በዓለም ላይ ዘር ፣ ቀለም፣ ዝና፣ ማንነት እና ቦታ ሳይገድባቸው ለሰዎች በጎ አድርገው ያለፉ ግለሰቦች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው:: በተለይም ደግሞ ባሕር አቋርጠው፤ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው በምንም ለማይዛመዷቸው ችግረኛ ሰዎች እንደሻማ ቀልጠው የሚኖሩ ሰዎችን ማግኘት አዳጋች ነው:: በጣታችን አንድ ሁለት ብለን ከምንቆጥራቸውና የበጎነት ማሳያ ከሆኑ ምርጥ ግለሰቦች መካከል ደግሞ የሰዎች ለሰዎች የእርዳታ ድርጅት መሥራች ካርልሄይንዝ በም አንዱና ግንባር ቀደሙ ናቸው::
ኢትዮጵያና መላው ሕዝቦቿ የማይዘነጓቸው እኚህ የሃገር ባለውለታ እ.ኤ.አ መጋቢት 16 ቀን 1928 ዓ.ም ዳርምስታድ ጀርመን ውስጥ ከስመጥር የሙዚቃ አቀናባሪ ኦስትሪያዊ አባታቸው ዶክተር ካርል ሄይንዝ በም እና ከታዋቂ ድምፃዊት እናታቸው ቲያ ሊንህርድ ብቸኛ ልጅ ሆነው ተወለዱ።
ካርል ወደ እርዳታ ፊታቸውን ከማዞራቸው በፊት በአገራቸው ጀርመን እና ኦስትሪያ እጅግ ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ነበሩ። ‘ሲሲ’፣ ‘ፎክስ ኤንድ ሂዝ ፍሬንድስ’ ፣ ‘ላ ፓሎማ’፣ ‘ዘ ስቶው አዌይ’ እና ‘ካም ፍላይ ዊዝ ሚ’ን ጨምሮ፤ በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ በኦስትሪያና በሌሎች አገሮች በተሠሩ 45 ያህል ፊልሞች ላይ በመተወን ችሎታቸውን ያስመሰከሩ ተዋናይ ነበሩ።
በካርል የሕይወት ዘመን አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው እ.ኤ.አ በ1981 ዓ.ም ነበር:: በወቅቱ ተወዳጅ በነበረ የጀርመን ቴሌቪዥን ፕሮግራም ‹‹ቨተን ዳሽ›› ላይ በመቅረብ በጀርመን፣ በኦስትሪያና በስዊዘርላንድ ፕሮግራሙን ከሚከታተሉ 18 ሚሊዮን ተመልካቾች ጋር ባልተለመደ ሁኔታ ተወራረዱ:: ካርል በቀኝ እጃቸው አንድ ዶች ማርክ (የጀርመን ገንዘብ) ይዘው ‹‹እንወራረድ፤ ይህንን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ከምትከታተሉት 18 ሚሊዮን ተመልካቾች ውስጥ አንድ ሦስተኛችሁ እንኳን በአፍሪካ በድርቅና በረሃብ ለሚሰቃዩ ሕዝቦች የዕርዳታ እጃችሁን ለመዘርጋት ፈቃደኛ አይደላችሁም›› በማለት ተናገሩ:: በውርርዱ ከተረቱ ራሳቸው ካርል የዕርዳታውን ገንዘብ ይዘው ወደ አፍሪካ በመሄድ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ያህል የሰው ልጅ በረሃብ እንዳይሞት እንደሚታደጉ ቃል ገቡ:: ካርል በውርርዱ ባይሸነፉም፣ ቀድሞውኑ ውርርዱ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልት ነበረና የተሰበሰበውን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የጀርመን ማርክ ሆነ። ካርልም በዚህም ገንዘብ “ሰዎች ለሰዎች” (Menschen für Menschen) የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅታቸውን መሠረቱ።
ካርል የኢትዮጵያ ሥራቸውን እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም በሐረርጌ ክፍለ ሀገር የኤረር ሸለቆ አካባቢ በጦርነት እና በረሃብ የተፈናቀሉትን ሁለት ሺ የሐዊ ጎሳ አባላትን በማቋቋም ነበር የጀመሩት:: በማስከተልም በ1980ዎቹ አጋማሽ በኢሉባቦር አካባቢ ለሠፈሩ መቶ ሺ ያህል ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ አድርገዋል:: ይህን የበጎ አድራጎት ጥረት ወደ ተቀናጀ የገጠር ልማት በመቀየር ዛሬ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች 56 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍን አካባቢ ላይ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል::
በሠላሳ ዓመቱ የልማት ጉዞ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በጤና፣ በንፁሕ የመጠጥ ውኃ፣ በግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት፣ የሴቶችን አቅም በማጎልበት፣ በቤተሰብ ምጣኔ እና በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ፕሮግራም ያለ አንዳች የሃይማኖት፣ የጎሳና ፖለቲካ ልዩነት ተጠቃሚ ሆኗል::
በዚህ ድርጅት አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ 363 ትምህርት ቤቶች፣ ስምንት የማሠልጠኛ ተቋማት፣ ዘጠኝ መዋዕለ ሕፃናትና ከትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው አንድ የቴክኒክ ኮሌጅ በመገንባት እና በቁሳቁስና በትምህርት መርጃ መሣሪያዎች በማሟላት ተማሪዎች ንፁሕ፣ ብሩህ፣ ምቹና የተሟላ የመማሪያ አካባቢ እንዲኖራቸው ተደርጓል:: 102 ሺ 117 ገበሬዎች በኢ-መደበኛ ክህሎት ሲሠለጥኑ፣ 279ሺ777 ጎልማሳች መሠረታዊ የማንበብ እና መጻፍ ትምህርት ተከታትለዋል:: በተጨማሪም 1ሺ329 ተማሪዎች በመደበኛው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በዲፕሎማና ዲግሪ ተመርቀው በቀሰሙት ዕውቀት ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ::
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ሴቶች በማለዳ እንሥራ ተሸክመው መማሠንን ለማስቀረት 1ሺ862 የውኃ ጉድጓዶችና ምንጮች ጎልብተዋል:: ከዚህም ባሻገር 70 የመስኖ ሥራዎችና 77 ውኃ ማጠራቀሚያዎች ተገንብተዋል::
ለምስኪኖች በጎነት ማድረግ የማይታክታቸው ካርል በጤናው ዘርፍ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለእናቶችና ለሕፃናት ልዩ ትኩረት የሰጡ ሲሆን፣ ሦስት ሆስፒታሎች እና የጅማ ሆስፒታል ማሻሻያ፣ 37 ክሊኒኮች፣ 14 ጤና ጣቢያዎችና 49 የጤና ኬላዎች ተገንብተዋል:: 39 አምቡላንሶች ለተለያዩ ከተሞች በማቅረብ የአገር አቀፍ ጤና አገልግሎት ሽፋን ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል:: ለ52 ሺ 847 የዓይን ሕሙማን የሕክምና ዕርዳታ ተደርጓል:: በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች የሥልጠና ዕድል አግኝተዋል:: ስለኤች.አይ.ቪ ኤድስ የግንዛቤ መድረኮች ተፈጥረዋል:: በበሽታው ለሚሰቃዩ ወገኖችና ለወላጅ አልባ ሕፃናት ድጋፍ ተደርጓል:: በርካታ ሴቶች የአጭርና ረጅም ጊዜ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል::
ልበ ሩህሩሁ ካርል የሴቶች ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እስካልተሻሻለ ድረስ ኢትዮጵያ ከድህነት እንደማትወጣ እርግጠኛ በመሆናቸው፣ የሴቶችን አቅም ለማጎልበትና የፆታ እኩልነት ለማስፈን 20 ሺ 351 ሴቶች በማኅበር ተደራጅተው ብድር በማግኘት ለሥራ ተሰማርተዋል:: እንዲሁም 60 ሺ 429 እማ ወራዎች በባልትና ፣ በቤት አያያዝ ፣ በግልና አካባቢ ንጽሕና ሠልጥነዋል:: በተጨማሪም 188 ሺ 738 ማገዶ ቆጣቢ ምርጥ ምድጃዎች እንዲሠራጩ ተደርጓል:: ንፁሕ የመጠጥ ውኃ በመንደራቸው አቅራቢያ በመገኘቱ የሴቶችን የሥራ ጫና እና ድካም የቀነሰ ሲሆን፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ የሚደረገው የተጠናከረ ዘመቻ መብታቸው እንዲከበር አስተዋጽኦ አበርክቷል::
ካርል በመሠረቱት በዚሁ ድርጅት አማካኝነት ተፈጥሮን በማያዛባ ሁኔታ የእርሻ ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግና በምግብ ራስን ለመቻል ለአነስተኛ ገበሬዎች ተገቢው የእርሻ ቴክኖሎጂ እና የመስኖ ዘዴ የማስተዋወቅ፣ ምርጥ ዘር የማቅረብና የአፈር እና ደን አጠባበቅ ሥልጠና ተሰጥቷል:: ከ150 ሚሊዮን ያህል ችግኞች ለገበሬዎች ተከፋፍለዋል::
ከዚህም ባሻገር 46 ሺ 702 ኪሎ ሜትር የድንጋይና አፈር፣ 4ሺ 068 ኪሎ ሜትር የቬቲሽር አፈር ጥበቃ እርከን፣ 18 ሺ 841 የተሻሻሉ መኖሪያ ቤቶች ተሠርተዋል:: የእንስሳትን ተዋፅዖ ለማሳደግ 30 የእንስሳት ሕክምና ጣቢያዎች ተገንብተዋል:: ለገበሬዎች የተሠራጩት 6 ሺ 228 ዘመናዊ ቀፎዎች አማራጭ የገቢ ምንጭ ፈጥረዋል:: እንዲሁም በገጠር መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ 2 ሺ 942 ኪሎ ሜትር መንገድና 15 ድልድዮች የተሠሩ ሲሆን፣ እንደ አብዲ ቦሪ የሕፃናት መንደር ያሉት ማኅበራዊ ተቋማት ወላጅ ለሌላቸው ሕፃናትና ወጣቶች የተሻለ የኑሮ አማራጭና የትምህርት ዕድል ፈጥረዋል::
የበጎነት አብነት የሆኑት ካርልሄይንዝ በም ለ33 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረጉት ሰብዓዊ በጎ አድራጎትና የልማት አስተዋፅዖ ከተለያዩ የአውሮፓና የኢትዮጵያ ተቋማት ሽልማቶችና የክብር ማዕረጎች አግኝተዋል:: ከእነዚህ መካከል የኦስትሪያ የኤስል ማኅበራዊ ሽልማት(2011)፣ የስዊዘርላንድ ባልዛን ሽልማት (2007)፣ የጅማና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት(2003)፣ እንዲሁም ታላቁ የጀርመን ኦርደር ኦፍ ሜሪት(2001) ይጠቀሳሉ::
ካርል የላቀ ትርጉምና ስሜት የሚሰጣቸው ግን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጣቸው የክብር ዜግነት እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል:: ኢትዮጵያን እንደ አገራቸው፣ሕዝቧን እንደወገናቸው ሲቆጥሩ ለኖሩት ካርል፣ “ከእንግዲህ አንተ ባዕድ ሳትሆን ከእኛ እንደ አንዱ ነህ” ተብለው ሕልማቸው እውን የሆነበትን ቀን እጅግ ይደሰቱበታል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ አደባባይ በስማቸው የሰየመ ሲሆን፣ የሰዎች ለሰዎች ፕሮጀክቶች ተጠቃሚዎች ገንዘብ በማዋጣት የመታሰቢያ ሐውልታቸው እንዲቆም ተደርጓል:: በመርሐቤቴ ዓለም ከተማ ደግሞ ሐውልት ቆሞላቸዋል። እሳቸው ሐውልቱ በተመረቀበት እለት ለተሰጣቸው እውቅና እና ኢትዮጵያውያን ላሳያቸው ፍቅር ‹‹እኔ ፈረንጅ አይደለሁም ኢትዮጵያዊ እንጂ!›› በማለት በስሜት ተናግረዋል::
ትናንት ካርል ባነፀው የሜንሽን ኮሌጅ የሠለጠኑ የጤና ሳይንስ ባለሙያዎች ብዙዎችን ኢትዮጵያውያን እናቶች ከምጥ ገላግለዋል፣ ብዙ የወደፊቱን ሀገር ተረካቢ ሕፃናትን አዋልደዋል:: የብዙዎችን ስቃይ አስታግሰው ወደ ፈውስ መልሰዋል:: ካርል አስተምሯቸው ያለፈው የኤሌክትሪካል ሣይንስ ባለሙያዎች ሀገራቸውን አገልግለዋል:: ካርል የመሠረተው ይህ ድርጅት ያስመረቃቸው የሜካኒካል ሳይንስ ባለሙያዎች ዛሬ በየተሽከርካሪው ኢንዱስትሪ፣ በየጋራዡ፣ በየፋብሪካው በብርቅ የሚፈለጉ ብቁ ሙያተኞች ሆነዋል:: ካርል የረዳቸው፣ ያስተማራቸው ሕፃናት ዛሬ አድገው ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ፣ ሌሎችን የሚረዱ፣ የታነፀ ንፁሕ ዜጋ የሚያፈሩ ድንቅ ዜጎች ሆነዋል::
ካርል መኪናም ሆነ መንግሥት በማይዘልቃቸው ሩቅ ሩቅ የተረሱ የሀገሪቱ ክፍሎች ድረስ ሄዶ የሠራው ሆስፒታልና በየጫካው መሐል ምንም ነገር ሳያግዳቸው እንደ ትንግርት ደርሰው ለሕዝቡ ጤናን እያላበሱ ያሉ፣ ቢያንስ ቢያንስ የአንዲት ቀን ስቃዩን እያስታገሱ የቆዩ የእፎይታ ተቋማት ሆነዋል:: ካርል ከሁሉ ቀድሞ በከርቸሌ የሚገኙ እስረኞች በሜንሽን ፎር ሜንሽን ሠልጥነው የመስኖ እርሻ እንዲያለሙ፣ ለአካባቢያቸው ሕዝብ በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ እንዲመግቡ፣ እና ከገቢውም ተጠቃሚ ሆነው በመታሰራቸው ኑሮ የጎደለባቸውን ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ፣ ለራሳቸው የማይደበዝዝ ዋጋ ያለው ሰውነት፣ ለቤተሰቦቻቸው የትም ይሁኑ የት በአለኝታነት የሚቆሙ ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጋ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድም ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው::
መጠለያ የሚሆን ቤት በማጣታቸው ብቻ፣ የገንዘብ ዋስትና የሌላቸው ደሃ-አደግ በመሆናቸው ፣ መጠጊያ የሚሆናቸው ቤተሰብ ስለሌላቸው ብቻ ሀገራቸው ምን ደሃ ብትሆን በሜዳ ተበትነው እንዳይቀሩ፣ የባዕድነት ሥሜት በውስጣቸው ዘልቆ እንዳይጎዳቸው፣ ቅስማቸው እንዳይሰበር ካርል ብዙ ብዙ ሕፃናትን እና ወጣቶችን ከያሉበት ጥግ እየሰበሰበ በአዳሪ ትምህርት ቤት እያስገባ እስከ ኮሌጅ አስተምሯል::
ካርል በዚህ ድንቅ ሰብዓዊ ሥራው ጥቁር ነጭ አላለም፤ ዘር አልቆጠረም፤ ኦሮሞ አማራ ሰው አለየም:: ካርል በስህተት እንኳ የቆጠረው ዘር ቢኖር አንድ ብቻ ነው:: እርሱም ክቡሩ የሰው ልጅ ዘር ብቻ::
ካርል ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከአልማዝ ተሾመ ጋር ትዳር መስርተው ልጆች ያፈሩ ሲሆን ጡረታ በወጡም ጊዜ የድርጅታቸውን አመራር ያስተላለፉት ለባለቤታቸው ለአልማዝ በም ነበር:: እኚህ ታላቅ ሰው በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠራማ ክልሎች የሠሯቸው ልማቶች እጅግ ሰፊ ናቸው።
በኢትዮጵያ በርካታ ሰብዓዊ ሥራዎችን በመሥራት ውለታን ከውለታም በላይ መሆን እንደሚችል ያሳዩት የሰው ለሰው ድርጅት መሥራቹ ካርል ሄንዝ በም ለረዥም ጊዜ በሕመም ሲሰቃዩ ቆይተው ግንቦት 21/2006 በጀርመን ሳልበርግ ሕይወታቸው ያለፈው::
በአንድ ወቅት በምድረ አውሮፓ ስመጥር የፊልም ተዋናይ ብቻ ሳይሆን ከሀብታም ቤተሰቦችም የወጣው ካርል ሄንዝ በም በሰውነት ሚዛን የላቀ እና ፍፁም ከወረደ ዘረኝነት የጸዳ፣ ጤናማ የሆነ የሰው ልጅ መልካም አስተሳሰብ ባለቤት መሆኑን ያለምንም ተጨማሪ ቃል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፈው ሕይወት ብቻውን ቁልጭ አድርጎ ይመሰክርለታል:: ታላቁ ይህ የኢትዮጵያውያን ወዳጅ በእነዚህ እና በሌሎች ተነግረው በማያልቁ ምክንያቶች የተነሣ ነው ዛሬም ሆነ ወደፊት ስሙ ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ ይታያል:: በሰብዓዊ መንፈሱና በማይሞቱ ሰብዓዊ ሥራዎቹ ገና ወደፊት ለትውልድም ካርልነቱን በተግባር እየተረጎመ፣ ብዙዎችን እያስተማረ፣ ብዙዎችን መልካምነት እያላበሰ፣ ዜጎቻችንን እያነፀ መኖሩን ይቀጥላል::
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም