በአዲስ አበባ ከተማ የተሽከርካሪ ብዛት እየጨመረ ይገኛል። ከተማዋ ይህን የተሽከርካሪ ብዛት ታሳቢ ያደረገ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ሳይኖራት ዓመታትን አሳልፋለች። የመኪና ማቆሚያ ቦታ በበቂ ሁኔታ አለመኖር በመኪና ባለቤቶች፣ በመኪናዎች እንዲሁም በከተማዋ ነዋሪዎች የእለተ እለት እንቅስቃሴ ላይ ተግዳሮት ሲፈጥር ቆይቷል።
ይህን ችግር ለመፍታት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ህንጻ ገንቢዎች በምድር ቤታቸው የመኪና ማቆሚያን ታሳቢ ያደረገ ግንባታ እንዲያካሂዱ እየተደረገ ነው። ከተማዋ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችን ወደ መገንባት መግባቷም ይታወቃል።
ቀደም ሲል በመገናኛ፣ በመርካቶ አንዋር መስኪድ አካባቢ የመኪና ማቆሚያዎችን መገንባታቸው ይታወሳል። ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ደግሞ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በመስቀል አደባባይና በአንድነት ፓርክ አካባቢ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ የመኪና ማቆሚያዎች በምድር ውስጥ ተገንብተዋል። ከፍተኛ ወጪ በመመደብ ነው ግንባታው የተካሄደው። የመስቀል አደባባይ የመኪና ማቆሚያ አንድ ሺህ 400 መኪናዎችን፣ የአንድነት ፓርክ መኪና ማቆሚያ ደግሞ አንድ ሺህ መኪናዎችን ማቆም ያስችላሉ።
ሁለቱ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የመኪና ማቆሚያ ችግር የማስታገስ አቅም ቢኖራቸውም፣ በከተማዋ ካለው የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጥረት አንጻር ችግሩን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፉ ግን አይደሉም። በከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ከፍተኛ በሆነባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የመኪና ማቆሚያዎችን መገንባት የግድ ነው።
የከተማዋ አስተዳደርም ይህን ታሳቢ ያደረገ የመኪና ማቆሚያ ግንባታ በሾላ ገበያ አካባቢ እያካሄደ ነው። በከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት የሚካሄደው የዚህ የየካ -2 የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ተወካይ መሃንዲስ ኢንጂነር ደስታ ግደይ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ አረንጓዴ ስፍራን ጨምሮ በሰባት ሺህ 247 ስኩዬር ሜትር ስፋት ላይ እየተገነባ ይገኛል።
የመኪና ማቆሚያው ከመሬት በታች እና ከመሬት በላይ እየተሰሩ ባሉ ወለሎች ከ920 እስከ አንድ ሺህ ተሽከርካሪዎችን እና የተወሰኑ የንግድ ሱቆችን ማካተት እንዲችል ተደርጎ አየተገነባ ሲሆን፤ የግንባታ አፈጻጸሙም እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2015 ዓ.ም 43 በመቶ ደርሷል።
የመኪና ማቆሚያውን በፊት የአዲስ አበባ የኮንስትራክሽን ቢሮ በባለቤትነት ሲያስገነባ ነበረ፤ ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ወደ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተዘዋውሯል። ፕሮጀክቱ ወደ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ከመዘዋወሩ በፊት ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳልተከናወነ የሚያስታውሱት ኢንጂነር ደስታ፤ በተለይም ግንባታው በሚካሄድበት ቦታ የነበሩ ሰዎችን ለማስነሳት ጊዜ መውሰዱን ይናገራሉ። በመሃል በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ተቋርጦም እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በፕሮጀክቱ ላይ ማሻሻያ መደረግ ስለነበረበትም በ2022 ግንቦት ወር ወደ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት መጥቷል ነው የሚሉት። ፕሮጀክቱ ከቢሮው ወደ ጽህፈት ቤቱ እስኪዘዋወር በአምስት ዓመት ውስጥ የግንባታ አፈጻጸሙ 22 በመቶ እንደነበር አንስተዋል። ወደ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ሲዘዋወር በ24 ወራት ወይም በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኢንጅነር ደስታ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከዓመታት በፊት ሲጀመር በግማሽ ቢሊየን ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ግንባታው ተቋርጦ ወደ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ተላልፎ ግንባታው ዳግም ሲጀመር የግንባታው ወጪ ወደ 1 ነጥብ 19 ቢሊየን ከፍ ብሏል።
የአገሪቱና የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ለስሟ በሚመጥን መልኩ ውብ ለማድረግ የየካ- 2 መኪና ማቆሚያን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው ከፍ ያለ ነው የሚሉት ኢንጂነር ግደይ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታም ይህንኑ ትልም ለማሳካት በሚረዳ አኳኋን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሾላ ገበያ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ ባለመኖሩ መኪናዎችን በመንገዱ ግራና ቀኝ ማቆም የተለመደ መሆኑን የሚናገሩት ኢንጂነሩ፤ በዚህም ምክንያት መንገዱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጨናነቀ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ የመኪና ማቆሚያ ለከተማዋ ውበት ከመጨመሩ ባሻገር በሾላ ገበያ አካባቢ ያለውን የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጥረት በመቅረፍ የትራፊክ ፍሰትን ያሳልጣል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በመገንባት ላይ ከሚገኙት ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ፕሮጀክት የተወሰኑ የመኪና ማጠቢያዎችንም ያካተተ የመኪና ማቆሚያ ህንጻ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር ደስታ፤ መኪና ማቆሚያው የራሱ ዘመናዊ የጥበቃ ካሜራዎች የሚገጠሙለት እንደመሆኑ የመኪና ባለቤቶችን ስጋት የሚያስወግድ ምቹና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ይላሉ።
የመኪና ማቆሚያው በአገራችን እምብዛም ያልተለመዱ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመዱ የመጡ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ የሚደረግበት ሲሆን፣ ከእነዚህ ቴክኖሎጂዎች መካከል መኪናዎችን ወደላይና ወደታች የሚያንቀሳቅሱ አሳንሰሮች እንደሚገጠሙለት አስታውቀዋል። አሳንሰሮቹ በዋናነት በመኪና ማቆሚያ ለመጠቀም ችግር ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ተሽከርካሪዎችንም ለማንቀሳቀስ ያስችላሉ ተብሏል።
የየካ 2 መኪና ማቆሚያን ጨምሮ አብዛኞቹ የመኪና ማቆሚያዎች ግንባታ በቻይና ኩባንያዎች መሰራታቸውንና በመሰራት ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ኢንጂነር ደስታ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በግንባታው ላይ ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ዜጎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር እውን ለማድረግ እድል ይፈራል ብለዋል። በቀጣይ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የመኪና ማቆሚያዎችን ይገነባሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የጋራ ርብርብ የፕሮጀክቱ ግንባታ ደግም ነፍስ እንዲዘራ ማስቻሉን የጠቆሙት ኢንጂነር ደስታ፣ ከከንቲባዋ ጀምሮ እስከ ወረዳ አመራር ባሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የሚደረገው ክትትል እና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ወደ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ከተዘዋወረ ወዲህ ጥሩ መሻሻል እንደታየበት ገልጸው፤ ሆኖም በተያዘለት የጊዜ ገደብ በመሄድ ረገድ የተወሰነ መጓተት እንዳለበት አስታውቀዋል። ፕሮጀክቱ በዚህ ወቅት 50 ነጥብ15 በመቶ ሊጠናቀቅ ይገባ ነበር የሚሉት ኢንጂነር ፍስሃ፤ በሆነ ፐርሰንት ወደኋላ መቅረቱንም ጠቁመዋል።
ኢንጂነር ፍስሃ፣ በፕሮጀክቱ ላይ የተወሰነ መጓተት እንዲከሰት ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶችንም ጠቅሰዋል። የመኪና ማቆሚያው የሚገነባበት ቴክኖሎጂ እንደ አገር በፓርኪንግ ደረጃ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፖስትቴንሺንስ በሚባል መሳሪያ እንደሚገነባም ጠቁመዋል። ለፖስቴንሺን የሚውል ገመድ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ አገር እንደሚገባም ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ እንዲጓተት ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ይህንን ገመድ ከውጭ የማስገባት ሂደት ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ነው ብለዋል።
የግብኣት እጥረትም አንዱ ችግር እንደነበር ኢንጅነሩ ጠቅሰዋል። የሲሚንቶ እና የብረት እጥረት ሲያጋጥም ነበር። በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ውስጥ ሲፈጠሩ የነበሩ የዋጋ መዋዠቆችም በፋይናንስም ሆነ በቁስ አቅርቦት ላይ ጫና አድርሰዋል ሲሉም ገልጸው፣ አሁንም ባለው ሁኔታ የሲሚንቶ አቅርቦት መኖሩ ሳይረጋገጥ ስራ ለመስራት አስቸጋሪ ሆኗል። በአንድ ጊዜ በብዛት መያዝ ስለሚያስፈልግ በብዛት ነው የሚገባው ይላሉ።
እንደ ኢንጅነር ፍስሃ ገለጻ፤ በገበያ ውስጥ ፒፒሲ እና ኦፒሲ የተሰኙ ሁለት የሲሚንቶ አይነቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ለመኪና ማቆሚያው ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውለው ኦ ፒ ሲ የተሰኘው የሲሚንቶ አይነት ነው። ይህ የሲሚንቶ አይነት በገበያ ውስጥ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም። ይህም በፕሮጀክቱ ላይ የራሱን ጫና አሳድሯል። የብረት አቅርቦት ችግር ሌላኛው ነው። የብረት አቅርቦትም የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል። ይህም ሌላኛው ተግዳሮት ነው።
ፕሮጀክቱ በጥራት እንዲሰራ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው። ከዚህ በፊት በአገራችን ውስጥ ባልተለመደ መልኩ አንዳንድ ለግንባታው የሚውሉ ግብአቶች ፍተሻ የሚካሄደው ከአገር ውጭ በዱባይ ነው። ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ ይወስዳል፤ በአሁኑ ወቅት ግን ለግንባታው በጣም አስፈላጊ እና ውድ የሚባሉ ቁሶች ተፈትሸው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል። በመሆኑም ለግንባታው ከሚውሉ ቁሳቁስ ጥራት አንጻር የሚያሰጋ ነገር አይኖርም።
ኮንክሪቱን በተመለከተ በየሜትር ኪዩቡና በየጊዜው የጥራት ፍተሻ ይሰራል። በላብራቶሪ እየተጣራ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ የኮንክሪት ጥራት ቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ የግንባታው ባለቤት የሆነው የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤትም ሆነ ኮንትራክተሩ ለፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም ኢንጅነር ፍስሃ ጠቅሰው፣ በተለይም ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ የሲሚንቶም ሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቶሎ እንዲፈታ እያደረገ ነው ብለዋል።
የወሰን ማስከበር ችግሮች የሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ባደረገው ርብርብ ተፈትተዋል። በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያም ኮንትራክተሩም የሚያስፈልጉትን ይጠይቃል። ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱም ጥያቄው አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ያደርጋል ያሉት ኢንጅነር ፍስሃ፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የሲሚንቶ እጥረትና የመሳሰሉ ውጫዊ ችግሮች ላይ ጫና ካልፈጠሩ በስተቀር ፕሮጀክቱ አሁን እየተገነባበት ባለው አካሄድ በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።
ኢንጅነር ፍስሃ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት እየጨመረ ካለው የኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚጠቀሙ መኪናዎች አንጻር በመኪና ማቆሚያው ውስጥ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታ ቢኖር እጅግ ተመራጭ ነው። ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ሲጀመር የኤሌክትሪክ ቻርጅ የሚጠቀሙ መኪናዎችን ቻርጅ ማድረጊያ ቦታ ታሳቢ ሳይደረግ ግንባታው እየተካሄደ ነው። በፕሮጀክቱ ባለው ክፍት ቦታ ኤሌክትሪክ ቻርጅ ተጠቃሚ መኪናዎች ቻርጅ የማድረጊያ ቦታ ቢገነባ ዘመኑ ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር ፋይዳው የጎላ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2015