የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲናዋ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤት መገኛዋ አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስና ለነዋሪዎቿና ለእንግዶቿ፣ ምቹ ለመሆን መሥራቷን አጠናክራ ቀጥላለች፤ ለእነዚህ አገልግሎቶች ብቁ የከተማ ቁመና እንዲኖራት ለማድረግ በብርቱ እየተጋች ትገኛለች።
በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የግሉ ዘርፍ ከሚያደርጋቸው ግንባታዎች በተጨማሪ የከተማዋ አስተዳደር የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳለጥ የላቀ ትርጉም የተሰጣቸው የበርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ማካሄዱን ተያይዞታል።የከተማ አስተዳደሩ ይህን የሚመራ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት አቋቁሞም ነው ሥራውን እያካሄደ ያለው። ከተማዋ ከፕሮጀክቶቹ መካከልም ጥቂት የማይባሉትን አጠናቃ ለአገልግሎት አብቅታለች፤ አብዛኞቹን ደግሞ አጋምሳለች፤ አዳዲሶቹንም ጀምራ ግንባታቸውን እያጣደፈች ትገኛለች፡፡
ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የገቡት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገፅታ ከመቀየርና ውብ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪዎቿ ዘመናዊ እና ምቹ አገልግሎት እየሰጡም ይገኛሉ።ሌሎቹም ይህንኑ የሚከተሉ ይሆናሉ።
ፕሮጀክቶቹ ለነዋሪዎቿና እንግዶቿ ከሚሰጡት አገልግሎት ባለፈ፤ በፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከፍተዋል።ከዚህም ባሻገር በጉልበት ሥራ ተቀጥረው የሚሠሩ ዜጎች የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፤ ወጣቶች በጉልበት ሥራ ተቀጥረው በሚሠሩባቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች የእለት ጉርሳቸውን ከማግኘት አልፈው በግንበኝነት፣ በፌሮ ሥራ፣ በአናፂነት፣ በግንባታ ማሽን አንቀሳቃሽነትና መሰል ሌሎች በርካታ የሥራ ዘርፎች ላይ የሙያ ባለቤት የሚሆኑበት እና የተሻለ ገቢ ማግኘት የሚችሉበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።ይህም የፕሮጀክቶቹ ሌላው ሰው ተኮር ገፅታቸው ነው።
የዝግጅት ክፍላችንም በከተማዋ ተግባራዊ እየሆኑ ባሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመዘዋወር ዜጎች በኮንስትራክሽን ሥራው ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ መረዳት ችሏል።በጉልበት ሥራ ተቀጥረው ከሚሠሩ የቀን ሠራተኞች መካከል ወጣት ደምሴ ዋቤ አንዱ ነው።ወጣት ደምሴ የግብርና ምርቶች ማከማቻ እና መሸጫ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ድርጅት ውስጥ የጉልበት ሠራተኛ ሆኖ ሠርቷል።አሁን ደግሞ በግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከል የግንባታ ሥራዎች በተፈጠረለት እድል ተጠቅሞ በጠራቢነት እየሠራ በቀን 200 ብር እያገኘ መሆኑን ጠቁሟል።
“በዚህ ሳይት በቀን ሠራተኛነት ስሠራ በሙያ ተቀጥረው ለሚሠሩት ሰዎች ክፍያው ከፍ ያለ ስለሆነ አንድ ሙያ ማወቅ አለብኝ ብዬ በማሰብ የጠራቢነት ሥራ የሚሠሩ ሙያተኞች ረዳት ሆኜ በመሥራትና ሙያውን ለማወቅ ባለኝ ጉጉት በአጭር ጊዜ ውስጥ ልምድ መውሰድና ሥራውን በደንብ መሥራት ችያለሁ›› ሲል ወጣቱ ይገልጻል።የሙያ ባለቤት መሆን የቻልኩትም ሥራውን ቶሎ ለመማር ካለኝ ፍላጎት ባሻገር በዋናነት አብሬያቸው የምሠራቸው ሙያተኞችና የሥራው ተቆጣጣሪዎች ባደረጉልኝ የሙያ ድጋፍና ማበረታቻ ነው ይላል፡፡
ወጣት ደምሴ ቀደም ሲል በኮንትራክሽን ሥራዎች ድርጅት በቀን ሠራተኝነት ሲሠራ የፌሮ ሥራ ሙያተኛ በመሆን አገልግሏል።በዚህም በቀን 150 ብር ይከፈለው ነበር።አሁን ደግሞ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ባገኘው ልምድ በጠራቢነት የሙያ ባለቤት በመሆን በቀን የ200 ብር ተከፋይ መሆን ችሏል።
ሌሎች በርካታ ግለሰቦችም በተለያዩ የከተማዋ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመረጃ ሰብሳቢነት፣ በአናፂነት፣ በግንበኝነት እና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ጥሩ የሚባል ልምድ መቅሰም መቻላቸውን እና በኑራቸውም ጥሩ መሻሻል እንዳመጡ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
በግንባታ ፕሮጀክቱ በተፈጠረው የሥራ እድል የቀን ሠራተኞች የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የሙያ ሥልጠና ይሰጥ እንደሆን ለማወቅ በኦቪድ ኮንስትራክሽን የኮልፌ ቀራኒዮ የግብርና ምርቶች መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከል ግንባታ መሐንዲስ ኢንጂነር ሙሉጌታ ጠየቅናቸው።እሳቸው እንዳሉት፤በኮልፌ ቀራኒዮ ሳይት ለ33 ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል።ለቋሚዎቹ ረዳት ሆነው ለሚሠሩ 35 ወጣቶች ተጨማሪ ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሯል።በቀን ሠራተኝነት ደግሞ ለ330 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።
ከሥራ እድል ፈጠራው ጎን ለጎን በተለይም የቀን ሠራተኞች ሙያቸውን እንዲያሳድጉ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ይገልጻሉ።በዚህም እንደየሙያ ዘርፉ በደንብ የሚንቀሳቀሱ የጉልበት ሠራተኞችን ረዳት በማድረግና ሥልጠና በመስጠት ወደ ፌሮ፣ ግንበኛ፣ ማሽን ኦፕሬተርና ሌሎች ሙያዎች የማሳደግና ወደ ተለያዩ ሙያዎች የማሠማራት ተግባር እንደሚከናወን ኢንጂነር ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡
ሙያውን እንዲያሳድጉ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የሥራ ባሕልን ለመቀየር በትኩረት እየተሠራ ነው የሚሉት ኢንጂነር ሙሉጌታ፤ ከዚህ ቀደም በዋናነት የተለመደው የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት ነው።ኦቪድ ኮንትራክሽን ግን የግብርና ምርቶች ማከማቻ እና መሸጫ ማዕከላት ግንባታ በቀን በፈረቃ እስከ 16 ሰዓት እያሠራ ነው።በዚህ ሂደት ውስጥ በፕሮጀክቱ ውስጥ እየሠሩ ያሉ ተቋራጮችም ሆኑ የቀን ሠራተኞች የሥራ ባሕላቸው እየተቀየረ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ፕሮጀክት አስተባባሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ጉርሜሳ ረታ እንዳሉትም፤ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት በከተማዋ በሦስት ቦታዎች እየተገነቡ ባሉ የግብርና ምርቶች መሸጫና ማከማቻ ማዕከላት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በቀን ሠራተኝነት ከመሥራት ባሻገር ሙያቸውን እንዲያሳድጉ፣ እውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡
ከቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት የትልቅ ማዕከል ግንባታ ለሀገር በቀል የኮንትራክሽን ድርጅት የተሰጠበት ዋነኛው ዓላማም የሀገር በቀል ድርጅቶችን አቅም ማሳደግ፣ በስሩ የሚሠሩ ሠራተኞችን የሙያም፣ የእውቀትም አቅም ለማሻሻል ነው ያሉት ኢንጂነር ጉርሜሳ፤ ሀገር በቀል ኮንትራክተሮችን አቅም ለማሳደግ በሚል የተላለፈው ውሳኔ ፍሬያማ መሆኑን ጠቅሰዋል።ሀገር በቀል ድርጅቶች ትላልቅ ፕሮጀክቶች የመገንባት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ይላሉ፡፡
የውጭ ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ከሥራቸው የሚሠሩ ንዑስ ተቋራጮችን ከራሳቸው ሀገር የማምጣት ልምድ እንደነበራቸው የሚጠቅሱት ኢንጂነር ጉርሜሳ፤ በዚህም ሀገር በቀል የግንባታ ተቋራጮች ተጎጂ ነበሩ ይላሉ። አንዳንድ የውጭ ተቋራጮች ሠራተኛም ጭምር ከውጭ ሀገራት አምጥተው ያሠራሉ።ይህም ሀገሪቱ ላይ ከሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ጫና ባሻገር በቀጣይ አቅም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ ነው ነው ሲሉ ያብራራሉ። የግብርና ምርቶች መሸጫና ማከማቻ ማዕከላትን እየገነባ ያለው ተቋራጭ ግን በስሩ ሌሎች ሀገር በቀል ንዑስ ተቋራጮችን ቀጥሮ ለአነስተኛ ሀገር በቀል ተቋራጮችም አቅም እየፈጠረ፣ እርስ በርሳቸው እየተማማሩ፣ ቴክኖሎጂዎችን እያላመዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ኢንጂነር ጉርሜሳ ማብራሪያ፤ ሀገር በቀል ድርጅቶች በቀጣይ እጅግ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንም ለመገንባት የሚያስችል ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው።ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያንን ቀጥሮ እያሠራ ነው።በዲዛይኑም፣ ፕሮጀክቱን በመምራትም፣ በግንባታም ኢትዮጵያውያን ናቸው እየሠሩ ያሉት።በመሆኑም በፕሮጀክቱ ግንባታ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችም እውቀትና ቴክኖሎጂዎችን እየቀሰሙ ነው።የማያውቁትን እንዲማማሩ፣ አቅም እንዲያሳድጉ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡
ሠራተኞች ሙያቸውን እንዲያሳድጉ የሚደረገው ጥረት ከግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ፕሮጀክት በተጨማሪ በሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የፕሮጀክቶቹ ሥራ አስኪያጆች ገልጸዋል።
በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ማስተዋል ኃይለክርስቶስ እንደተናገሩት፤ ድርጅታቸው በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ በትኩረት እየሠራ ነው።በቀን ሥራ የሚገቡ ሠራተኞች ወደ ሚያዘነብሉበት ሙያ እንዲያተኩሩ ይበረታታሉ።ከዚህም ባሻገር በየጊዜው ሙያቸውን እያሳደጉ እንዲሄዱ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል።አሁን ባሉበት ፕሮጀክት ላይ ተቀጣሪ ሆነው እየሠሩ ቢሆንም በቀጣይ የራሳቸውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲስ አረጋይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል።በ2013 ዓ.ም ለ2ሺ 016 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።በ2014 ደግሞ ለ2ሺ836 ሰዎች በ2015 ደግሞ ከ4ሺ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።በአጠቃላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት 8ሺ380 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።እነዚህ የሥራ እድሎች በተቋራጮቹ እና በአማካሪዎች የተፈጠሩ ሙያዊ እንዲሁም በመለስተኛ ደረጃ በማሽኖች ኦፕሬተርነት፣ በግንበኝነት፣ በለሳኝነት፣ በቀለም ቀቢነት፣ በፌራዮ፣ በጥበቃ፣ በፈታሽነት የሥራ መስኮች የተፈጠሩ ናቸው።
ከተጠቀሰው 8ሺ380 የሥራ ዕድል በተጨማሪ በግንባታ አካባቢዎች ኢ-መደበኛ የሥራ እድሎችም ተፈጥረዋል።የመኪና ማቆሚያ የፓርኪንግ አገልግሎቶችን በመስጠት፣ በተላላኪነት፣ በሊስትሮነት፣ በፕሮጀክት አካባቢዎች ተጠግተው የሚሠሩ በርካቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።ፕሮጀክቶቹ ሳይመረቁ በሂደት ላይ እያሉ እንኳ የፈጠሩት የሥራ እድል ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አዲስ፤ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ደግሞ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የሥራ እድል ከመፍጠራቸው ባሻገር በፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑት በርካቶች ከቀን ሠራተኝነት ተነስተው የሙያ ባለቤት መሆናቸውን አቶ አዲስም ገልጸዋል።በርካታ የቀን ሠራተኞች ከአሠሪዎቻቸው እውቀት እየቀሰሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የቀሰሙትን እውቀት ተጠቅመው ከቀን ሠራተኝነት ወደ አናጺነት፣ ፌራዮነት፣ ለሳኝነት ተሸጋግረው የተሻለ ገቢ ማግኘት የቻሉ ዜጎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።ሠራተኞቹ ሙያቸውን እንዲያሳድጉ አሠሪዎቻቸው ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ጽሕፈት ቤቱ አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን ለማድረግ ተቀጥረው በሚሠሩት ዜጎች ላይ ከሚሠራው ሥራ ጎን ለጎን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ፕሮጀክቱ ቦታ ድረስ በመምጣት ፕሮጀክቶቹን እንዲጎበኙ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2015