የፈረንጆቹ አዲስ አመት ሰሞኑን ተከብሯል።መቼም አዲስ አመት ሀገሩ ቢለያይም ወጉ አንድ ነውና ባለ አዲስ አመቶቹ ሀገራትም የየራሳቸውን አዲስ እቅድ ያቅዳሉ።በአዲሱ አመት ሊጓዙበት የሚፈልጉትን መንገድም ከአሁኑ ያስተዋውቃሉ። ታዲያ እኛ ምን አገባን የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። የምንኖረው ሉላዊ በሆነች አለም ውስጥ ነውና የእነሱ እቅድ እኛ ላይ የሚኖረው ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ተጽእኖ ቀላል የማይባል በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ማየት ተገቢ ነው ።
እንደሚታወቀው አሁን ያለው የአለም ስርአት ለምእራባውያኑ እንዲያመች ተደርጎ የተቀረጸ ነው።እኛ በዚህ ወቅታዊ የአለም ስርአት ውስጥ ተሳታፊ እንጂ የጨዋታውን ህግ የምናበጅ ሀገር አይደለንም።ስለዚህም እነሱ በቀጣዩ አመት ጨዋታውን እንዴት ሊጫወቱ እንዳሰቡ ሲናገሩ ልብ ብሎ መስማት ውዴታ ሳይሆን ግዴታችን ጭምር ነው።
ለመሆኑ በቀጣዩ አመት የአለም ፈተናዎች ምንድን ናቸው ተባለ? የአሜሪካ የትኩረት አቅጣጫ ወዴት ነው? የአውሮፓ ህብረትስ? የሩሲያስ? የሌላውስ? ….።አሁን ያለው የዩክሬን ጦርንትን በተመለከተ ምን አይነት አቅጣጫ እንደሚከተሉ ሩሲያስ ሆነ ምእራባውያኑ ምን አሉ? የቻይና እና የታይዋን ጉዳይስ? የነዳጅ ዋጋ በአዲሱ አመት ወዴት ይሄዳል?።
አሁን ያለው ኢኮኖሚያዊ መንገጫገጭ በአዲሱ አመት ይጠበቃል? ወረርሽኝስ? አሜረካ በየትኛው አለም አቀፍ ጉዳይ ላይ የፖሊሲ ለውጥ ልታደርግ ትችላለች? አይ ኤም ኤፍ ስለ ቀጣዩ አመት የሀገራት የኢኮኖሚ ሁኔታ ምን ተነበየ? የትኛው ምርት በአዲሱ አመት ተፈላጊ ይሆናል? የትኛውስ ምርት ዋጋ ያጣል? ወዘተ…። እነዚህ ሁሉ እኛን ሊያሳስቡን እና ልንዘጋጅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
ባለፈው አመት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ብዙ ትግል የገጠምንበት አመት ነበር።በትግራዩ ጦርነት እና በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ብዙ ጫናዎችን አስተናግደናል። ደህና በሚባል መልኩ መክተናል ማለትም ይቻላል። ነገር ግን የአምናው ድል ለዘንድሮ ብዙም የሚፈይደው ነገር የለም። ቢበዛ የሞራል ስንቅ ቢሆን ነው።ከዚያ ውጭ ምእራባውያኑ በአዲሱ አመት በአዲስ መልክ ታጥቀው ነው የሚመጡት።ምናልባት የአምናውን ጫና ላያስቀጥሉ ይችሉ ይሆናል።ነገር ግን አዲስ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት እንደሚኖራቸው መጠራጠር አያስፈልግም።ስለዚህ ቆፍጠን ብሎ መጠበቅ ግድ ነው።
ከሁኔታዎች እንደምንረዳው አሜሪካ ብዙም አዳዲስ ለውጦች የምታስተናግድ አይሆንም።ከወራት በፊት ያካሄዱት የኮንግረስ እና ሴኔት ምርጫ ዴሞክራቶች ሴኔቱን ይዘው እንደሚቀጥሉ የሚያሳይ ሆኗል።ስለዚህም ለቀጣይ ሁለት አመታት በአሜሪካ በኩል ብዙም የአቋምም ሆነ የሹማምንት ለውጥ የማይታይበት ነው የሚሆነው። አሜሪካውያኑ ዘንድሮ ይዘው የከረሙትን አቋም በአዲሱም አመት ይዘው የሚቀጥሉ ይሆናል ማለት ነው።
ከዚህ በመነሳት እንዴት ነው ዘንድሮስ ከአንቶኒ ብሊንከን ፤ ሳማንታ ፓወር ፤ ጄክ ሱሊቫን ፤ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊል እና መሰሎቻቸው ጋር አብረን ልንዘልቅ የምንችለው ? በየትኛውስ ጉዳይ ላይ ዘንድሮ ጠንካራ ፍጥጫ ይገጥመናል? የሚለውን በትክክል መተንበይ እና መዘጋጀት ይገባናል።
በአውሮፓ ህብረት በኩልም ነገሮች በአብዛኛው ተመሳሳይ ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል።ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ ነገሮች የመሻሻል አዝማሚያ ቢኖራቸውም ቅሉ አሁንም ቢሆን ብዙ የቤት ስራዎች በዚያ በኩል ይቀሩናል።እየተደረገብን ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲቀንስ እና የታገዱ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ማድረግ ቅደሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።መንግስት በርካታ አዎንታዊ እርምጃ እየተራመደ ባለበት በዚህ ወቅት ከዚያኛውም ወገን ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን ተግባራዊ በጎ እርምጃ እንዲኖር መግፋት ያስፈልጋል።
በአዲሱ አመት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ እስካሁን የያዝነውን አቋም እንዴት እናስቀጥላለን? ወዳጃችን ሩሲያን ሳናስከፋ ሰላም እንዲሰፍን እንዴት ማድረግ እንችላለን? የሚለው ዋነኛ ሀሳብ ይሆናል። ይህ ጦርነት በእጅ አዙር ብዙ ጉዳት አስከትሎብናል ስለዚህም ሰላም መምጣቱ ቅድሚያ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ይህን በልእለ ሀያላን መሀከል ባለ ፍልሚያ መሀል እንዴት የሀገራችንን ጥቅም ማስከበር እንችላለን የሚለው ጉዳይ ጥንቃቄ ይፈልጋል።
ምእራባውያኑ ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት እነሱ የደገፉትን እንድትደግፍ የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከራቸው አይቀርም።ስለዚህም በአዲሱ አመት ይህን ጫና ተቋቁሞ በተለይ ሞስኮው በጸጥታው ምክር ቤት እያደረገችልን ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ማስቀጠል ወሳኝ ይሆናል።በቻይናም በኩል አዲስ የተሾሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሀገራችን ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ፤ ቤጂንግም የነበራትን የልማት አጋርነት ሚና እንድታጠናክር ማበረታታት ትልቅ ስራ ይጠይቃል።
በአፍሪካ ጉዳይም ፓን አፍሪካኒዝምን ማጠናከር ፤ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለውን ውስብስብ ግንኙነትም በተቻለ መጠን ቅርጽ ማስያዝ ወሳኝ ጉዳይ ነው።ዛሬ ላይ ሀያላኑ ሀገራችንን የሚያጠቁት ጎረቤቶቻችንን እንደ ማኮብኮቢያ በመጠቀም በመሆኑ ጎረቤቶቻችንን እንዴት እንደምንይዝ ማወቅ አስፈለጊ ነው።እንደሚታወቀው ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የምእራቡን የቀን አቆጣጠር የሚጠቀሙ ሲሆን ከምእራባውያኑ በተለየ በየጊዜው የስርአትም ሆነ የፖሊሲ ለውጥ የሚፈጠር በመሆኑ ከየትኛው የአፍሪካ ክፍል ምን አይነት ፖለቲካዊ ነፋስ እንጠብቅ የሚለውን ማወቅ የእኛ የቤት ስራ ይሆናል።
ሲጠናቀቅ ይህ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ለእኛ የበጀት አመት አጋማሹ ላይ የሚከበር በመሆኑ ያለፉትን 6 ወራት የዲፕሎማሲ ስራችንን አፈጻጸም ገምግመን የእነሱንም የአዲስ አመት እቅድ አይተን ማስተካከያ ለማድረግ እድል የሚሰጥ ነው።ስለዚህም ይህን አጋጣሚ መጠቀም እና ለቀጣይ 12 ወራት የአለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ነፋስ አቅጣጫን መገምገም አለብን። ወቅቱ ዲፕሎማሲያዊ መዝረክረክ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍልበት ዲፕሎማሲያዊ ቅልጥፍና ደግሞ ብዙ ስኬት የሚያመጣበት ነው። ስለዚህ እንቀላጠፍ። ድል ከፊታችን ነው።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30 /2015