ሳይመን ሊ ይሰኛል፤ የ52ዓመቱ የጎዳና አዳሪ ጎልማሳ። ይህ ሰው «የእኔ» የሚለው ቤት ንብረትም ሆነ ቤተሰብ ስለሌለው በሆንግ ኮንግ ጎዳናዎች ላይ ላለፉት ሰባት ዓመታት ኑሮውን ገፍቷል። መቼም ይህንን ሲሰሙ ከንፈር መምጠጥዎ አይቀርም፤ ከዚያ በፊት ግን አንድ ነገር ሹክ ልበልዎ።
ሊ ኑሮውን ከመንገድ ዳር ያደረገው እንደ ብዙዎች አማራጭ አጥቶ አሊያም በህይወት ስንክሳር ተገፍቶ ሳይሆን ፈልጎ ነው። ለእርሱ፤ የተመቸ ኑሮ፣ የሞቀ መኝታ፣ የጣፈጠ ምግብ እንዲሁም ሲያሰኘው ከኪሱ መዥረጥ አድርጎ ያሻውን የሚሸምትበት ገንዘብ ቦታ የላቸውም።
ነገሩ ግር ሊያሰኝዎት ይችላል፤ ግን እውነት ነው። የሞቀ ኑሮውንና የቢሮ ስራውን በፍቃዱ ትቶ መኖሩ ስለተስማማው «እናቋቁምህ፤ እንርዳህ» ሲሉት «አሻፈረኝ» ማለቱን ኦዲቲ ሴንትራል ነው ያስነበበው። እንዲህ በመሆኑ ደግሞ ኩራት ይሰማዋል፤ ለምን ቢሉ «ነጻነት
አለዋ! ኪራይ አልከፍል፣ ቤት መግዛትም አይጠበቅብኝ፣ የትም መተኛት እችላለሁ፣ … እንዲያው በአጠቃላይ ጎዳና ማደሬ በርካታ ችግሮቼን ፈትቶልኛል» ይልዎታል።
ይህ ከተለመደው ተቃራኒ የሆነ ሰው፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም በኬሚስትሪ ምሩቅ ነው። በዚህ ሙያውም እአአ እስከ 1997 ድረስ ከአንድ መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ሲሰራ ነው የቆየው። ታዲያ ህይወቱን በዚህ መንገድ መምራቱና በስራ መጨናነቁ ስላሰለቸው መልቀቂያውን አስገብቶ፤ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ማኩዋ የተባለች ከተማ ያቀናል። ለጥቂት ዓመታትም ተማሪዎችን እያስጠና ኑሮውን በዚያ ይገፋል።
እአአ በ2004 ደግሞ አንድ ቦታ መርጋት አይሆንለትምና እንደለመደው ዙሃይ ወደተባለ ከተማ ያቀናል፤ እዚያ በቆየባቸው ሁለት ዓመታትም ያጠራቀመውን ገንዘብ ጨርሶ ወደ ማኩዋ ይመለሳል። ከዚህ በኋላም በቁማር ምክንያት እጁ ላይ ያለውን ሁሉ ያራግፋል። ኑሮውም በጎዳና ላይ ይሆናል፤ ይህንን የተመለከቱት የከተማዋ ባለስልጣናትም እአአ በ2010 ሊን ወደ መጣበት ሆንግ ኮንግ ይመልሱታል።
ሆኖም ከጎዳና ሊላቀቅ አልፈለገም፤ እንዲያውም የዕለት ጉርሱን ከታወቁ ምግብ ቤቶች በሚያገኘው ፍርፋሪ፣ የዓመት ልብሱንም ቢሆን ሰዎች በእርዳታ እየሰጡት ህይወቱን ይመራል።
መኝታውም ቢሆን ከከተማዋ ጎዳናዎች አሊያም ከአትክልት ስፍራዎች ነው፤ መንግስት ለእርዳታ ከሚሰጠው ገንዘብም ቤስታ ቤስቲ አይቀበልም። ምክንያቱም ነገ ስለሚሆነውም ቅንጣት አይጨነቅም፤ በዚህ ቅጽበት እየሆነ ስላለው ብቻ ማሰቡም ከኑሮ ጭንቀት ገላግሎ ደስተኛ እንዳደረገውም ነው የሚያስበው።
ለዚህ ተግባሩም «ለህብረተሰቡ የሚሆነውን ሀብት መቆጠብ ችያለሁ፤ ገንዘብ ስለማልጠቀም ለማግኘት የማደርገው ጥረት አይኖርም፣ ቁሳዊ ነገርም አያስጨንቀኝም፣…» የሚል ማብራሪያ ያክላል። ማንም ሊያደርገው የማይፈቅደውን ነገር በማድረጉም ኩራት ቢጤ እንደሚሰማውም አይሸሽግም።
ሊ ቀኑን የሚያሳልፈው መንግሥት በፈቀደለት ነጻ ዕድል በቤተ-መጽሐፍትና የኢንተርኔት ቤቶች ነው። ከንባቡ ባሻገርም በማህበራዊ ድረገጾች ከሌሎቻችን ስለተለየውና ህይወትን በተለየ መልኩ ስለሚመለከትበት መነጽር እንዲሁም በጎዳና ኑሮው ስላሳለፈው ሁሉ ልምዱን ለሰዎች ያካፍላል።
በዚ ህም የተጋነነ ባይባልም 6ሺ ተከታዮችን ግን ለማፍራት ችሏል። «ደስተኛ መሆን ካሻህ ሰዋዊ ሸክም የሆነብህን፤ ኩራትና ክብር ጥለህ እንደ እንስሳ ሁን» ሲልም ምክሩን ያለ ስስት ይለግሳል።
በግላዊ ህይወቱም ቢሆን ከሰዎች ጋር መቀራረብን አይፈቅ ድም፤ ፍራቻው ደግሞ ወደኋላ እንዳይጎትቱት ነው። ሊ ከሶስት ዓመት በፊት የሴት ጓደኛ ነበረችው፤ ይሁን እንጂ ግንኙነቱ ዕድሜ ስላልነ በረው ወደ ብቸኝነቱ ተመልሷል። ከቤተሰቡም ቢሆን ተቆራርጧል፤ ከወላጆቹ ባሻገር ሶስት ወንድሞችም ነበሩት። ከእነርሱ ጋር መቀራረብ ትርፉ ጭንቀት ስለሆነበትም የተዋቸው ከዓመታት በፊት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በብርሃን ፈይሳ