«የኢትዮጵያ እና የግብጽ ዲሎማሲያዊ ግንኙነት ከጥንት እስከ አሁኑ ዘመን» የሚለው መጽሐፍ በደራሲ ግርማ ባልቻ ተጽፏል። በአሥራ ሰባት ምዕራፎች፤ በአራት መቶ ሃምሳ ገጾች የተዘጋጀው ይሄ መጽሀፍ 200 ብር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለት ለንባብ የበቃ የደራሲው ሁለተኛው ስራ ነው። የመጀመሪያ ስራው “የናይል እና የግብጽ ይዞታ” የሚል ሲሆን ዛሬ ለመጽሐፈ አስተውሎት የመረጥነው ግን የሁለተኛ ስራውን ውጤት ነው።
መጽሐፉ ምን ይዟል?
የአገሮች ግንኙነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ በንግድ፣ በባህል፣በወታደራዊና ሌሎች መስኮች ይታይ ነበር። የአንዳንድ አገሮች ግንኙነት ደግሞ በንግድ ላይ ብቻ ይመሰረታል፤ የሌሎች ደግሞ ባህል ላይ ሊመሰረት ይችላል። በሌላ በኩል ሁሉንም አጣምሮ የሚይዝ የንግድ እና የባህል ግንኙነት መሠረት አድርጎ የሚፈጸም ሊሆን ይችላል። ከባህል መገለጫ አንዱ የሆነው ሃይማኖት የመንግስታት የግንኙነት መሳሪያ ወይም መገልገያ በመሆን የአገራቱን ግነኙነት የሚያስተሳስር ወይም በተጻጻሪው የጠብ እና የግጭት መንስኤ ሲሆን ተስተውሏል።
መጽሐፉ ስለቀደምት የኢትዮዽያ እና የግብጽ ነባራዊ ግንኙነት እጅግ ጥንታዊና ከሰው ልጅ ታሪክ ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያትታል። እነዚህ ሁለት አገሮች በጋራ የሚጋሩት ድንበር የሌላቸው ቢሆንም ግንኙነታቸው ግን በፍራቻ የታጠረ እንደነበር ያስታውሳል።
ለዚህም ደራሲው በመጽሐፋቸው ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ። የመጀመሪያው “ኢትዮዽያ በናይል ወንዝ ላይ ግድብ በመስራት ወደ ታችኛው ተፋሰስ አገሮች የሚፈሰውን የውሃ መጠን በመቀነስ የግብጽን ህልውና ፈተና ውስጥ ትጨምራለች” የሚል ሲሆን ሁለተኛው እና ዋናው ብሎ መጽሀፉ የሚያነሳው ደግሞ “በፋትሚድ ስርወ መንግስት እአአ በ1090 አካባቢ የናይል ወንዝ ፍሰት በእጅጉ ቀንሶ በታየበት ወቅት የግብጽ ሱልጣን ለኢትዮጵያውያን ነገስታት የላከው ደብዳቤ” መሆኑን ታሪኩን ይጠቅሳሉ።
በ1970ዎቹ መጨረሻ ከዘጠኝ መቶ ዓመታት በኋላ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት የካምፕ ዲቪድን ስምምነት ከእስራኤል ጋር በተፈራረሙበት ወቅት
“ግብጽ ከእንግዲህ ወደ ጦርነት የምትገባ ከሆነ ከውሃ ችግር ጋር በተያያዘ ምክንያት ብቻ ነው።” በሚል ያደረጉት ንግግር የአገራቱ ግንኙነት ለረጅም ዘመናት ስጋት እና ጥርጣሬ መሆኑን የሚያመላክቱ አብነቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።
ሁለተኛው በአገራቱ ግንኙነት ላይ ስጋትን ሲጥል የኖረው ችግር ከአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባት ትሰይም ከነበረችው የአሌክሳንደሪያዋ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ጋር አንድ አቡን (ጳጳስ) ሲሞት ተተኪ አቡን ለማስመጣት በሚደረግ ጥረት ዙሪያ ይፈጠር የነበረውን ፖለቲካዊ ውዝግብ ሲሆን ይህም እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ በአገራቱ ግንኙነት ላይ ሲያሳድር የነበረው ተፅዕኖ ነው።
ከእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ውጪ የሁለቱ አገራት ግንኙ ነት ተካርሮ ጣራ የነካበት ወቅት በዋናነት ግብጽ በሱዳን እና በቀይ ባህር ዳርቻዎች አካባቢ ታደርጋቸው ከነበሩ የግዛት ማስፋፋት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ውዝግብ ነበር። በዚህ የግብጽን አፍሪካ ኢምፓየርን የመፍጠር ህልም ይዞ የተነሳው ቃዳፊ አስማኤል ባካሄደው ወረራ አገራቱ ከአንዴም ሁለቴ ወደ ጦርነት የገቡ ሲሆን በውጤቱም በግብጽ ጦር ሽንፈት መደምደሙን ያሳያል።
የአክሱማውያንን ውድቀት ተከትሎ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የኢትዮጵያ ነገስታት ያካሂዷቸው የነበረው የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ዘይቤ የመስቀል (ሃይማኖት) ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገ እንደነበር ይጠቁማል። በወቅቱ የነበረው መንግስታዊ መዋቅርም በስርዓት ተቀርፆ የሚመራ እንዳልነበረም ያትታል። ይህ መርህ አልባ አመራር ደግሞ በውጭ ግንኙነት ረገድ በአመዛኙ የሚከታተል ፣ የሚመራ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል በእጅጉ ዝቅተኛ አልነበረም ብሎ ማለት የሚያስችል ነበር።
መጽሐፉ ከላይ ላነሳቸው ጉዳዮች ማሳያዎችን ያስቀመጠ ሲሆን “ኢትዮጵያ በግብፆች ላይ የተቀዳጀችው የጉንደት እና የጉርዐ እንዲሁም በጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው የአድዋ አንፀባራቂው ወታደራዊ ድሎች በዲፕሎማሲያዊ መስክ የተደገፉ አልነበሩም። በወታደራዊ መስክ የተገኘውን ድል ተጠቅሞ በዲፕሎማሲያዊ መስክ በተሸናፊው ሃይል ላይ ጫና በመፍጠር የድርድር መድረኮች ተጠቅሞ የላቀ ውጤትን ማምጣት ሲቻል ባክነው የቀሩ የታሪክ አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል።” የሁለቱ አገራት ግንኙነት ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ከመሆኑም አንፃር ይህን መፅሐፍ ለማዘጋጀት እጅግ ፈታኝ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፤ የመፅሐፉና የጸሐፊው ዋና አላማ የአገራቱ ግንኙነት ያለፈበትን ሂደት በማጥናት ለአንባቢያን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በማሰብ የተዘጋጀ እንጂ የታሪክ ተመራማሪዎችን ስራ ለመሻማት ሃሳቡም፣ ፍላጎትም እንዲሁም እውቀቱም የለውም። በመሆኑም መፅሐፉ ታሪክ ቀመስ እንዲሆን ሁኔታዎች አስገድደውታል።
ፀሐፊው በግብፅ በዲፕሎማትነት ያሳለፉቸው የስድስት ዓመታት ቆይታ በርካታ እውነታዎችን ለመገንዘብ እና ለመረዳት እድል አግኝተዋል። በዋነኛነት እአአ ከ2006 እስከ 2010 ባሉት ጊዜያት የናይል ተፋሰስ አገሮች የወንዙን አጠቃቀም አስመልክቶ ያካሄዷቸው ድርድሮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ከመሆኑ አኳያ መፅሐፉን ለማዘጋጀት የሚረዱ በርካታ ፅሁፎች በግብጽ ጋዜጦች ይወጡ ስለነበር ለመረጃ ምንጭነት በማገልገል ለፅሁፍ የጎላ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
ለመፅሐፉ ጥንካሬ ሊሰጡ የሚችሉ በግብፅ ጸሃፍት የተዘጋጁ መፅሐፎች የሌላውን ወገን ታሪክ እና አሠራር እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በግብፅ ግንኙነት ዙሪያ የሚራመዱ አስተሳሰቦችን ለመረዳት ያበረከቱት አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው።
የሰው ልጆች እውቀት በየጊዜው እየሰፋና እየዳበረ እንደሚሄድ የታወቀ ነው፤በመሆኑም በስልጣኔና በቴክኖሎጂ በማደግ ላይ ባለችው አለማችን የሰው ልጅ የእውቀት አድማስ ከዚህ ቀደም የነበሩ እውቀቶችን በአዳዲስ ግኝቶች መበልፀጉ የማይቀር ጉዳይ ነው።
የዚህ መፅሐፍ ዝግጅት ተጠናቆ የመጨረሻውን ቅርፅ የማስያዙ ስራ እየተከናወነ ባለበት ወቅት በመሪራስ አማን በላይ ተዘጋጅቶ የቀረቡ “የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ” የሚል መፅሐፍ በፀሐፊው እጅ ገብቶ የማየት እድል አግኝቶ ነበር። ከዚህም ቀደም ሲል በመፅሐፉ በጥቅል ያስቀመጣቸውን አንዳንድ ሃሳቦች በዝርዝር የሚያብራራ ሆኖ በመገኘቱ አዳዲስ ግንዛቤዎችን ፀሐፊው መጨበጥ ችሏል።
ይህ መፅሐፍ የታሪክ ምርምር የማድረግ አላማን ይዞ የተነሳ ባለመሆኑ የሰው ልጆች ስልጣኔ የጀመረው በኢትዮጵያ ነው ወይስ በግብፅ? ክርስትናን መጀመሪያ የተቀበለችው ኢትዮጵያ ናት ወይስ ግብፅ? የኢትዮጵያ ነገስታት የግዛት አድማሳቸው ግብጽን ጨምሮ መካከለኛው ምስራቅን በሚጠቀልል መልኩ የነበረ ሰፊ ግዛትን ያስተዳድሩ ነበር ወይስ ዛሬ በምናየው መልኩ ነበር? የሚሉ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ትቶ አንባቢያን የየራሳቸውን እውቀት እና ግንዛቤ ጨብጠው፤ ፀሐፊው ሊያነሳቸው የፈለጋቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ታሪካዊ ሂደት ትኩረት አድርገው እንዲያነቡ የሚጋብዝ ነው።
ዛሬ በላይኛው ግብጽ እና በሰሜን ሱዳን ሰፍረው የሚገኙ የኑባ ህዝቦች የኩሽ ዝርያ ያላቸው እና ከጥንት ኢትዮጵያውያን ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንደነበራቸው ይታመናል። የመፅሐፉ ፀሐፊ በግብፅ በነበረው ቆይታ አስዋን በመባል የሚታወቀውን አካባቢ የመመልከት ዕድል አግኝቶ ነበር። በወቅቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በነበረው ግንኙነት ፍፁም ኢትዮጵያዊ ገጽታ ፣ ሰፋፊ አጥንቶች እና ረጃጅም ቁመና ያላቸውን ሰዎችን ማየት ችሏል። እነዚህ ሰዎች በአገራችን ከሚገኙ ማህበረሰቦች ጋር ያላቸው ተመሳሳይነት አግራሞትን እንደፈጠረበትም ያትታል።
በአጠቃላይ በመፅሐፉ ኢትዮጵያ እና የግብፅ ከክርስቶስ ልደት በፊት እና በኋላ ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚያስቃኝ ሲሆን ከአክሱም ዘመነ መንግስት ወድቀት ጀምሮ የተነሱ አዳዲስ ሁነቶችንም በምልሰት ያስቃኘናል። በተጨማሪም የሰለሞን ስረወ መንግስትን ከግብጽ ማሙለካውያን መንግስተ ሱልጣኔቶች ጋር ያለውን የታሪክ ግንኙነት ይነግሩናል። በኢትዮጵያ የተነሱ መሪዎች ማለትም ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፤ ከግብፅ ደግሞ ከመሃመድ ዓሊ እስከ አብዱልፈታህ አልሲሲ ያለውን በናይል እንዲሁም በአገራቱ የተካሄዱትን የተለያዩ ስምምነቶችና ትብብሮች እንዲሁም ዙሪያ ገብ የሆኑ ጉዳዮችን እያነሳ ያስነብበናል።
በዚህ መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ሳደርግ ከመጽሐፉ ገጽና ምዕራፍ እየጠቀስኩ ማስቀመጡ ምቹ አልነበረም። ምክንያቱም የቱ ተጠቅሶ የቱ ይቀራል? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን አስተውሎት ነው። በዚያ ላይ መጽሐፉ የስነ ጽሑፍ መጽሐፍ ቢሆን የሃሳብ ልዩነትም ይኖር ነበር። ስለዚህ ማለት የሚቻለው መጽሐፉ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ዲሎማሲያዊ ግንኙነት ከጥንት እስከ አሁኑ ዘመን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ አንባብያን እንዲያነቡት እንጋብዛለን።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ