ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል፣ ክብሯንና ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ የገቡትን ቃል ኪዳን አክብረው በተለያዩ የውጊያ ዐውዶች ከተዋደቁ ምርጥ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ አንዱ ናቸው። በተለይም በወታደራዊ ግዳጅ ከሚጠይቀው በላይ በሶማሌ ወረራ ወቅት በጅጅጋ በድሬዳዋና በኦጋዴን ሰማዮች ላይ የአሜሪካን ስሪት F5 ተዋጊ አውሮፕላኖችን እያበረሩ የጠላትን ሚጎች በመደምሰስ ወደር የሌለው ጀግንነት መፈጸማቸው ይወሳል። ለዚህም ከመንግሥት የላቀ የጦር ሜዳ ሜዳይ ለመሸለም በቅተዋል። እኚህ ታላቅ የሃገር ባለውለታ ትውልድ የሚኮራበት፣ አስደማሚ የሆነው የውጊያ ብቃታቸው የታየበት ድንቅ ታሪኮችን ሠርተዋል። ከእነዚህም ድንቅ ጀብዶች መካከል በሶማሊያ ጦርነት ወቅት በአየር ለአየር ውጊያ የጠላት ሚጎችን ዶግ አመድ ማድረጋቸው ተጠቃሽ ነው። ምርጡ የኢትዮጵያ ልጅ ኮሎኔል ባጫ በተናጠልም ሆነ ከጓዶቻቸው ጋር በመሆን በሌሎች ዐውደ ውጊያዎች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆነው በታላቅ ጀግንነት ለአገራቸው ዳር ድንበር መከበር ተዋግተዋል።
ልጅነት
ባጫ ሁንዴ የተወለዱትም ሆነ ያደጉት ሆለታ ገነት ነው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ሆለታ ገነት በሚገኘው በቀድሞው ደጃዝማች መንገሻ ይልማ ትምህርት ቤት በመቀላቀል እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሩ። በልጅነታቸው ሳቅና ጫወታ ይወዱ እንደነበር የትምህርት ቤት ጓደኛቸው ኃይለ ማርቆስ ፈይሣ ይናገራሉ። ‹‹ባጫን ባወቅሁት ጊዜ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ባጫ ብይ ጫወታ ይወዳሉ። ከክፍል ለእረፍት ስንወጣ በረው ሜዳ ነው የሚሄዱት›› በማለት ይገልፃሉ። እንደሌሎቹ ተማሪዎች ትምህርት ላይ ከማተኮር ይልቅ ጨዋታ ያዘወትሩ እንደነበርም ነው የሚያነሱት። ያም ሆኖ ግን ባጫ በተፈጥሮ ጥሩ ጭንቅላት የታደሉ በመሆናቸው ምንም ሳይጨናነቁ የላቀ ውጤት ያመጡም እንደነበር ጓደኛቸው ይመሰክራሉ።
ጎበዙ ባጫ የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናን በጥሩ ውጤት ቢያልፉም በወቅቱ ብዙዎቹ የአውራጃም ይሁን የወረዳ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከስምንተኛ ክፍል በላይ ስለማያስተምሩ ወላጆቻቸው በቀጥታ አምቦ ወደሚገኘው ማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተብሎ ይጠራ ወደነበረው ትምህርት ቤት አስገቧቸው። የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉም በአንድ ያልተጠበቀ ቀን በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ አንድ ዜና ተሰማ፤ ይኸውም የአየር ኃይል ምልመላ ሊያደርግ መሆኑ ነው።
አየር ኃይል
በሰኔ ወር 1957 ዓ.ም የማዕረገ ሕይወት ትምህርት ቤት የዓመቱ ትምህርት በተጠናቀቀበትና ሁሉም ፈተናቸውን በወሰዱበት አጋጣሚ እነዚያ በሚያምር ዩኒፎርማቸው ደምቀው፣ በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው ብቅ ያሉት የአየር ኃይል መልማይ መኮንኖች የአብዛኛውን ተማሪ ቀልብ ሳቡት። ታዳጊው ባጫም እንደሌሎቹ ተማሪዎች ሁሉ አየር ኃይል ለመቀጠር ከተመዝጋቢዎች ተርታ ለመሰለፍና ፈተና ለመውሰድ ፈፅሞ አላመነቱም። እናም ፈተናውን በማለፉ ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋር ደብረ ዘይት ተወሰዱ። የ65 ቅጥር ምልምሎች ጋር በመሆን ሲ 54 በተሰኘ አውሮፕላን ተሳፍረው ለወታደራዊ ሥልጠና ወደአሥመራ ተላኩ።
ባጫ በእድሜም ሆነ በአካል ከሌሎች ሠልጣኞች ያነሱ ቢሆንም የአየር ኃይሉን ፈታኙን ወታደራዊ ልምምድ በፅናት አለፉ። ገና ከጅምሩ በሥነ-ምግባርም ሆነ በሥራቸው ምስጉን መሆን ቻሉ ። ጥቅምት ወር 1958 ዓ.ም ሥልጠናው ተጠናቆ ሁሉም ከምልምልነት ወደ አፕሬንትስነት ተሸጋገሩ። በቀጣዩ የሕይወት ጉዞ ሁሉም እውቀትን የሚቀስሙበትና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የሚተዋወቁበት ጊዜ በመሆኑ ትምህርት ለሚወስዱት ባጫ አስቸጋሪ አልሆነባቸውም ። ከሁለት ዓመት በኋላ ለምርቃት ሲደርሱ አፕሬንትስ ባጫ ሁንዴ በ 15ቱም የትምህርት ዓይነቶች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አለፉ። በተለይም በእንግሊዝኛና በሒሳብ ትምህርት፣ በአውሮፕላን አካልና ሞተር (ኢንጂን) እውቀት፣ ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በጠቅላላው አብረዋቸው ከሚማሩት ተማሪዎች ሦስተኛ በመውጣት በመጨረሻ የጁኑየር ኤርክራፍትማን ማዕረግ በማግኘት ወደሥራ ገቡ።
የሥራ ዓለም
የጁኑየር ኤርክራፍትማን ባጫ ሁንዴ የሥራ ዓለም የሚጀምረው ከምርቃት በኋላ በሁለተኛው አየር ምድብ አሥመራ፣ የአንደኛው ተዋጊ ስኳድሮን 126 ኛው የጥገና ስኳድሮን ክፍል ከተመደቡበት 1960 ዓ.ም የጥቅምት ወር ጀምሮ ነበር። በስኳድሮኑ ውስጥ በተለይ በኤፍ 86 ተዋጊ አውሮፕላን መካኒክነት ሲመደቡ በእርግጥም የሕይወት አቅጣጫ መልካሙን ጎዳና የተያያዙ መሰሉ፤ ጁ/ኤክማን ባጫ በአውሮፕላን ሜካኒክነት አሥመራ ለ15 ወራት የቆዩ ሲሆን በእነዚህ ጊዜያትም በትምህርት የቀሰሙትን እውቀት በሥራ ላይ በማዋል በአለቆቻቸው ዘንድ ምስጋናንና አድናቆትን ለማትረፍ በቅተው ነበር። በወቅቱ ጁ/ኤክማን ባጫ አየር ኃይሉ በየዓመቱ እንደሚያደርገው ለቴክኒሽያኖችና ለሌሎችም የአየር ኃይል አባላት ወደአብራሪነት እንዲቀላቀሉ ማስታወቂያ ያወጣበትና ባጫ ያንን እድል ለመጠቀም ማመልከቻ ያስገቡበት ጊዜ ነበር። እናም ሁሉም ተሳካና በሕዳር ወር 1961 ዓ.ም. ከቴክኒሽያንነት ወደአብራሪነት የመሸጋገር ጉዞ ጀመሩ።
ከምድር ወደ ሰማይ
አየር ኃይሉ ያወጣውን የውስጥ የአብራሪነት እድል ለመጠቀም ብዙዎች ቢመኙም የጤና ምርመራውንና ሌላውንም ዓይነት ፈተና አልፈው ያንን እድል ለማግኘት የሚችሉ በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። በዚያ ዓመት ከተወዳደሩት መካከል ሁሉ ነገር ሰምሮላቸው ወደበረራ ትምህርት ቤት ለመግባት ከቻሉ ጥቂት ወጣቶች መካከል ባጫ ሁንዴ አንዱ ነበሩ። ጁ/ኤክማን ባጫ ሁሉንም የአብራሪነት መስፈርት አሟልተው ፒ 19 ኤ የተሰኘውን ኮርስ ባልደረባ በመሆን ድሬዳዋ ይገኝ የነበረውን የ31ኛውን የመጀመሪያ ደረጃ በረራ ትምህርት ስኳድሮንና ቀጥሎም አሥመራ የነበረውን 32ኛው የመሠረታዊ የበረራ ትምህርት ስኳድሮን ተቀላቀሉ።
ፈጣኑ እድገት
የምክትል መቶ አለቃ ባጫ እድገት ፈጣን እንደነበረ የሚመሰክሩት ባልደረቦቻቸው በተለይ ለበረራ ባላቸው ዝንባሌና ችሎታ ያለማቋረጥ ከደረጃ ደረጃ ከፍ እያሉ እንደነበረ ይናገራሉ። ለዚህ አስረጂ የሚሆነው ደግሞ በአብራሪነት ከተመረቁ በኋላ ወዲያውኑ በጥቅምት ወር 1963 ዓ.ም ሐረር ሜዳ ይገኝ የነበረውን የ33ኛውን የጄት በረራ ትምህርት ስኳድሮን በመቀላቀል የጄት ማስተማሪያ በሆነችው ቲ 33 የምትባል አውሮፕላን ላይ እንዲሠለጥኑ መመደባቸው ነበር። እስከ ጥር ወር 1964 ዓ.ም ድረስም የቲ 33 ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ አሥመራ በሚገኘው የ1ኛው የተዋጊ ስኳድሮን ኦፕሬሽን ዊንግ ተመድበው ግዳጅ ላይ መሳተፍ ጀመሩ። በመካከልም በማዕረጋቸው ወደሙሉ መቶ አለቅነት ከፍ ለማለት በቁ። በኤፍ 86 ኤፍ አውሮፕላን የግዳጅ በረራ ቆይታቸው በተለይ የሰሜን ጦርነት እየተጋጋለ በሄደበት ወቅት ከ80 በላይ የበረራ ምልልስ አኩሪ ተግባር ከመፈፀማቸውም ባሻገር በጦርነት ወቅት የነበራቸው ወኔና ቁርጠኝነት በሚገባ የተገለፀበት አጋጣሚ እንደነበረ ተመዝግቦላቸዋል።
ባጫ አሥመራ በቆዩበት አጋጣሚም ከ10ኛ ክፍል ላይ አቋርጠውት የነበረውን መደበኛ ትምህርታቸውን በማታ ክፍለ ጊዜ በመቀጠል እዚያው አሥመራ ውስጥ የ12 ክፍል መልቀቂያ (ማትሪክ) ለመፈተንና ጥሩ ውጤት ለማምጣት በቅተዋል። ይህ ትጋታቸውም በተለይ በአለቆቻቸው ዘንድ መልካም ግምትን ያሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ኃላፊነት ቢሰጣቸው ሊሸከሙ እንደሚችሉም ያመላከተ ነበር። ይህ በመሆኑም በ1967 ዓ.ም በጥቅምት ወር የበረራ አስተማሪነት ኮርስ እንዲወስዱ እድሉ ተሰጥቷቸው ከተማሩ በኋላ ብቁ አስተማሪ እንደሆኑ ተረጋግጦ የምስክር ወረቀት አገኙ።
ሆኖም በዚያው ወቅት አየር ኃይሉ ከኤፍ 5 ኤ በተጨማሪ አዲስ የሆነችውን ኤፍ 5ኢ የተሰጠችውን የአየር ላየር ተዋጊ አውሮፕላን ለመታጠቅ ዝግጅት በማድረግ ላይ ስለነበሩ መ/አ ባጫን ጨምሮ በዚህ ጊዜ ወደአሜሪካ በጥሬ ገንዘብ ተከፍሎላቸው የሄዱት ስድስት አብራሪዎችና ሰባት ቴክኒሽያኖች ከፍተኛ ኃላፊነት ነበር የተጣለባቸው። የሚሰለጥኑባት ኤፍ 5ኢ አውሮፕላን የአየር የበላይነታችንን ለማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ከመሆኗም በላይ የዚያድ ባሬ መንግሥት የጋረጠብንን ወረራ የሚከተለውን የአየር ጥቃት በብቃት ለመመከት ፍጹም አስፈላጊ ነበረች። በዚህም መልኩ እጅግ ጥብቅ የሆነውንና ሰባት ወራት የፈጀውን መሠረታዊ የሽግግር ሥልጠናና የአስተማሪነት ኮርስ በሙሉ በመጋቢት ወር 1968 ዓ.ም አጠናቀው ወደሃገራቸው ተመለሱ።
ወሳኙ ግዳጅና የጄት አብራሪነት
ባጫ ወደሀገር በተመለሱበት ወር ማዕረጋቸው ከመቶ አለቅነት ወደ ሻምበልነት ሲያድግ የሥራ ምድባቸውም ቀድሞ ከነበረበት የአሥመራው 1ኛው ተዋጊ ስኳድሮን ወደሐረር ሜዳው ዘጠነኛው ታክቲካል ተዋጊ ስኳድሮን በመዘዋወር በኤፍ5 ኢ አውሮፕላን አብራሪነትና በተደራቢም በበረራ አስተማሪነት ማገልገል ጀመሩ። ይህ ወቅት ሻምበል ባጫ ለሥራ ያላቸው ትጋት ምን ያህል ጠንካራ እንደነበረ ያስመሰከሩበት ወርቃማ ጊዜው ነበር። እንዲያውም ያንን አስመልክቶ በቅርብ አለቆቻቸው ሻምበል ባጫ ሁንዴ በመደበኛም ሆነ በተደራቢ ሥራቸው እንከን የማይወጣላቸው መሆኑን፣ ከወሬና ከቀልድ ይልቅ ቁምነገርንና በሥራ መጠመድን መምረጣቸውን፣ የተደማጭነት የመፅሐፍ ንባብ ልምድ ያላቸው መሆኑን በተመደቡበት ሥፍራ ብቁ ብቻም ሳይሆን ምትክ የማይገኝላቸው መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል።
በተለይም ወቅቱ ከፍተኛ ውጥረት የነበረበትና የ1969ኙ የሶማሊያ ወረራ የሚያስገመግምበት ስለነበረ አየር ኃይሉም ወረራውን ለመመከት ከፍተኛ ትግል የሚያደርግበት፣ ዳር ድንበርን የመከላከልና የሶማሊያን ትንኮሳ በቅርበት የመከታተል፣ አስፈላጊ ሲሆንም በጠላት ላይ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቅ ስለነበር አስገምጋሚው ጦርነት ሲፈነዳ ሻምበል ባጫና ባልደረቦቻቸው የሀገራቸውን የአየር ክልል ላለማስደፈር ቀን ከሌሊት የሚተጉበት በሚገርም ሁኔታ በአንድ ቀን ብቻ ከስምንት ጊዜ በላይ የበረራ ምልልሶችን ለማድረግ የተገደዱበትና በአየር ላይ ግዳጅ ከሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ጋር የሞት ሽረት ግብ ግብ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጠረ። የሻምበል ባጫ ሁንዴና የባልደረቦቻቸው የነለገሠ ተፈራ፣ አሸናፊ ገብረፃዲቅ፣ በዛብህ ጴጥሮስ፣ መንግሥቱ ካሣ፣ እንዲሁም የሌሎቹም ኤፍ 5ኤ ላይ የነበሩ ጀግኖች አይተኬነትና ወደር የሌለው ገድል በአደባባይ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ግልፅ ሆነ።
የጠላትን ተዋጊ አውሮፕላኖች ከአየር ላይ በማርገፍ ከአፍሪካ ባሻገር በዓለም ዙሪያ አድናቆትን የተቸረው ገድል ፈፅመውም የሀገራቸውን የአየር ክልል አስከበሩ። በምድርም ለመከላከያ ሠራዊቱ የቅርብ የአየር ድጋፍ በመስጠትና የቅኝት በረራዎች በማድረግ ወደር የሌለው ገድል ፈፀሙ። ለሁሉም ምርጥ ጀግኖች እንደተደረገው ሁሉ ሻምበል ባጫም በግላቸው ሁለት የጠላት ሚግ አውሮፕላኖችን አየር ላይ መተው በመጣል፣ እጅግ ወሳኝ በነበሩ የሐርጌሣና በርበራ የማጥቃት ግዳጆች ከባልደረቦቻቸው ጋር ተሳትፈው ግዳጃቸውን በብቃት በመፈፀም ላደረጉት ተጋድሎ የሀገሪቱን ሁለተኛውን ከፍተኛ የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ ለመሸለም በቁ። ከሽልማቱም ቀደም ብሎ በዚያው በጦርነቱ ወቅት በቅድሚያ ሹመት የሻለቅነት የማዕረግ ዕድገት በማግኘት ከፍ ወዳለው የመኮንንነት ማዕረግ ለመሸጋገር ቻሉ።
በዚያ ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ የተከፈለው መስዋዕትነት ቀላል አልነበረም፤ ብዙዎች መስዋዕት ሆነዋል። ብዙዎችም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአየር ኃይል ውስጥ የሻለቃ ባጫ የቅርብ ጓደኞችና ባልደረቦች አውሮፕላናቸው በጠላት ፀረ አውሮፕላን እየተመታ ለመዝለል የተገደዱ፣ በጠላት እጅ የወደቁ፣ በዚያም ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ወይም ለዓመታት በእሥር የማቀቁ ነበሩ። ግን ሁሉም ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ነበረና በእነሱ መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር በማባረር ዳር ድንበሯን አስከበረች። የጀግኖቹ ገድልም እነሆ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ሕያው የታሪክ ማስታወሻ ሆኗል።
ቀጣዩ ዕጣ ፈንታ
ለከፍተኛ ውዳሴና ማዕረግ የበቁት ጀግና ሕይወት ምስቅልቅል ውስጥ መግባት የጀመረው ከ1972 ዓ.ም በተለይም ድሬዳዋ ይገኝ ወደነበረው የ3ኛው ተዋጊ ሬጂመንት የዘመቻና ትምህርት መኮንን ሆነው ከተዛወሩበትና ሚግ 21 አውሮፕላን ላይ የሽግግር በረራ አድርገው ከተመደቡበት ጊዜ አንሥቶ ነበር። ሻለቃ ባጫ ወደሚግ 21 የተሸጋገሩት የሶማሊያው ጦርነት በድል ከተደመደመ በኋላ አብሮ ውድቀቷ ይፋ የሆነው፣ ብዙ ጀግንነት የተፈፀመባት፣ ለሀገራችንም ብዙ ውለታ የሠራችው የኤፍ 5 አውሮፕላን በመለዋወጫና በሌላ ምክንያት ከአገልግሎት ስትወጣ እዚያ ላይ የነበሩ አብራሪዎችም ወደሌሎች አውሮፕላኖች መሸጋገራቸው ግድ ስለነበረ ነበር።
የሻለቃ ማዕረግ ላይ የደረሱት ባጫ ሁንዴ ከመስመራዊ መኮንንነት ወጥተው ለከፍተኛ መኮንንነት የሚያበቃቸውን ልዩ የዕዝና ስታፍ ሥልጠና በመውሰድና ያለምንም እንከን በአጥጋቢ ውጤት በማለፍ ማጠናቀቅ ችለዋል። ይሁንና ከዚያ በኋላ የነበረው ሕይወት እሳቸው እንደሚጠብቁት ሊሆን አልቻለም። ልክ እንደመብረቅ በድንገት ብዙ ነገሮች ተደራረቡባቸው። በፊት ከፍተኛ አድናቆትን ሲለግሷቸው ከነበሩት አለቆቻቸው ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ። ከ1972 ዓ.ም እስከ 1978 ዓ.ም ድረስ ሕይወታቸው የስቃይ እንጂ የሰላም አልነበረም። እኛ በአንባቢነታቸው፣ በአስተዋይነታቸውና በትህትናቸው በእጅጉ የሚታወቁት ጀግና በድንገት የኑሮ አቅጣጫቸው ተለወጠ። በድንገትም ወደላይ እየተወነጨፈ የነበረው የአየር ኃይል እድገታቸው መገታት ብቻም ሳይሆን ቁልቁል መውረድ ጀመረ።
ይህ ሁሉ ነገር ለምንና እንዴት ተከሰተ? የሚለውን ነገር በዚህ እትም ሁሉንም ባንዘረዝረውም ብዙዎች ባልደረቦቻቸው በቅርበት አሳምረው የሚያውቁት ሁሉ አንድ የጋራ የሆነ አስተያየት ነበራቸው። በኋላ ላይ የሌ/ኮሎኔል ማዕረግ ላይ የደረሱት ባጫ ሁንዴ ለዚያ ሁሉ ያበቃቸው ያመኑበትን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ፣ መብታቸውን የማያስነኩ፣ ለሰዎች ፍላጎትም ሆነ አላስፈላጊ ጫና የማይንበረከኩ መሆናቸው እንደሆነ ያነሳሉ። ይህ ባሕሪያቸውም በተለይ ከጥቂት አለቆቻቸው ጋር ግጭት ውስጥ ሲከታቸው እሳቸው ደግሞ የያዙትን እውነት ይዘው መሞትን እንጂ ሽንፈትን ላለመቀበል በፅናት መቆማቸው እንደሆነ ይነሳል። ከሥራ መታገድ፣ እስር፣ ደሞዝ መከልከል ወዘተ ቀጣይ እሳቸውን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ሆኑ።
ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ የነበረው ሕይወት እንደበፊቱ የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ብሩህ ቀጣይ ዘመንን የሚያንፀባርቅ አልሆነም። ግጭቱና ፍትጊያ ለዓመታት እንደቀጠለም ሌ/ኮሎኔል ባጫ ራሳቸውን ከሰው እያገለሉ፣ በአቋማቸው ይበልጥ እየፀኑ የሚመጣባቸውን ፈተና ሁሉ በፅናት ለመቀበል ዝግጁ ሆኑ። ብቸኝነቱ እየገዘፈ፣ ከሰዎች ይበልጥ እየራቁ በሄዱ መጠን ይበልጥ ብሩህ ከነበረው የሕይወት ራዕያቸው እየተለያዩ ሄዱ። በመጋቢት ወር አጋማሽ 1977 ዓ.ም ቀድሞ ከተመደቡበት ከዘመቻ መምሪያ የበረራ ደህንነት ክፍል ኃላፊነት ተነሥተው ወደስድስተኛው የአየር ምድብ በመዛወር የሴሲና አብራሪ እንዲሆኑ ተመደቡ። እዚያ እያሉ ነው እንግዲህ በሀገር ውስጥ ከሰው እንደራቁ፣ ብቸኝነትን እንደመረጡ ሁሉ በመጨረሻም ሁሉንም ጥለው ከሀገር መውጣትን መፍትሔ ያደረጉት።
በሚያዝያ ወር 1978 ዓ.ም ሌ/ኮሎኔል ባጫ የሴሲና አብራሪ በነበሩበት ወቅት አንድ የተሰጣቸውን በረራ ለማከናወን ወደአሥመራ ይላካሉ። እዚያ ጉዳዩን ከፈፀሙ በኋላ የመልስ በረራ ይጀምራሉ። መዳረሻቸው ግን ሱዳን ነበር። እንዲህም ሆኖ የስደት ሕይወታቸው ተጀመረ። ከሱዳን አሜሪካ በመግባት ካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ሕይወታቸውን አደረጉ።
ለ30 ዓመታትም እዚያው ከብቸኝነት ሳይወጡ ዘመናትን አሳለፉ፤ በ 2008 ዓ.ም ግን በድንገት ቤታቸው ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰማ። በመጨረሻ ዘመናቸው ደስ ሳይላቸው ኖረው በአስከፊ ሁኔታ ወገን ሳይደርስላቸውት ሞተው መገኘታቸው ለሁሉም ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከባድ ፀፀትን ነበር ያስከተለው። ይሁን እንጂ ሞት የሕይወት ሌላው ገፅታ ነውና ሕልፈታቸው ሲሰማ በውጭ የነበሩ የአየር ኃይል አባላትና ልጆቻቸው ተረባርበው የቀብራቸውን ሥነ ሥርዓት አከናወነዋል። ሦስቱ ልጆቻቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ስለአባታቸው ሕልፈት ክፉኛ ሐዘን ቢሰማቸውም ለሀገራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅዖ ያንገበግባቸዋልና በሕይወት ወደሀገራቸው ባይመለሱም እንኳን አፅማቸው በእናት ሀገራቸው ይረፍ በማለት ከሰሞኑ በክብር እንዲያርፉ ሆኗል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም