ከትናንት በስቲያ አንድ ወጠምሻ የፈነከተኝን የግንባሬን እሽግ ላስፈታ ክሊኒክ ቁጭ ብያለሁ። ተራዬ ደርሶ ስሜ እስኪጠራ ድረስ አጠገቤ ካለች ህጻን ልጅ ጋር እዳረቃለሁ።
‹ምን ሆነህ ነው? ሽቅብ አንጋጣ በፋሻ የታሸገ ግንባሬን እያየች ጠየቀችኝ።
‹ተጋጭቼ ነው› አልኳት።
‹ከምን ጋር?
‹ከግንብ ጋር..›
‹ግንቡ ፈረሰ?
‹አልፈረሰም!
‹እና?
‹እናማ እኔ ፈረስኩ። ፈርሼ ነጭ ኩታ ተከናንቤ አታይኝም፣ ከላይ ጥቁር ከታች ነጭ የጃፓን ባንዲራ መስዬ› አልኳት።
ሳቀችብኝ..ቂቂቂ..። ንጹህ ሳቅ፣ ነውር የሌለበት ፈገግታ አደመጥኩ። ከወንበሯ ጠጋ ብላ ጭኔ ላይ ደገፍ አለች..። በእጇ አገጬን እየነካካች ‹አይዞህ እሺ! አለችኝ።
ነፍሴን ሰጠኋት። ነፍስ የሚሰጠው እንደእሷ ላሉ ለንጹህ ነፍስ የሚሆን የተቀደሰ ቦታ ላላቸው አንዳንዶች እንደሆነ በመሀይምነቴ ውስጥ የማውቀው እውነት አለ። የውሻ ቁስል ያድርግልህ ብለው መልካም ምኞታቸውን ከገለጹልኝ የቅርብና የሩቅ ወዳጆቼ በላይ የእሷ እውነት አሻለኝ። ህመሞቻችን ሳይሆኑ የሚያሙን ከህመሞቻችን ጀርባ ያሉ ልክ ያልሆኑ ስሜቶች እንደሆኑ ደረስኩበት። ንጽህናዋ እንዲጋባብኝ ወደአምላኬ ጸለይኩ። ሰው በልጅነቱ እንደ እግዜር ነበር እላለው። ይሄን እውቀቴን የሚሽር እውቀት እስካሁን አላገኘሁም። ስንወለድ እግዜርን ሆነን እንወለድና በሂደት አለም ለራሷ እንድንመቻት ሰው ታደርገናለች።
ሰውነት ከአምላክነት ቀጥሎ የምናገኘው ሁለተኛው ጸጋችን ነው። መጀመሪያችን አምላክነት ነበር። ክፋት በልጅነት የምናገኘውን አምላክነታችንን የምናጣበት ሂደት ነው። ሀጢዐት በውልደት የተዋሃደንን ጸጋችንን የምናሳድፍበት ነው። ይቺ ህጻን ገና አምላክነቷ ከውስጧ ተጠቃሎ አልወጣም። ቢወጣ ኖሮ በዙሪያዬ ተቀምጠው እንደማያቸው አዋቂ ሰዎች በዝምታ ‹ምን ሆኖ ይሆን? አላርፍ ብሎ አንዱ ደብድቦት ይሆናል። ይገባዋል! አርፎ አይቀመጠወም ነበር? ምን አቅለበለበው..› የምትል ትሆን ነበር። ግን መጥታ እንደ ጌታ አገጬን እየነካካች በብዙ ማባበል አይዞህ አለችኝ።
ወደ ወጠምሻው ሸፈትኩ። አምላክነት ከውስጡ ተንጠፍጥፎ አልቆ በሰይጣንነት ብቻ የቀረ ስል ስም ሰጠሁት። ለጠየቀኝ ሁሉ ከግንብ ጋር ተጋጭቼ ነው እላለው። እንዴትም ባስብ ያን ወጠምሻ ከግንብ ውጪ የምገልጽበት ቃል የለኝም። ድብድብ ልዩ ተሰጥኦው ይመስላል። ደረቱን ገልቦ፣ ክንዱን አፈርጥሞ ሲንገዋለል ላየው የሚፈልገኝ ካለ ይምጣ የሚል ነበር የሚመስለው። እኔስ መች ቀረልኝ! በየትኛውም መንገድ ቢታይ ለቡጢ በማይበቃ ጠብ ነው ግንባሬን የተረከከኝ። መላኩ ይተርክከውና።
አሁን ያ የሚያስመታ ነበር? እላለው እንዴት እንደደበደበኝ ትውስ ሲለኝ። ህልሜ ድረስ መጥቶ ሲዝትብኝ ነው የሰነበተው። የማዝነው ያን ሰውነት፣ ያን ወንድነት ባሌ ብላ አቅፋው ለምትተኛው ሴት ነው። ምን ብሏት ይሆን ፍቅረኛው ያደረጋት? እንዴት ቀርቧት፣ ምን ነግሯት አመነችው? እላለው ግራ ሲገባኝ። ወንዶች በሴቶች ላይ እንደፈለግን የምንሆነው በደካማ ጎናቸው በኩል ነው። መጀመሪያ ቀን አፈር አይንካሽ ሲል ያለችበት እየሄደ አገኛት። በሚቀጥለው ቀን ያለበት እንድትመጣ የምትወደውን ነገር አዘጋጅቶ እንደሚጠብቃት አበሰራት።
የሚቀጥሉትን ቀናት ምን አይነት የተባረከ ሰው አገኘሁ እስክትል ድረስ አጋንትነቱን ደብቆ መላዕክት መስሎ ቀረባት። ቀጥሎ የሚነግራትን ሁሉ አመነችው። እጁ እስክትገባ ድረስ ሁሉንም ሆነላት። እንዳመነችው ሲያውቅ ወደራሱ ተመለሰ..ወደ አውሬነቱ። ይሄ ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር የወንዶች ሴቶችን የማማለያና የማጥመጃ የተደገመና የተደጋገመ ግን ደግሞ ሴቶች ከመሸነፍ የማይድኑበት መላ ነው። ምን ይታወቃል ጉልበቱን ተጠቅሞ ሳትፈልግ እንድትፈልገው አስገድዷትም ይሆናል ስል በማያገባኝ ገብቼ ብዙ ዘባረኩ።
እንደ አፌ ደመኛ የለኝም።አፉ የማያርፍ ሰው ታውቃላችሁ? እንደዛ ነኝ። በማያገባኝ መግባት ተሰጥኦህ ምንድነው ስባል የምመልሰው መልሴ ነው። ሳልደበደብ ወይም ሳልገላመጥ ቤቴ ገብቼ አላውቅም። የሰውነቴ አብዛኞቹ ጠባሶች በምላሴ በኩል የተዋወቁኝ ናቸው። በትንሽ ነገር እኮ ነው የቀጠቀጠኝ። ብነግራችሁ አታምኑም.. ግን ልንገራችሁ። በተቀመጥኩበት በቅርብ አቅራቢያ ላይ ምን እንደገጠመው እንጃ አንድ ወጠምሻ በንዴት ወዲያ ወዲህ ይላል። እየተቀመጠና እየተነሳ፣ መሬቴን በርግጫ እየደለቀ፣ የፊትለፊቱን ጠረጴዛ በጡጫ እየነረተ ጥርሱን የሚነክስ ወጠምሻ።
ሰዐቱን ደጋግሞ ያያል፣ ደጋግሞ ይደውላል፣ ተደጋግሞ ይደወልለታል። ከአፉ በሚወጣው የብልግና ስድብ ተነስቼ ሴት እየጠበቀ እንደሆነ ገባኝ። ይደውልና እስኪበቃው ደንፍቶ ስልኩን ይዘጋባታል። መልሳ ትደውልለታለች..ሰድቦና አንቋሾ የምትለውን ሳይሰማ ደግሞ ይዘጋዋል። ላረፈደ ልብ ይሄ ሁሉ ዱላ ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው? ምን አይነት ሴት ትሆን እንደዛ እየተሰደበች የምትደውልለት፣ ምን አይነት ሴት ትሆን እንደዛ እየተሰደበች ወደ እሱ የምትመጣው? ስል ራሴን እጠይቃለው። ይቺን ሴት ለማየት ጓጓሁ።
በተቀመጥንበት መናፈሻ ለበሩ የቀረብኩት እኔ ነበርኩና ከርቀት አንዲት ቆንጆ ሴት በጥሩ አለባበስ፣ ስጋት ባጠላበት ፊት ወደ መናፈሻው ስትገባ ተመለከትኩ። ይቺን ከሆነ እንደዛ የሰደባት እግዜር ዛሬውኑ መምጣት አለበት፣ ያለዛ እንደ ኒቼና ኦሾ የለም ስል እክደዋለው አልኩ። እውነት እላለው አይደለም ያን ያክል ስድብ ቀርቶ ቁጣ እንኳን የማይገባት አይነት ናት። እሷ ባልሆነች ስል ሆና ተገኘች።
አልደረሰችም እኮ! ገና ከርቀት ‹ውዴ ታክሲ እኮ አጥቼ ….! ቃሉን አልጨረሰችውም እንዴት እንደተነሳ መላኩ ይወቀው ወፍራም መዳፉን ፊቷ ላይ አሳረፈው። ዘልዬ መሀል ገባሁና…‹እንዴት ሴት ትመታለህ? ባለጌ ነህ› ማለቴን አስታውሳለው..ከዛ በኋላ የሆነውን አላስታውስም። ማታ ነው የመናፈሻው በር ሊዘጋ አቅራቢያ ራሴን ከሳትኩበት የነቃሁት። በቃ ይሄው ነው።
እዛ መሀል መግባት ያለእድሜ መቀጠፍ እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነው። ለዛ መዳፍ መዳረግ ኒውክሌርን በጨበጣ መግጠም እንደሆነ ጠባሳዬን ከታቀፍኩ በኋላ ነው የተገለጠልኝ። ችግሩ ብዙ ነገሮች የሚገቡኝ ከተፈነከትኩና በቃሬዛ ቤቴ ከገባሁ በኋላ ነው። ቀድሞ የገባኝ ምንም ነገር የለም።
አጠገቤ ወዳለችው ህጻን ዞርኩ። የመጫወቻ አሸንጉሊቷን ጸጉር እየሰራች አገኘኋት። ሀሳብ ከቀለለኝ ብዬ ከእሷ ጋር መጫወት አማረኝ። ህጻናት ሀዘን ማስረሻዎች እንደሆኑ የገባን ጥቂቶች ነን።
‹አንቺ እዚህ ምን እያደረግሽ ነው? ስል ወሬ ጀመርኩ።
‹ከእህቴ ጋር መጥቼ ነው› አለችኝ።
‹እህትሽ አሟት ነው?
‹ቢኒ ደብድቧት ልትታከም› አለችኝ።
ምንድነው ነገሩ ታሪኬ ሁሉ ከድብድብ ጋር ተዛመደሳ አልኩ በውስጤ። ቀጥዬ ‹ቢኒ ማነው..? አልኩ።
‹ባሏ ነው› አለችኝ በህጻን አንደበት።
አገጭዋን እየነካካሁ ‹አይዞሽ እሺ! አልኳት።
በጭንቅላቷ እሺ አለችኝ። ይሄ በሆነ በወዲያው አንድ ሴት ፋሻ በፋሻ ሆና ከፊት ለፊታችን ካለው ክፍል ስትወጣ አንድ ሆነ። ነፍሴ ትርክክ አለች..። ባለፈው በማያገባኝ ገብቼ የተፈነከትኩላት ልጅ ናት። ከዛ መዳፍ ተርፋ ድጋሚ ለመቀጥቀጥ መብቃቷ አስደነቀኝ። እኔን በምኑ እንደነካኝ ሳላውቅ ቀን ሙሉ ያስተኛኝ እሷን እንዴት አድርጓት ይሆን ስል ሳስብ ነበር።
በጣም አዘንኩ..። መላኩ ከረዳኝና እንደ ዳዊት ቢኒን የምጥልበትን አቅመ ወንጭፍ ከሰጠኝ ቀጣይ እቅዴ ቄስ ይጥራውና ቢኒን ከእሷ መለየት ይሆናል ስል ጥርሴን በመንከስ አረጋገጥኩ።
ያን ወጠምሻ ደፋሪ ጉልበተኛ መጥፋቱ እያንገበገበኝ ወደወጣችበት ክፍል እሽጌን ላስፈታ አመራሁ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2015