በአገራችን ዕቃ ለመሸመት ገበያ የወጣ ሸማች ለሚያነሳው ዋጋው ስንት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቢሆንበት መልሶ ለምን? የሚል ጥያቄ ያስከትላል። ለዚህም የሚሰጠው ምላሽ ምርቱ የውጭ አገር መሆኑና ጥራቱን የጠበቀ እንዳለው ነው።
የዛሬው ጽሑፍ መነሻዬም እኔ ላቀረብኩትም ሆነ ሌሎች ለጠየቁት የተወዷል ጥያቄ ሲሰጠን የቆየው ‹‹ይሄ እኮ የአገር ውስጥ ምርት አይደለም ከውጭ የገባ ነው›› የሚል የቀብራራ ሻጭ አስተያየት ነው። በዚህ ውስጥ የሻጮቹን የአገር ውስጥ ምርት የማጣጣል መንፈስና የውጭ ምርት በመያዛቸው ውስጣቸው ያለው ቀብረር የማለት ስሜት ጎልቶ ይሰማል።
ታዲያ ሁሌም እውነት የኢትዮጵያ ምርት እንዲህ የሚታፈርበት የውጭ አገራትን ምርት መያዝስ እንዲህ የሚያንቀባርር ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ሁሌም በአእምሮዬ ይመላለሳል። ለዚህም ያገኘሁት መልስ ቢኖር አብዛኛው የአገር ውስጥ ምርቶች አዲስ ምርት ከማምረት ይልቅ ሌላ ሰው የፈጠረውን ምርት አስመስለው በመሥራት የተጠመዱ በመሆናቸው መምሰል እንጂ መሆን አይቻልምና የጥራት ጉድለት ይታይባቸዋል።
በዚህ የተነሳ የገዥና የሻጭ ጭቅጭቅ ከማያጣው የአገራችን ገበያ መሀል በአገር ባህል አልባሳት መሸጫነቱ የገነነው ሽሮ ሜዳ ተጠቃሽ ነው። የአገር ባህል ልብስ በትእዛዝ ለማሰፋት የፈለገ ሸማች ሽሮ ሜዳ ከሚገኙ የአልባሳት መሸጫ ሱቆች ጎራ ማለቱ የተለመደ ነው።
ታዲያ ከባለሱቆቹ ታዋቂ የአገራችን አርቲስቶችና ሞዴሎች የተዋቡበት አልበም መርጦ የፈለገውን ማዘዝ እንደሚችል ይገለጽለታል። ገዥም ልቡ ያረፈበትን፤ ቀልቡ የፈቀደውን ፎቶ በመምረጥ ቀብድ ከፍሎና ተለክቶ ልብሱ የሚደርስበት ቀን ለመውሰድ ተስማምቶ ይለያያል።
ጸቡ የሚጀምረው ከዚህ ነው፤ በተባለው ቀን ካለመድረስ፤ እየማለ እየተገዘተ እራሱ እንደሚሸምን ብሎም እንደሚጠልፍ ሲገልጽ የነበረው ሻጭ ልብሱ በተባለው ቀን ላለመድረሱ የሚያቀርበው ምክንያት ማለቂያ የለውም። ሸማኔው ለቅሶ ገጥሞት፤ መብራት ጠፍቶ፤ ጠላፊዋ ታማ … ይቀጥላል። በዚህ ሁሉ ታልፎና ከተባለው ቀን ዘግይቶ የደረሰው ልብስ በሸማቹና በሻጩ መሀል ይሄን አላዘዝኩምና ይሄን ነው የታዘዝኩት የሚል ጸብን ይወልዳል።
ዋነኛው የጸቡ ምክንያትም ባለሱቆቹ የልብሱ ዲዛይነሮች የፈጠራ ልጃቸው የሆነው ልብሳቸውን እራሳቸው ለብሰው ወይም ታዋቂ ሰዎችን ከፍለው አልብሰው ያነሱት ፎቶ በየሱቁ የራሳቸው ምርት እንደሆነ እራሱን ፎቶ አሳይተው ሸማችን ይስውዱበታል። የመጨረሻው ምርት ሲቀርብ የገዢ ፍላጎትና ምርቱ አይገናኝም።
ከከለር አገባብ አንስቶ እስከ መነኑ ጥራቱን የጠበቀ አለመሆን በገዢ ይነሳል። «ካፈርኩ አይመልሰኝ ያሉ» ሻጮች የታዘዘው ትእዛዝና ያቀረቡት ምርት አንድ ለመሆኑ አሳማኝ የሚሉትን ነጥብ ይዘረዝራሉ። በዚህ ሁሉ የምናየው በአገራችን አዲስ ነገር ለመፍጠር የሚያበረታታ ሁኔታ አለመኖሩን ነው። ስንት ሌሊት እንቅልፍ አጥቶ ተጨንቆና ተጠቦ አዲስ ፈጠራ ፈጠርኩ ያለ ዲዛይነር በነጋታው የሱን መሰል አልባሳት ገበያውን ያውም በአነስተኛ ዋጋ ያጨናንቁታል።
ለምን ቢል ሰሚ የለም፤ ለፈጠረው ፈጠራ ምንም ዓይነት እውቅናም ሆነ ጥቅም የሚያገኝበት ሥርዓት የለም። በዚህም ፈጣሪ የነበረው ሰው በሂደት ምን አለፋኝ በሚል ኮራጅ ይሆናል። የጫማ ገበያውም ተመሳሳይ ነው። የጫማው እንዲያውም ከአገር ውስጥ አልፎ ከውጭ የሚገቡትም የተሻለ የገበያ ተፈላጊነት አለው ብለው የሚያስቡትን ብራንድ አስመስለው የሚሠሩ ይበዛቸዋል።
የአገር ውስጥ ምርት ተብለው በአገሬ ምርት እኮራለሁ ኪሴንም እጠብቃለሁ ብሎ የተጫማ ሸማች በገዛው ማግስት መንገድ ላይ ጫማው ተገንጥሎ ሊስትሮ መፈለጉ የተለመደ ሆኗል። ሁሉም ማለት ባይቻልም አብዛኛው አምራች ዛሬን እንጂ ነገን አሻግሮ ሲያይ አይታይም ።
ዛሬ ባመረትኩት ምርት ምን ያህል አተርፋለሁ እንጂ፤ ለነገ የሚሆን ተመራጭ ጥራት ያለው ብራንድ መገንባት ላይ አይጨነቁም። ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት በገፍ ይመረታል፤ ከውጭም በገፍ ይገባል። ይህ ሂደት የኢንዱስትሪ ምርታችን ላይ ብቻ ሳይሆን የግብርና ምርት ላይም ይታያል።
ወተትን ለማብዛት የማይገባበት ነገር የለም፤ ገበያው ላይ ንጹህ ማር አለ የሚል ማስታወቂያ በየቦታው ቢታይም አብዛኛው ሸማች ማር ብዬ ሌላ ነገር ከምወስድ ቢቀርብኝ ይሻላል ብሏል። በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የሆለታ የእንስሳት ምርምር ማዕከል በጋራ ባጠኑት ጥናት በአዲስ አበባ በሱቆች፣ በሱፐር ማርኬቶችና አዟሪዎች እጅ ከሚገኘው ማር እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ጤንነቱ ያልጠበቀ መሆኑን አሳይቷል።
ማር ለብዙ በሽታዎች ጠቃሚ መሆኑ ቢታመንም በምርመራ እንደተረጋገጠው በአዲስ አበባ ለሸማች ከቀረበው ማር ጋር ስኳር፣ ሙዝ፣ የተፈጨ ጠርሙስ፣ ከረሜላዎች እና ሌሎችም ባዕድ ነገሮች ይቀላቀሉበታል። እኛ ጋር ሌላው ቀርቶ መሠረታዊ ፍላጎት ለሆነው ምግብ ፍጆታ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች ባእድ ነገር ይቀላቀልባቸዋል። በዚህም በቂ ንጥረ ነገር ያላገኘ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ እናፈራለን።
ባደጉት አገራት ሁሉም አምራች የሚያመርተው ምርት በውስጡ ምን ይዘት እንዳለው በግልጽ ያስቀምጣል፤ ታላቅ ቅናሽ ካሉ እውነትም ታላቅ ቅናሽ ማለታቸው ነው። የሌላን ምርት አስመስሎ መሥራት ወንጀልም የራሳቸውን ብራንድም መግደል ነው።
ይህ መሆኑ ሁሌም ለአዲስ ፈጠራ ያነሳሳቸዋል፤ መኮረጅ ከትርፉ ይልቅ መዘዙ ብዙ ነው። ከዚያም በላይ ሲሠሩ ከዛሬ ይልቅ ስለነገ አሻግረው ያያሉ፤ በዚህም ለገበያ ባቀረቡት ምርት ላይ ትንሽ እንከን ሲያጋጥም ከይቅርታ ጋር ከደንበኞቻቸው ሙሉ ምርቱን ይሰበስባሉ። በአገራችንም የብራንድ ጽንሰ ሀሳብ ገብቷቸው ከዛሬ ትርፍ ይልቅ ለነገ ራዕይ የሰነቁ እንደ ሶል ሬብልስና መሰል ድርጅቶች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ከራሳቸው አልፈው ለአገር መታወቂያ ሆነዋል።
በአገራችን ኢትዮጵያ ታምርትና መሰል እንቅስቃሴዎች መኖራቸው አምራቾች ከብዛት በዘለለ ጥራት ያለው ነገር እንዲያመርቱ እንደሚያነሳሳቸው ተስፋ አደርጋለሁ። አዲስ ፈጣሪዎቹ ሊበረታቱ ሲገባ ኮራጅ ተማሪን መምህሩ እንደሚቀጣው ሁሉ ኮራጅ አምራቾችም ሀይ ባይ ያሻቸዋል ።
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015