ጠንካራ እጆቿን አየኋቸው። ከቀድሞ በባሰ ጠቁረዋል፣ ሻክረዋል። ንግግሯን ከመጀመሯ በፊት ገጽታዋ ላይ መከፋት ያየሁ መሰለኝ። እንዲህ መሆኑ አያስገርምም።
አሁን ሙሪዳ እንደትናንቱ አይደለችም። ደርሶ ዕንባ ያንቃታል፣ በቶሎ ይከፋታል። ሁሌም ስለጎጆዋ እረፍት የለሽ ብትሆንም ኑሮና ሕይወት በእጅጉ እየከበዳት ነው። በየጊዜው የሚጨምረው የቤት ኪራይ ሲያሳስባት ውሎ ያድራል። ልጆቿ ሁሌም ሮጠው ለሚያድሩት ወላጆቻቸው ተስፋዎች ናቸው። ጥንዶቹ እናት አባት ናቸውና እስካሁን ‹‹እንዲህም እንዲያም›› እያሉ አኑረዋቸዋል።
ሙሪዳን እንደምንም አረጋግቼ ወደራሴ መልሻታለሁ። ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ የከፋትን፣ ያስጨነቃትን እውነት ልታወራኝ ጀምራለች። ጭውውታችንን አንድ ሁለት እያልን በወጉ ከመግፋታችን በአካባቢው ድንገቴ ሩጫና ግርግር ተነሳ። እኛን ጨምሮ በስፍራው ያለ ሁሉ ድንጋጤ ቀደመው ።
ወዲያው ሙሪዳ በአሮጌ ማዳበሪያ ከመሬት የዘረጋችውን አትክልት ከወዲያ ወዲህ ጠቅልላ ከአጠገቤ ተፈተለከች። የፍጥነት ሩጫዋ በእጅጉ አስገረመኝ። ከትከሻዋ ያረፈው ቀላል የማይባል ጓዝ ከወደ አንገቷ አጉብጧታል። አሯሯጧ የእመጫት አይመስልም። በአንድ እጇ ልቧን ደግፋ፣ ድንጋጤ በዋጣቸው ዓይኖች ዙሪያዋን እየቃኘች ነው።
እሷን መሰል ነጋዴዎች ከአጠገቧ ቆመዋል። በርከት የሚሉት በእጅና ትከሻቸው የያዙትን ይዘው ከአስፓልት ማዶ ሊሻገሩ ከመኪኖች ጋር ግፊያ ይዘዋል። ሁሉም በሚባል ሁኔታ ስለራሳቸው የሚያስቡ አይመስልም። ከአዳኞቻቸው ለማምምለጥ አደጋውን ችላ እንዳሉት ያስታውቃል።
ጥቂት ቆይቶ ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ አራት ደንብ አስከባሪዎች በአካባቢው ታዩ ። በቅርብ ርቀት ሁለት ፖሊሶች ተከትለዋቸዋል። ከሁለቱ አንደኛው በትከሻው ክላሽ የሚሉትን መሣሪያ አንግቷል። አጭር ስለሆነ መሣሪያው ከቁመቱ ጎልቶ እየታየ ነው።
ሰዎቹ በገበያው መሀል አልፈው ራቅ እንዳሉ ሁኔታዎች ተለውጠው የነበረው እንደነበረው ሆኖ ቀጠለ። ከመሬት ጓዛቸውን ያነሱ መልሰው በቦታው ዘረጉ። አስፓልት ተሻግረው የራቁ በፍጥነት ስፍራቸውን ተቆጣጠሩ። ጀሞና አካባቢው በአንድ አፍታ ወደሞቀው ግርግርና ትርምሱ ተመለሰ።
የልብ ወግ…
ሙሪዳና እኔ ዳግመኛ ተገናኘን። ሁለታችንም ውላችንን አልረሳነውም። ጅምር ወጋችንን ልንቀጥል ወደቀደመው ስፍራ ተመልሰናል። ሙሪዳ ልታወጋኝ የነበረው አንዱ ስጋት ከደቂቃዎች በፊት ያጋጠመውን ዓይነት ሀቅ እንደነበር እየተከዘች ነገረችኝ ።
የእሷ የዓመታት መተዳደሪያ ከመንገድ ዳር ተቀምጦ አትክልት መቸርቸር ነው። ከዚህ ቀድሞ ለገበያ የምታውለውን ግዢ የምታመጣው ፒያሳ ከነበረው አትክልት ተራ ነበር። የዛኔ በማለዳ ወጥታ ግብይቱን ከጨረሰች ሰፈር በሚያደርሳት ታክሲ ጓዟን ይዛ ትገባለች።
በወቅቱ የነበረው የገበያ ዋጋ ተመጣጣኝና ለእሷም የሚዋጣ በመሆኑ በገበያ ውለዋ አትራፊ የምትባል ነበረች። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአትክልት ገበያው ‹‹ጋርመንት›› ወደተባለው አካባቢ ተዛውሯል። እንዲህ መሆኑ ለምትኖርበት ሰፈር የቀረበ ነውና አልተከፋችም።
ገበያው ወደ ጋርመንት በመዞሩ ብቻ ግን ለሙሪዳ ያቀለለላት ሸክም የለም።ዛሬም እንደቀድሞው ማልዳ ከአትክልት ተራው መድረስ ፣ ተሻምታ፣ ከሌቦች ተጋፍታ የተሻለውን መምረጥ ግድ ይላታል። ገበያው ደግሞ እንደትናቱ አይደለም ።በየቀኑ ሽቅብ የሚጎነው የአትክልት ዋጋ ከሚታመነው በላይ ሆኗል። ይህን ሁሉ አቻችሎ በጉልት ችርቻሮ ትርፍ ይዞ መግባት ፣ የልጆችን ጉሮሮ መዝጋት በእጅጉ አዳጋች እየሆነ ነው።
ሙሪዳ በዚህ ሁሉ ልፋት የገዛችውን አሸክማና በታክሲ አስጭና ለማምጣትም በብዙ ችግርና ፈተናዎች ማለፍ ይኖርባታል። ችግሩ ግን እንዲህ መሆኑ ብቻ አይደለም ። አትክልቱን በታክሲ ይዛ ካለችበት ለማድረስ ከጉልበት ድካሟ በላይ ባለታክሲዎች በየጊዜው የሚጭኑባት ዋጋ የእጇን አቅም እያራገፈው ነው።
ሙሪዳ ዛሬ ባስጫነችበት ዓይነት ዋጋ ነገን ልሞክር ብትል ‹‹በጄ›› የሚላት የለም። በየቀኑ እንደየሰዉ ባህርይ የባለታክሲዎችና ረዳቶቻቸው የክፍያ ዋጋ ይለዋወጣል። እንደምንም ታግላ ከሰፈሯ የምታደርሰውን ሸክም አሁን ላይ በቅርብ አስቀምጣ በአደራ አልያም በክፍያ የምታቆይበት ቦታ የለም።
ቀድሞ ጓዟን የምታኖረው በየቀኑ ለሥራ ከምትውልበት የገበያ ስፍራ በአንዱ ነበር። ዛሬ ግን ፈጽሞ ይህን ለመሞከር አልተቻላትም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከአካባቢው የፈረሱት በርካታ የገበያ ሱቆች የእሷን ህልውና ጭምር አናግተዋል። ይህ ክፉ አጋጣሚም ከታክሲ ጣራ የምታወርደውን የሞላ ማዳበሪያ በባጃጅ ፣ አልያም በሰው ትከሻ አገላብጣ ወደቤቷ እንድታደርስ አስገድዷታል።
ኑሮን በፈተና ..
ሙሪዳ በየጊዜው በድካም የምታመጣውን የአትክልት ማዳበሪያ ከቤቷ አድርሳ መልሳ ወደገበያ ማመላለስ ይጠበቅባታል። ይህ ዓይነቱ የየዕለት ልማድ ደግሞ አሁን ላይ የጤና ችግር እያስከተለባት ነው። ብዙ ጊዜ ወገቧን ያማታል።ራስ ምታት ይፈትናታል። ባስ ባለ ጊዜም ለቀናት በቤቷ ተኝታ ትከርማለች። ይህኔ ለሽያጭ ያመጣቻቸው አትክልቶች ለመበላሸት አይዘገዩም።
ሙሪዳ ህመም ቢጠናባትም። ለራሷ ፊት አትሰጥም። እንደምንም ወገቧን አስራ፣ ጥርሷን ነክሳ ወደሥራዋ ትመለሳለች። አንዳንዴ ምርር ባላት ጊዜ ሁሉን ትታ፣ ቤተሰቦቿን ይዛ ሀገር ቤት ልትገባ ታስባለች። መልሳ ደግሞ ሀሳቧን እርግፍ አድርጋ ከራሷ ትመክራለች። እሷና ባሏ ከገጠር አዲስ አበባ ሲመጡ ራሳቸውን ለመለወጥ፣ ሕይወታቸውን ለማሻሻል ነው። ከእነሱ በፊትም ሆነ በኋላ በርካቶች ከቀያቸው ወጥተው ያሰቡትን ሞልተዋል። ሙሪዳ ይህ ሲገባት ተስፋዋን ታለመልማለች፣ ነገ የተሻለ እንደሚሆን ታልማለች።
የዘንድሮው ክረምት ለሙሪዳና መሰሎቿ የፈተና ጊዜ ሆኗል። እንደአምና ካቻምናው የያዙትን የጉልት አትክልት እንዳሻቸው አይሸጡም። የገበያዎቹ መፍረስ፣ የአካባቢው መለወጥ መድረሻ አሳጥቷቸዋል። የያዙትን ይዘው ከአስፓልቱ ብቅ ሲሉ ቆመጥ የያዙ ደንቦች ፈጥነው ይደርሱባቸዋል። አንዳንዶቹ ጓዛቸውን ጣጥለው ‹‹እግሬ አውጭኝ› ይላሉ።
የአካባቢው ደንብ አስከባሪዎች በእጃቸው የገባውን ማንኛውንም ነገር አይምሩም። የቻሉትን ሁሉ ተሸክመው ይወስዳሉ። የተቀረውን በእግራቸው እየበተኑ፣ እየረገጡ ያባክኑታል። በዚህ ጊዜ እነሱን ለምኖ ተለማምጦ የሚቀናው አይኖርም።
ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ የብዙዎችን ጉልት ቸርቻሪዎች አንገት ያስደፋል። በ‹‹ሞላ ጎደለ›› የሚመሩትን ሕይወት ያጨልማል። ሙሪዳ ከዝናቡ ተጋፍታ፣ ከፀሐይዋ ተለማምጣ ከአንዱ ጥግ ስትቀመጥ ዓይንና ልቧ አያርፍም። የሚገዟትን መንገደኞች ትቃኛለች። የደንቦችን ኮቴ ታደምጣለች። ድንገት ቢመጡባት የቱን ይዛ ፣ የቱን እንደምትለቅ ታስባለች።
በተስፋ መቁረጥ ውስጥ …
ሙሪዳና ቤተሰቦቿ የቤት ተከራዮች ናቸው። በቅርቡ ደግሞ ዓመታትን ከኖሩበት መኖሪያ ለመልቀቅ ተገደዋል። አከራዮቹ በየጊዜው የሚጭኑባቸው ኪራይ በእነሱ አቅም የሚቻል አልሆነም። በቅርቡ ከተከሰተው የቤቶች መፍረስ ጋር የተከራዮች አካባቢውን መያዝ በቀደሙት ተከራዮች ላይ ከባድ ጫና አሳርፏል።
አሁንም ሙሪዳ ባለችበት ቤት ምቾት እየተሰማት አይደለም። ዓመታትን ከኖረችበት አንድ ክፍል ወደ ሌላ ጠባብ ክፍል የዞረችው በቅርቡ ነው። ይህን ማድረጓ የኪራይ ጭማሪውን መቋቋም ባለመቻሏ ነበር። አሁንም ግን ከመስከረም ጀምሮ ጨምሪ የተባለችው አንድ ሺህ ብር ዕንቅልፍ ነስቷታል። ቀን መሽቶ ቀን በመጣ ቁጥር በሀሳብ ትዋጣለች።
ጠንካራዋ ሳቂታዋ ሙሪዳ ዘንድሮ የተከፋችበት ጉዳይ እስክትነግረኝ ምክንያቱን ሳላውቅ ቆየሁ። ሁሉን ከተረዳሁ ከገባኝ በኋላም ከልቤ አዘንኩ።ይህ ዓይነቱ ስሜት በእርግጠኝነት የእኔ ብቻ አይሆንም። በየስፍራው ራሳቸውን ለማሸነፍ፣ ኑሯቸውን ታግለው ለመጣል የሚጥሩ ነፍሶች የኑሮ ውድነቱ እንደበዛባቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
እንደ መልዕክት…
ሙሪዳን የመሰሉ የሚሠሩ እጆች፣ ለትጋት የሚሮጡ እግሮች ያሏቸው ትጉዎች ከፍጥነታቸው እንዳይገቱ ፣ ከሕይወታቸው እንዳይታጎሉ ያሻል። አዎ! ነገ ሳይሆን ዛሬ የትኩረት ዓይኖች ይመልከቷቸው ፣ መልካም ልቦናዎች ከልብ ይጎብኟቸው እንላለን።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015