መምህር ፍቅሬ ሀብቴ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቡልቡላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ለ21 ዓመት አገልግለዋል። በዚህ ቆይታቸው በሁለተኛ ዲግሪ ስኩል ሊደርሽፕ ትምህርትን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተከታትለዋል። ሆኖም የተማሩትን መሬት ላይ ለማውረድ ይቸገሩ ነበር። ለዚህ ምክንያት የሆነው ደግሞ እንደ ሀገር የነበረው ምልከታና የአሰራር ሁኔታ የፈጠረው መሰላቸት የራስ ተነሳሽነት እንዲጠፋ ማድረጉ ነው።
እንደ መምህር ፍቅሬ ሃሳብ፣ የርዕሰ መምህርነት ሥራን የአስተዳደር ሥራ ብቻ አድርጎ የመቁጠር ዝንባሌ መማር ማስተማሩን በመደገፉ በኩል እምብዛም እንዲሰራበት ሲያደርግ አይታይም። ርዕሰ መምህር የሚመረጥበት መንገድም ከሙያ ይልቅ ፖለቲካ ላይ ትኩረት ማድረጉ ለዚህ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ መምጣታቸውን የጠቀሱት መምህር ፍቅሬ፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ መሰረት የተለያዩ ስልጠናዎችና ክትትሎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ለዚህም ማሳያ አድርገው የሚያስቀምጡት በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍና በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት Education Development Trust (EDT) የተሰኘ ስልጠና ማግኘታቸውን ነው። ‹‹ዛሬ ለምረቃ የበቃንበት የተግባር ትምህርት ከንድፈ ሀሳብ ያየለበት ስልጠና ነው›› ያሉት መምህር ፍቅሬ፣ መሰል ስልጠናዎች የርዕሰ መምህርነት ሥራ በእውቀት እንዲመራ ያግዛል ብለው ያምናሉ፡፡
ስልጠናው አዳዲስ ሀሳቦችን እያመነጩ ለሀገር የሚተርፉበትን መንገድ ያመላክታል የሚሉት መምህር ፍቅሬ፣ በተለይም ትምህርት ቤቶች ከፖለቲካ አመራር ተለይተው እንዴት በእውቀት ከሙያው ጋር ተሰናስለው መመራት አለባቸው የሚለውን ጉዳይ ለማየት ስልጠናው እንደሚረዳ ያስቀምጣሉ። ይህ ስልጠና መምህራንን ደግፎ፣ ማህበረሰቡን አሳትፎና ተማሪዎችን በተሻለ እውቀት አንጾ እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በሚገባ የሚያረጋግጥም እንደሆነም ያነሳሉ።
እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለፃ፣ መሰል ስልጠናዎች ተወዳዳሪ ትምህርት ቤት ከመፍጠር አኳያም የማይተካ ሚና አላቸው። ስኩል ሊደር ያልተማሩ መምህራንም ቢሆን ጥሩ እውቀት ይጨብጡበታል። በዚህም ቀጥታ ከመምህርነት ወደ ርዕሰ መምህርነት የሚገቡ ባለሙያዎችን በተለመደው አሰራር ከመያዝ ይታደጋቸዋል። መምህር ፍቅሬ እስከዛሬ በነበረው ልምዳቸው ከእቅድ ጀምሮ ያለው ሁኔታ ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ይናገራሉ። አሁን ግን ከተለመደው አሰራር ወጥተው በራሳቸው አዳዲስ ነገር እየፈጠሩ እንዲጓዙ ስልጠናው እድል የሚፈጥር መሆኑን ያስረዳሉ።
ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ሱፐርቫይዘር ሳይቀር ግብረ መልሶችን ሲሰጥ በዘልማድ እንጂ በእውቀትና ትምህርት ቤቱን እንዲሁም መምህሩን በሚያሻሽልበት ሁኔታ አልነበረም። እናም ይህ ስልጠና መሰል ክፍተቶችን ይሞላል የሚል እምነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ከዚህ ባሻገር ይህ ስልጠና እንደ ሀገር ከርዕሳነ መምህራን አንጻር በተለይ ሴቶች ላይ መስራት ቢቻል ብዙ ውጤታማ የሚያደርግ ነው ሲሉም ይናገራሉ።
ይህንን ሲያብራሩም፣ ‹‹ሴት ርዕሰ መምህራን ትምህርት ቤቶችን ሲመሩ ከቤታቸው አይለዩም። በእውቀትና በአሰራር የተሻሉም ናቸው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ሴቶች የሚመሯቸውን ትምህርት ቤቶች ብቻ መመልከት ነው። እናም ልምዳቸውንና አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እንዲህ አይነት ስልጠና እጅግ ያስፈልጋቸዋል። ወንዶችን በልጠው ተወዳዳሪ ሴት አመራሮችን የሚፈጥሩበትን እድልም ይሰጣቸዋል፡፡›› ይላሉ።
በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴርም የጀመረውን ስልጠና ማስፋት እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። መምህር ፍቅሬ ሴቶች በእንዲህ አይነት ስልጠናዎች (በኢዲቲ) ሲደገፉ ጥሩ የመማር ማስተማር ሁኔታን ከወንዱ በላቀ መልኩ ይፈጥራሉ የሚል ሃሳብ አላቸው። ነገር ግን ይህ ሥራ ለትምህርት ሚኒስቴር ወይም ለክልል ትምህርት ቢሮዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን እንደ ትምህርት ቤትም የሚሰራበት ሊሆን እንደሚገባ ያስቀምጣሉ።
ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ኃላፊነትን እንዲለማመዱና እድሉን እንዲያገኙ በተለያየ ዘርፍ ላይ ማበረታታት ያስፈልጋል። ለአብነት የትምህርት ክፍሎች ተጠሪ፣ የክበባት መሪዎች፣ በተማሪ በኩል ደግሞ የክፍል አለቆች እያደረጉ ወደፊት ማምጣት ያስፈልጋል። ይህም ሲያድግ መምራት እንችላለን ብለው እንዲያምኑ ያደርጋል። በዚህም ርዕሰ መምህርነትን ኃላፊነት ተወዳድረው በብቃት እንዲያገኙና የሀገር ተስፋ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል የሚል ሀሳብ እንዳላቸው መምህር ፍቅሬ ይናገራሉ።
ለተከታታይ ስምንት ወር የተሰጠው ይህ ስልጠና፤ በዩኒቨርሲቲ ኢንስትራክተሮች እገዛ ተግባር ተኮር ሆኖ የቀጠለ ነው። ይህም እነ መምህር ፍቅሬ በርካታ ለውጦችን በትምህርት ቤታቸው ውስጥ እንዲያመጡ አስችሏል። ለአብነትም የአመራር ስርዓት መቀየር አንዱ ነው። ከወላጆችና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመስራት የሚደረገውም ጥረት የስልጠናው ውጤት ነው።
ለርዕሰ መምህራኑ የተሰጠው ስልጠና ተጨባጭ ውጤት ያመጣ እንደሆነ በየክልሉ ያሉ ትምህርት ቢሮዎች ተሞክሯቸውን በሚያካፍሉበት ጊዜ ለመገንዘብ ተችሏል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ነው። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተክሉ አዱላ፤ ስልጠናው የትምህርት ማህበረሰቡን ከውጭው ማህበረሰብ ጋር በእጅጉ ያስተሳሰረ መሆኑን ይመሰክራሉ። ስልጠናው ማህበረሰቡ ለትምህርት ቤቱ ትምህርት ቤቱም ለማህበረሰቡ ምን ማበርከት እንዳለበትም ያሳየ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተክሉ፣ አሁን ሁለቱ አካላት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነዋል ይላሉ።
ይህ ለርዕሳነ መምህራንና የሱፐርቫይዘሮች የተዘጋጀ ስልጠና በራስ አቅም መስራትን የገነባ ነው። ለዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር ስልጠና ውጭ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ጅምሩን የማስፋት ሥራ ሰርተዋል። ይህም የሚታይ ለውጥ አምጥቷል። ለዚህ አብነት የሚሆነውም ማህበረሰቡና ትምህርት ቤቶች አብረው የሚሰሩበትን እድል አመቻቸት መቻሉ ነው።
የኦሮሚያ ክልል በስልጠናው መጠቀሙን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ይናገራሉ። ይህን ሲያብራሩም፤ ‹‹ስልጠናው በሰጠን እድል ከክልል ፕሬዚዳንቶች ጋር ሳይቀር መቀራረብና መሥራት ጀምረናል። በቋሚነት የምናሰለጥንበት ማዕከል ለመስራት አስበን በአዳማ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ስልጠናው ለትምህርቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን አስተምሯል። አዳዲስ ሀሳቦችን ለማመንጨትም አስችሏል›› ይላሉ።
ከስልጠናው ጋር በተያያዘ በEducation Development Trust የሀገር አቀፍ የርዕሰ መምህራን ስልጠና ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ትዕግስት ተፈራ፣ ስልጠናው ከእንግሊዝ መንግስት በተገኘ ድጋፍ ላለፉት ሦስት ዓመታት ትምህርት ሚኒስቴር ሲተገብረው የቆየ መሆኑን ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ ብዙ መፍትሄዎችን ያመላከተ ከመሆኑ ባሻገር ቀደም ሲል የነበሩ ስልጠናዎችን ለመቃኘት እድል ሰጥተል። ‹‹የቀደሙ ስልጠናዎች የሥራ ላይ ክህሎትን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም። ዋና ትኩረታቸው ንድፈ ሀሳብ እንጂ ተግባር አይደለም። ይህ ደግሞ ስልጠናን ከሀሳብ እንዳያልፍ አድርጎታል›› ይላሉ አስተባባሪዋ ሲያብራሩ።
በተለያየ ዙር ለተለያዩ ሰልጣኞች ለተከታታይ ስምንት ወራት የሚሰጠው ይህ ስልጠና ርዕሰ መምህራን ሥራቸውን እያከናወኑ የወሰዱት ነበር። ይህ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠውን መስፈርት ማሟላት የሚችሉ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ትምህርት ቤቶችን ያበራክታል ተብሎ ይጠበቃል። ከምንም በላይ ደግሞ በስነምግባር የታነጹና በአቅም የጎለበቱ እንዲሁም ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት ያስችላል። የስልጠናው በአምስት ክልሎች ላይ በ40 ትምህርት ቤቶች የተጀመረ ሲሆን አመርቂ ለውጥ በማሳየቱ በሌሎች ክልሎች እንዲሰፋ ተደርጓል። አሁን ላይ በ500 ትምህርት ቤት ላይ ሥራው ተከናውኗል። ይህ ደግሞ 4ሺህ 500 ርዕሰ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችን የስልጠና ተጠቃሚ አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 800 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
በመምህራን ደረጃ እንደ ሀገር 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ሆኖም በርዕሳነ መምህራን ደረጃ ከ10 በመቶ አይበልጡም። ሴቶችን ወደአመራርነት ሊያመጣ የሚያስችል አሰራር አለመዘርጋቱ ደግሞ ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው። ይህም እስከዛሬ የትምህርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው ስልጠና ላይ የሚሳተፉ ሴት ርዕሳነ መምህራንን ቁጥርን እጅግ አናሳ አድርጎታል። ለዚህም እንደ ሀገር በስልጠናው የተካፈሉ ሴቶች ከ12 በመቶ ልቆ አለመገኘቱ ተጠቁማል። ትምህርት ሚኒስቴር ግን የሴት አመራሮችን ቁጥር ሃምሳ በመቶ ለማድረስ በዓመት እቅዱ አካቷል።
በዚህ ረገድ እየተተገበሩ በሚገኙ አንዳንድ ሥራዎችና በአስገዳጅነት በሚወጡ መመሪያዎች መሻሻሎች እየታዩ ናቸው። አንዱ በዚህ ስልጠና የታየው ነገርም ይህ ነው። የሴት አመራሮችን በብቃት ወደፊት ለማምጣት ሲባል ከየትምህርት ቤቱ ከሚላኩት ሰልጣኞች ውስጥ ቢያንስ አንዷ ሴት እንድትሆን ተደርጓል። በዚህም እንደ እቅድ አምስት መቶ ተይዞ ከዚያ በልጦ እየተገኘ ነው፡፡
በዚህ ስልጠና ብዙ ስኬቶች ተመዝግበዋል። አንዱ የስልጠናውን ጥቅም ተረድቶ በተግባር መተርጎም ሲሆን ሌላው የአስተዳደር ስራው ላይ ሰፊ ልዩነትና መሻሻል መታየቱ ነው። የመማር ማስተማሩን ሂደት ለመደገፍም የተሻለ እድል ተፈጥሯል። መምህራንን የሚያግዙ፣ የመማር ማስተማር ሥራውን የሚመሩ፣ ለተማሪዎች አመቺ የትምህርት ቤት ምህዳር የሚፈጥሩ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተባብረው የሚሰሩ፣ ትምህርት ቤት የሚመራው በግል ሳይሆን በጋራና በትብብር እንደሆነ የሚረዱ ርዕሳነ መምህራንንና ሱፐርቫይዘሮችን መፍጠር ተችሏል። የባህሪ ለውጥም አምጥቷል።
ሴቶችን ወደአመራርነት እንዳያመጡ ያደረጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ከሃይማኖት፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካና ባህል የሚጠቀሱ ናቸው። ስለዚህም የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት፣ የቅጥርና ምደባ ስርዓቱን ለሴቶች በሚመች መልኩ ማስተካከልና ሴቶችን ወደኋላ ሊጎትቷቸው የሚችሉ ነገሮችን ማቅለል ለችግሩ መፍትሄ እንደሆኑ ታምኖባቸው ወደሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ በስልጠናው የተካፈሉ ሴቶች አስተያየት ሰጥተዋል።
መምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉቀን ሙላቱ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የትምህርት ቤት አመራር ንድፈ ሀሳባዊ ነው። በዚህም ርዕሰ መምህራን አስኳል የሆነውን የመማር ማስተማር ሥራ በመተው ፖለቲካው የሚያዛቸውን በመተግበር ይጠመዱ ነበር። ይህ ደግሞ አቅም ያላቸው መምህራን ወደፊት እንዳይመጡና ሙያውን እንዳይወዱት አድርጓቸዋል። ይህንን መቀየር የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት።
አሁን በትምህርቱ ዘርፍ ሀገር የምትፈለገው ነገር የተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ መስራት ነው። ርዕሳነ መምህራን ደግሞ የዚህ ሥራ ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው። ለስራቸው ራሳቸውን የሰጡ መሪዎች ያስፈልጋሉ። ተወዳዳሪ የሆኑ የትምህርት ቤቶችም እንዲሁ። ስለዚህም አመራሮች አርቆ አሳቢ፤ አካታች የሆኑ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። ትምህርት ቢሮዎች ደግሞ መደገፉ ላይ መበርታት ይኖርባቸዋል። ይህ ከሆነ ስልጠናው ተግባራዊ ይሆናል፣ ሀገርም ትለወጣለች።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ለሁሉም የትምህርት ቤት አመራሮች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን አስምረውበታል። በመሆኑም ሁሉንም በአንዴ መድረስ አይቻልምና በየጊዜው በስልጠናው የትምህርት ቤት አመራሮችን ሚና ማሳደግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ለርዕሳነ መምህራን ስልጠና የሚሰጥ ተቋም እንዲኖር ይደረጋል ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ‹‹የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅ ፍላጎትና አቅም ያላቸውን ርዕሳነ መምህራንን ከማሰልጠን ባሻገር በአስተሳሰብ ላይ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። ስለሆነም መሰል ስልጠናን በስፋት የምንቀጥልበት ይሆናል›› ሲሉም ፕሮፌሰሩ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ተናግረዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም