የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችበትን ትምህርት ቤት መቼም ቢሆን አትረሳውም፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ የልጅነት ትዝታዎች አሏት። በዛ ለጋ እድሜዋ ከክፍል ጓደኞቿ ጋር በግቢው ቦርቃለች፡፡ በመምህራኖቿ ተግሳፅና ምክር ተኮትኩታ አድጋበታለች፡፡ እውቀትን ከትምህርት ቤቱ ያለገደብ ገብይታለች፡፡ የትምህርት ቤቱ ምድረ ግቢ፣ ከእርሷ ጋር የተማሩ የክፍል ጓደኞቿንና መምህራኖቿ አሁንም ድረስ በአይኗ ውል ይላሉ፡፡
ይህ በውስጧ ሲንቀለቀል የቆየው የረጅም ዓመት የትምህርት ቤት ትዝታ ዛሬም አለቀቃትም፡፡ በግዜው አብረዋት የተማሩ ሁሉንም የክፍል ጓደኞቿን ብታገኛቸው አትጠላም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹን የማግኘት እድል ገጥሟት ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉንም አግኝታ የድሮ ትዝታዎቿን ማጣጣም አልቻለችም፡፡ እናም አንድ ሃሳብ መጣላት፡፡ ይኸውም አብረዋት የተማሩ የክፍል ጓደኞቿን የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማፈላለግና ማሰባሰብ ነበር፡፡ እነሆ ፍለጋው ቀጠለ፡፡ እርስ በእርስ መጠያየቅም ተጀመረ፡፡
አቶ አምሐ አለቃም አዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው ሰፈረ ሰላም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪ ነው፡፡ ከ1978 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በዚህ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል። በግዜው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል አብሯቸው የተማሩ የክፍል ጓደኞቹን የቤተሰብ ያህል በደምብ ያውቃቸዋል። ይህ መተዋወቅ እያደገ መጥቶ ትምህርቱን ካጠናቀቀም በኋላ ግንኙነቱን ለማስቀጠል ከተለያዩ አብረውት ከተማሩ ተማሪዎች ጋር ይጠያየቅ ነበር፡፡
ይሁንና በትምህርት፣ በሥራና በሌሎችም ምክንያቶች ግንኙነቱ እየተቆራረጠ መጣ፡፡ አንድ የመሰብሰቢያ መድረክ እንዲኖር በማድረግና ማኅበር መሥርቶ የግንኙነት መድረክ በመፍጠር የተቋረጠውን ግንኙነት ማስተካከል እንደሚቻል መቅደስ ታምሩ በተባለች የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ በኩል ሃሳብ ቀረበ፡፡
በመቀጠል ስልክ በመለዋወጥ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ማን ማንን እንደሚያውቅ መጠያየቅና መፈላለግ ተጀመረ፡፡ በዚሁ ዓመት ኅዳር 2015 ዓ.ም የቀድሞ ተማሪዎቹ እንገናኝ ተባብለው የመጀመሪያ ቀጠሮ ያዙ። ሀያ ሰባት የሚሆኑ ተማሪዎች ተሰብስበው በሰፈረ ሰላም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ግዜ ተገናኙ፡፡ በዚሁ ግንኙነት በአካል የተገናኙት እንዳሉ ሆነው በውጪ ሀገር የሚኖሩ የቀድሞው የዚህኑ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም በቨርችዋል ኦንላይን ተሳትፈው አውርተዋል፡፡ የቀድሞ የሰፈረ ሰላም ትምህርት ቤት አብሮ አደግ ተማሪዎች ማኅበርንም መሠረቱ፡፡
ከሀያ ሰባት ዓመት በኋላ በአካል የተገናኙት ሀያ ሰባቱ የቀድሞው የሰፈረ ሰላም ትምህርት ቤት ተማሪዎች በ1985 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ነበር ትምህርት ቤቱን ለቀው የወጡት፡፡ ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባም ገና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካጠናቀቁም በኋላ አብዛኛዎቹ ወደተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተበትነዋል፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ነበር በመካከላቸው የግንኙነት ክፍተት የተፈጠረው፡፡ ከዛ ግዜ ጀምሮም ግንኙነቱን ለማስቀጠል በተማሪዎቹ በኩል መፈላለጉ ነበር፡፡
አሁን ደግሞ ካደጉ በኋላ አብዛኛዎቹ ወደ ሥራው ዓለም ሲገቡና በተለያዩ ምክንያቶች ሲራራቁ የእንገናኝ ሃሳቡ መጥቶ ለመጀመሪያ ግዜ በጋራ ለመሰባሰብ በቅተዋል፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ በድጋሚ በጥር ወር 2015 ዓ.ም ተገናኝተው ግንኙነታቸውን ይበልጥ አጠናከሩ። በዚሁ ግንኙነታቸው ወቅትም አንዱ የሌላኛውን አሁናዊ ሕይወት፣ የኑሮ ሁኔታና ሥራ ለመረዳት ችሏል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በመወያየትም ‹‹የኛ ክፍል ተማሪዎች›› የሚል የቴሌግራም ገፅ በመክፈት ሌሎች ያልተካተቱ የቀድሞ ተማሪዎች ቡድኑ ውስጥ እንዲቀላቀሉ ሁኔታዎች ተመቻቹ፡፡
በዚሁ የቴሌግራም ገፅ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሃገር ያሉ የቀድሞ የሰፈረ ሰላም ተማሪዎች ሲያወሩ በተገናኙበት አጋጣሚ የታዘቧቸውን ነገሮች በውስጥ መስመር ከአንዳንድ ተማሪዎች ጋር ለማውራት ችለዋል፡፡ በዚህም የግል ችግሮች ያሉባቸው ተማሪዎች እንዳሉና በዚሁ ልክ ደግሞ መርዳት የሚችሉ አቅም ያላቸው የቀድሞ ተማሪዎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ መነሻነትም አቅም ላጡ ሁለት የቀድሞ የሰፈረ ሰላም ተማሪዎች እርዳታ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለሁለት ተማሪ ልጆቻቸውም ተመሳሳይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ያለባቸውን ወቅታዊ ችግር በማየትም ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ፣ ለተወሰኑ ወራት የሚያገለገል ቀለብ መሸመቻ የሚሆን የኪስ ገንዘብም ተበርክቶላቸዋል፡፡ አንድ ለቀድሞ መምህራቸውም የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። አንዳንድ የቀድሞ ተማሪዎች ደግሞ የጤና ችግር እንዳለባቸው በመረዳት ዘላቂ የጤና ክትትል እንዲያገኙ በውጪ ሀገር ያሉ ተማሪዎች በመድኃኒት፣ በሕክምና እንዲሁም በገንዘብ የተለያዩ እርዳታዎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
የሰፈረ ሰላም የቀድሞ አብሮ አደግ ተማሪዎች አሰባሳቢና አስተባባሪ አቶ አመሐ እንደሚለው አሁን የተደረገው ድጋፍ ጅምር ቢሆንም በቀጣይነት የሚደረገው ድጋፍ በተሻለና ዘላቂ በሆነ መንገድ ይቀጥላል፡፡ በተለይ ደግሞ መሠረታዊ የሆኑ የልጆች ትምህርት ቤት ወጪዎችና የቤት ኪራይ ድጋፍ ለሚሹ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ይደረጋል፡፡ የአእምሮ መታወክ የደረሰበትና የዚሁ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪ ለነበረ ጤንነቱ እንዲመለስ በቀጣይ ለማገዝም ታቅዷል፡፡
ምንም እንኳን የሰፈረ ሰላም የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር በአሁኑ ግዜ ትኩረቱ እርስ በርስ መረዳዳት ላይ ቢሆንም በቀጣይ ትምህርት ቤቱ ላይ በማተኮር የተለያዩ ሥራዎችን የመሥራት እቅድ አለው፡፡ የአብዛኛዎቹ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችም አንዱ ምኞት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ ቋሚ ማስታወሻ ማስቀመጥ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ገና እንደተገናኙ በቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውና መምህራኖቻቸው ላይ ያልጠበቁት ነገር ስለገጠማቸው ሙሉ ትኩረታቸውም እነርሱ ላይ ነበር፡፡ ይሁንና ተማሪዎቹ በአካል ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ከዚህ ባለፈ በርካታ ነገሮችን ትምህርት ቤቱ ላይ መሥራት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ከተማሪዎቹ መካከል በልዩ ልዩ መስኩ አቅም ያላቸው አሉ፡፡
በዚሁ መሰረት በሰፈረ ሰላም ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎቹ የእነሱን ዘመን ሊገልፅ የሚችልና የአሁኑ ዘመን ተማሪዎች ሊጠቀሙበት የሚያስችል አንድ ነገር ለመሥራት አስበዋል፡፡ በቀጣዩ ሐምሌ ወር ሲገናኙም ለአንድ ተማሪ አንድ መጽሐፍ በሚል መሪ ቃል ያሰባሰቧቸውን መጽሐፍቶች ለተማሪዎች ለማስረከብ እቅድ ይዘዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ያሉበት ጉድለቶች ካሉም ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸውን የቀድሞ ተማሪዎችን በማስተባበር ለማሟላት ውጥኖች ተይዘዋል፡፡
ለተማሪዎች የደምብ ልብስ፣ ከመሠረታዊ የትምህርት መሣሪያ ፍላጎት ጀምሮ የተቸገሩ ተማሪዎችን የቀድሞ ተማሪዎች ለአንድ ተማሪ እንደ ወኪል ወላጅ እንዲሆኑ በማድረግ ልጆቹን እንዲንከባከቡ በዛ ወቅት ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህም ቅስቀሳ ተደርጎ አንዳንዶቹ የቀድሞ ተማሪዎች ወኪል ወላጅ ለመሆን ቃል ገብተዋል፡፡ ለዚሁ እንቅስቃሴ ገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በሦስት የቀድሞ ተማሪዎች ስም አንድ የባንክ ቁጥር (አካውንት) ተከፍቶ ገንዘብ ተቀማጭ እየተደረገ ይገኛል፡፡
መምህር ተሾመ በቀለ የቀድሞ ሰፈረ ሰላም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው፡፡ የመምህርነት ሥራቸውን በዚህ ትምህርት ቤት በ1975 ዓ.ም ሲጀምሩ ገና የአስራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ በግዜው የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ማስተማር ስለሚቻል እሳቸውም በትምህርት ቤቱ ሳይንስና የሰውነት ማጎልመሻ የትምህርት አይነቶችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን በሂሳብናና በሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ዲፕሎማቸውን ይዘዋል። ቀጥለውም በማኔጅመንት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ አሁን ደግሞ በዳግማዊ ብርሃን ትምህርት ቤት የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ያስተምራሉ፡፡
መምህር ተሾመ ከ1978 እስከ 1985 ዓ.ም ባለው ግዜ ውስጥ በሰፈረ ሰላም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበሩ ተማሪዎችን አስተምረዋቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹን ተማሪዎቻቸውንም ያውቋቸዋል፡፡ ከእርሳቸው በበለጠ ደግሞ ተማሪዎቻቸው በደምብ ያውቋቸዋል። ተማሪዎቻቸው ለእርሳቸው ያላቸው ክብርና ፍቅርም የተለየ ነው፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ ተማሪዎቻቸውን እንደልጆቻቸው ነው የሚመለከቷቸው፡፡
መምህር ተሾመ እንደሚናገሩት የቀድሞ ተማሪዎቻው ‹‹የእኛ ክፍል ተማሪዎች›› በሚል የተናጠል ማኅበር ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ትምህርት ቤቱ ሀምሳኛ የምሥረታ በዓሉን በቅርቡ የሚያከብር በመሆኑ በየክፍሉ ያሉ ተማሪዎች የየብቻቸውን ማኅበር ከሚያቋቁሙ ሁሉም ተማሪዎች በአንድ ቀን ተገናኝተው የቀድሞ የሰፈረ ሰላም ተማሪዎች በሚል ማኅበር እንዲመሠርቱ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
ይህም ተማሪዎቹ ድሮ በአንድ ክፍል ይማሩ የነበሩ እንደመሆናቸው ትምህርት ቤቱን በተለያዩ መንገዶች ማገዝ እንዲችሉ፣ እርስበርሳቸውም እንዲረዳዱና አንጋፋ መምህሮቻቸውን እንዲያግዙ ያስችላቸዋል፡፡ ‹‹እኔ እራሱ ወደ አንጋፋነት እያመራሁና ወደ ጡረታ መውጪያ ጊዜዬ እየተቃረብኩ ነው›› የሚሉት መምህር ተሾመ፤ ከዚህ ቀደም ዓይናቸውን አሟቸው ዶክተር ኑሩ መሐመድ በተባለ የቀድሞ ተማሪያቸው አማካኝነት ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ የዓይናቸውን ጤንነት ወደነበረበት እንደመለሰ ይመሰክራሉ፡፡
በተመሳሳይ ዶክተር ኤፊሶን የተባለና ቀደም ሲል እርሳቸው ያስተማሩት ተማሪም በተፈጥሮ ምክንያት የወለቀው ጥርሳቸው ሕክምና አግኝቶና በሌላ አርቴፊሻል ጥርስ ተተክቶ ፈገግታቸው ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረጉንም ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል የቀድሞ ተማሪያቸው የነበረና ዶክተር ነብዩ የሚባል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የኩላሊት ስፔሽያሊስት ሐኪም የሆነ ሙሉ ሕክምና እንዲያገኙና በየሦስት ወሩ የጤና ክትትል እንዲያደርጉ መርዳቱንም ይጠቁማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መረዳዳትና መደጋገፍ ቢጠናከር ለብዙ ሰዎች የሚተርፍ በመሆኑ የቀድሞ ተማሪዎችን በማሰባሰብ የሰፈረ ሰላም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ሀምሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ለማክበር ማስፈለጉንም ይጠቅሳሉ መምህር ተሾመ፡፡
በአሁኑ ወቅት የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን የራሳቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ አካውንት) በመክፈትና ሌሎችንም ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም መረጃዎችን እየተለዋወጡ እንደሚገኙና ግዜው ረጅም ከመሆኑ አንፃር በብዙዎቹ ተማሪዎች በኩል የተለያዩ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ እንደሚገኙ የብዙዎች ትዝታዎችም እንደተቀሰቀሱ ይናገራሉ፡፡ አሁን እንደ አዲስ የተፈጠረውን ግንኙነት በማጠናከር ወደቁም ነገር ለመለወጥ በአካል ተገናኝቶ ከመነጋገር ጀምሮ በዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሃሳቦችን ሲለዋወጡ እንደነበርም ይጠቁማሉ፡፡
ስለዚህ የሰፈረ ሰላም የቀድሞ ተማሪዎች ዳግም መገናኘትና ማኅበር መሥርተው መንቀሳቀስ እርስ በእርስ ከመረዳዳት ባለፈ ቀደምት መምህራንን በልዩ ልዩ መልኩ ለመደገፍ ብሎም አቅም ያነሳቸውን የአሁኑ ተማሪዎችን ለማገዝና ትምህርት ቤቱ የጎደሉትን ነገሮች ለሟሟላት እንደሚያስችልም መምህር ተሾመ ተናግረዋል፤ እንዲህ አይነቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ወደሌሎች ትምህርት ቤቶችም ጭምር መጋባት እንዳለበት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
ሰፈረ ሰላም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በቅድሚያ የግል፣ በመቀጠል የሕዝብ አሁን ደግሞ የመንግሥት አንጋፋ ትምህርት ቤት ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበሩትን አሊ ረዲ እና ጀማል ጣሰውን፣ የተለያዩ የጥበብ ሰዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የሌሎች ሙያዎች ባለቤት የሆኑ ግለሰቦችን አፍርቷል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም