ስትገነባ ሲፈርስባት ደግማ ስትክበው መልሶ ሲናድ … እኔ አንድ ጫማ ሰፍቼ ጨረስኩ። ከመደቧ ላይ ትንንሽ ቋጥኞች አስመስላ እንደየ ዓይነታቸው ማሰናዳት ከጀመረች ቆይታለች፤ ግን አልሆነላትም። አንዱን ደርድራ ስታበቃ ሌላኛው ይፈርስባታል።
ድንቹን ያስተካከለች መስሏት ዘወር ከማለቷ ተደርምሶ ከሽንኩርቱ ይቀላቀላል። እርሱን ለማስተካከል ስትጥር ደግሞ ከወዲያ የከመረቻቸው ሎሚዎች ተዘረጋግፈው ስራዋን ያበዙባታል። ነገሯ «ውሃ ቅዳ፤ ውሃ መልስ» ስለሆነባት አሳዝናኝ እርሷኑ መከታተል ያዝኩ።
ይህቺ ሴት ከጎረቤት መደቦች በላይ ስራ እንደሚበዛባት ከኔ በላይ ምስክር አያሻም። በጉሊታችን ከበዛው ወጪ ወራጅ ይልቅ ዓይኔ አዘውትሮ የሚያርፈው እርሷ ላይ ነው። እርግጥ ነው፤ የእኔ ቆጥ ከእርሷ ፊት ለፊት መገኘቱ ሳልፈልግም ጭምር እንዳያት ያደርገኛል። የማያት ግን በምክንያት ነው፤ ነገረ ስራዋ ሁሉ
ታሪክ ስላለው።
አንገቷን አቃንታ አይኖቿን ስመለከት በስሱ ጭል ጭል ከሚል ዓይነ ውሃዋ ተቀድቶ የማያልቅ ታሪክ አነባለሁ። ከአጥንቷ ከተጣበቀው የጉንጯ ቆዳ ላይ የበለዘው ስፍራም አንዳች የህይወት ካርታ የተሳለበት ይመስለኛል። አሁንም አሁንም በድንችና ሽንኩርት ቁልል መሃል ወዲያ ወዲህ ከሚል የእጇ አይበሉባ የተዘረጉት የደም ስሮቿም መድረሻ የሌለውን አቅጣጫ የሚጠቁሙ ይመስለኛል።
ካጠረው ቁመቷ ላይ የከሳው ሰውነቷ ተዳምሮ ወገቧ ሰበር ማለቱን ላስተዋለ፤ አንድ ሃሙስ የቀራት በሽተኛ ትመስላለች። ከመደቧ ስትቀመጥ ኮስሟና ሰውነቷ ከቁልሎቹ አይጎላም፤ በዚያ ላይ ጃንጥላ ስትደርብበት ደግሞ ከነመኖሯም አትታይም። እንዲያም ሆኖ ቀኑን ሙሉ እየካበች የሚፈርስባትን አትክልት በሸክም የማጓጓዝ ብርታት አላት።
መኖሯ የሚታወቀው ሁሌም ከእርሷ አቅጣጫ ግርግር ስለማይጠፋ ነው። ብቻዋን የምታሳ ድጋቸው ልጆቿ ቢደርሱላትም እናታቸውን
የሚያሳርፉ አልሆኑም፤ ሁሌም የገበያተኛውንና ነጋዴዎችን ቀልብ የሚይዝ ሰቀቀን ይጭሩባታል። እረፍት የሚነሷት ጎረምሳ ልጆቿ ድንገት ደርሰው አንዳች ረብሻ ይፈጥሩባታል።
ብዙ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች ስሞታ ሲያነሱላት እመለከታለሁ። «ልጆችሽ እንዲህ አድርገው፤ እንዲህ አጥፍተው» እያሉ ይከሱላታል። ይህን ሲሏት በሰቀቀን ከሳሾቹን አሻቅባ ከመመልከት በቀር የምትፈጥረው ነገር ባይኖርም፤ በልጆቿ ፋንታ ይቅርታ ትጠይቃለች። እንደምት ገስጻቸውና እንደሚታረሙም ታስረዳለች። እን ዲህ ሆና ሳያት እንደ ድንቾቿ ሁሉ ከቀለሰችው ጎጆ አንድ ማገር፤ ከገነባችው ህይወቷም ቅንጣት ተስፋ ሲናድ ይታየኛል።
ወዲያው ሃሳብ ይይዛታል፤ እንደ ሌሎች ነጋዴዎች ገበያዋን በንቃት አትጠብቅም። ከሳሾቹ ከሄዱም በኋላ አገጯን ከእጇ ላይ አስደግፋ በሃሳብ ጭልጥ ትላለች። እንዲህ ስትሆን ታሳዝነኛለች፤ የእኔም ሃሳብ በእርሷ ላይ ይደረባል። ከትካዜዋ መለስ የምትለው ገበያተኛ ሲመጣ ነው።
አፍታም ሳትቆይ ሁለመናዋ እርሷን የማይመስል ሴቷ ልጇ ትመጣለች። ከልብሷም ከመልኳም እንዳማረች እናቷን ትጠጋለች፤ አይናማዋን ልጅ ስመለከት ልቤን ይሞቀዋል። ግን ብዙም አይቆይም፤ ከእናቷ ጋር ከምታደርገው ጥቂት የቃላት መመላለስ በኋላ ስሜቴ በበረዶ ይተካል።
እናት አንገቷ ላይ ከምታንጠለጥለው ከረጢት መሰል ቦርሳዋ ከሸጠችው ቆንጥራ ትሰጣታለች። ልጅት ግን ተጨማሪ ካልተሰጣት አትንቀሳቀስም። እርሷን ከመሸኘቷ በዱቤ የቤት ዕቃ የሚሸጠው ነጋዴ ደርሶ ያፈጥባታል። በችርቻሮ የምትለቃቅመው ገንዘብ ከቤቷ ሳታደርስ እዛው ትጨርሰዋለች።
እርሷን መከታተል ከጀመርኩ እንስቶ የደሃ መጫሚያዎችን እየጠገንኩ በምገፋው ኑሮዬ ማዘንና ማማረር አቁሜያለሁ። በጊዜ ብዛት ጠረን የፈጠሩት ጫማዎችም ቢሆኑ ለአፍንጫዬ ቤተሰብ ሆነዋል። ቀልቤ ከዚያች ሴት ስለሚሆን፤ ውሎዬን እንድትጋራ የምከፍታትን ሬዲዮንም አድምጫት አላውቅም። ዓይኔን ከወዲያ ጥዬ ቆዳውን ከሶሉ ለማያያዝ ስታገልም ወስፌ ከእጄ ቢሰካም የሚሰማኝ ነገር የለም።
አንድ ረፋድ ላይ አንድ ሁለት መደብ እንደ ሸጠች በሚሯሯጡ ሰዎች ትንሿ ጉሊታችን ትረበሽ ጀመር። ከፊት የቀደመው ተባራሪ የመከረኛዋ ሴት ልጅ ነው፤ አባራሪዎቹ ከኋላው ድንጋይና ዱላ ይዘው ሊደበድቡት ይከተሉታል። እናት ለማስጣል ተነሳች፤ እርሱ እንደ ልጅነቱ ከእናቱ ጉያ ሊደበቅ፤ እርሷም ልትሸሽገው ነበር። ግን አልደረሰችበትም ዓይኗ እያየ ደብድበውት ሄዱ።
ሰዎች ከአንድ ጥግ አስቀምጠው ሊያረጋግጉት ሞከሩ፤ ለቅሶዋ ግን የሞተ ያህል ነበር። እኔ ብቻ የምመለከተው ምሬቷ አፍ አውጥቶ መናገር ጀመረ። ውስጧ ያለው ብሶት አንድም በእንባ አንድም ሳግ በሚቆራርጠው ሳጓ ሲፈስ ይበልጥ አዘንኩላት።
ለምን እንደሆን እንጃ እያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ መንፈስን የሚይዝ ታሪክ አለው። አጋሮቿ ከበው ሊያባብሏት ሲሞክሩ፤ ልቤ አብሯት እያነባ ነበር። ከሰው ፊት እንዳላነባ ስለሰጋሁ ወትሮውንም ብከፍት እንጂ የማልሰማውን ሬዲዮ ድምጽ ጨመርኩበት።
በአስገምጋሚ ድምጹ ዜና የሚያነበው ጋዜጠኛ «… በተባለ ስፍራ በተቀሰቀሰ ግጭት፤ … ያህል ሰዎች ሲሞቱ … የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀሉ» ይላል። ጋዜጠኛው ሃተታውን ሲቀጥል የእኔ ቀልብ መልሶ ከዚያች ደሃ ሴት አርፈዋል።
እንባ ያቀረሩት አይኖቼ እንባዋን ሲመለከቱ አእምሮዬ ጥያቄውን ማዝነብ ጀመረ። ቀልቧ ከቀልቤ ለምን እንደተሳሰረ፣ ሳያት ለምን እንደምፈዝ፣ እያንዳንዱ የአካል ክፍሏ ለምን ታሪክ እንደሚሆብኝ፣ ሁኔታዋ ሁሉ ለምን አንጀቴን እንደሚያላውሰው፣ …። የገባኝ ቆይቶ ነው፤ ለካስ በእርሷ ውስጥ ስመለከት የቆየሁት ስትክብ የሚናድባትን፤ ልጆቿ ሁሉ ጎርምሰው በግልፍተኝነት ችግር የሆኑባትን ሃገሬን ነበር።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በብርሃን ፈይሳ