እንደምንመለከተው ከሆነ ዝናቡ ዛሬና ነገ የመቆም ምልክት የለውም። እንዳጋተ፣ ዳመናውን እንዳረገዘ፣ ነጎድጓዳማ ድምፁን በማሰማት፤ ሰዓቱን አክብሮ በመዥጎድጎድ ላይ ይገኛል።
ለአንዳንዶቻችን ክብደቱ ሀሳብ ላይ እየጣለን እንዳለው ሳይሆን የወቅቱ ዝናብ ፋይዳ በርካታ ሆኖም ተገኝቷል። ከዝናቡ ትሩፋቶች በመጀመር አንዳንድ ሀሳቦችን እናንሳ።
ከሰሞኑ የባለሙያዎች አስተያየቶች መረዳት እንደተቻለው የወቅቱ ዝናብ በርካታ ትሩፋቶችን ይዞ የመጣ ሲሆን፣ ሰሞኑን ይህ ጋዜጣ የተለያዩ ክልሎችን የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በማነጋገር “ዝናብ አጠር አካባቢዎችን ተስፋ ያሰነቀው የበልግ ዝናብ” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃው ሰፋ ያለ ዘገባ ለዚህ አስተያየታችን አንድ ራሱን የቻለ ጥሩ ማሳያ ነው።
“ከፊል አርሶ አደሮች መሬታቸው ጦም አድሮ፣ አርብቶ አደሮችም ለከብቶቻቸው የሚያጠጡት ውሃ አጥተው አይናቸው እያየ ከብቶቻቻውን አጥተዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም ለተረጂነት ተዳርገዋል። ለአራት ተከታታይ ዓመታት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የሚገልፀው ሐተታው፣ በአሁኑ ዝናብ ምክንያት “ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ ስርጭት ከተጠበቀው በላይ ነው። ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። በተሠሩት አነስተኛ ግድቦችም ውሃ በመያዝ የሚጠበቀውን ግብም ማሳካት ተችሏል።” ሲልም ያክላል።
“ከየካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከመካከለኛ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለመጣሉ በሚትዎሮሎጂ ጣቢያዎች መመዝገቡን” የሚነግረን ጋዜጣው በኦሮሚያ “ቦረናን ጨምሮ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ከ72 በላይ አነስተኛ ግድቦችን ለመገንባት በእቅድ ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል። ከፀጥታ መደፍረስና በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸው ከተስተጓጎለው በአራቱ የወለጋ አካባቢዎች ውስጥ ሊከናወኑ የታቀዱ ስምንት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋና ጉጂ አካባቢዎች በስተቀር በአጠቃላይ በክልሉ ሊከናወኑ ከታቀዱት አነስተኛ የግድብ ሥራ ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ 56 ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል። ከነዚህ ውስጥ ወደ 32 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በበልጉ የጣለውን ውሃ ይዘዋል። ከተከናወኑት ፕሮጀክቶች 14ቱ በቦረና ዞን የተሠሩ ሲሆኑ፣ ቀደም ሲል ከነበሩት ግድቦች ጋር ተደምረው በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ወደ 18 ግድቦች ይገኛሉ። በግድቦቹ የተያዘው ውሃም ከ20 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ በላይ ይገመታል።” ሲልም የወቅቱን የበልግ ዝናብ በሚገባ የመጠቀም ሁኔታ መኖሩን ይነግረናል። ይህ በሁሉም ክልሎች እየተደረገ ከሆነ እሰየው ነውና ሊበረታታ ይገባል።
ለእኔ ብጤዎች፣ ዝናቡ አይሏል ለምንለውም ጋዜጣው ከባለሙያ ያገኘውን መልስ ያጋራን ሲሆን “ዝናቡ በዝቷል ተብሎ እንደ ስጋት ለሚነሳውም ስጋቱ አንጻራዊ ሊሆን እንደሚችል፤ ስጋቱ የመጣውም ቀደም ባሉት አምስት የበልግ ተከታታይ ወቅቶች ከመደበኛ በታች ከነበረው ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል [. . .] ከዓመታዊ የዝናብ መጠን እስከ 55 በመቶ የሚሆነው የዝናብ መጠን የሚገኘው በበልግ ወቅት እንደሆነም” ተገልጿል።
ወደ ዛሬው ዐቢይ ጉዳያችን፣ ወደ ከተሞች እንመለስና ዝናቡን ተከትሎ እየሆነ፣ እየታየ ያለውን የከተሞችን እውነታ ከአዲስ አበባ አንፃር አለፍ አለፍ እያልን እንመልከት።
ምንም ጥርጥር የለውም፣ ዝናቡ ከባድ ነው። በተለይ የእኛን ከተሞች ለመሳሰሉ ክብደቱ ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ሁሉ ነው። በመሆኑም እዛም እዚህም አደጋዎች ሲያጋጥሙ እየታየና እየተሰማ ነው።
ከቅርቡ (እሁድ ዕለት) ብንጀምር እንኳን ቀጨኔ መድኃኒዓለም የቀብር ስፍራ አጥር ተንዶ የሁለት ሰዎች /በግ ሻጭና ገዥ/ እና ከመቶ በላይ በጎች ሕይወት አልፏል። እዛው አካባቢ ሲካሄድ በነበረ የሕንፃ ግንባታ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ወጣቶች (የቀን ሠራተኞች) አፈሩ በላያቸው ላይ ተደርምሶ የሁለቱ ሕይወት ወዲያው ከማለፉንም በላይ አስከሬናቸው የተገኘው ከቀናት ቁፋሮ በኋላ መሆኑ ችግሩን ውስብስብ አድርጎት ተመልክተናል ::
አንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎችም እንደዚሁ አይነት አደጋ በዚሁ ሰሞን ደርሶ እንደ ነበር የሚታወስ ነው። ከሳምንታት በፊት መርካቶ አካባቢ አንድ ከድንጋይ የተሠራ የድሮ ቤት ተደርምሶ ዙሪያውን ሲነግዱ ከነበሩት ነጋዴዎች ሕይወት አልፏል:: እንግዲህ እነዚህና እነዚህን መሰል አደጋዎች ብዛታቸው በርካታ እንደሚሆን ምንም መጠራጠር አይቻልምና ከአደጋው ራስን ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ ሊደረግ ይገባል ማለት ነው።
ሌላውና ከዝናቡ ጋር ተያይዞ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ የዛፎች ድንገተኛ መገርሰስ ነው። በተለይ ሰሞኑን በከተማዋ እየተስተዋለ እንዳለው እድሜ ጠገብ ዛፎች በቀላሉ እየተገረሰሱና ፍንግል እያሉ፤ ቤትና አጥር ብቻ ሳይሆን መኪኖች ላይ ሳይቀር ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። ይህ ቀስ እያለ ወደ የሰው ሕይወት ላይ አደጋ ወደ ማድረስ አይሸጋገርም ማለት አይቻልምና ከወዲሁ ሊታሰብበት የግድ ይላል። በነገራችን ላይ፣ እንዴት የዛፎችን የመውዲቂያ (የእርጅና) ዘመን ለይቶ በማወቅ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት፣ ከወዲሁ የሚያስወግድ አንድ ባለሙያ እንኳን ይጠፋል? ሁሌም የምናየው ራሳቸው ሲወድቁ እንጂ ባለሙያ አስቀድሞ ሲያስወግዳቸው አይደለም። ይህም ያሳስባልና ቢታሰብበት መልካም ነው።)
ሌላው ከሕንፃዎች ጋር በተያያዘ የተስተዋለው ችግር ነው። በአንዳንድ ፎቆች ስር ያሉ (መግቢያቸው ዘቅዘቅ ያሉ) የሕንፃ ስር መኪና ማቆሚያዎች በዝናብ ውሃ ተሞልተውና ጢም ያለ ሐይቅ ሠርተው ታይተዋልና ወደ ፊት የሚገነቡ ሕንፃዎች ግንባታ (እስካሁን ስለተገነቡት ምን መደረግ እንዳለበት ባላውቅም) ላይ ይህም ታሳቢ ቢደረግ ለማለት ነው። ሌሎቹን በሌላ ጊዜ እንመለስባቸዋለን።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015