ለመስኖ ትኩረት ሰጥተው የሰሩ ሀገራት በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች እስከ መትረፍ ደርሰዋል:: መስኖ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማስቻሉ ባሻገር የበርካታ ሀገራት የኢኮኖሚያቸው መሰረት ሆኗል:: የግብርናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እየሆናቸው ይገኛል፤ የኢንዱስትሪዎቻቸው ግብአት ምንጭ በመሆንም ያገለግላል::
እንደ ኢትዮጵያ በዝናብ ጥገኛ የሆነ ግብርና ያላቸው ሀገራት ደግሞ በምግብ ራሳቸውን ለመቻል ሲቸገሩ ቆይተዋል፤ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ሲፈተኑም ይታያሉ:: መስኖን በአግባቡ የተጠቀሙ ሀገራት በምግብ ራስን ሲችሉ፤ መስኖን በአግባቡ ያልተጠቀሙ ሀገራት ደግሞ ዛሬም በምግብ ራስን ለመቻል ሲቸገሩ መታየታቸው መስኖ በምግብ ራስን ለመቻል ዋና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያመላክታል::
ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሃብት እና ለእርሻ ምቹ ከሆነው ሰፊ የመሬት ሀብቷ አንጻር በምግብ ራሷን አለመቻሏ ትልቅ ተቃርኖ ሆኖ ቆይቷል:: ይህም በሚገባ ያስተዋለው መንግስት በመስኖ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል:: ከአደረጃጀት አንስቶ ለውጥ በማድረግ እየተከናወነ ባለው ተግባር የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት አንዲካሄዱ፣ የበጋ መስኖ ልማት እንዲጀመርና ተጠናክሮ አንዲቀጥል እየተደረገ ነው::
በዛሬው የመሰረተ ልማት አምዳችን በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት በመስኖ ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች እንዲሁም መስኖን ለማስፋፋት እየተደረገ ባለው ጥረት ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የሚያተኩር ይሆናል:: የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ኢትዮጵያ ለመስኖ ትልቅ እምቅ አቅም አላት:: በመስኖ ሊለማ የሚችል እስከ 20 ሚሊየን ሄክታር መሬት ያላት ሀገር ነች:: ይህም ማለት ኢትዮጵያ በመስኖ ልታለማ የምትችለው መሬት ስፋት ከአንዳንድ ሀገራት የቆዳ ስፋት የሚበልጥ ነው::
ይሁን እንጂ እስካሁን በመስኖ እየለማ ያለው መሬት ስፋት ሲታይ ካለው አቅም አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የ2015 በጀት አመት የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙን ከክልሎች አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅርቡ ገምግሟል:: የዘጠኝ ወራት አፈጻጸምን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ እንዳብራሩት፤ የአስር ዓመት እቅድ ሲዘጋጅ እንደ ሀገር በየዓመቱ ሃምሳ ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ወደ መስኖ ልማት እናስገባለን የሚል እቅድ ነበር::
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ግን በየክልሎቹ ከአነስተኛ እስከ ትላልቅ መስኖዎች ወደ አንድ ሺህ 80 ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ወደ መስጠት ተሸጋግረዋል:: በዚህም 251 ሺህ 550 ሄክታር አዲስ መሬት ወደ መስኖ ልማት ገብቷል:: በመሆኑም የተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተካሄደ ይገኛል:: ይህም በአንድ ዓመት ለማሳካት ከታቀደው ከአምስት እጥፍ በላይ ማሳካት መቻሉን አመላካች ነው ብለዋል::
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እና አዳዲስ መሬቶችን ወደ መስኖ ልማት ማስገባት ብቻም ሳይሆን ከዚህ ቀደም ተገንብተው አገልግሎት የማይሰጡ፤ በጎርፍ፣ በደለል፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ሲሰጡ ያልነበሩ ትልልቆቹን የመስኖ አውታሮችን ጨምሮ 744 የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል:: ክልሎች፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት አቅም መረባረብ በመቻሉ ፕሮጀክቶቹ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መደረጉን ያብራሩት ኢንጂነር አይሻ፤ በዚህም በአጠቃላይ 43 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት የመስኖ አውታሮችን በመጠገን ማልማት ተችሏል ብለዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ ካለፈው ክረምት ጀምሮ በርካታ የፓምፕ ስርጭት የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ከ54ሺህ በላይ ፓምፖች እንደ ሀገር ተሰራጭተዋል:: የፌዴራል መንግሥት፣ የተለያዩ የልማት አጋሮች፣ ክልሎች በራሳቸው ለህብረተሰቡ ፓምፖችን እያቀረቡ ይገኛሉ:: በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም ፓምፖችን ገዝቶ ለማቅረብ ጥረት የተደረገ ሲሆን፤ በእነዚህ ፓምፖችም 280 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ማሳ ማልማት ተችሏል::
ፓምፖቹን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ክፍፍል እንዲደረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርግ ነበር ያሉት ኢንጂነር አይሻ፤ ከፓምፕ ስርጭት ባሻገር በውሃ አጠቃቀም ላይም ኢ ፍትሃዊነት እንዳይኖር ክትትል ተደርጓል ነው ያሉት:: ምክንያቱም ከላይ ያሉት ብቻ ውሃውን የሚጠቀሙ ከሆነ ከታች ያሉት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል:: በተለይም ክልሎች ለውሃ ስርጭት ትኩረት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው፣ ይህንንም እውን ለማድረግ በየቦታው የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር እንዲደራጅ መደረጉን አመልክተዋል:: ‹‹የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር በየክልሉ እንዲሁም በየውሃ አውታሮች በየሰፈሩ እንዲኖር በመደረጉ የውሃ አጠቃቀሙ ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል::
የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር እንዲኖር መደረጉ የውሃ ስርጭት ኢ- ፍትሃዊ እንዳይሆን ከማስቻሉ ባሻገር ውሃው ባለቤት እንዲኖረው አስችሏል:: በውሃ ስርጭት ኢ- ፍትሃዊነት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችንም አስቀድሞ መከላከል መቻሉንም ነው ሚኒስትሯ ያብራሩት::
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የመስኖ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የቴክኒክ ድጋፎች አስፈላጊ ናቸው:: የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በዓመት ሁለት ጊዜ ለክልሎች ቴክኒካል ድጋፍ እያደረገ ይገኛል:: ክልሎቹ የሚያቀርቧቸው እቅዶችም ምን ያህል አዋጭ እንደሆኑ በመገምገም ለገንዘብ ሚኒስቴር እየላከ ነው:: በዚያው መሰረት ገንዘብ እየተለቀቀላቸው ነው::
ምንም እንኳ ችግሮች ቢኖሩም፣ የፌዴራል መንግሥት እና ክልሎች ለመስኖ ሥራ ትኩረት ሰጥተው እየተረባረቡ ናቸው ያሉት ኢንጂነር አይሻ፣ አሁን የሚታየው እንቅስቃሴ በዘርፉ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል::
በአሁኑ ወቅት ለመስኖ ሥራ የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ከቀጠለ በአስር ዓመት የተቀመጠውን እቅድ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻልም ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት:: በአስር ዓመት ለማሳካት ከታቀደው በላይ መድረስ እንደሚቻል እስካሁን ያለው አፈጻጸም ያሳያል ሲሉ ጠቅሰው፣ የአስር ዓመት እቅድ መከለስ እና እንደገና ማየት ይገባልም ብለዋል::
እንደ ሀገር በመስኖ ዘርፍ ለማሳካት የታቀደው ሀገሪቱ ካላት አቅም ጋር የማይጣጣምና አነስተኛ እቅድ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ ያላት አቅምና እየለማ ያለው መሬት ምንም እንደማይገናኙ ተናግረዋል፡፤ ሀገሪቷ ካላት እምቅ አቅም አንጻር ከዚህም በላይ መሥራት እንደሚቻል መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል:: እቅዱን መከለስ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ መረጃ አለ ብለዋል::
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመስኖ ልማት ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ የተመዘገበ አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፤ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በማለፍ ስኬት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል::
በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የመስኖ ሥራዎችን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ትላልቆቹ ችግሮች የጸጥታ፣ የግብዓት ዋጋ መናር እና እጥረት እንዲሁም ከካሳ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል:: እነዚህ ችግሮች ፕሮጀክቶችን እየፈተኑ ስለመሆናቸው ክልሎች በተደጋጋሚ ለመንግሥት ማቅረባቸውን አመልክተው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በባለቤትነት በሚገነባቸው ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይም እነዚህ ችግሮች በተደጋጋሚ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል:: ተግዳሮቶቹ ለፕሮጀክቶች መጓተትም ትልቁን ሚና እያበረከቱ ናቸው ብለዋል::
በየቦታው የነበሩ የጸጥታ ችግሮች በመስኖ በፕሮጀክቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበራቸው የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ከጸጥታ ችግር ባሻገር እንደ ሀገር ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን እየገጠመው ያለው ሲሚንቶን ጨምሮ የግንባታ እቃዎች እጥረት ዘርፉን እየተፈተኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል:: በሌላ በኩል በዋጋ ግሽበቱ ምክንያት የመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭ ወደ አለመሆን እየሄዱ እንደሚገኙም ነው ያመለከቱት:: ግብዓቱ በጊዜ ካለመገኘቱ ባሻገር ሲገኝም በውድ ዋጋ የሚገኝ እና በተደጋጋሚ የዋጋ ክለሳ የሚጠየቅ መሆኑ ተቋራጮችን ትልቅ ዋጋ እያስከፈለ እንዳለና አቅማቸውን በጣም እየተፈታተነ መሆኑንም ሚኒስትሯ አመልክተዋል::
አብዛኞቹ ገንቢዎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሆናቸውን የጠቆሙት ኢንጂነር አይሻ፤ የሲሚንቶ እጥረት በገንቢዎች አቅም ላይ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል:: ችግሩ የገንቢዎችን የመፈጸም አቅም በእጅጉ እየሸረሸረ መሆኑንም ነው ያነሱት::
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ እንደ ሀገር የመስኖ ዘርፍን እየፈተነ ያለው ሌላኛው ተግዳሮት የካሳ ዋጋ መናር እና ብልሹ አሰራር ነው:: በመንግሥት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች አካባቢዎች የተጋነነ ዋጋ የመጠየቅ ሁኔታዎች ይታያሉ:: በአንዳንድ አካባቢዎች ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚታዩ አላስፈላጊ ጥያቄዎች አሉ:: እስካሁን ድረስ የካሳ ጉዳይ በየጊዜው ሥራ እስከማስቆም እየደረሰ ነው:: በካሳ ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶችም አሉ::
የመስኖ ዘርፉን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጸጥታ ሁኔታ ከአካባቢ አደረጃጀቶች ጋር ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው:: ማህበረሰቡን ባለቤት የማድረግ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል:: ማህበረሰቡ ፕሮጀክቶቹን የራሱ አድርጎ የሚጠብቃቸው ከሆነ የጸጥታ ችግሮቹ ይፈታሉ ብለዋል::
በሌላ በኩል የዘርፉ ተግዳሮት የሆነውን የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የዋጋ ንረቱን ማካካሻ ይሆን ዘንድ የዋጋ ማሻሻያዎችን በተቻለ መጠን ባለው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለማስተካከል ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል::
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከሲሚንቶ አቅራቢዎች እና አምራቾች ጋራ በመሆን ፕሮጀክቶች በቀጥታ ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው:: እንደዚያም ሆኖ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ማለት አይቻልም:: አሁንም የሲሚንቶ ጉዳይ ፈተና መሆኑ አልቀረም::
ከካሳ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የተጋነኑ ጥያቄዎችን መንግሥት በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለማስተካከል ሙከራ እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ እስከዚያ ግን በጣም ጋሽቦ የሚመጣው የካሳ ጥያቄዎች ከአካባቢው አስተዳደር ጋር በመሆን ለማስተካከል ሙከራ የሚደረግ መሆኑን አመላክተዋል::
በግምገማ መድረኩ የተገኙት የተለያዩ ክልሎች የመስኖና ቆላማ አካባቢ ቢሮ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለሚዲያዎች እንደተናገሩት፤ በ2015 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል:: በርካታ መለስተኛና አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ፕሮጀክቶች ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጋቸውን አስታውቀዋል:: በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን ጥገና የሚያስፈልጋቸውን የመጠገን ስራ እየተሰራላቸው መሆኑን ተናግረዋል::
የኦሮሚያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ የውሃ ሀብትን ለግብርና ስራ ለማዋል በዋናነት በቆላማ አካባቢዎች ያለውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የአካባቢውን የኑሮ ዘይቤ መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም በ2015 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ስራዎች ተሰርተው አመርቂ ውጤቶችም ተመዝግበዋል ብለዋል:: እንደ ኦሮሚያ ክልል በአነስተኛና መካከለኛ መስኖ እንዲሁም በአነስተኛ ግድብ ስራዎች ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል::
የአማራ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዳኝነት ፈንታ በበኩላቸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የጠቆሙት:: በጥናትና ዲዛይንና በግንባታ አፈጻጸም ስራዎች እንዲሁም በመስኖ ተቋማት አስተዳደር ረገድ ሰፊና ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል:: በክልሉ በመስኖ መልማት ከሚችለው መሬት አንጻር በአሁኑ ወቅት እየለማ ያለው አነስተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዳኝነት፣ በመስኖ ላይ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል:: ጥሩ ጅምሮችን በማጠናከር እና ችግሮችን ነቅሶ በመፍታት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015