ህዝብ የስልጣን ምንጭና ባለቤት ነው። የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት አምነው የተንቀሳቀሱ ሀገራት በእድገት መንድገው ፤በዴሞክራሲ አብበው ታይተዋል። በተቃራኒው ከህዝብ ፍላጎት ውጪ የራሳቸውን አጀንዳ ለመጫን የሚሹ መንግስታት የሚመሯትን ሀገር ለሁከትን ለብጥብጥ ከመዳረጋቸውም ባሻገር ድህነት እንዲንሰራፋና ዴሞክራሲ እንዲቀጭጭ ምክንያት ሲሆኑ ታይተዋል። በዓለም የኋላ ቀርነት፣ የድንቁርና እና የድህነት ተምሳሌት ተደርገው ሲጠቀሱ መስማት የተለመደ ነው።
በማንኛውም መንገድ ህዝብ መደመጥን ይፈልጋል። ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ይፈልጋል። ለጥያቄዎቹ ተግባራዊ ምላሽ ይሻል፤ ካልሆነም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያላገኙበትን ተጨባጭ ምክንቶች ማዳመጥን ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ሰሚ እንዳጣ፤ ተገቢው ክብር እንዳልተሰጠውና እንደተናቀ ሊቆጥር ይችላል። ይህ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ ከላይ እንደተገለጸው ሁከት ፤ብጥብጥ፤ ጦርነትና ድህነት ነው።
በተለይም በዚህ የቴክኖሎጂና የግሎባላይዜሽን ዘመን ከህዝብ ፍላጎት በተጻራሪ ቆሞ የስልጣን ዘመንን ማራዘም ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት በተረጋገጠበት ክፍለ ዘመን ውስጥ እንገኛለን። የእያንዳንዱ ዜጋ ድምጽ ትልቅ ዋጋ አለው። የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና መስጠት ሊታለፍ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተቀባይነት እያገኙ መሄድ ጀም ረዋል።
ኢትዮጵያም የአለም አንዷ አካል ናትና ይህን እውነታ መጋራቷ አይቀርም። በእርግጥ ኢትዮጵያ ለዘመናት በንጉሳዊ፤ በወታደራዊና ከዛም ቀጥሎ በመጣው ቡድን ፈላጭ ቆራጭ ስርአት ስር በመቆየቷ የዴሞከራሲያዊ መንግስት ባህል ገና አልጎለበተም። በህገ መንግስት ደረጃ የሰብዓዊ መብትና ድንጋጌዎች ከመደንገጋቸው ባሻገር ዜጎች ከመንግስት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢገለጽም በተግባር ብዙ ርቀት የሚቀረው ነው።
ሆኖም ሰሞኑን የአዲስ አበባ ኤሌትሪክ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ለተፈጠሩ ችግሮች ህዘቡን ይቅርታ በመጠይቅ ያሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያደርግ ነው። ሌሎች ተቋማትም ልምድ ሊቀስሙበት የሚገባ ተግባር ነው። ሁለቱም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኤሌትሪክ አቅርቦትም ሆነ በውሃ ስርጭቱ ላይ መስተጓጎል መፈጠሩን ሳይሸሽጉ ይፋ ከማድረጋቸውም በላይ ለተፈጠረው ችግር ከህዝብ ይቅርታን ጠይቀዋል። ይህም ድርጊታቸው ተቋማቱ ለህዝብ ያላቸውን ከበሬታ ከማሳየቱም በላይ በቀጣይ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ያላቸውን ተነሳሽነት ያሳያል።
በእርግጥ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት ይቅርና ባደጉትም ሀገራት ቢሆን ሁሉንም የህዝብ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም። የህዝብ ፍላጎቶች ከሰው ልጆች ፍላጎቶች የሚመነጩ ናቸው። የሰው ልጅ ፍላጎቶች ደግሞ ማብቂያ የላቸውም። በየጊዜው እየጨመሩ የሚሄዱ ናቸው። ሆኖም የታቀደው ነገር ያልተሳካበትን ሁኔታ መግለጽና ለህዝብም ተገቢውን መረጃ መስጠት ግን የህዝብ አገልጋይነትንና ቅንነትን መላበስን እንጂ በኢኮኖም ማደግን ፤ በቴክኖሎጂ መገስገስን አይጠይቅም። ዋናው ነገር የሕዝብ አገልጋይነት ስሜትና ቅንነት ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ መለመድ ካለባቸው መልካም ተግባራት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማክበር አንዱ ነው። አገር በመምራት ላይ ያለው ገዥ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማክበር ነው። ህዝብን ሳያከብሩ በፖለቲካ ምህዳር ውስጥ መንቀሳቀስ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገሪቱ ጠብ የሚል ነገር ሊያስገኝ አይችልም። የህዝብን ፍላጎት ማክበር እና ለህዝብ ዋጋ መስጠት ከሁሉም ነገር በላይ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ ሊሆን ይገባል። እያንዳንዱ እርምጃቸውን ከህዝብ ፍላጎት አንጻር መመዘን አለባቸው።
ሆኖም አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎቶቻቻው ሲስተጓጎሉ ምን እንዳልተፈጠረ ዝም ብለው የሚቀመጡ፤ በማን አለብኝነትና በአምንቸገረኝኘት የተወጠሩና ምንም አይነት ህዝባዊ ተቆርቋሪነት የማይታይባቸው ናቸው። ለህዝብ ክብር የሌላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡን በማስተጓጎል ሌበነትና ብልሹ አሰራር እንዲሰፍን ታትረው የሚሰሩና አገልግሎትን በምልጃና በትውውቅ የሚፈጽሙ ናቸው። በዚህም ህዝብን ማንገላታትን የዕለተ ዕለት ተግባራቸው ያደረጉ የሚመስሉ ናቸው። በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የሚፈጸሙ ተግብራት እውን ተቋማቱ ህዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ መሆናቸውን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው።
መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ዜጎች እንግልት ደረሰብን፣ በሙስናና ብልሹ አሰራር ተሰቃየን ፤ ውጣ ውረዱ አንገላታን የሚሉ አቤታዎችን ማዳመጥና ይህንኑ ተግባር የፈጸሙ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰድ የሚጠበቅ ነው። የሚወሰዱ እርምጃዎች ደግሞ አንድ ሰሞን ብቻ ተወስደው የሚተው ሰይሆን ሁል ጊዜም ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። የሚወሰዱ እርምጃዎችም በቀጣይ ጊዜያት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስተማሪ ሊሆኑ ይገባል። ከዛ በመለስ ግን ቢያንስ ለተስተጓጎሉ አገልግሎቶች ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ግን ሊለመድ የሚገባው አሰራር መሆን አለበት። ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ስህተትን የሚያክም መድሃኒት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ይቅር ማለትን ያውቅበታል።
ይህ ሲሆን በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ይኖራል። በህዝብና መንግስት መካከል መተማመን ሲፈጠር የማይናድ ተራራ፣ የማይፈነቀል ድንጋይ፣ የማይሰነጠቅ አለት የለም። በሁለቱ መካከል መተማመን ሲኖር የመንግስት ዕቅዶች የመተግባር አቅማቸው ያድጋል፤ ልማት ይፋጠናል፤ ብልሹ አሰራር ይቀንሳል፤ ዕድገት ይፋጠናል፤ የዜጎችም ህይወት ይለወጣል። ሀገራዊ ብልጽግናም እውን ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015