
የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ ጭማሪ አደረገ። አሁን የተደረገው ጭማሪ ባለፉት 16 ዓመት ከተደረገው ሁሉ ከፍተኛው ነው ተብሏል። ማዕከላዊ ባንኩ እርምጃውን የወሰደው ዋጋን ለማረጋጋት በሚል ነው።
የፌዴራል ሬዘርቭ የወለድ ምጣኔን የጨመረው በ0 ነጥብ 25 ፐርሰንት ነው። ይህ ጭማሪ በ4 ወራት ለ10ኛ ጊዜ የተደረገ ነው። የወለድ ምጣኔ ጭማሪው በዓለም ትልቁ ምጣኔ ሃብት ላይ ለተበዳሪ ወጪን የሚጨምር ነው። ይህም ማለት ሰዎች ከባንክ ሲበደሩ ወለዱ ከፍተኛ ይሆንባቸዋል።
በተለይም ከባንክ ተበድሮ ቤት የመግዛትን አማራጭ በወለድ ምጣኔው ከፍተኛነት የተነሳ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ይህም ምናልባት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባንኮች መንኮታኮት መጀመራቸውን ተከትሎ የመጣ ውሳኔ ሳይሆን እንዳልቀረ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለባንኮች መንኮታኮት አንዱ የሚነሳው ችግር ያለ በቂ ዋስትናና ጥንቃቄ ለቤት ገዢዎች ገንዘብ ማበደራቸው ነው። የፌዴራል ሪዘርቭ ሊቀመንበር ጄሮም ፖል ይህ ጭማሪ ለጊዜው የመጨረሻው ይሆናል ብለዋል። ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔ ጭማሪን ከፍ እያደረገ የመጣው በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የዋጋ ንረት መባባስን ተከትሎ ነበር።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ ብቻ ሳይሆን የዩኬ እና የአውሮፓ ባንኮችም የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ተመሳሳይ እርምጃን ወስደዋል። ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ተመን ቤት በባንክ ብድር መግዛትን አስቸጋሪ ከማድረጉም ባሻገር ለቢዝነስ ማስፋፊያም ሆነ ሌሎች የብድር ጥያቄዎች ደንበኞችን አያበረታታም። ይህም በኢኮኖሚው ላይ የራሱን ጥላ ማጥላቱ አይቀርም።
ይሁንና ይህ የብድር ምጣኔ ተመን ጭማሪ ሽቅብ
እየተመዘገበ ያለን የዋጋ ንረት ለማቀዝቀዝ ሁነኛ መፍትሄ ነው። የፌዴራል ሪዘርቭ የብድር ምጣኔ ተመን ጭማሪ ማደረጉን ተከትሎ በአሜሪካ የዋጋ ንረት መረጋጋትን አሳይቷል። በመጋቢት ወር የዋጋ ንረት (ዋጋዎች የሚጨምሩበት ደረጃ) 5 በመቶ ነበር። ይህም በሁለት ዓመት ውስጥ ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ነገር ግን ለፌዴራል ሪዘርቭ ይህ አሐዝ አጥጋቢ የሚባል አልሆነም። 5 በመቶ የዋጋ ንረት ወደ 2 በመቶ እንዲወርድ ይፈልጋል።
የወለድ ምጣኔ ተመን ጭማሪ ብድርን የማያበረታታና ቢዝነስ እንዲስፋፋ አሉታዊ ሚና ያለው ቢሆንም የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት ከፍተኛ ሥራን በመፍጠር ይበል የሚያሰኝ ውጤትን ባለፉት ቅርብ ዓመታት አሳይቷል። ባለፈው የካቲት ወር ብቻ የአሜሪካ ኢኮኖሚ 311ሺህ ሥራ ፈጥሯል። የሥራ አጥ ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ 3 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ነው። በጥር ወር ደግሞ የሥራ አጥነት ምጣኔ 3 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን ይህም ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ በ50 ዓመታት ዝቅተኛ ሆኖ መመዝገቡን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015