የቅድመ ልጅነት በሰው ልጆች የሕይወት ዑደት ውስጥ በቀጣይ የሕይወት ዘመን ብሩህና አምራች ዜጋን ከማፍራት አንፃር ወሳኝነት አለው። ሳይንሱ እንደሚያመላክተው በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ወሳኝና አእምሮ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት የሚያድግበት ነው። ታዲያ በዚህ ፈጣን የዕድገት ለውጥ የተሻለ ምግብ፤ የጤና አገልግሎት፤ ሁለንተናዊ እንክብካቤና የትምህርት ዕድል መስጠት አስፈላጊ እንደሆነም ሳይንሱ ይጠቁማል። ይሄ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገትም ሆነ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት መስፈን የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ይጠቀሳል።
ይሁንና በቅድመ ልጅነት ዘመን የሚሠራው ሥራ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር እንደ ግለሰብ ጀምሮ እንደ አገር የጎላ ጉዳት ያስከትላል። በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው። ለአብነት ከጠቅላላው ሕፃናት 55 በመቶው የትምህርት ዕድልን አለማግኘታቸው ተጠቃሽ ነው። ሩቅ ሳንሄድ ባሳለፍነው ዓመት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ነጥብ አግኝተው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት ሦስት በመቶ ብቻ መሆናቸውም ሌላው ማሳያ ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ይሄን ታሳቢ በማድረግ ብሔራዊ የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ መርሐ ግብርን በሂልተን ሆቴል ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድ ገትና ትምህርት በአገራችን በፖሊሲ ማዕቀፍ ደረጃ ትኩረት አግኝቶ የተጀመረው በ2005 ዓ.ም ነው። ይሄን መሠረት አድርጎም በቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ረገድ ሁለንተናዊ የሕፃናት እንክብካቤ በጤና፤ በትምህርትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል። ለአብነትም ልጆች ደህንነቱ በተጠበቀ ምቹ አካባቢ እንዲኖሩ፤ በቂና የተመጣጠነ ምግብ በተጨማሪም ቀዳሚ ማነቃቃቶችና የቅድመ አንደኛ ወይም መደበኛ ክፍል ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ሲሠሩ ከነበሩት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ታዲያ በመድረኩ መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ስለ ቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ፋይዳ ‹‹በልጆች ዕድገትና ትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ማህበራዊ ፋይዳን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል›› ሲሉ ገልፀውት ነበር።
እንዳሉት በልጆች ዕድገትና ትምህርት ላይ ሙዓለ ንዋይ ማፍሰስ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ማህበራዊ ፋይዳን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል። ይህ የሙዓለ ንዋይ ፍሰት በልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት የሚደረገውን ጥረት ያማከለና ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። የልጅነት ዕድገትና እንክብካቤ ከጨቅላነት ጀምሮ አቀራረቡን ሁለንተናዊ በማድረግ ከልጆች ማህበራዊ፤ አካላዊ፤ ስሜታዊና መንፈሳዊ ደህንነት እንዲሁም የመማር ዕውቀት ገጽታዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ መንግሥት ሲቪል ማህበራት ወላጆች፤ ለጋሾችና ማህበረሰሰቡ በትብብር ሲሠሩ ነው። እንዲህ ዓይነት ጥረቶች ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፈውን የድህነት አዙሪት በማቋረጥ ሂደት ውስጥ የጎላ ድርሻ አላቸው። ለሁለንተናዊ የአገር ብልጽግናም መሠረት ይጥላሉ። ሁለንተናዊ የሕፃናት ልማት በሚተገበርበት ወቅት ትምህርት በቅንጅት ሥራና ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግሥት ለቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት ተገቢውን ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
‹‹የሕፃናት ሁለንተናዊ ልማት በአገሪቱ አጠቃላይ የሰው ሀብት ልማት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው››
ለዚህም መንግሥት ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲኖር ቅድሚያ ለሕፃናት በመስጠት ኢንቨስት እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። በልጆች ላይ የሚሠሩ ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተቀናጀ መልኩ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል ከገባው አንዱ የጤና መታወክ ተጋላጭ ለሆኑ በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ የሚገኘውን የቅድመ ትምህርትና የማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል ለሁሉም ሕፃናት ድጋፍና ዕድል በመስጠት የሕፃናትን ፍላጎት ማሟላት ነውም ብለዋል። ሁለንተናዊ ሕፃናት ዕድገት ውስጥ ከዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ትምህርት ሚኒስቴር የተሻለ የትምህርት አካባቢ በመገንባትና የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ትኩረታቸው ጥረቶችን በማስተባበር ሁሉንም ተሳታፊ በማድረግ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በተሻሻለው የፖሊሲ ማዕቀፍ እያንዳንዱ ልጅ ወደፊት አምራች ዜጋ እንዲሆን በሚደረገው ሂደት ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ወላጆች፤ ማህበረሰቦች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ቅድመ ትምህርትን ለማሻሻል የቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገትና ትምህርት አገልግሎት በመስጠት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና በግልጽ የሚረዳ መሆኑንም አውስተዋል። በቅድመ ልጅነት ዘመን ዕድገት በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሦስት በመቀጠልም በመጀመሪያዎቹ ሰባት ዓመታት የሚደረግ እንክብካቤና ጥበቃ ለሕፃናት ጤናማ ዕድገትና ለቀጣይ የሕይወት ዘመናቸው መሠረት የሚጥል በመሆኑ እጅግ ወሳኝ ነውም ብለዋል።
በዚሁ መድረክ በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የተወከሉት ዶክተር መሠረት ዘለዓለም እንዳሉትም በቅድመ ልጅነት ዘመን ለሕፃናት ጥሩ የጤና አገልግሎት በቂና የተመጣጠነ ምግብ፤ ደህንነትና ጥበቃ፤ ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ፤ ቀዳሚ ማነቃቃትና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል አለማቅረብ ሕፃናት በቀጣይ ሕይወት ምርታማ ዜጋ እንዳይሆኑ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። እንደ ተወካይዋ የተሻለ ሕይወት የመምራት ዕድላቸውን ያሰናክላል። የተለያዩ ጥናቶች የሚያመላክቱትን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፤ የቅድመ ልጅነት ዕድገትና መዳበር ላይ መሥራት እንዲሁም የሕፃናትን ጤና መጠበቅ በአካል፤ በአእምሮ በማህበራዊ ኑሮና በስሜት ክዋኔያቸው በዕድሜያቸው ሊደርሱበት በሚችሉት የላቀ የመዳበር ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል። ወደፊት ለሚኖራቸው ስኬታማ ሕይወትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለአገር መረጋጋት፤ የላቀ ዕድገትና ልማትም ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አለው። ቅድመ ልጅነት ላይ የታለሙ መርሐ ግብሮችን መተግበር የሰው ኃይል ካፒታል የመመለስ ትልቅ አቅም አላቸው። የቅድመ ልጅነት ዕድገት መዳበርና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ከጽንስ እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሕፃናትና ወላጆቻቸው ወይም ተንከባካቢዎቻቸው የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚያመላክት ሁሉን አቀፍ ፖሊሲና መርሐ ግብር አካቷል። በመሆኑም ሊተገበር የሚችልና አዋጭ እንዲሆን የፖሊሲው መተግበር የአገራችን ሕፃናት የተሻለና ጤናማ ሕይወት ጅማሬ እንዲኖራቸው አንድ እርምጃ ለመራመድ ያስችላል።
ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ ያግዛል። በድምሩ በቅድመ ልጅነት ዘመን ያለውን የአመጋገብ፤ የጤና፤ ደህንነትና ጥበቃ ምላሽ ሰጪ የተለያዩ ዘርፍ ተቋማትን ድጋፍ በብርቱ ይፈልጋል። የቅድመ ልጅነት ዘመን ያለውን የአመጋገብ፤ የጤና ደህንነትና ጥበቃ ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ ቀዳሚ ማነቃቃትና የቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎት ማዳረስና ማሻሻል ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማስገኘቱንም ገልፀዋል።
83 በመቶው የአገራችን ሕዝብ በገጠር መኖሩን ያወሱት ዶክተር መሠረት ‹‹ሁሉም ሕፃናት ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸው ብዬ አስባለሁ›› በቅድመ ልጅነት ፖሊሲ ማዕቀፍ ትግበራው ገጠር የሚኖሩ ሕፃናት ተጠቃሚ መሆን አለባቸውም ብለዋል። በተለይም በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደሩ ዘንድ ሥራው መስፋፋትና ወላጆችም ትግበራውን በዘላቂነት ማስቀጠል እንዳለባቸውም አመልክተዋል። እንዲህ ሲባል ከተሞች ላይ ያሉ ሕፃናት ተጠቃሚ መሆን የለባቸውም ማለት አይደለም። ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ያሉ ሕፃናት የግድ የትግበራው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ሁለንተናዊ ፍትሐዊነትን ማረጋገጥም አስፈላጊ ነው። ትምህርት፤ ጤና፤ ስነ ምግብ፤ የአካባቢ ደህንነት፤ አጠቃላይ ሁለንተናዊ ሁኔታቸው መጠበቅና ሕፃናት የቅድመ ልጅነት ዘመናቸውን እነዚህ በተሟሉበት ሁኔታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ለአገር ዕድገትም ሆነ ከድህነት ለመውጣት ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክትም በአገራችን በሕፃናት ዕድገት ዙሪያ የተሻሉ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ይሁንና አሁንም ገና ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለአብነት በተለይ በሕፃናት አስተዳደግ ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፤ በሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማሳያ ናቸው። በአገራችን በዕድገት ደረጃቸው ለሕፃናት ሊሰጡ የሚገቡ የቅድመ ልጅነት አገልግሎቶች አለመስፋፋታቸውም ሌላው ነው። ሦስተኛው ለልጆች ምቹና ተስማሚ መኖሪያ ለመፍጠር ያለመቻል፤ በዚህ ላይ የተጠናከረ የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓትም መጓደል፤ በነዚህና ሌሎች በርካታ እጥረቶች ምክንያት የቅድመ ልጅነት ዘመን ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተገቢው አያያዝ አልተደረገላቸውም። ባለተመቻቸ ሁኔታ የሚገኙ ናቸው። በዚህም ምክንያት ለተለያዩ ችግሮችና ጥቃቶች ለመጋለጥ ተዳርገዋል። መንግሥት በ2009 ዓ∙ም ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲ መሠረት የሕፃናት መብትና ደህንነት በማክበር፤ በማስከበርና ፍላጎታቸውን በማሟላት ረገድ እየወሰደው ያለው እርምጃ ይበልጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በሕፃናት መልካም አስተዳደግና ስብዕና ግንባታ፤ የቤተሰብ፤ የማህበረሰብና የመንግሥትን ሚና ለማሳደግ ተችሏል። ፖሊሲው የአገራችን ሕፃናት የቅድመ ልጅነት ዘመናቸውን በአግባቡ የሚያሳልፉበት ሁኔታ ለማመቻቸት መልካም ስብዕና የተላበሰ ዜጋ ማፍራት ይቻል ዘንድ የተቀናጀ ጥረትና ድጋፍ በተሻሉ የሕፃናት አስተዳደግ ዘዴዎች የቤተሰብ ተንከባካቢዎችና መምህራን ክህሎት ማሳደግ፤ የማህበረሰቡን ሚና ማሳደግ፤ የማህበረሰቡን ሚና ማጎልበት፤ ምቹና ተስማማሚ አካባቢን መፍጠር፤ የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓት ማጠናከር ፤ ለሕፃናት መልካም ዕድገት አስተዋጽኦ ያላቸው አገልግሎቶቹን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢማጅን ዋን ደይ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ማናጀር የሆነችው ወጣት ሀዊ ዓለሙ እንደተናገረችው፤ ድርጅቷ በ2030 ሁሉም ሕፃናት ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የማድረግ ጥረቱን ከጀመረ ዘንድሮ 16 ዓመቱን ይዟል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥራውን የጀመረበትን ትግራይ ጨምሮ በስድስት የአገራችን ክልሎች በተለይ በአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ልጆች ዙሪያ ብዙ ሠርተዋል። ከሥራቸው ዋናው በነዚህ በአርብቶና አርሶ አደር አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶችና የማህበረሰብ ክፍሎች ዘላቂ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸውና የልጅ አስተዳደግና አያያዝ አመለካከታቸው እንዲሻሻል ማድረግ ነው። ከገቡበት ክልል ዘላቂ የሆነ ለውጥ ሳያመጡ በፍፁም አይወጡም። በተለይ እነኝህን ሁለት ሁኔታዎች አሟልቶ መውጣት የኢማጅን ዋን ዴይ መርህ ነው። ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ጀምሮ በቁሳቁስ እስከማሟላትና የአካባቢውንና የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ አቅም እስከማጎልበት የሚሠሩት ሥራ ሦስት ዓመት እንደሚፈጅባቸውም ወጣቷ ነግራናለች። በዚህ አሠራር 946 ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ማድረግ ችለዋል። ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥም 123ቱን የገነባቸው ድርጅቱ ነው። በዚህም ከ175 ሺህ በላይ የትምህርት ቤት ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ሕፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉን ታነሳለች። ከ453 ሺ በላይ የሚሆኑ ሕፃናትን የሕፃናት ጥበቃና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረጉንም ታወሳለች። ትምህርት ቤቶችንና ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የንፁህ ውሃና የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ሕፃናት የቅድመ ልጅነት ዘመናቸውን በተመቻቸ ሁኔታና ሥፍራ እንዲያሳልፉ አድርገዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ እንደሚሉት ከተሻሻለው ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አንፃር የቅድመ ልጅነት ዘመን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው መቻሉን ያነሳሉ። ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በትምህርት ባለድርሻዎችና በሌሎች ቅንጅት እንዲተገበር መደረጉንም በማሳያነት ያወሳሉ። ይሄንና ሁሉንም ሕፃናት ተደራሽ አላደረገም ነበር። 55 በመቶው ሕፃናት የመማር ዕድል ሳያገኙ መቅረታቸውም ሌላው ነው።
«ወላጆች በቂ ግንዛቤ ኖሮን ጤናቸውን ጠብቀን አንልክም፤ የምንሰጠውም የትምህርት አገልግሎት ውጤታማ አልነበረም›› ያሉት ኃላፊው የፖሊሲ ማዕቀፉ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ሊፈታ በሚችል መልኩ የተቀመጠ መሆኑን ያወሳሉ። እንደሳቸው ፖሊሲ ማዕቀፉ ወደ ቅንጅታዊ ትግበራ ሲገባ ልጆች ጤንነታቸው ተጠብቆ ምግብ በአግባቡ አግኝተው ያደርጋሉ። ይሄን ካገኙ አስተሳሰባቸው የተሻለ ይሆናል። በዚህ ልክ የመጡ ሕፃናት ዕድሜያቸው አራት ዓመት ሲሆን ጥራት ያለው ትምህርት ቤት ውስጥ ይገቡና አገልግሎቱን ያገኛሉ። ወደ ቤት በሚመለሱበት ጊዜ ደህንነታቸው ይጠበቃል። የትምህርት ጥራት የመሻሻሉም በጣም ከፍተኛ ይሆናል። ትምህርት ቤቶች ምቹ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ ለማስቻል የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በቅርቡ ይፋ ይሆናል።
እኛም ሁሉም አካላት በዚህ መልክ ተቀናጅተው በቅድመ ልጅነት ዘመን ላይ ቢሠሩ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ተነቃቅተው ይመጣሉ፤ በአግባቡ ይመገቡና ጤናቸው ይጠበቃል፤ እንደ አገር ያሰብንበትም በመድረስ እድገታችንን በዘላቂነት መሥራት እንችላለን በማለት ጽሑፋችንን ቋጨኝ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015