አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ የመጣ ነው። አንዱና ዋነኛው ደግሞ የፈተና አሰጣጥና የክፍል ደረጃዎች ልየታ ነው። ከእነዚህ መካከል ታችኛው ክፍል ላይ ይሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ ፈተና ከስድስተኛ ክፍል እንዲጀምር መሆኑ በዋናነት ይጠቀሳል። የስምንተኛ ክፍል ፈተናም ቢሆን እንደስከዛሬው ሁለት ክፍሎችን አካቶ ፈተና የሚወጣበት ሳይሆን በአንዱ ክፍል ትምህርት ላይ ብቻ ተመርኩዞ አቅማቸው የሚታይበት ተደርጓል። ይህ ደግሞ ለፈተና አውጪዎችም ሆነ ለተፈታኞች ጫናን የሚቀንስ ነው። ተማሪዎች በአሉበት የክፍል ደረጃ ሊኖራቸው የሚችለውን ብቃትና እውቀት በተጨባጭ የሚያረጋግጥም ያደርገዋል። እኛም ይህን ስኬት ያጎናጽፋል የተባለለት የፈተና አሰጣጥና ዝግጅቱ በክልሎች ምን ይመስላል ስንልም በዛሬው የ‹‹አስኳላ›› አምዳችን ለማቅረብ ወደናል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አንዱ ፈተናውን ከሚሰጡ መካከል ሲሆን፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን ሳይቀር ለመስጠት የዝግጅት ሥራዎችን አጠናቋል። የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር እንደሚናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን የጀመረው ከመጽሐፍ ስርጭትና መማር ማስተማር ሥራ ነው። በዚህም ሁሉም ተማሪ ቀድሞ መጽሐፍ አግኝቶ እንዲማርና ይዘቶቹ ሙሉ ለሙሉ እንዲሸፈኑ ከማድረግ አኳያ ሲሰራ ቆይቷል። በተጨማሪም በየምዕራፉ መጨረሻ የሞዴል ፈተናዎችን እየወሰዱ ዝግጅት እንዲያደርጉ አግዟል።
አሁን ላይ ተማሪዎቹ ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ይሰማናል የሚሉት ኃላፊው፤ በፈተናው የሚሳተፉ ተማሪዎች በመደበኛም ሆነ በማታ እንዲሁም በርቀት የሚማሩ ተማሪዎችን የሚያሳትፍ ነው። በዚህም ስምንተኛ ክፍል ላይ ሲመጣ በአማርኛው ሥርዓተ ትምህርት ስድስት የትምህርት አይነቶችን ተማሪዎች የሚፈተኑ ሲሆን፤ በኦሮምኛው ደግሞ ስምንት የትምህርት አይነቶችን እንዲፈተኑ ይደረጋል። በኦሮምኛ ቋንቋ የተጨመሩት ሁለት ትምህርቶች አፋን ኦሮሞና ገዳ ናቸው። ስድስተኛ ክፍል ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ የሚፈተኑ አራት እንዲሁም በአፋን ኦሮሞ የሚፈተኑ አምስት የትምህርት ዓይነቶችን የሚወስዱ ይሆናል። በዚህ መሠረት የሒሳብ፣ የአካባቢ ሳይንስ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛና እንግሊዝኛ የትምህርት ዓይነቶች ይሰጣሉ።
በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ አንደኛ ምዕራፍ የሚባለው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሲሆን፤ ሁለተኛ ምዕራፍ የሚባለው ከሰባት እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚገኘው ነው። በዚህም የመጀመሪያ ምዕራፍ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚያጠናቅቁት ስድስተኛ ክፍል ላይ ይሆናል፤ ቢሮው በቂ ዝግጅት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠውን የስድስተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ተማሪዎች ከታች ጀምረው ራሳቸውን እያነጹ እንዲመጡ ያግዛልና የመጣውን እድል እንዲጠቀሙበት እንዳደረግን ይሰማናል ይላሉ አቶ ወንድሙ።
ይህ እድል በየደረጃው ያለውን የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ጥቅም አለው የሚሉት ምክትል ሃላፊው በዘንድሮው ፈተና በግል እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ከ 75 ሺ በላይ የ 6 ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲፈተኑ ይሆናሉ ብለዋል። የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ከስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም። ምክንያቱም ስምንተኛ ክፍሎች ቀደም ሲል በነበረውም የትምህርት ሥርዓት ተፈታኝ ናቸው። ስለዚህም የትምህርት ሥርዓቱ ለውጥ ካልሆነ በስተቀር ጫና አይኖርባቸውም። የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ግን ብዙ ነገሮች አዲስ ይሆኑባቸዋል። ስለሆነም በሥነልቦናም ሆነ በትምህርት መታገዝ አለባቸውና እንደከተማ አስተዳደር ይህ ተደርጓል ይላሉ።
ለአብነትም ለሁለቱም ክፍል ተፈታኞች በፈተናው ብቁ እንዲሆኑ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን አንብበው እንዲዘጋጁ እየታገዙ መሆኑን ገልጸው በተመሳሳይ በየክላስተሩ ላሉ ትምህርት ቤቶች ወጥ በሆነ መልኩ ሥልጠና በመስጠት ትምህርት ቤቶች ራሳቸው ፈተናዎችን እንዲያወጡና እንዲፈተኑ ተደርጓል። በአዲሱ ሥርዓት ትምህርት በየምዕራፉ ማጠናቀቂያ ላይ ለተማሪዎች ፈተና እንዲሰጥም ሆኗል። የተፈታኞች ምዝገባን በኦንላይን እንዳካሄዱ የጠቆሙት አቶ ወንድሙ፤ ይህ መደረጉ ተማሪዎች በፈለጉበት ቦታ ሆነው የተመዘገቡበትን የስም እና ዕድሜ ስህተት እንዳይኖር ማረጋገጥ እና ማስተካከል ይችላሉ። በዚህም በ2015 ዓ.ም 75 ሺ 100 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችና 75 ሺህ 078 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከተማ አቀፍ ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል ብለውናል።
ሌላኛው ክልል አቀፍ ፈተናዎችን ከሚሰጡት ውስጥ የሚጠቀሰው የኦሮምያ ክልል ሲሆን፤ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እንዳሉን፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁለቱንም የክፍል ደረጃ ያካተተ ፈተና አይሰጥም። ምክንያቱም በአዲሱ ትምህርት ሥርዓት የተዘጋጀው የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ፈተናን በተዋጣለት መልኩ ለመስጠት መሟላት ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፤ ከዚህም መካከል የመጸሐፍ ስርጭትና የፈተና በጀት ሲሆን ክልሉ ካለው የተማሪዎች ብዛት አንጻር ይህንን ለማድረግ በእጅጉ ይፈተናል። ስለሆነም በዘንድሮው ዓመት የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናውን ብቻ ለመስጠት ወስኗል።
በኦሮምያ ክልል የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ብዛት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ ነው። የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ 490ሺህ 167 ናቸው። ስለሆነም ሁለቱን አጣምሮ ለማስፈተን ብዙ በጀት ይጠይቃል። በመጽሐፍ ሕትመት ብቻ በርካታ ወጪዎች በመውጣታቸው የተነሳና መሟላት ያለባቸው በርካታ ነገሮች ስላልተሟሉ የስድስተኛ ክፍሉን ፈተና በማዘግየት ስምንተኛ ክፍል ላይ ያሉ ተማሪዎች በቂ መጻሕፍትና ግብዓት አግኝተው የተሻለ ተፈታኝ እንዲሆኑ ሲደረግ ቆይቷል።
ዝግጅቶቹ የጀመሩት ቀደም ብሎ በመሆኑ ሌሎች የክፍል ደረጃዎች መጽሐፍ ሳያገኙ ስምንተኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ የሚያገኙበት እድል ተመቻችቷል። መምህራንና አስፈላጊ ግብዓቶችም ቀድሞ እንዲሟላላቸው ሆኗል። የትምህርት ሽፋኑ ጭምር እንዳያስቸግራቸው በማሰብ በተለያየ መልኩ እንዲማሩም ተደርጓል። በተመሳሳይ የተማሪዎችን አቅም ልዩነት ለማቀራረብ በወረዳ ደረጃ ብቃት ባላቸው መምህራን የሞዴል ፈተናዎች ተዘጋጅተው እንዲፈተኑም ሲደረግ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ለተሻለ ውጤት ያበቃቸዋልም ይላሉ።
የዘንድሮው ክልል አቀፍ ፈተና ብዙ ነገሮች የሚለዩበት ነው። የመጀመሪያው አዲሱን የትምህርት ሥርዓት የተከተለ በመሆኑ ተፈታኞች እንደ ክፍል ፈተና በዓመት ውስጥ ብቻ የተማሩትን የሚፈተኑበት ነው። ማለትም እንደዚህ ቀደሙ የሁለት ክፍሎችን ትምህርት አያነቡም። ይህ ደግሞ ጫናቸውን ቀንሶ በቂ እውቀት መጨበጣቸውን ያረጋግጣል። ይህንን አልተማሩትም የሚለውን ወቀሳም ያስቀራል። ምክንያቱም በየምዕራፉ ማጠቃለያ ፈተና ይወስዳሉ። ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ የተዘጋጁ ሞዴሎችንም እንዲያልፉ ይደረጋሉ።
በዚያ ላይ ክልል አቀፍ ፈተናውን ሳይቀር እንዲሰሩ ይደረጋሉ። ይህ ፈተና ደግሞ ከሌሎች ክልሎች ጋር ተመሳሳይነት እንዲኖረውና በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደ አገር በወጣ አቅጣጫ (ቴብል ኦፍ ስፔስፊኬሽን) አማካኝነት የሚከናወን ነው። እናም በዚህ ሁሉ ዝግጅትና ፈተና ውስጥ ያለፈ ከዚያም አልፎ ከ50 በላይ ውጤት ያመጣ ተማሪ ቀጣዩ ክፍል ሲገባ በቂ እውቀት አልጨበጠም ሊያስብለው አይችልም። ይህንን ከማድረግ አኳያ ክልሉ በስፋት እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
የአማራ ክልልም በዘንድሮው ዓመት ለስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና አይሰጥም። ምክንያቱ ደግሞ የመጽሐፍ ስርጭት ጉዳይ ሲሆን፤ የዶላር ዋጋ መጨመርና መጽሐፍቱ በሀገር ውስጥ አለመታተማቸው በታሰበው ጊዜ ተማሪዎቹ እጅ ላይ እንዳይደርስ አድርጎታል ፤ በመሆኑም በዘንድሮው ዓመት ክልሉ የሚፈትነው የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን ብቻ እንደሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሳዬ አባተ ይናገራሉ።
አቶ ካሳዬ እንደሚሉት፤ ተማሪዎች በክፍል ትምህርትም ቢሆን በቂ ግብዓት ተሟልቶላቸው መማር ይኖርባቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ክልሉ አልቻለም። የስምንተኛ ክፍልን እንኳን ለማስፈተን በብዙ መልኩ ችግር እየገጠመ ይገኛል። ከችግሮቹ መካከል ደግሞ መጻሕፍቱ ለተማሪዎች በጊዜው አለመድረስ ሲሆን፤ የመምህራን ማስተማሪያም ቢሆን በብዙ ልፋት እንደደረሰ ይናገራሉ። ሆኖም ቢያንስ አንዱን ክፍል መፈተን ይኖርብናል በማለት በተቻለው ሁሉ ዝግጅት ለማድረግ እንደተሞከረም ያነሳሉ።
ሳይማሩ መፈተን በምንም መልኩ የሚቻል አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሩ በዚህም መጽሐፉ ባይደርሳቸውም በሶፍት ኮፒና መምህራን በብላክቦርድ ላይ እየጻፉ አስተምረዋቸው ለፈተና ዝግጁ አድርገዋቸዋል። የማስተማሪያ መጽሐፍቱን ተከትለውም በሚገባ እያስተማሯቸው ይገኛሉ። አሁን ያላቸው ጊዜም ብዙ ለመስራትና ለመደጋገፍ በቂ ነው። በተለይም በየደረጃው የሚወጡትን የሞዴል ፈተናዎችን መስራት ከቻሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አብራርተዋል። በሌላ በኩልም የዘንድሮ ተፈታኞች እንደቀድሞ ሁለት ክፍል አያጠኑም። በዓመት ውስጥ የተማሩትን ብቻ ስለሚፈተኑ ውጤታማ ይሆናሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
የስምንተኛ ክፍል ተፈታኞች ምንም እንኳን መጽሐፍትን ባያገኙም የሚታገዙበት ነገር በየደረጃው እንዲከናወን ተደርጓል የሚሉት ዳይሬክተሩ አንዱ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የመማሪያ መጽሐፍት እንዲገኙና በመደጋገፍ እንዲያጠኑ እድሉ ማመቻቸት ሲሆን ሌላው ደግሞ ትምህርቱ አገር አቀፋዊ በመሆኑ ተመሳሳይነት ያለው ፈተና ይወጣልና እርሱን የተከተለ ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር ነው። በከተሞች አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ ሶፍትኮቢውን ጭምር እንዲያገኙ ተደርጓል። በመስክ ምልከታም የታየው ጥሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ይላሉ።
ለፈተና ተፈታኝ ትምህርት መስጠት ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ ዝግጅትም ማገዝ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ካሳዬ፤ እንደ ክልል ይህ ተግባር በበቂ መልኩ ተከናውኗል። በራሳቸው ሰርተው እንዲያልፉና አቅማቸውን በችግር ውስጥም ሆነ ማሳየት እንዲችሉ ታግዘዋል። ስለሆነም በዚህ ዓመት በስምንተኛ ክፍል ደረጃ 347 ሺ 866 ተማሪዎች ተመዝግበው ፈተናውን ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል። ይህ ማለት በመደበኛው ፕሮግራም 345 ሺህ 66 ተማሪዎች የሚፈተኑ ሲሆን፤ በማታው ፕሮግራም ደግሞ 900 የሚሆኑ ተማሪዎች ለፈተናው ተመዝግበዋል። በግሉ ዘርፍ ደግሞ ወደ 2ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች ምዝገባውን አከናውነዋል።
እንደ ክልል 5ሺ 752 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 95 ቱ በአዲስ መልክ የተቋቋሙና ለመጀመሪያ ጊዜ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን የሚሰጡ ናቸው። ስለዚህም በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ በተለያየ መልኩ መታገዛቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም