ከተሞች ከዓለማችን ሕዝቦች የግማሽ በመቶው መኖሪያ ከመሆናቸው ባሻገር ወረርሽኞችን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ ለሰው ልጆች ፈታኝ የሆኑት ችግሮችን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። ፈተናዎቹን ለማለፍ ከሀገራት አቅም ይልቅ የከተሞች አቅም ወሳኝ መሆኑ ይታመናል። በአሁኑ ጊዜም ከተሞች ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እየሆኑ መጥተዋል። ይህን ያላቸውን ጉልህ ሚና የበለጠ ማጠናከር የሚቻለው ደግሞ የከተማ አመራሮች ወይም ከንቲባዎች ተቀራርበው መመካከርና መወያየት ሲችሉ ነው።
ለዚህም ነው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት የዓለም የከንቲባዎች ፎረም ተቋቁሞ ከንቲባዎች እንዲመካከሩ እየተደረገ ያለው። የመጀመሪያው የከንቲባዎች ፎረም እ.አ.አ በ2020 የተካሄደ ሲሆን፣ ሁለተኛው የከንቲባዎች ፎረም ደግሞ በ2022 በሲዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሂዷል። በነዚህ የከንቲባዎች ፎረሞች የከተሞች ከንቲባዎች ስትራቴጂካዊ እቅዶቻቸውን፣ የድርጊት መርሐ ግብሮቻቸውን የፈተና ማሸነፊያ መንገዶችን ለመንደፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር የማድረግ ባሕል እያዳበሩ ይገኛሉ።
የከንቲባዎች ፎረም ከተሞች መልካም ተሞክሮዎቻቸውን የሚጋሩበት፣ እንዲሁም ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች የሚፈቱበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ይገለጻል። ፎረሙ የ2030 የልማት አጀንዳንና የባለብዙ አስተዳደር ቅንጅትን ለማሳካት አስተዋፅዖው የጎላ እንደሆነም ይታመናል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተለመደ በመጣው በዚህ አሠራር ከንቲባዎች በጋራ ተገናኝተው የሚወያዩበትን፣ ልምድ የሚለዋወጡበትን፣ አንዱ ከሌላው ትምህርት የሚቀስሙበትን ሥርዓት እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ በኢትዮጵያ ከሁለት ሺ500 በላይ ከተሞች መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ የአከታተማቸውን፣ ውበትና መሠረተ ልማቶቻቸውን ሁኔታ ለተመለከተ ብዙ ጥያቄዎች የሚነሳባቸው ናቸው።
እነዚህ ከተሞች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ መክረው በጋራ ለማደግ ‹‹የተሻለ ከተማ ለተሻለ ሕይወት›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከንቲባዎች በቋሚነት ተገናኝተው ስለከተሞች ጉዳይ የሚመክሩበት፣ እርስ በርስ ትስስር የሚፈጥሩበት፣ በችግሮች ዙሪያ በጋራ መፍትሔ የሚፈልጉበት መድረክ ለማመቻቸት የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም በ2013 ዓ.ም ተቋቁሟል።
ፎረሙ የታለመለትን ዓላማ ከማሳካት አኳያ ብዙ ርቀት አለመጓዙንና በሚፈለገው ልክ ለከተሞች ማበርከት ያለበትን አስተዋፅዖ እንዳላበረከተ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቅርቡ ግን በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የኢትዮጵያ የከንቲባዎች ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል። ከንቲባዎቹም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። በዚሁ ጊዜም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር ወይንም ማዕከል ያደረጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ከንቲባዎቹ ጎብኝተዋል።
በከንቲባዎቹ ከተጎበኙት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከልም ወደ ሥራ የገቡት የወዳጅነት ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ አብርኆት ቤተ መጽሐፍት እንዲሁም የእንጦጦ ፓርክ፣ እንዲሁም በመገናኛ አካባቢ ግንባታው እየተካሄደ ያለው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ማዕከል፣ ሲ ኤም ሲ አካባቢ በመንግሥት አጋርነት እየተገነባ ያለው የአዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ እየተገነባ ያለው ዓድዋ ሙዚየም፣ የለሚ የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከልም ከንቲባዎቹ የጎበኙዋቸው ፕሮጀክቶች ናቸው።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በከንቲባዎቹ ፎርም ላይ ተገኝተው የከንቲባዎች ሚና ለከተማ ብልጽግና በሚል መሪ ሀሳብ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ቀጣይ የሥራ አቅጣጫም አስቀምጠዋል።
ከንቲባዎቹ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው ልምድ እንዲወስዱ ከማስቻሉም ባሻገር በየከተሞቻቸው ያለውን ጸጋ ወደ ሀገራዊ ጥቅም ለመቀየር እንደሚያግዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከፎረሙ ተሳታፊዎች መካከል የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ አንዱ ናቸው። ከከንቲባው ጋርም ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቆይታ አድርጓል። ከንቲባው ስለሚመሯት ሀዋሳ ከተማ እንደገለጹት፤ ሀዋሳ በፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች። ከተማዋን የንግድና የቱሪዝም ከተማ ሊያደርጓት የሚችሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው። በአዲስ አበባ በተካሄደው ፎረም መሳተፋቸው፣ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው እንዲሁም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ጽሑፍ የሀዋሳ የከተማን ልማት እና እድገት እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና የሚጫወተውን የከተማዋን አመራር ራዕይ እና አስተሳሰብ በሚገባ አስተካክሎ ለመምራት ስንቅ የሚሆን ሆኖ አግኝተውታል።
በአዲስ አበባ ከተማ የጎበኟቸው ፕሮጀክቶች ሀዋሳ ከተማን ሊያሻግሩ፣ ሊያሳድጉ የሚችሉ እና ከተማዋን ለመለወጥ ለሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ብዙ ልምዶችን የቀሰሙባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ተሞክሮው የበለጠ በኃላፊነት እንዲሠሩ ያስቻላቸው መሆኑንም አመልክተዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ እንደሆነች የሚያሳዩ ፕሮጀክቶችን መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ኢትዮጵያን መቀየርና ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተሠራውን ያህል መሥራት ከተቻለ ወደፊት የሀገሪቷን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ያዩበት መርሐ ግብር እንደነበርም ጠቁመዋል።
ሌላኛው በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣሕሉ በበኩላቸው በአዲስ አበባ በጥራት እና በአፈጻጸም የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ፕሮጀክቶችን መጎብኘታቸው በቀጣይ ባለሃብቱን እና ነዋሪዎችን በማሳተፍ ለሚሠሩዋቸው ሥራዎች እገዛ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። በተለይም በአረንጓዴ ልማት ላይ ኅብረተሰብን ማሳተፍ በሌሎች ከተሞች ብዙም ያልተለመደ መሆኑን በመጥቀስ፤ አዲስ አበባ ትላልቅ ድርጅቶች የሚገኙባት እንደመሆኑ እነዚህ ትላልቅ ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተሠሩ ሥራዎች እጅግ የሚያስደስቱ መሆናቸውን አብራርተዋል። ለሌሎች ከተሞች እንደ ትምህርት የሚወሰድ መሆኑንም አንስተዋል።
ባህር ዳር ከተማም አረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገች መሆኑዋን የጠቆሙት ዶክተር ድረስ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ረገድ የተሠሩ መልካም ሥራዎች ለባሕር ዳር ከተማ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር ድረስ ሣሕሉ አክለውም፤ በለሚ ኩራ የእንጀራ ፋብሪካ ያዩት ነገር መልካም ናቸው። በየቦታው ተቆራርጦ የሚሠራውን ሥራ በአንድ አደራጅቶ የሚሠራበት ሴት ተኮር ፕሮጀክት በሌሎች ከተሞችም ሊለመዱ የሚገባ ነው። በለሚ ኩራ የተሠራውን እንጀራ ማዕከሉ ካዩ በኋላ ቁጭት እንዳደረባቸው እና ትምህርት እንደወሰዱበት አንስተዋል። በለሚ ኩራ የታየውን ፈለግ መከተል ቢቻል ድህነትን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በትላልቅ ፕሮጀክቶች የተደረገው ጉብኝትም ከንቲባዎች እንዲተዋወቁ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ማኅበራዊ ትስስርን ያጠናከረ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ድረስ፤ ፎረሙ ሀገራዊ አንድነት የበለጠ እንዲጠናከር ትልቅ መሠረት የሚጥል ፎረም መሆኑን አንስተዋል።
ሌሎች የመድረኩ ተሳታፊ ከንቲባዎችም በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ውስጥ ያዩዋቸው ሥራዎች አስደሳች መሆናቸውን አስታውቀዋል። ተስፋ የሚሰጡ፣ ሕዝቡም በተስፋ የሚጠብቃቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንደሆኑና ይህን ማየት የቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
አንዳንድ ከንቲባዎች እና የከተማና የመሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባዩት ነገር መደነቃቸውን በተመሳሳይ ስሜት ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ለሀገሪቱ ከተሞች ተሞክሮ የሚሆኑ ሥራዎችን ሠርቶ ማሳየት መቻሉን አንስተዋል።
በከተሞቻቸው አንድን ፕሮጀክት ለማቀድ ከ90 ቀናት በላይ እንደሚፈጅባቸው በማንሳት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ግን በ90 ቀናት ውስጥ እስከ ባለ 12 ወለል (ጂ+12) ሕንጻዎች ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተው ማየታቸው ራሳቸውን እንዲጠይቁ፣ በከተሞቻቸው እየተከናወነ ያለውን የፕሮጀክቶች አፈጻጻም እንዲገመግሙ እና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ የሚያደርጓቸው ማነቆዎችን እንዲለዩ እና በቀጣይ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በቁጭት ለሥራ እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸው በየበኩላቸው ገልጸዋል።
ፎረሙን አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ የከንቲባዎች ፎረም በ2013 ቢመሠረትም፣ ትኩረት ተሰጥቶበት ወደ ሥራ አልተገባበትም ነበር። ከምሥረታው በኋላ ክፍተቶች ነበሩ። መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ረገድ ክፍተቶች ነበሩ። ክፍተቶቹን የመሙላት ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል።
አሁን መልሶ የማደራጀት እና ፎረሙን መመሥረትና ወደ ሥራ መግባት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ፎረሙ መመሥረቱን አስታውቀዋል። ከአሁን በኋላ ፎረሙ ቀጣይነት ይኖረዋል፤ ከንቲባዎች እየተገናኙ ልምድ ይለዋወጣሉ ሲሉም ነው ያስታወቁት። በቅርቡ ከ270 በላይ ከተሞች ከንቲባዎች አዲስ አበባ መጥተው ልምድ መለዋወጣቸውን ጠቅሰው፣ አዲስ አበባ ላይ የተጀመረው የከንቲባዎች ፎረም በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከተሞች እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ፎረሙ እጅግ ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ኢትዮጵያ፣ ከንቲባዎች በቅርበት እንዲተዋወቁ እድል የፈጠረ መሆኑንም ነው የጠቆሙት። ከንቲባዎቹ በአዲስ አበባ የተገነቡትን እና በመገንባት ላይ የሚገኙትን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በሚጎበኙበት ወቅት በአንድ አውቶብስ ላይ ሆነው እንዲጎበኙ መደረጉን የሚያነሱት አቶ ኢትዮጵያ፣ ይህም ከንቲባዎች የበለጠ እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ በቀጣይ ጊዜያት በተለያዩ ጉዳዮች በቅርበት እንዲመካከሩ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ መድረኩ ከተሞች ሰላማዊ ውድድር ለመፍጠር ፣ፉክክሩ አንዱ ከሌላው ተሽሎ ለመገኘት፣ ከተሞች ያሏቸውን እድሎች በአግባቡ እንዲረዱ ከማድረጉም ባሻገር ለተሻለ ሥራ እንዲነሳሱ ያግዛል። በቀጣይ ጊዜያት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመወዳደሪያ መስፈርቶችን በማውጣት የተሻለ አፈጻጻም የሚያስመዘግቡበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በአንድ ዙር አንዱ ከተማ ሲሸለም ለቀጣይ ሌላኛው ከተማ ተሸላሚ ለመሆን እንዲንቀሳቀሱ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል። በዚህ ሂደት ከተሞች ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲነሳሱ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
አቶ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት፤ በፎረሙ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያቀረቡት ጽሑፍ የከተሞች ከንቲባዎች በከተሞቻቸው ያሉትን መልካም እድሎች ማመንጨት የሚችሉባቸውን እይታዎች ማስተካከል የሚያስችላቸው ነው። ከንቲባዎች ከተሞች ያላቸውን እድሎች መፈተሸ እንዲችሉ እና የከተማ ነዋሪዎቹን አውቀው እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። የከተማው ኅብረተሰብ ምን እንደሚፈልግ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን እንዴት መስጠት እንዳለባቸው እንዲያውቁ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015