ሰዎችን መርዳት ህሊናችን ጥሩ ዕረፍት ከሚሰጡን ነገሮች አንዱ እንደሆነ በብዙዎቻችን ዘንድ ይነገራል።
ነገር ግን መቼ እንስጥ፣ ለማን እንስጥ፣ እንዴትስ እንስጥ፣ ምን እንስጥ የሚሉ ነገሮች በተወሰነ ደረጃ ሊያሳስቡን ይችሉ ይሆናል። በእርግጥ በዚህች ዓለም ላይ ሰጪ እጆች ይኑሩ እንጂ እጃቸውን ዘርግተው የሚቀበሉአካላት አይጠፉም፤ ሊጠፉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓለም የሰጪና ተቀባዮች ድምር ውጤት ናት። መስጠት ከሥነ-ልቡናዊ እይታ አኳያ ዋጋው ከፍ ያለ ስለመሆኑም መረጃዎች ያስረዳሉ።
መስጠትን በተመለከተ በርካታ ፀሐፍት በብዕራቸው ከትበውታል፤ አንደበት ርቱዕዎች ተናግረውታል፤ አቅም ያላቸው
ለጋሾች ደግሞ በተግባር አሳይተውታል። መስጠት በባህሪው ደስ የሚል ነው። የሚሰጡ እጆችም ዕድለኞች ናቸው። ሰጪ እጆች በአብዛኛው ከላይ የሚሆኑ ናቸው።
በመስጠትና በመቀበል አውድ ውስጥ ብዙ ሥነ ልቡናዊ፣ አዕምሯዊ፣ አካላዊና፣ ማህበራዊ እሳቤዎች አሉ።
የሳይንስ ሊቃውንት ከተናገሩትና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ካገኘሁት መካከል፤ አንድ ሰው ጥሩ ነገር ከሠራ በኋላ ስሜቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሻሻል፣ ለራሱ ያለው ግምት ከፍ እንደሚል እና ደስ የሚል ስሜት ከውስጥ እንደሚገባ ያስረዳሉ። የሥነ ልቡና ባለሙያዎች እንደሚሉት ደግሞ የሚሰጡ እጆች አይረኩም፤ ይልቁንም በማድረጋቸው በእጅጉ ይደሰታሉ። ሌላ ጊዜም ለመስጠት በእጅጉ የሚጓጉ ናቸው። ከማህበረሰባዊ እይታ አኳያም መስጠት ያስከብራል።
የሚሰጥ ወይንም የሚለግስ ማህበረሰብ በጠቅላላ ዕይታው ያለውና የተከበረ ተደርጎ ይወሰዳል። እንደ ሀገርም ሉዓላዊነት ከፍታ ተደርጎ ይወሰዳል። ለአብነትም አሜሪካ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎችን ትመግባለች። ይህም በመሆኑ የዓለም ሀገራት በአብዛኛው አሜሪካ የተትረፈረፈ ሀብት ባለቤት እና በመስጠት ልዕልናዋን በእጅጉ ከፍ ያለች ሀገር እንደሆነችአድርገው ይስሏታል።
ዜጎቿም በግብራቸው በሄዱበት ይከበራሉ። ይህ በሁሉ የሆነው ሀገራቸው በምታደርገው ልግስና ነው። ይህም ማለት እንደ ሀገርና ማህበረሰብ መስጠት ዋጋው በእጅጉ የላቀ ስለመሆኑ ማሳያ ነው። መስጠት መንፈሳዊ እሳቤውም ከፍ ያለ እና ከሁሉም እይታው ገዘፍ ያለ ነው። በብዛት የሚሰጡ ሰዎች በሃይማኖታዊ እይታ ውስጥ ራሳቸው ያጠሩ እና ለጽድቅ የሚሰሩ፤ የሰማዩን መንግስት ወይንም ከሞት በኋላ ላለው ሕይወት ተድላ እና ደስታን አብዝቶ የሚመኙም ጭምር ናቸው።
በርግጥ ቅዱሳን መፅሕፍት የተቸገሩትን ማገዝ ትልቅ ርዝቅ እንዳለው ያስረዳሉ። ይህ ምንም ስህተት የለውም። ግን አሰጣጣችን ወይንም ደግሞ የተቸገሩ ሰዎችን ማገዝ በምን ዓይነት መልኩ መሆን አለበት የሚለውን መገንዘብ ተገቢ ነው።
በዚህ ረገድ ሰሞኑን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ ካሣ፤ ዓመታዊ በዓላትን ተገን በማድረግ ስለ ስጦታ እና ያለንን ለሌሎች እናካፍል በሚሉ ሰዎችን ማዕከል አድርገው እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹ብዙዎች በዓልን በቤታቸው ያከብራሉ፤
ከተቸገሩት ጋር የሚካፈሉት ግን ጥቂቶች ናቸው። ነገር ግን የተቸገሩትን ማገዝ ያለብን በበዓላት ወቅት ብቻ አይደለም። በዚህ ላይ አንድ የአረዳድ ስህተት ያለ ይመስኛል።
የተቸገረን ሰው ማልበስ ወይንም ማብላት እንደ ጽድቅ ሆኖ እየተቆጠረ ነው። እውነት ነው ፅድቅ ይገኝበታል። ግን እነርሱ ከእኛ ማንነት ውጭ ሆነው እነርሱን ረድተንና ጠቅመን እኛ የእግዚአብሔርን መንግስት እንወርሳለን የሚለው አደገኛ አተያይ ነው። እነርሱን መጠቀሚያ ማድረግ ነው። ልብስና ትንሽ ሳንቲም ሰጥቶ እነርሱን እንደ መጠቀሚያ ማሰብ አይገባም›› ነበር ያሉት።
ሰው የምንም ዕምነት ተከታይ ቢሆንም፤ ወይንም እምነት አልባም ቢሆን ክቡር ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ ሰዕብናን እንደ እቃ ወይንም መሳሪያ መጠቀም አይገባም። እንደ ክርስትናም ያለው አስተምህሮ ይህ አይደለም። የተቸገሩ ሰዎችን የምንረዳው የእኛን ማንነትን ዕውን ለማድረግ ነው። እነዚያ ሰዎች የእኛ አካል ናቸው፤ የስዕብናችን አካል ናቸው። ጎዳና የወደቁ አረጋውያን ሀገር ያቀኑ ናቸው። ለእኛ ማንነት የእነርሱ ላብና ደም አለበት። ስለዚህ እነርሱን በዚህ ሁኔታ ማሰብ አግባብ አይደለም። እናትና አባት ደክመውና ጎዳና ላይ ወድቀው እኛ ጥሩ ማዕድ መጋራት የለብንም።
በየትኛው አስተምህሮና የሞራል ልዕልናም ይህ አግባብም አይደለም። የተቸገሩ ሰዎችን ማሰብ ሰብዓዊ ማንነትን ሙሉዕ ለማድረግ እንጂ በታይታ የተምነሸነሸ ሕይወትን ለማሳየት መሆን የለበትም። መስጠት በመንፈሳዊ ሆነ በዓለማዊ እይታ ዋጋው ከፍ ያለ ነው፤ ዳሩ ግን በመስጠትና በመቀበል መካከል ያለው አረዳድና አተያይ መስተካከል አለበት። መስጠት በግራ እጅ ቀኝ እጅ እንደማከም ነው። የሰውነት እና የማንነት አካል ናቸው። ስለዚህ እገዛ የሚሹ ወገኖችን በዓል ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ልናስባቸውና ልናግዛቸው ይገባል። እንደ ሀገርም ማስቀደም ያለብን እነርሱን ነው። ከጎዳና ላይ ህፃናትና አረጋውያንን ማንሳትና መሰብሰብ
አለብን። ከንግግር በላይ ተግባራችን መቅደም አለበት። ሀገር ግንባታም የሚጀመረው ከዚህ ነው።
በአጠቃላይ መስጠት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑ የሚካድ ባይሆንም የሚሰጥበት አውድ ግን ብዙ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
ምንም እንኳ የሚሰጡ እጆች የተባረኩ ቢሆኑም፤ አሰጣጣቸውና ድጋፍ አደራረጋቸው ግን በብዙ የሚያነጋግር ነው። ምክንያቱም መስጠት በሰዎች ታይታና እና ሆይሆይታ ለመድመቅ ከሆነ አግባብ አይደለም። ማገዝና መደገፍም በዓላትን ብቻ አስታኮ ከሆነ ከመሰረታዊ ችግራችን መውጣት አይቻለንም።
በመሆኑም መስጠት በመንፈሳዊ እይታ ሲሆን ፈጣሪ ብቻ የሚመለከተው እንጂ የካሜራ ጋጋታ የሚታጀብ መሆን የለበትም። መስጠት በሥጋዊ ዓይን ከሆነም መሰረታዊ የሚባሉ ችግሮችን ለማቃለል እንጂ የግለሰቦችን ልዕልና ለማግነን በተቃደ አኳኋን ማድረግ ተገቢ አይደለም።
መስጠት በሥነ ልቦናዊ እይታ የተጎዱ ልቦችን ለመጠገንና ማህበራዊ ቀውሶችን በተወሰነደረጃም ቢሆን ለማረም በሚያስችል ትህትና በተላበሰመንገድ ካልሆነ ፋይዳ ቢስ ይሆናል።
ስለዚህ ሰዎችን መርዳት ከሰብዓዊነት የመነጨ እንጂ ለታይታና ግለሰባዊ ግንባታ መሆን የለበትም። የመስጠትና መቀበል ወይንም ሰዎችን የማገዝና የመታገዝ ተፈጥሯዊ እሳቤው ሰብዓዊነትን ማዕከል ያደረገ ነው።
ዓመታዊ ክብረ በዓላትን ብቻ ተገን በማድረግ ሳይሆን የአዘቦት ሥራ መሆን እንዳለበት መረዳት ያስፈልጋል። በመሆኑም ሰዎችን መርዳት ሰብዓዊነትን ምሉዕ ለማድረግ እንጂ ለታይታ መሆን የለበትም።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ጥር 5/ 2015 ዓ.ም