ስሜ ገነት ነው “My name is Genet ” የተሰኘውን ፊልም በዳይሬክተርነት ያዘጋጀው ሚግዌል ጎንዛሌዝ የተባለ ሰው እንዲህ አለ፤ «በፊልም ልንናገር በምንመርጠው ታሪክ፤ ለውጥ ለመፍጠር የሚያስችል ግንዛቤና ማኅበራዊ ንቃት መፍጠር እንችላለን» በጎንዛሌዝ የተዘጋጀው ይህ ፊልም ዲግሪ ለመያዝ የመጀመሪያ ስለሆነችው መስማትና ማየት የተሳናት ኢትዮጵያዊት የሚተርክ ነው።
ይኸው ፊልም የፊታችን ሚያዝያ 22 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄደው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ላይ ለዕይታ ከሚቀርቡ ፊልሞች መካከል ሆኗል። ዘጋቢ ፊልሞችን በተለየና በበለጠ ትኩረት የሚያቀርበው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ነው ከተለያዩ የዓለም ክፍላት የተውጣጡ ፊልሞችን በአንድ ሳምንት ቆይታ ለዕይታ የሚያቀርበው።
የፌስቲቫሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክቡር ገና፤ ይህ የፊልም ፌስቲቫል በአፍሪካ ደረጃ የላቀ ድርሻ ያለውና በዕድሜም ይሁን በጥራት ከፍ ያለ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ እንደምን ነው ቢሉ የዶክመንተሪ ፊልም ፌስቲቫል በአፍሪካ ደረጃ ሲዘጋጅ ከዕድሜው አንፃር ገና ለጋ የሚባል ቢሆንም፤ የአዲስ ፊልም ፌስቲቫል የ13ዓመታት ያልተቋረጠ ጉዞና በየሂደቱ የሚያሳየው ውጤት ቀዳሚ አድርጎታል።
አቶ ክቡር መለስ ብለው ሲያስታውሱ፤ አዲስ ፊልም ፌስቲቫል አጀማመሩ ሰብአዊ መብት ላይ ያተኮረ ነበር። በአጀማመሩም «የሰብአዊነት ፌስቲቫል» የሚል ይዘት የነበረው ሲሆን፤ በብዙ ውጣ ውረድና መንገድ አልፈው እያንዳንዱ ግለሰብ መብቱ እንዲከበርለትና እንዲጠበቅለት ትግል የሚያደርጉትን የሚያሳዩ በዓለም ዙሪያ የተሠሩ ዘጋቢ ፊልሞች የሚታዩበት መድረክ እንዲሆን ነበር ዓላማው።
«ነገር ግን ቀደም ሲል በወጣው የበጎ አድራጎት ሕግ መሰረት፤ ልናገኘው የምንችለውን ድጋፍ ለማግኘት ስላልቻልን ፌስቲቫሉን ካሰብነው ሰፋ በማድረግ በጠቅላላው ፊልም ፌስቲቫልነት እንዲቀጥል ሆኗል።» አሉ አቶ ክቡር፤ ዘንድሮ ግን በፌስቲቫሉ ለዕይታ ከሚቀርቡ ፊልሞች መካከል 80 ከመቶ በላይ ፊልሞች ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ናቸው።
ፌስቲቫሉ ከዓመት ዓመት እያደገ መሄዱን አያይዘው ገልፀዋል። ይህም በአንድ በኩል ለዕይታ የሚቀርቡ ፊልሞች ጥራት መሻሻልን በማሳየቱ የሚገለጥ ነው። በተጓዳኝ በፌስቲቫሉ የሚታዩና ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆነው የሚገኙ ፊልሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑት ናቸው። ይህም ፌስቲቫሉ ትኩረት መሳብ ለመቻሉ ምስክር ነው።
በዘንድሮው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ላይ፤ ከመላው ዓለም ከተላኩ ከ450 ፊልሞች መካከል 60 ፊልሞች ሰብአዊነትን መሰረት በማድረግ ተመርጠዋል። በአገራችን የተሠሩ 14 አጫጭር ፊልሞችም ይሳተፋሉ። በተጨማሪም ለዘጋቢ ፊልም ሠሪዎችና የሚመለከታቸው ሊሳተፉበት የሚችሉ አውደ ጥናቶችም ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
ፊልም ፌስቲቫሉ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ከኢትዮጵያ አልያም ከአፍሪካ ለሆኑ ፊልሞች ነው። ታዲያ በዘንድሮውም እነዚህ 60 ፊልሞች ለዕይታ የተመረጡት ከሰብአዊ መብት ጋር መያያዛቸው፣ የዘጋቢ ፊልምን አሠራር የተከተሉ መሆናቸው ተረጋግጦና ጥራት እንዲሁም ወቅታዊነታቸው ሁሉ ታይቶ ነው።
አቶ ክቡር አሉ፤ «የዚህ ፌስቲቫል አንዱ ዓላማ ህዝብን ከፊልሞች ጋር ማገናኛት ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎችን ማስተዋወቅና ፌስቲቫሉ ከታየ በኋላ ፊልሞቻቸው ወደሌላ ፌስቲቫል ቀርበው በዛ ደግሞ የተለየ ሽልማትና እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ነው።»
ታድያ ይህንን ተከትሎ በፌስቲቫሉ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ ዘጋቢ ፊልሞችን የሠሩ ዳይሬክተሮችን በመጋበዝ የልምድ ልውውጥ እንደሚኖረውም ነው አቶ ክቡር የገለፁት። በዚህም መሠረት ተጋብዘው ልምዳቸውን ለማካፈል አስር የፊልም ዳይሬክተሮች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ከእነርሱም ጋር ውይይትና ምክክሮች ይኖራሉ።
ፌስቲቫሉ የፊልም ባለሙያዎች የሚገናኙበትን ዕድል ከመፍጠር፣ ልምድ ልውውጦችን ከማመቻቸት፣ የአገር ውስጥ ፊልሞች ለውጭ ዕይታ እንዲቀርቡ በማድረግ በኩል ጠንክሮ ይሥራ እንጂ፤ ከዚህ ውጭ የተለየ ድጋፍ እንደማያደርግ አቶ ክቡር ገልፀዋል። «እውቅና እንሰጣለን።» ብለዋል።
«የዘንድሮውን ፌስቲቫል ከቀደመው የሚለየው ነገር ይኖር ይሆን?» ለአቶ ክቡር የቀረበ ጥያቄ ነው። እርሳቸውም እንዳሉት የዘንድሮው ፊልም ፌስቲቫል ትኩረቱን ዳግም ወደ ሰብአዊ መብት አድርጓል። ፌስቲቫሉ የተጀመረ ጊዜ በአገራችን ስለ ሰብአዊ መብት መናገረና መጻፍ ብዙም የተከለከለ አልነበረም። በኋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ። ከበጎ አድራጎት ሕጉ ምቹ አለመሆን ጋር ይህ ተደምሮ ፌስቲቫሉ በታሰበው መልክ መሆኑ ቀረ።
«መጀመሪያ አካባቢ ከዲሞክራሲና ከሠላም እንዲሁም ከሰብአዊ መብት ጋር የሚገናኙ ሥራዎችን ነበር የምንሠራው። በኋላ ላይ ቀርቶ ነበር። የአሁኑ ጊዜ ግን የበለጠ ለማሳወቅ የምንችልበት ወቅት ላይ ነን ብዬ ነው የማስበው።» አሉ የፊልም ፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ክቡር። ለዕይታ የሚቀርቡት አብዛኞቹ ዘጋቢ ፊልሞችም የሌሎች ትግል እንዴት ተነሳ፣ የት ደረሰ የሚለውን የሚያሳዩና ማሳየት የሚችሉ ናቸው።
በዓመት ብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፊልሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሠራሉ። ሰው ሁሉንም ማየት አይችልም፤ ነገር ግን የፊልም ፌስቲቫሎች በባለሙያ ዓይን የተመረጡ ፊልሞችን ያቀርባሉ። ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆዩ ፊልሞችም የሚታዩት እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሲፈጠር ነው። ታዲያ ግን እንደተባለው ፌስቲቫሉ እውቅና ይሰጣል እንጂ ውድድር የለውም።
አቶ ክቡር እንዳሉት፤ የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ደረጃ ሰጥተው ፊልሞችን ለማወዳደር ፈልገው ነበር። ለዕይታ ከቀረቡ ፊልሞችም መካከል በፊልም ባለሙያዎች ዕይታ እንዲሁም በተመልካች ምርጫ ምርጥ የተባሉትን የመሸለሙም ነገር መጀመሪያ ላይ ተካሂዷል። ነገር ግን የተለያዩ ውዝግቦችና አለመግባባቶችን ሲመለከቱ እንደቀረና፤ «ነገሩን በደንብ እስክናጤን ብለን ትተነዋል (አቆይተነዋል።» የአቶ ክቡር አስተያየት ነው።
አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ እንደሌሎቹ በግለሰብና በጥቂት ሰዎች ጥረት እንደሚካሄዱት በቁጥር ሦስት እንደማይሞሉት የፊልም ፌስቲቫሎቻችን ሊደነቅ የሚገባው ነው። ይህም ደግሞ ከሌሎቹ በበለጠ የአፍሪካ አገራትን በማቀራረብና በአፍሪካም ቀዳሚና አንጋፋ ሆኖ በመሥራቱ ከዓመት ዓመት ይበል ማለታችን አይቀርም።
ከዚህ ባሻገር ለሥራው አንድ ዓይነት አደረጃጀት እንዲኖርና በታሰበው ልክ ውጤታማ ለመሆን የመሠረተ ልማት ጥያቄም ይነሳል። አቶ ክቡር እንዳሉት፤ ከሦስት ዓመት በፊት ለግንባታ የታሰበ አንድ ህንፃ አለ። ይህንንም አዲስ አበባ መሐል ለመሥራት የሚመለከታቸውን ዳግም እየጠየቁ መሆኑንና ጥሩ ምላሾች እንደተገኙ አያይዘው አንስተዋል።
በታሰበው መንገድና መልኩ ከተሠራ ግንባታው ከ70 እስከ 90 ሚሊየን ዶላር ሊፈጅ ይችላል። «ወጪውን ፈርተን ግን ይህን አንሠራም አንልም።» ያሉት አቶ ክቡር፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ መልሶና አብልጦ የሚከፍል በመሆኑ፤ ከተባበርንና ከተሰባሰብን፤ ገቢውም ብሩን የሚመልሰው ስለሆነ ብዙ አያስጨንቅም ብለዋል።
በ1999 ዓ.ም በጣሊያን ባህል ማዕከል 11 ፊልሞችን በማሳየት የጀመረው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ የ13 ዓመት ልጅ ሆኗል። የተቋም ዕድገት የግድ እንደ ሰው ልጅ የሚያዘግም ባለመሆኑም፤ የሚደነቁ ዕድገቶችና መሻሻል የሚገባቸው ድክመቶችንም አስተናግዷል።
እናብቃ! የዘንድሮው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ከሚያዝያ 22 እስከ ሚያዝያ 27 / 2011ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። በሚኖረው የስድስት ቀን ቆይታም፤ የተባሉትን የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ፊልሞች በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሱስ፣ በቫምዳስ መዝናኛ ማዕከል፣ በአገር ፍቅር ቴአትር፣ በጣሊያን ባህል ማዕከል እና በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ይካሄዳል። ሠላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሊድያ ተስፋዬ