ሽኩቻ የበዛበት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፍ በየጊዜው የማይገመት እና ተለዋዋጭ ከሆነ ሰነባብቷል። በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ አዲስ የኃይል አሰላለፍ ለመፍጠር እሽቅድድሙ በዝቷል። ዓረቦች መጥተዋል፡፡ ኃያላን አገራት በሌላ ቀጣና የሚያደርጉትን ፍጥጫ በዚህም ደግመውታል። አዳዲሶቹ ተገዳዳሪ ኃይሎች (ቱርክ እና ኢራን) ወደ ቀጣናው ተመልሰዋል። የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አመጣጥ ግን በተቃርኖ የታጀበ ነው፡፡
የተለያዩ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን በተመለከተ እንደሚገልፁት ዓረቦች ወደ ቀጣናው በሁለት መንገድ ነው የመጡት። የመጀመሪያው የሳዑዲ እና ኢራን ርእዮተዓለማዊ እና የእምነት አስተምህሮ ልዩነት የፈጠረውን ፍጥጫ መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የዓረቦች የእርስ በእርስ ሹክቻ የፈጠረው መስፋፋትን የተከተለ – ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በኳታር እና ቱርክ ላይ አኩርፈው የከፈቱት ዘመቻን ተከትሎ የመጣ እሽቅድድም ነው፡፡
የአሜሪካ እና አውሮፓ እንዲሁም የእስያ አገራት የፍላጎት መለያየት እንዳለ ሆኖ የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ ከመቼውም ጊዜ በላይ በባህረ-ሰላጤው አገራት ተቃራኒ ፍላጎት ተወጥሯል። ይህ የዓረቦች የፍላጎት ተቃርኖ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ ከባድ ጣጣ ይዞ እየመጣ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያዋ ደግሞ አንድነቷ አደጋ ላይ ያለው ሶማሊያ ናት።
ሌላኛዋ፣ ኃያላኑ «ደህንነታችንን ለማስጠበቅ» በሚል ሰበብ በጦር ሰፈር ግንባታ የወረሯት አገር ደግሞ ጎረቤታችን ጅቡቲ ናት። ከአሜሪካ እስከ ሩስያ፤ ከቻይና እስከ ፈረንሳይ የጅቡቲን ገዢ መሬቶች በመያዝ እርስ በርስ ተፋጥጠዋል። ይህም ሄዶ ሄዶ ከጅቡቲ አልፎ ለቀጣናው አገራት የደህንነት ስጋት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
እንደ አካባቢው ጂኦፖለቲካ ተመራማሪ ሞሮኮአዊው ህሻም ኤድ ገለፃ የዓረቦች ወደ አፍሪካ ቀንድ የመምጣት ምክንያት ሁለት ነው፡፡ የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ እና የንግድ አድማስን የማስፈት ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት። ከምጣኔ ሀብት ፍላጎት አንፃር ሲታይ ዓረቦች አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከባድ የሆነ የምግብ እና የውሃ እጥረት ተደቅኖባቸዋል። የውሃ ጂኦፖለቲካ ደግሞ ገና ብዙ የሚያቃቅር ጉዳይ ሆኖ የሚዘልቅ ነው፡፡
እንደ ብዙዎች ግምት ነዳጅ የዓረቦችን ገፅታ እንደቀየረ ሁሉ የውሃ ፖለቲካም የአፍሪካን ቀንድ የመቀየሩ ሁነት ቢውል እንጂ የሚያድር ጉዳይ አይደለም። ምናልባትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሃ ነዳጅን ይተካው ይሆናል፡፡ እነዚህን ፍላጎቶች ለማሳካት ዓረቦች በአፍሪካ ላይ ሲከተሉት የነበረውን ፖሊሲ በፍጥነት እየለወጡት ይገኛሉ፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ አፍሪካ ዓረቧን ግብፅ ልብ ይሏል፡፡ ግብፅ በቀጣናው የበላይነትን ለመግኘት የማትፈነቅለው ድንጋይ ስለማይኖር፡፡
በቀደመው ጊዜ ወደ ውስጥ ይመለከታል የሚባልለት የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይቀር እየተቀየረ «ትኩረት ለአፍሪካ ቀንድ» በሚል እየተከለሰ መጥቷል። እነዚህን ዘላቂ ፍላጎቶች ለማሳካት ወደ እኛ ቀጣና፣ ማለትም ወደ ምሥራቅ አፍሪካ በሁለት መንገድ እየገቡ ይገኛሉ፤ በወታደራዊ የጦር ሰፈር ግንባታ እና የወደብ ልማት።
በአካባቢው በቢሊዮን ዶላሮች በወደብ ልማት እና በወታደራዊ ጦር ሰፈር ግንባታ ስም እየፈሰሰ ነው፡፡ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኤርትሪያ እና ጂቡቲ ደግሞ በእነዚህ አገራት መካከል በሚደረግ አሽቅድድም ትኩረት ያገኙ አገራት ናቸው፡፡
በርግጥ የዓረቦች ወደ አፍሪካ ቀንድ መምጣት አዲስ ነገር እንዳልሆነ በሳዑዲ ኢራን ፍጥጫ ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡት እና ከሦስት ዓመት በፊት «የአፍሪካ የግድብ ፖለቲካ የግጭት መነሻ» በሚል ጥናት ያቀረቡት ሀር ቬር ሆቬን እንደሚሉት፤ የአፍሪካ ቀንድ እና ዓረቦች በውል ያልተዋወቁ ጎረቤታሞች ናቸው። ዓረቦች እና የአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ ተዋንያን የቆየ የባህል እና የሃይማኖት ትስስር ያላቸው፤ ግን ደግሞ በስጋት ፖለቲካ በመታመስ ማዶ ለማዶ ሲተያዩ የከረሙ ጎረቤታሞች ናቸው፡፡
በስፋት ወደ ቀጣናው እየመጡ፣ የገንዘብ ዲፕሎማሲ እያስፋፉ ያሉት ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ናቸው። የዲፕሎማሲ ተንታኞች የሳዑዲን የአፍሪካ ቀንድ ፍላጎት እና የፖሊሲ አማራጮች ለመቅረብ ሲሞክሩ ወደ ኋላ ተጉዘው ንጉሥ ፈይሰል ላይ ያቆማሉ። እኝህ ንጉሥ የቀድሞ የሳዑዲ መሪ የነበሩ ሰው ናቸው። ንጉሡ የሳዑዲ የልማት ድርጅትን ለቻድ፣ ለሶማሊያ እና ሱዳን ድጋፍ ለመስጠት በሚል መስርተዋል። በኋላ ላይ ግን ድርጅቱ አድማሱን ወደ ሁሉም የቀጣናው አገራት አስፋፍቷል።
ሳዑዲ ወደ አፍሪካ ቀንድ የተመለሰችው እኤአ 2015 ንጉሥ ሰልማን በትረሥልጣናቸውን በያዙ ማግስት እንደሆነ በብዙዎች ይነገረል፡፡ የእሳቸው ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የመመልከት ምክንያቶች ሦስት ናቸው ይላሉ የፖለቲካ ታንተኞች፤ ኢራንን ከቀጣናው መግፋት፣ ለየመን ጦርነት ገዥ መሬት ማግኘት እና የቡድን 20 አባል አገራትን ጎራ የመቀላቀል ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት ናቸው፡፡
ወቅታዊው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የአፍሪካ ቀንድ ፍላጎትን በተመለከተ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ጉዳይ ተንታኞች በዋናነት አራት ነጥቦችን የሚያነሱ ሲሆን፤ የቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ እና የጦር ሰፈር ግንባታ፣ የወደብ ልማት፣ የናይል ወንዝ ውሃ ፍላጎት እና የሶማሊያ ደካማ የአገረ መንግሥትነት እና የሱዳን እና የኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ጉዞ ተዛማጅ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡
እኤአ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የእስያ አገራት የቀይ ባህር መዳረሻ ለማግኘት፣ ወደብ ለማልማት እና የጦር ሰፈር ለመገንባት ቢሊዮን ዶላሮችን እያፈሰሱ ነው፡፡ አህጉራዊ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ኅብረት የእነዚህን አገራት ፍላጎት ከኅብረቱ መርህ አንፃር ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ከኃያላኑ እስከ ትናንሽ አገራት ድረስ የጂኦፖለቲካ ገመድ ጉተታ በገቡበት ቀጣና እየመጣ ያለውን የደህንነት ስጋት ለመቅረፍ ኢትዮጵያ በምን መልኩ እየተዘጋጀች ነው የሚለው የሁሉንም ትኩረት እየሳበ ነው፡፡
የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ከጀርባ ያለው የኃያላኑ ሴራና እያስከተለ ያለው ስጋትም በቀጣናው ውጥረትን እያባባሰ ይገኛል። የዓባይ ቀጣናን የመቆጣጠር የረዥም ጊዜ ፍላጎት ያላት ግብፅ በሱዳን የእኔ ነው የምትለው እና የትሮይ ፈረስ ሆኖ የሚያገለግላት መሪ የማስቀመጥ የቆየ ፍላጎት እንደላት የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ አሁን በሱዳን ባለው ጦርነት ድብቅ ተሳትፎ አይኖራትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
በመሆኑም፣ በቀጣናው ካለው ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር አብሮ መራመድ በሚያስችል መልኩ በሁሉም ረገድ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል የሚለውን በመለየት ብርቱ ሥራ መሥራት ይጠበቃል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015