ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የወቅቱ ነገሥታት ከተቀበሉት ከ4 ተኛው ምዕተ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሟላ ሁሉን አቀፍ የትምህርት ሥርዓት ዘርግታ መደበኛ ትምህርት መስጠት ጀምራለች፡፡ ይህ ከ1500 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የትምህርት ሥርዓት በዓለማችን ከሚገኙ ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርቶች አንዱ ያደርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሥርዓተ ትምህርት አማካኝነት የራሷን ፊደል፣ ሥርዓተ ጽሕፈት፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ዜማ፣ ወዘተ. ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ ኖራለች፤ አሁንም እያስተላለፈች ትገኛለች፡፡
የአብነት ት/ቤት በተለምዶ ተለዋጭ ስሙ “የቆሎ ት/ቤት” እና “የቤተ ክህነት ት/ቤት” በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች በማእከላዊ መንግሥትም ሆነ በየአካባቢው ገዥዎች የገንዘብ ድጎማም ሆነ ሌሎች ድጋፎች አያገኙም፡፡ እነዚህ አካላትም በሥርዓተ ትምህርቱ ቀረጻም ሆነ በአስተዳደራቸው ውስጥ ጣልቃ ሳይገቡባቸው እራሳቸውን በራሳቸው ሲመሩና ሲያስተዳድሩ የኖሩ ናቸው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ተመሳሳይ ቢሆንም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት የራሱ ነፃ አስተዳደር፣ የራሱ የብቃት (የጥራት) ደረጃ አለው፡፡
በአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ተማሪ በመጀመሪያ ‹‹ሀ፣ሁ፣…›› ብሎ ፊደል ቆጥሮ ዳዊት እስኪደግም ወንጌል፣ መልእክተ ዮሐንስ፣ ግንዘት፣ አረጋኖን፣ መቅድምና ተአምረ ማርያም፣ ተአምረ ኢየሱስ የተባሉትን መጻሕፍት በአስተማሪው ረዳትነት ተነሽና ወዳቂውን ሩቅና ቅርቡን ወንድና ሴቱን ነጠላና ብዙውን ለይቶ ዘርፍና ባለቤቱን አገናኝቶ ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ንባብ ቤት በየቤተክርስቲያኑና በብዙ መንደሮች የተስፋፋ፣ በቀድሞው ጊዜ በየመኳንንቱ ግቢ የሚገኝ በአንድ አስተማሪ የሚካሄድ ትምህርት ነው፡፡ በዘመናዊው የትምህርት አሰጣጥ አንደኛ ደረጃ ጨረሰ እንደ ማለት ነው፡፡
‹‹በ1956 ዓ.ም. 12,913 ቤተክርስቲያኖች፣ እንዲሁም በ1978 ዓ.ም. 885 ገዳማት 1804 አድባራት እና 14,971 የገጠር ቤተክርስቲያኖች በኢትዮጵያ እንደነበሩ ከቤተክህነት መዝገብ ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ቢያንስ አንድ ንባብ ቤት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ይህ አኀዝ የንባብ ቤት ስፋትን ያመላክታል›› በማለት ኃይለ ገብርኤል ዳኜ “ባህልና ትምህርት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው በገጽ 18 ላይ አስፍረውት ይገኛልና ስፋቱ ከፍተኛ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡
ተማሪው ዳዊት ከደገመ በኋላ በመቀጠል በዜማ ትምህርት ‹‹ሰላም ለኪ›› ብሎ የውዳሴ ማርያምን ዜማ ሲጀምር ድምጹ አልገራለት እያለው ሽቅብ ቁልቁል በማለት መምህሩን ከማስቸገሩም በላይ የዜማ ምልክቶቹንና ዓይነቶቹን እንዲሁም ከዜማ ጋር የተያያዙ ትምህርቶችን እስኪለይ፣ እስኪያጠና እና እስኪያስመሰክር ብዙ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል፡፡ በዘመናዊው ትምህርት ሁለተኛ ደረጃ ጨረሰ ማለት ነው፡፡
ከዜማ ትምህርት በኋላ ቀጣዩ የቅኔ ትምህርት ነው፡፡ የቅኔ ትምህርት እንደ ሒሳብ ትምህርት ያንጎል ትምህርት ነው፡፡ ተማሪው በባልንጀሮቹ የቅርብ ረዳትነት እየተመራ አንዳንድ ግስና ነባር ማጥናት ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም ጉባኤ-ቃና የተባለውን የቅኔ ትምህርት መግቢያ እያጋጠመ ወደ መሪጌታው ፊት ቀርቦ መናገር ይሞክራል፡፡ መሪጌታውም ጉባኤ-ቃናውን እያረመና እያስተካከለ ይረዳዋል፡፡ ከዚህም አያይዞ ቀስ በቀስ ከጉባኤ-ቃና እስከ መወድስ እያሰበ ቆጥሮ ለመናገር፤ የቅኔን ሞያ ከነአገባቡ አጠናቆ ለማወቅ ይችላል፡፡ አንዳንድ ክብረ በዓል በሆነበት ቀን በየቤተ ክርስቲያኑ እየሄደ ብዙ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ‹‹ይበል›› እያሰኘ ዋዜማ፣ ሥላሴና ዕጣነ ሞገር የተባሉትን ሰምና ወርቅ ቅኔዎች ይቀኛል፡፡
የቅኔውን ሞያ ከነአገባቡ በደንብ ካወቀ በኋላ ተመልሶ ድጓ የተባለውን የዜማ ትምህርት ይቀጥላል፡፡ ድጓውን ሲጨርስ አቋቋም የተባለውን የዜማ ዓይነት ይጀምራል፤ ወይም ወደ መጽሐፍ ትርጓሜ ትምህርት ቤት ይዛወራል፡፡ በዘመናዊው ትምህርት ኮሌጅ እንደመጨረስ ማየት ይቻላል፡፡
ተማሪው የቅኔ ትምህርትን ካጠናቀቀ በኋላ ሐዲስ፣ ብሉይ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትና መጻሕፍተ መነኮሳት ለማጥናት በመጻሕፍት ትምህርት ቤት ይገባል፡፡ የመጽሐፍ ትርጓሜ፣ አንድምታና ሐተታ እንዲሁም ብሉያትን ከሐዲሳት፤ ሐዲሳትን ከሊቃውንት ጋር ማገናዘብ፣ የተዛባውን ንባብ ማቃናትና ማስተካከል በትምህርት ቤቱ ይሰጣል፡፡ በዘመናዊው ትምህርት ደረጃ ዩኒቨርሲቲ እንደማለት ነው፡፡ ከዘመናዊ ትምህርት አሰጣጥ ጋር እያነጻጸሩ የመከፋፈል ሁኔታ በአብነት ት/ቤት አልፈው ዘመናዊውን የተማሩ እንደ መምህር ኪዳነማሪያም ጌታሁን ያሉ አብዛኞቹ የሚስማሙበት ነው (መምህር ኪዳነማሪያም ጌታሁን፣ “ጥንታዊው የቆሎ ተማሪ”፣ ጥር 5 ቀን 1954 ዓ.ም. ይመልከቱ)
በቤተ ክህነት የሚሰጡ ትምህርቶች ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጹ ራሳቸውን በቻሉ የትምህርት (የጉባኤ ቤቶች) በተከፋፈሉና ሥርዓትን በተከተለ መንገድ ንባብ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና ትርጓሜ መጻሕፍት በመባል ይጠራሉ፡፡ ከመጽሐፍ ትርጓሜ ቀጥሎ አቡ-ሻክር (ባሕረ ሐሳብ) እና አክሲማሮስ የተባሉትን የቁጥርና የሥነ ፍጥረት ትምህርት አንዳንድ ሊቃውንት ይማራሉ፡፡
የአብነት ት/ቤት ተማሪ ዕውቀት በቃልና በመጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መጻሕፍት እንደ አሁኑ በሕትመት ስላልተባዙና እንደልብ ስለማይገኙ እንዲሁም ‹‹በክፉ ዘመን ጠላት ያጠፋቸዋል በሚል ከሰላሳ እስከ አርባ በመቶ የሚሆነው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በቃል የሚጠና ነው›› የሚሉ አሉ፡፡ በሥራ ላይ የሚውለውም በቃል ተይዞ ነው፡፡
የአብነት ት/ቤቶች ለቤተ ክርስቲያን ታላላቅ መምህራንና ሊቃውንትን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም መኩሪያ የነበሩ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን እና ሀዲስ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎችን አፍርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከመኳንንቱ፣ ከመሳፍንቱ እና ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ በጽሑፍ ሥራ በማገልገል ይሰማሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት አማካኝነት ዘመናዊ ትምህርት በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት መከፈት ጀምሮ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ ት/ቤቶች ሲከፈቱ አስተማሪዎች ከውጭ እየመጡ አስተምረዋል፡፡ በእነዚህ ት/ቤቶች ከጊዜ በኋላም ቢሆን ተደልድለው አማርኛ፣ ግዕዝ እና ግብረ ገብ እንዲያስተምሩ ከአብነት ት/ቤት የተወሰዱ ምሁራን ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብላታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ የመሳሰሉ በቋንቋ፣ በቴያትር እና በጽሑፍ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “Ernest Work on Ethiopia Education” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1975 በታተመው በኢትዮጵያ የትምህርት መጽሔት ላይ እንደገለጹት በ1921 ዓ.ም. ኤርነስት ዎርክ በተባለ አፍሮ አሜሪካዊ አመራር በዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት መምህራንን ለዝቅተኛ ክፍሎች ማሰልጠን ተጀምሮ በ1922 ዓ.ም. 12 መምህራን አስመርቋል፡፡ የኤርነስት ዎርክ ዓላማው ኢትዮጵያ ከውጭ ጥገኛ ሳትሆን የራስዋን የትምህርት ሥርዓት እንድትዘረጋ ለማስቻል ነበር፡፡ ምኞቱን ሲገልጹም የትምህርት ሥርዓቱ እንግሊዛዊ ወይም ፈረንሳዊ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ እንዲሆን እንደነበር በመግለጽ ጽሑፍ አስፍረው ይገኛል፡፡ ይህ ዓላማና ምኞቱ ተግባራዊ ሆኖ ቢቀጥል ከአብነት ት/ቤት የሚወሰደው ሥርዓተ ትምህርት ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡
ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ከአብነት ት/ቤት የትምህርት ሥርዓት ምን የወሰዳቸው ነገሮች አሉ? ሊጠቅሙ የሚችሉ ያልወሰዳቸው ምንድን በጎ ነገሮች ነበሩ? ባለመውሰዱ የተከሰቱ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሣት ምሁራን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ አቅርበናል፡፡
መምህር ደሴ ቀለብ በአብነት ት/ቤት እስከ ትርጓሜ መጽሐፍ ድረስ ተምረዋል፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነልሳንና ፊኖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ ‹‹ዘመናዊው ትምህርት በኢትዮጵያ በዳግማዊ ምንሊክ ት/ቤት ሲጀመር የአብነት ትምህርት ይሁን ሌሎች ሀገር በቀል የትምህርት ሥርዓቶችና ዕውቀቶች ተፋተው ነው የተጀመረው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋምም ሀገር በቀል የትምህርት ሥርዓትና ዕውቀቶች አልተካተቱም፡፡ አስተማሪዎቹ የውጭ ሀገር መምህራን ስለነበሩ በውጭ ሀገር ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተቀረጸና በዛው የቀጠለ ነበር፡፡ ንጉሡ ግን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ሲጀመር ትምህርቱ የሀገር በቀል ዕውቀት ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን በንግግር ደረጃ ገልጸው ነበር፤ በተግባር ግን አልተፈጸመም፡፡ የአብነት ትምህርቱ በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ ቢካተት ለኢትዮጵያውያን ብዙ ሊጠቅም የሚችል ሥርዓተ ትምህርትና ቀመር ያለው በመሆኑ ሊያደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ ሳያበረክት ቀርቷል፡፡ አንዳንድ በአብነት ት/ቤት የተማሩ በሥነ ምግባርና በአማርኛ ስዋስው አስተማሪነት ከመግባት ውጭ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት በሥርዓትና በወግ የቀጠለበት ሁኔታ የለም፡፡ በቅድሚያ የአብነት ትምህርት የተማሩ ሰዎች ዘመናዊው ቀሏቸው ተምረው ፕሮፌሰር ደረጃ የደረሱ አሉ፡፡
በአብነት ት/ቤት እንደሚሰጠው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሥርዓትና ምልክቶች እንዲሁም የቅኔ ትምህርት ሂስና አንድምታ አሰጣጥ በዘመናዊው ትምህርት ውስጥ ማካተት ይጠቅማል፡፡ ዜማና ቅኔ ብቻ ሳይሆን ታሪክና ፍልስፍናው በውስጡ አለ፡፡ ለምሳሌ የቅኔ ተማሪ ይማራል፣ ይዘርፋል፣ ይነግራል፣ ይቆጥራል፤ ዓርብ ዓርብ ደግሞ የማህበር ቅኔ የሚባል አለ፡፡ ዓርብ ዕለት ባለ ተራ ይሰጠውና አንዱ ተማሪ ሲያቀርብ ሌላው ተማሪ ይህን እንዲህ ብታደርግ፣ ይሄኛው እንዲህ ቢሆን እያለ ያስተካክላል፤ የሚሞገስም ከሆነ ‹ይበል› ብሎ ያደነቀበትን ምክንያት ጭምር በማቅረብ ሂስ ይሰጣል፡፡ አድማጭ ከሆኑት ተማሪዎች ውስጥ በመጨረሻ ‹ለምን ይህን ሂስ ሳትሰጥ አለፍከው፤ ይህኛውን የነቀፍክበትና ያኛውን ያሞገስክበት ሂደት ይበል የሚያስብል ነው› በማለት አስተያየታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይህን ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች እንዲበረቱ፣ እንዲፈጥሩና እንዲፈላሰፉ ያደርጋል፡፡
በግዕዝ ቋንቋ ብዙ የፍልስፍና፣ የህክምና፣ የስነ ልቦና፣ የታሪክ፣ የማህበራዊ፣ ወዘተ. ዕውቀቶች የያዙ መጽሐፎች የተጻፉበት ነው፡፡ የግዕዝ ቋንቋን ባለማወቅ፣ በግዕዝ የተጻፉ ሀይማኖታዊ ናቸው በሚል ብዙ የጥበብ መጽሐፎች እንደማይጠቅም ተጥለዋል፤ ከዕውቀት ማህደር ተገለዋል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግዕዝ ቋንቋ መሰጠት ነበረበት፡፡
ዘመናዊው ትምህርት ሲጀመር የአብነት ት/ቤትን ሥርዓተ ትምህርት ‘የደብተራ ትምህርት’ በማለት አግልሏል፡፡ ፊደል ይቀነስ ከማለት ጀምሮ የላቲን ፊደል እንጠቀም እስከማለት ተደርሶ ነበር፡፡ ዘመናዊውን ትምህርት ብቻ የተማሩት ከሀገር በቀል ዕውቀት ባዶ ሆኑ፤ የውጭ አምላኪ ሆኑ፤ ተቀባይ ብቻ ሆኑ፡፡ ‹አቀባይ ነኝ› የሚል የውስጥ ሥነ ልቦና እና ልበ ሙሉነት ጠፋ፤ ‹ምንም ነገር የለንም› የሚል መጣ፡፡ በመቀጠል የማርክሲዝም ሌኒንዝም ርዕዮተ ዓለምን ሀገር በቀል የሆነ ዕውቀት ስለሌላቸው እንዳለ ‹ሆ› ብለው ተቀብለውት ሀገር ውስጥ ዘረገፉት፡፡ ማንነት ሳይኖረው ይህን ይቀበላል፣ ያንን ይቀበላል፤ በመሆኑም መልኩ (ማንነቱ) ይሄ ነው ለማለት የማይቻል ሆኗል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት አድርጎ ስላልተቀረጸ በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ማንነቱ ወዲህና ወዲያ የሚል በቀላሉ የሚወድቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በአብነት ት/ቤት የንባብ ትምህርቱ ለማንበብ ማራኪ በሆነ መልኩ ስለሚቀርብ ዘላቂ የንባብ ባህል እንዲኖር የሚያደርግ ነው፤ ሥርዓተ ትምህርቱ ሲቀረጽ ከመቶ ሃምሳ ወይም ሰባ አምስት አምጥቶ የሚታለፍ ሳይሆን ከመቶ መቶ አምጥቶ የሚታለፍበት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የአብነት ትምህርት የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ያለው መሆኑ ታውቆ በፍኖተ ካርታው እውቅና እና ትኩረት ተሰጥቶት በጥናት ታግዞ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንዲካተት ቢደረግ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው›› በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ታደለ ገድሌ በጥንት ጽሑፍ ጥናት የፒኤች ዲግሪ አግኝተዋል፤ በአብነት ትምህርት እስከ ዜማ፣ ቅኔ እና አቋቋም ተምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እንደሳቸው አስተያየት ‹‹ዘመናዊው ትምህርት በኢትዮጵያ ሲጀመር ‹የውጭ ሀገር ሥርዓትና ባህልን መሠረት አድርጎ የተጫነ ስለሆነ በሀገራችን የአብነት ትምህርት መቃኘት አለበት› በሚል ኢትዮጵያዊ ምሁራን ብዙ ክርክር አድርገው ነበር፡፡ ከሀገር በቀል ዕውቀት ቢነሣ ኖሮ ትውልዱ ከሚያውቀው ነገር ላይ ተነስቶ ሌላውን ስለሚያካትት የተሻለ ዕውቀት ባለቤት ይሆን ነበር፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርስ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከዜማ ጋር የሚደረገው የንባብ ስልት ለሽምደዳ የአጠናን ዘዴ የሚሰጠው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡ በግዕዝ የተጻፉ መጽሐፎች ውስጥ ፍልስፍና፣ ቅኔ፣ መድኃኒት ቅመማ፣ ዘመን አቆጣጠር፣ ሥነ ምግባር፣ ባህል፣ ሙዚቃ፣ ታሪክ፣ ወዘተ. አሉባቸው፡፡ በየዓይነቱ ሲከፋፈል ከ250 በላይ ጽሑፎች ተጽፈውበታል፡፡ የግዕዝ ቋንቋ በዘመናዊው ትምህርት ባለመካተቱ ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ የዕውቀት ክምችት ምን ያህል እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ በጥንታዊ ስልጣኔ ያላት ቦታ ምን እንደሆነ እና ፊደል ስርዓት ባለው ሁኔታ እንደሚጻፍ ሳያውቅ ቀረ፡፡
ዘመናዊው ትምህርት ሲጀመር ሀገር በቀሉን ዕውቀት ገሸሽ በማድረግና በመናቅ ስለተጀመረ ተማሪዎቹ ሀገራቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ማንነታቸውን፣ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ባለቤት መሆናቸውን እንዳያውቁ ተደርገው አይናቸውን ወደ ውጭ እንዲያማትሩና ሀገራቸው ምንም ነገር የሌላት ባዶ እንደሆነች እንዲመለከቱ ሆነዋል፡፡ በመቀጠል በሀገሪቱ ውስጥ የእምነት መሠረት እንዳይኖር በማድረግ ግብረ ገብነትና መከባበር እንዲሸረሸር ሆኗል፡፡ የሶሻሊዝም አስተሳሰብን እንደእምነት በመቀበል ብዙ ጥፋት ጠፍቷል፡፡ ግብረገብና መከባበሩ ስለቀነሰ አሁን ላይ እየተከሰቱ ለሚገኙት ችግሮች መነሻ ምክንያት ሆኗል፡፡
አዲስ የሚሠራው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሀገር በቀል ዕውቀት የሆኑትን የልጅ አስተዳደግ ሥርዓት፣ የእርቅ ሥርዓት፣ የመረጃ ሥርዓት፣ የደን አጠባበቅ ሥርዓት፣ ወዘተ. የሚያካትት ከሆነ ልታመልጥ የነበረች ነፍስ ወደ ራስ የመመለስ ያህል ሊቆጠር ይችላል፡፡ በግዕዝ ቋንቋ ኢትዮጵያዊ የሆኑ እውቀቶች የተጻፉበት ስለሆነ አውቀው እንዲመረምሩት ግዕዝ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ እንዲሰጥ ቢደረግና ግዕዝ ተናጋሪ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ሀገር በቀል በሆነው ዕውቀት ተኮትኩተው ዘመናዊውን ትምህርት ተምረው የነበሩ ተማሪዎች ሁለቱን በማዋሃድ ‹ለሀገር የሚጠቅም ምን አለው?› በማለት ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎች ሰርተዋል›› በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ ፋንታሁን ዋቄ በግብርና ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋማት ልማት አግኝተዋል፤በማኅበረ ቁዱሳን የተቋማት ልማት ዘርፍ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹ዘመናዊው ትምህርት ሲጀመር አዘምነን ሳይሆን ቀድተን በመጀመራችን የተቀዳበትን ሀገር ባህልና ማንነት እያስያዘ ሄዷል፡፡ በአብነት ት/ቤት ‹አ› ብሎ ‹አልፋ› በማለት ከመንፈሳዊ ነገር ጋር ያያይዘዋል፡፡ በዘመናዊው ‹A› ብሎ ‹Apple› በማለት ከቁስ ጋር ያገናኘዋል፤ በመሆኑም ከቁስ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ብዛት ያላቸው የሀገር በቀል ዕውቀቶች በግዕዝ ቋንቋ ሲተላለፉ ቆይተዋል፡፡ ሕዝቡ ግዕዝ እንዳይነጋገር ሲሸማቀቅና መነጋገሩን ሲያቆም በቃል ሲተላለፉ የነበሩ ዕውቀቶች ተገቱ፡፡ በሀገራዊ ሀብት፣ ፍልስፍና እና አቅም ላይ መሠረት አድርጎ ሊለማና ሊዘምን ይችል የነበረ ዕውቀት ተወገደ፤ በተውሶ ላይ እራሱን በማሳረፍ በልምድ ልውውጥና በልመና የሚመጣ ዕውቀት ላይ መንጠልጠል አምጥቷል፡፡ ግዕዝ ከሕዝብ ንግግርና ከትምህርት ስርዓት ባይወጣ የማርክስዝም ፍልስፍና ብርቅ አይሆንብንም ነበር፡፡ የዘመናዊ ትምህርቱን ሥርዓተ ትምህርት ስናይ አሁን ባለው ፍኖተ ካርታ እንኳን በተውሶ የሚካሄድ እንቅስቃሴ ነው የሚታየው፡፡ በተውሶ የተከተለና አሽከር የሆነ እንጂ ያደገ ሀገር የለም፤ያደገ ቢመስልም በትንሽ ነገር ይፈርሳል፡፡
የትምህርት ፍኖተ ካርታው በሚቀጥሉት 10 እና 15 ዓመታት የኢትዮጵያ ትምህርት ወዴት እንደሚሄድ ማዕቀፉን ነው የሚያሳየው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እውቅና ሰጥቶ በሚቀጥሉት 3 እና 5 ዓመታት ውስጥ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን መመርመሪያ ቋንቋዎችን አጥንቼ ለይቼ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል የሚል ግብ ቢቀመጥ፤ በመቀጠል ሀገር በቀል ዕውቀቶች በየትምህርት ክፍሉ መጽሐፍ የሚዘጋጅበትንና ትምህርት የሚሰጥበትን ጊዜ ቢያስቀምጥ፤ ኢትዮጵያዊነት የሚመለስበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህን ለማድረግ ከሀይማኖት ተቋማትና ሀገር በቀል ዕውቀቱ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ዕውቀቱ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማስመሰል ያህል ሳይሆን ከምር ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሳተፉ እና የሚተገበረውን በየጊዜው እንዲተቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አሁንም ከውጭ ሀገራት እና ዩኔስኮ ተጽዕኖ ውጭ መሆን ካልተቻለ ተከታይ ነው የሚኮነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በስልት ከማኅበረሰቡ ሕይወት እንድትወጣ በመደረጓ ድንጋጤ ውስጥ ነው ያለችው፤ ትርጉም ባለው መልኩ በትምህርት ስርዓት ውስጥ መሳተፍ እንዳለባት እድሉ ያላት ስላልመሰላት በመሸማቀቅ ላይ ነች፡፡ ከድንጋጤና ከመሸማቀቅ ወጥታ በአዳራሽ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ብቻ ሳይሆን ትርጉም ባለው ሁኔታ መሳተፍ እንድትችል መጋበዝና መፈቀድ አለበት፡፡ መንግስት እንዲጋብዝና እንዲፈቅድ ደግሞ ነገሩ የገባን ሰዎች መንግስትንና የሀይማኖት አባቶችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በሬድዮ፣ በቴሌቭዥንና በጽሑፍ ማሳሰብና ማሳወቅ አለብን፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀት ያለበትን ቦታ እና መንግስትን ማቀራረብ አለብን፡፡ አሁን በግል ተነሳሽነት ሁለቱን ለማቀራረብ እየተጀመረ ያለ ነገር አለ፤ተቋማዊ እንዲሆን መንግስትም ተነሳሽና ቁርጠኛ ቢሆን ኢትዮጵያ በጊዜ ሂደት በሀገር በቀል ዕውቀት እራሷን የምታሳድግበትና የምትቀድምበት ሁኔታ ይፈጠራል›› በማለት ገልጸዋል፡፡
አቶ ይድነቃቸው ስሜ እና አቶ በለው ብዙነህ የሀገረሰብ ወኩምስ አማካሪዎች ድርጅት ውስጥ በአማካሪነት የሚሰሩ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው በትምህርት፣በማህበራዊ፣በኢኮኖሚ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ያማክራል፡፡ እንደ ድርጅታቸው አቋም ሀሳባቸውን ሲገልጹ ‹‹በሀገር ደረጃ የተፈጠሩ ችግሮች የዘመናዊው ትምህርት ስርዓት ያመጣው ችግር ውጤት በመሆኑ በፍኖተ ካርታው በዋናነት መካተት የሚገባቸው የተዛባ የትምህርት ስርዓት ኢትዮጵያዊ በሆነ ሀገር በቀል የትምህርት ዘይቤ መተካት፣የመማር ማስተማሪያ ቋንቋ በደንብ ተጠንቶ ኢትዮጵያዊ የሆነ የማሰቢያ ቋንቋ ማዘጋጀት፣በሀገሪቱ እውነት ላይ የተመሰረተ ከላይ ከላይ ሳይሆን ከስር የጀመረ የዕውቀት መንገድ ማስተካከልና ግለሰባዊና ማኅበራዊ እሴቶችን እንዲሁም ሀገራዊ ማንነትን መመለስ አለበት፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት የመገልበጥ፣ የመሸምደድ እና ፈተና የማለፍ ላይ ብቻ ሳያተኩር በህይወት ውስጥ በቀጣይነት አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል መልኩ ሊቀረጽ ይገባል፡፡
የዕውቀት ምንጩን ሀገራዊ ካላደረግን መሰረታዊ ችግሮች ሳይፈቱ ጥገናዊ ለውጥ ሆኖ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው የሚሆነው፤መጠጋገን ደግሞ ወደ ከፋ ችግር ውስጥ ይዞ ይሄዳል፡፡ ጥልቀት ያለው ሀገራዊ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በስብሰባና በወርክሾፕ ብቻ ሳይሆን ትርጉም ባለው መልኩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ መሆን አለበት፡፡ የፈረንጆቹን መሰረት አድርጎ ሳይሆን እንደግብአት መውሰድ ይቻላል፡፡ ፍኖተ ካርታውን ለሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል በ2003 ዓ.ም. በድርጅታችን ኃላፊ አቶ ገነነ ቡዙነህ የታተመውን “ሀገረሰብ ትምህርት በኢትዮጵያ” እና በ2010 ዓ.ም. የታተመውን “ለኢትዮጵያ ምን አይነት የትምህርት ሥርዓት እና የአገር ምሪት እውቀት?” የሚሉትን መጽሐፎች ሰጥተናል፤በፍኖተ ካርታ ቀረጻው ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ አቅርበን ስራው እየተካሄደ ቢሆንም እስካሁን ጥሪ አልቀረበልንም፡፡ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሀሳባችንን ለጠቅላይ ሚንስትሩ በዲ ኤች ኤል እንዲሁም ለትምህርት ሚኒስትሩና ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አቅርበናል›› ብለዋል፡፡
ዶክተር ስርግው ገላው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የፊኖሎጂ ማዕከል ኃላፊ ከመሆናቸው በተጨማሪ በግዕዝ ቋንቋና ስነጽሑፍ በመምህርነትና በተመራማሪነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአብነት ት/ቤት እስከ ቅኔ፣ዜማን እስከድጓ ተምረው መርጌታ እስከሚያደርሰው ደረጃ ተምረዋል፡፡ የሳቸውን አስተያየት ሲያቀርቡ ‹‹የዘመናዊው ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ከአብነት ትምህርት ቤት በመውሰድ ሊያካትት ይገባው የነበረው የግዕዝን ቋንቋ ማስተማር አንዱ ነበር፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ የሆነው ታሪክ፣ባህል፣ፍልስፍና፣ወዘተ. ተጽፎ የሚገኘው በግዕዝ ስለሆነ ለማወቅና ለመመርመር ግዕዝ ቋንቋ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የሆነውን የቅኔ፣ የዜማ፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና ወዘተ. ዕውቀት መሰረት በማድረግ በጥናት ላይ በመመስረት አዋህዶ ማዘመን ይገባ ነበር፡፡ ሌላው ጠቃሚ የሆነን ሥርዓተ ትምህርትንም መውሰድ ያስፈልጋል፤መምህራኑ በመኖር(በየዕለት አኗኗራቸው) ነው የሚያስተምሩት፡፡ መምህራኑ የሚያስተምሩትን ተማሪ ብቁ አድርገው ነው የሚያወጡት፤ወደ ሚቀጥለው ትምህርት ለመሸጋገር መለስተኛ ወይም መካከለኛ ተማሪ መሆን አይበቃም፤የፈጀውን ዓመት ይፍጅ ጥርት አድርጎ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ዓይነት ሥርዓተ ትምህርት ማካተት ይገባ ነበር፡፡ ምዕራባውያን ሊያድጉ የቻሉት በፊት የነበራቸውን ዕውቀት ይዘው የሚጠቅምና የሚጎዳውን ለይተው ተከራክረው በመውሰድ ነው ያዘመኑት፡፡
ዘመናዊው ትምህርት ኢትዮጵያዊ ከሆነው ዕውቀት ተነስቶ ዘምኖ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ እድገት ይፋጠን ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ በውጭ ቋንቋ፣ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ወዘተ. ትምህርቱ በመሰጠቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠቅም ዕውቀት እንደሌለ የሚረዳና በጥልቀት ማወቅ የሚገባውን ሳይረዳ የማርክስና ሌኒን ፍልስፍና አቀንቃኝ ትውልድ ተፈጥሮ ተደማምጦ መረዳዳት የማይችል ሆኖ እርስ በእርሱ ተላልቋል፡፡ የአሁኑ ደግሞ የሚይዘው የሌለው ውጩን ናፋቂ ሆኗል፡፡ ስለሆነው በኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ውስጥ ‹ሀገር በቀል ዕውቀት ምንም የለውም ወይም ዜሮ ነው› ብሎ መነሳት የለበትም፤እድገት እንዲመጣ ከተፈለገ ዕውቅና ሰጥቶ በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ ከምር እንዲካተት ያስፈልጋል›› በማለት ገልጸዋል፡፡
መምህር ሰለሞን ከበደ በአብነት ት/ቤት ንባብ፣ ዜማ እና ቅዳሴ ተምረው በድቁና አገልግለዋል፤ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በስነ መለኮት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው በኮሌጁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክና የስነ መለኮት ትምህርት በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መንግስትና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ቁርኝት ስለነበራቸው አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊ ታሪኮችና ዕውቀቶች የተዘገቡትና ተጠብቀው የተቀመጡት በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ዘመናዊው ትምህርቱ ሲጀመር ኢትዮጵያዊ መሰረት፣ለዛና ቃና የሌለው ትምህርት በመሰጠቱ እና ከሀገራዊ እውቀት ጋር ባለመተሳሰሩ አሁን የምናየው የስነምግባር መላሸቅ እንዲሁም በውጭ ነገር እራስን ማስደገፍ ተፈጠረ፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች አጀማመራቸው በገዳማውያን አድርገው የነበራቸውን ሳይጥሉ ባላቸው ላይ እየገነቡ ነው ያሳደጉት፡፡
የቅድስ ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጁን የትምህርት አሰጣጥ ስናየው ሀገራዊ የሆነውን ኢትዮጵያዊ የአብነት ትምህርትን ዘመናዊ በሆነ አቀራረብ በማስተማር ተጀምሮ የሀገራችንን ጥንታዊ አስተሳሰቦችና ትምህርትን ከውጭው አስተሳሰብና ትምህርት ጋር አስተሳስሮ ተማሪዎቹ ሁለቱንም እንዲያውቁ በሚያስችላቸው ሁኔታ ተዘጋጅቶ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ በጥናትና ምርምር በመታገዝ በዲፕሎማ ደረጃ ይሰጥ የነበረው ትምህርት በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ መሰጠት ተችሏል፤ወደ ዩኒቨርሲቲ በማሳደግ በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርቱን ለመስጠት ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡ የትምህርት ስርዓቱ የአብነት ት/ቤትን መሰረት አድርጎ የተገነባ ስለሆነ የግዕዝ ቋንቋ፣ የዜማ፣ የቅዳሴ፣ የትርጓሜ መጽሐፍ ወዘተ. ትምህርቶች ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው በትምህርቱ ተካተዋል፤ በዲፕሎማ ደረጃም ግዕዝ ቋንቋ ይሰጣል፡፡
የሀገራችን መጻኢ ዕድል በእጃችን ላይ ይገኛል፤በተለይ ሥርዓተ ትምህርትን በተመለከተ ለማስመሰል ያህል ሳይሆን ቆም ብለን ልባችንን አስፍተን ልንነጋገር፣ልንወያይ፣ልንተች እና ጠቃሚ የሆነውን አጥርተን ልናወጣ ይገባል፡፡ ፍራቻ ሊኖር አይገባም፤ ለምሳሌ ግዕዝ ቋንቋ የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ታሪክ እና ጥበቦች የተጻፉበት በመሆኑ ከሀይማኖት ጋር ሳያያይዙ ቋንቋውን ማወቅና መጽሐፎቹን መመርመር ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የግዕዝ ቋንቋ በሥርዓተ ትምህርቱ መካተት ይገባዋል፡፡ ሀገር በቀል የሆኑ ዕውቀቶች ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑ ታውቆ በጥናትና ምርምር ታይተው ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ የሚካተቱበት አሰራር በፍኖተ ካርታው በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል›› ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ውስጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ጥሩሰው ተፈራ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ምክረ ሀሳብ በሚያዘጋጀው የስድስት መሪ ሀሳቦች አስተባባሪና በአጸደ ህጻናትና በአንደኛ ደረጃ በኩል ለሚያጠናው ቡድን መሪ ናቸው፡፡ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‹‹ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር ከአብነት ትምህርትም ሆነ ከሀገር በቀል ዕውቀት ያካተተው ነገር ባይኖርም የአብነት ት/ቤቶች ቅድመ መደበኛ ትምህርት በመስጠት ለዘመናዊ ትምህርቱ መጋቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች መጋቢ በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ዘመናዊው ትምህርት ከአብነቱ ሥርዓተ ትምህርት ሊወስድ የሚገባው ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ፊደል እንዲለዩና ስሌት እንዲያሰሉ ማድረጉ፣ የአቻ ለአቻ የማስተማር ዘዴን መከተሉ፣ እያንዳንዱ ተማሪ እንደአቀባበል አቅሙ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሄድ ሊፈጥንና ሊዘገይ የሚችልበትን አሰራር (አሁን እንደ አዲስ በዘመናዊ ትምህርት ተለማጭ ተብሎ እየተጠቀሰ ያለው)፣ አካል ጉዳተኞችን ለይስሙላ ሳይሆን እስከ ከፍተኛው የዕውቀት ደረጃ የሚያሳትፍ መሆኑ(እንደ አዲስ በዘመናዊው ትምህርት የአካቶ ትምህርት ተብሎ በዩኔስኮ እ.ኤ.አ.1994 ተካቷል)፣ በተማሪዎች ተተችቶ በአስተማሪው ወሳኝነት ብቻ በሚደረግ ግምገማ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ እንዲተላለፍ መደረጉ (በዘመናዊው እንደሚታየው በተለያየ ምክንያት እንዲያልፉ አድርጉ ሳይባል)፣ የመምህራኑ ጽናትና ቁርጠኝነት ውስጣዊ መሆኑ እንዲሁም ለተማሪዎቻቸው በተግባር ውስጣዊ ጽናቱንና ቁርጠኝነቱን ለማስተላለፍ የሚያደርጉት ሂደት፣ ማንኛውንም ተማሪ ትምህርቱን ለመከታተል ወጪ እንዲያወጣ የማይጠይቀው መሆኑ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጠቅላላው ከስነ ዘዴው፣ የተማሪው የግምገማ ስርዓት፣ ከመማር ማስተማር ሁኔታ ብዙ ነገሮች መቅሰም የሚቻል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት ከዘመናዊው በተሻለ በቀላሉ በአጭር ጊዜ ማንበብና መጻፍ የሚያስችል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ስርዓት ባለው አካሄድ መጻፍና ማንበብ የማይችሉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ የስነ ምግባሩ ትምህርት ተማሪዎችን መሰረት የሚያሲዝ እርስ በእርስ እንዲደጋገፍና እንዲተጋገዝ የሚያደርግ፤ ታላላቆቹንና ቤተሰቦቹን እንዲያከብር በማድረግ አጠቃላይ ሰብእና የሚገነባበት ነው፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸውን የእምነት ልዩነት ቢኖራቸውም ‹መጻፍና ማንበብ በአጭር ጊዜ ይችላሉ፤ እንዲሁም ስነ ምግባራቸው በጥሩ ሁኔታ ይታነጻል› በሚል እምነት በማሳደር አሁንም ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲማሩ አብነት ት/ቤት ይልካሉ፤ድጋፍም ያደርጋሉ፡፡
በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በህግ፣ ወዘተ. የሚገኙ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በትምህርት ፍኖተ ካርታው እንዲካተቱ ምክረ ሀሳብ አቅርበናል፤ ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ለመንግስት ይቀርባል፡፡ ተግባራዊ ይሁን ሲባል ከታችኛው ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ ሊመጥን በሚችል መልኩ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ሊተገበር ይገባል፡፡ የሚነበበው ትርክት፣ ጨዋታው፣ የመጫወቻ ቁሳቁሱ፣ ወዘተ. በበቂ ሁኔታ በሰለጠኑ መምህራን ሀገር በቀል ዕውቀትን ያካተተ መሆን ይገባዋል፤በቅድመ መደበኛ ትምህርት ሳይጀመር በአንደኛ ደረጃ መጀመሩ ውጤታማ አያደርግም፡፡ አሀዳዊ የትምህርት ስርዓት እንዲቀር ሀሳብ አቅርበናል፡፡ እንደ እኔ እምነት ሀገር በቀል እውቀትን ወደ ትምህርት ስርዓት ውስጥ ለማስገባት ኢንስቲትዩት በማቋቋም ጥናት፣ ምርምር እና ትንተና አድርጎ የበሰለ የበሰለውን እና የሚጠቅመውን ከዘመናዊው ጋር በማዋሀድ ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ ማስገባት ይገባል፡፡
የትምህርት ስርዓቱን በተለያየ መልኩ ሊይዙና ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከኋላ ሆነው የመምራትና እጅ የመጠምዘዝ ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን ያለው ሀገር በቀል ዕውቀት እንዲጠና፣እንዲመረመርና እንዲተገበር የመፈለግ ሀገራዊ እንቅስቃሴና ፍላጎት በምሁራኑ ዘንድ በመስረጹ ከዚህ በተቃራኒ የሆነን ሀሳብ እሺ ብሎ የሚቀበል አይኖርም፤ከዚህ በተጨማሪ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሁኔታውን ይሁን ብሎ የሚያልፈው አይመስለኝም›› በማለት በፍኖተ ካርታው ያላቸውን ተሳትፎ በሚያሳይ መልኩ ተናግረዋል፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ሲቋቋም ‹‹ይህ ዛሬ መርቀን የምንከፍተው ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ላይ የተመሰረተና ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ያጠራቀመችውን የታሪክና የባህል ቅርስ በረቂቅ በመመራመር ወደ ኋላ መለስ ብሎ በማስተዋል ዘመን አመጣሽ የሆነውን አተኩሮ በመመልከት የወደፊቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ አቅጣጫውንና የሚይዘውን መልክ ለመምራት የሚችልበትን ዕውቀት የሚገበዩበት የትምህርት አደባባይ ነው›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ በተግባር ግን የትምህርት ስርዓቱ ሀገር በቀል የሆነውን ዕውቀት አላካተተም፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ንግግር በኋላ እጓለ ገበረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚል በ1956 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ “በተዋኅዶ ከበረ” በሚለው ሀሳባቸው ገጽ 78 ላይ ‹‹በዘመናችን በየአንዳንዱ ምሁር ፊት የተደቀነው ስራ ይህ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱን ስልጣኔዎች የኢትዮጵያንና የአውሮፓውያን በገዛ መንፈሳችን ድልድይነት ማገናኘት፤በጥረታችን ግለትና ሙቀት እንዲዋሐዱ ለፍሬም እንዲበቁ ማድረግ፡፡ ዋናው ስራ ይህ ነው፡፡ መጀመሪያ የገዛ ራሳችንን ደህና አድርገን ማላመጥ፣መዋጥ፤ቀጥሎም ከውጭ የመጣውን በዚሁ መንገድ አሳልፎ መደባለቅ ማዋሐድ፡፡ ያን ጊዜ ከሁለቱ የሰረጸ በገዛ ወዛችን የተጥለቀለቀ አዲስ የመንፈስ ሕይወት ይታያል›› በማለት ምክረ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ሀሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ ባይሆንም “በተዋህዶ ከበረ” የሚለውን ሀሳባቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች በራሳቸው እሳቤ እስከ አሁን ድረስ እያነሱ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት መንግስትን የሚወተውቱ ምሁራን አፍርተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አቶ ገነነ ብዙነህ አንዱ ናቸው፡፡ “ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት የትምህርት ሥርዓት እና የአገር ምሪት እውቀት?” በሚል ርዕስ በ2010 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው በመቅድሙ ላይ ‹‹ከውጭ በገባ ዕውቀት ላይ የተጣለው የትምህርት ስርዓት መሰረቱ ጥልቀትና ስፋት ሊኖረው አልቻለም፡፡ ዕውቀቱ ጥልቀት ሊኖረው ይችል የነበረው በሀገሪቱ እውነታ ላይ ተጥሎ ቢሆን ነበር፡፡ የትምህርት ስርዓቱ የዕውቀት ምንጭ የበቅባቸዋል፡፡ እስያ ሀገራት ውስጥ አደጉ የሚባሉት ጃፓን፣ ኮሪያ እና ቻይና እዚህ ደረጃ የደረሱት የምዕራባውያንን ዘመናዊ ስልጣኔ ከባህላቸውና ከጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርታቸው ጋር በማዋሃድ ነው፡፡
ስሜነህ ደስታ