ቆዳ ከጥንት ጀምሮ ከሰው ልጆች የአኗኗር ዘይቤ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ የሰው ልጆች ከቆዳ አልባሳት፣ ጫማ፣ የጦር መሣሪያና ሌሎች መሰል መገልገያ ቁሳቁስን በመሥራት ሲገለገሉ መኖራቸውን ታሪክ ያመለክታል፤ ቆዳ በሀገራችን ታሪክ ቀዳሚውን ስፍራ ቢይዝም፣ እውቅና አግኝቶ ትኩረት ተሰጥቶት በመሥራት ረገድ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ባለሙያዎቹ አሁን ግን የቆዳ ምርቶች በተለይ በፋሽን ኢንዱስትሪው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱን በመጠቆም፣ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ያመለክታሉ፡፡ የኬርኤዥ ኢትዮጵያ ሌዘር ኤክስፖርት ማኑፋክቸሪንግ ባለቤት አቶ ዘላለም መርዓዊም ይህንኑ ሀሳብ ይጋራሉ፡፡
አቶ ዘላለም እንደሚሉት፤ ቆዳ በተፈጥሮ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ምርቶች የሚለይ ለፋሽን ኢንዱስትሪው የመጣ ቱሩፋት ነው፡፡ ቆዳ ራሱ ፋሽን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የሰው ልጆች የለበሱት የመጀመሪያ ልብስ ቆዳ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቆዳ ፋሽን እንደነበር፤ የፋሽን መነሻም ከኢትዮጵያ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
የሰው ልጆች አልባሳትን ሲለብሱ የነበረው እንሰሳትን አድነው ለምግብነት ካዋሉ በኋላ ቀሪውን ቆዳ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ከቀደምቶቹ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጡት የቆዳ ውጤቶች ምርቶች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እንደፋሽንም፤ እንደ ባህላዊም ልብስ ሆነው ይለበሳሉ፡፡ ለምሳሌ የሐመር ብሔረሰብን ብንመለከት የቆዳ አልባሳት አላቸው፡፡
የቆዳ ምርቶች እንኳን ዘመናዊውን ባሕላዊዎቹን ብንመለከት እስከዛሬ ድረስ ተለብሰው ያላለቁ ናቸው። ሐመር ብሔረሰቦችና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች 90 በመቶ የሚሆኑት አልባሳት ቆዳ ላይ ጌጣጌጥ ተጨምሮበት ወደ ፋሽን አድገው የሚሠሩ ናቸው፡፡ እስካሁንም ባህላቸውን ሳይለውጡ የሚጠቀሙት የእንሰሳት ቆዳ ነው፡፡ ይህም ቆዳና ፋሽን የጠነከረ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን እንደሚያሳይ ነው አቶ ዘላላም የጠቆሙት ፡፡
‹‹ቆዳ ከፋሽንነቱ በተጨማሪ በጦር መሣሪያነት ጭምር አገልግሏል፤ ትልቅ ታሪክ አለው›› የሚሉት አቶ ዘላለም፤ ዓድዋ ላይ አገልግል፣ጫማ ፣አልጋ ፣ጋሻ እና ከበሮ ሆኖ ዘምቷል፤ ነጋሪት ሆኖ የኢትዮጵያን ጦር አሰባስቦ መርቷል ይላሉ፡፡ ቆዳ መሰንቆና ክራር ሁሉን ነገር ሆኖ የሠራ፤ የሙዚቃ ቅኝቶች ለመፍጠር አስተዋፅዖ ያበረከተ ነው ብለዋል፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሰዎች በቅርበት ያገኙት ነገር ጠንካራ ለሁሉም ነገር መሆን የሚችል ነው ብለው የሚያስቡት ቆዳን ነው ይላሉ፡፡
ቆዳ አሁን ላይ አድጎ ዘመናዊ የሚባል ደረጃ መድረሱን የሚጠቅሱት አቶ ዘላለም፤ በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘመናዊ የሚባሉ ከቆዳ የሚሠሩ የቆዳ ውጤቶች ሌዘር ፈርኒቸር እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ሌዘር ሶፋ፣ ሌዘር የቢሮ ወንበር፣ሌዘር የቢሮ ጠረጴዛ እና የመሳሳሉት በርካታ ሥራዎች ከቆዳ የሚሠሩ ሲሆኑ በሌዘር ላይ የፈርኒቸር ሞኒፋክቸሪንግ ፋሽን አብዮት ተካሄዷል ይላሉ፡፡ በአውቶሞቲቭ ፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥም እንዲሁ ሌዘር ሲት፣ ሌዘር ዳሽ ቦርድ እና የመኪና አክሰሰሪዎች ጭምር በመሥራት እንደሆኑም ይገልጻሉ፡፡
አቶ ዘላለም እኛ ሀገር ሌዘር ሲባል ወደ አዕምሮአችን ቶሎ የሚመጣው ቦርሳ ወይም ጃኬት ነው፡፡ ሌዘር ግን ከዚህ አልፎ የማይገባበት ኢንዱስትሪ፤ የማይገባበት የፋሽን ጥግ የለም፡፡ ቆዳ ጥልቅ ነው፤ ቆዳ ፋሽን ነው፤ ቆዳ ብርቅ ነው፤ ቆዳ ረቂቅ ነው፡፡ እኛ ግን አበጃጅተን ሀገራችንን የፋሽን ኢንዱስትሪን ፈርጥ ማድረግ አልቻልንም›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ያሉ የመኪና አስመጪ ካምፓኒዎች መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢንቨስት ያደረጉት ቆዳ ላይ ነበር። ቆዳ እየላኩ አውቶሞቲቭ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ጀመሩ፡፡ ይህም ሌሎች ኢትዮጵያ በቆዳው ዘርፍ ያላት ሀብት አውቀው ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እስከዛሬ ድረስ እንዳልገባን ያሳያል፡፡ ቆዳ ያልገባን ኢንዱስትሪ በመሆኑ ምክንያት ይጣላል፤ ተቆራርጦ በጥሬው ከሀገር እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ እንዲሁም ለምግብነት ወደ ምዕራብ አፍሪካ ይላካል ብለዋል።
አንድ የበሬ ቆዳ ለያውም በጥሬው ሲሸጥ ቢበዛ 6 መቶ ብር ሊያወጣ ይችላል፡፡ እሴት መጨመር ቢቻል መቶ ሺ ብር ዋጋ ያወጣል፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ ከአንድ የበሬ ቆዳ አራት ቦርሳዎች መውጣት ቢቻል እያንዳንዳቸው 25ሺ ብር መሸጥ እንደሚቻል ነው አቶ ዘላለም የሚናገሩት፡፡ ይህን ሊሆን የሚችለው ቆዳ በባለሙያ ዲዛይን ተደርጎ፣ በሚገባ ሲመረትና በአካባቢው ተሰማሚ የሆነ የአመራረት ሂደት ተከትሎ ከተመረተና የዓለም ፋሽን ከለር ብዙ ነገሮች ግንዛቤ ውስጥ ሲሠራበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አቶ ዘላለም የኬርኤዥ ኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ በተለይ በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሪ ሆኖ መጥቷል። የፋሽን ኢንዱስትሪ በብራንድነት የሚመራ ሆኗል። አሁን ላይ የሚወዳደረው የዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ብራንዶች ከእነሄልሚት፣ ጉቺ፣ ሀርማኒ፣ ሽሜልና ከመሳሳሉት ጋር መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ አቶ ዘላለም በዓለም አቀፍ መድረኮች እነ ኒዮዎርክ፣ ፓሪስ፣ ቤጋስ፣ ሚላን ቶኪዮ የመሳሰሉት የፋሽን ፈርጥ የሆኑ ሀገራት ላይ የሚያዘጋጁትን ኤግዚቢሽኖችን በመካፈል ያገኙትን ልምድ ወደ ሀገሪቱ በማምጣት ሰዎች ልምምድ እንዲያደርጉ በማድረግ ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በፈርኒቸር ዘርፍ፣ በአልባሳት፣ በጫማ፣ በሌዘር፣ በቀበቶ በቆዳ ውጤቶች ፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ ቆዳ ሊሆን የሚችለውን ሁሉ በሙከራ ደረጃ ጥናት እየሠሩ ተግባር ላይ እያዋሉ እንደሆነም አቶ ዘላለም አብራርተዋል፡፡ እንደፋሽን ኢንዱስትሪው መሪነታችን ኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳዳሪ መፍጠር እንፈልጋለን የሚሉት አቶ ዘላለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኛን አርአያነት ተከትለው ከ3 መቶ በላይ ብራንድ ውስጥ ያሉ ብዙ ቆዳ አምራቾች ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው እየመጡ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ቆዳ በቀላሉ ዲዛይንና ብራንድ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ ኢንዱስትሪው እየመጡ ያሉት ሴቶች መሆናቸውንም ይጠቁማሉ። በአሁኑ ወቅት በርካታ ሴቶች ብራንድ እያደረጉ የእኛ አርአያነት እየተከተሉ ወደቆዳ ፋሽን ኢንዱስትሪው እየመጡ ነው ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ልክ ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ ተጨማሪ መዳረሻዎች እየሠራች እንዳለች ሁሉ በዚያው ልክ አብሮ ሊሄድ የሚችል የተለያዩ ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች የሚታዩበት ምስሎች ተሠርተው መታየት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የቆዳ ምርቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ሁሉንም በየዲዛይኑ የሚቀርብበት ሞል እንዲሁም በፋሽን ኢንዱስትሪ ምርቶችና ሌሎችም የሚቀርቡቡት የየራሳቸው ሞሎች ቢሠሩ ቱሪዝም ከመሳብ አንጻር ከፍተኛ ድርሻቸው እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡
‹‹ለፋሽን ኢንዱስትሪው ትኩረት ተሰጥቶ በመሥራት ጥሬ እቃን ከመላክ አስተሳሰብና ባሕል መውጣት አለብን›› የሚሉት አቶ ዘላለም፤ ቆዳ በጥሬ እንዲላክ ማድረግ ኢንዱስትሪውን የሚገድል ነውና አስፈላጊ ክትትል ቢደረግ ጥሩ ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡ እንደእነዚህ አይነት ፖሊሲዎችን በማረም ችግሮች በመፍታት መፍትሔ ብናደርግ ትልቅ ለውጥ ሊመጣ ይችላል›› ሲሉ መክረዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም